የቡርቃ ዝምታ እና አዲሱ አረጋ

ሂስ አንድን መጽሀፍ በሚገባ የተረዳ፣ የመረመረ እና ጠልቆም የፈተሸ ግለሰብ መጽሃፉን በሚገባ ካጠናው በኋላ የራሱን አተያይ ወይም ሂስ ከመጽሐፉ በሚያነሳቸው ነጥቦች እያስረገጠ ሂሱን አጉልቶ በማሳየትና ምክረ-ሃሳብ ወይም የድምዳሜ ነጥቦችን በማስቀመጥ የውይይት በር የሚከፍትበት አካዳሚያዊ ተግባር ነው። ሂሱን ለታዳሚ የሚያቀርብ ከሆነ ደግሞ ታዳሚን በሚመጥን መልኩ የደረሰበትን ሃሳብ አጉልቶ በማሳየት የራሱን የድምዳሜ ነጥቦች በዝርዝር በመተንተን ማቅረብና ማስረዳትም ነው።

አቶ አዲሱ አረጋ የቡርቃ ዝምታ በተሰኘው የተስፋዬ ገብረ አብ መጽሀፍ ላይ ያቀረበውን ጥናታዊ ሂስ የመታደም እድል ካገኙት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ከሂስ ቀረባው በኋላ እዚህም እዚያም የሚሰሙት ኮሸታዎች እና ወደ ጽሁፍ አቅራቢው የሚሰነዘሩት ያላዋቂ ትንተናዎች ይህችን ጽሁፍ እንድጽፍ አነሳስተውኛል፡፡ የጽሁፌ አቢይ ትኩረት የጸሀፊዎቹን እይታ ማረቅ አይደለም፤ በፍጹም፡፡ ምክንየቱም የአብዛኛዎቹ (ምናልባትም የሁሉም) የፌስቡክ መንደር ልሂቃን ትኩረት እና እውነት የኦሮሞ ታሪክ ወይም የኦሮሙማ ፍቅር ሳይሆን የፍቅረ ንዋይ እና የጭር ሰል አልወድም ልክፍት እንደሆነ ከእርግጠኝነትም በላይ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ማሳያ አንድ

አዲሱ አረጋ ሂስ ያቀረበበት መጽሀፍ ልቦለድ እንጂ የኦሮሞ ህዝብ የታሪከ ሰነድ አይደለም፡፡ የጯሂዎቹ አይን እና ልብ እስከተከፈተ ድረስ ይህንን ማረጋገጥ የሚያስቸሉ እልፍ ሰበቦችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ የታላቁን ህዝብ ታላቅ ታሪክ እና ዘመን ተሻጋሪ ገድል በአንዲት ልቦለድ ማንጸርያነት ቋጥሮ የቡርቃ ዝምታ ከተነካ ኦሮሞ ተነካ ብሎ ማላዘን አንድም ኦሮሞን ካለማወቅ ሁለትም የጩኸታቸውን ምክንያት ከማሳበቅ የዘለለ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ አሮሙማ ከተስፋዬ ገብረአብም ከቡርቃ ዝምታም በላይ ነው፡፡ የኦሮሞ ታሪክ የመሸነፍ፣ የመዋረድ፣ የአንገት መድፋት፣ የለቅሶ፣ የመደበቅ፣ የሮሮ እና የክሽፈት ታሪክ ብቻ እንደነበር አስመስሎ በመጻፍ ታላቁ ህዝብ ነገውንም በእዬዬ እና በቁዘማ እንዲሻገር ካልተፈለገ በስተቀር የቡርቃ ዝምታ ለኦሮሞ ጠብ የሚያደርገው አንዳችም በረከት የለም፡፡

ማሳያ ሁለት

የቡርቃ ዝምታ የተጻፈበትን የመነሻ መሰረት መመርመርም የነገሩን አካሄድ እንድንረዳ መንገድ ይሰጠናል፡፡ ጸሀፊው ተስፋዬ ገብረአብ ማን እነደሆነ ለማብራራት በመሞከር ደክሜ አላደክማችሁም፡፡ ተስፋዬ ያው ተስፋዬ ብቻ ነው፡፡ እናም ተስፋዬ ገብረአብ የጻፈውን መለስ ዜናዊ በሀሳብ ያዳበረውን፣ በረከት ስምኦን ያደተውን፣ ሜጋ ያተመውን፣ የቀድሞው ማስታወቅያ ሚኒስቴር ስፖንሰር ያደረገውን እና በመንግስት በጀት እና ሎጂስቲክ እያንዳንዱ የኦሮሞ ባለስልጣን እና ኦሮሞ ቤት እንዲገባ የተደረገውን መጽሀፍ ለኦሮሞ ታስቦ የተዘጋጀ ድርሳን አድርጎ ማሰብ በምን ሰበብ ልክ እንደሚሆን የሚያውቁት ያው የታሪክ ሰነዳችን ነው ብለው የሚጮሁት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ደጋግሞ ይል እንደነበረው “ኦሮሞ እምቢ ያለ ቀን ሁሉም ነገር ያበቃለታል”፤ አንድ ህዝብ “እምቢ!” የማለት ሞራል ይኖረው ዘንድ ደግሞ የአሸናፊነት ሞራሉን ከፍ የመያደርጉ ትርክቶች እና መሰረቶች ያስፈልጉታል የቡርቃ ዝምታ ደግሞ ከዚህ በተቃርኖው ሊጠቀስ የሚችል ዘመን ተሻጋሪ የሽንፈት ሙሾ ነው፡፡ ኦሮሞ “እምቢ!” ለማለት ዛሬውን መመርመር- መኖር፤ ነገውንም መተንበይ እና መፍጠር አለበት፡፡ ነገውን የመስራት ብቃት ያለው ህዝብ ትላንቱን እንደ መላቀሻ አምባ ሳይሆን እንደ መስፈንጠርያ ሜዳ (Spring Board) ሊጠቀምበት ይገባል፡፡እነ ተስፋዬ ግን “እምቢ ካለን ሁሉም ነገረ ያበቃለታል” በሚል ጽኑ ስጋት እና ስጋታቸውም በሚወልደው የሞኝ ፍርሀት ለሚመለከቱት ህዝብ ትላንቱን እንጂ ዛሬውን እንዳይኖር- ሽንፈቱን አንጂ ታላቅነቱን እንዳይዘክር- ዛሬ ላይ ሆኖ የነገ ብሩህ ቀኑን ከማበጀት ይልቅ ትላንት ላይ ተቸንክሮ እድሜ ዘመኑን እንዲፈጅ ብዙ ትብታብ ጎንጉነውበታል፤ ለምሳሌ የቡርቃ ዝምታ ከትብታቦቹ ውስጥ አንዱ ነው፡፡

በአለም ታሪከ ውስጥ እንደ አሜሪካ ጥቁሮች እና እንደ እስራኤል አይሁዶች የተበደለ ህዝብ የለም፡፡ ሁለቱም ብርቱ ህዝቦች ነጻነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የሄዱበት መንገድ ግን ፍጹም ለየቅል ነው፡፡ ጥቁሮቹ ወንድሞቻችን የሆነባቸውን እና የሆነው ነገር ሁሉ የጎዳቸውን እየተረኩ በደልን መዘርዘር የህይወታቸው ዘይቤ እስኪመስል ድረስ ህመማቸውን እያወሩ በከፋ ድህነት፣ በድንዛዜ እና ጥላቻ ላይ በመጣበቅ ክፉ አባዜ ታላቂቱ ሀገር ላይ በፍቃዳቸው ታናሽ ሆነው ዛሬ ድረስ አሉ፡፡ እስረኤላውያኑ አይሁዶች ግን ትላንትን ረስተው ሳይሆን ከሙሾ ወዲህ ከመዘከር ወድያ ለታሪካቸው ትተው ሌላ የታሪክ መም ላይ ሩጫ ጀመሩ፡፡ የትላንት ክፉ እጣቸው የመወርወሪያ እና ከፍ ብለውም የመብረርያ ክንፍ እንጂ በትርክት ሰንሰለት የመተብተብያ እግር ብረት አልሆነባቸውም፤ በፍጹም፡፡

ምርጫው ሁለት ነው — እውነት እና ውሸት በተጋመዱበት የትላንት ትርክታችን ወስጥ ተከናንበን ተኝተን በደላችንን እንዘርዝር ወይስ ከተዘጋጀልን ወጥመድ ነቅተን አምልጠን ትላንታችንን ዘክረን- ዛሬያችንን መርምረን እና ነገአችንን ተንብየን ወደ ከፍታችን እንመለስ? የኦሮሞ ህዝብ ምርጫ ይሄ ነው ብዬ መጻፍ አይዳዳኝም- ምክንያቱም ጥያቄው ራሱ መልስ ነው፡፡ ሀገር የማሰተዳደርን ሀላፊነት ትከሻው ላይ የተሸከመ እና አፍሪካን በአንድ የገዳ መቀነት በፍቅር ቀንታለሁ የሚል ሩቅ፣ ረቂቅ እና ጥልቅ ራእይ ያለው ታላቅ ህዝብ ገዥ መደቦች በፈጸሙበት ግፍ ሳብያ ጎኑ ካለ ደሀ ሀዝብ ጋር ቁርሾ ለመቋደስ የመፈለግ ቀጫጫ አዝማምያ በፍጹም አይመጥነውም- አይገባውምም፡፡

ማሳያ ሶስት

አዲሱ አረጋ በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ፣ ፍላጎት ጥቅም እና ማንነት ላይ በፍጹም የሚደራደር ሰው አይደለም፡፡ ጽሁፌ ለፌስቡከኞቹ ኦሮሞ የፖለቲካ ነጋዴዎችም ሆነ ለዲጅታል ወያኔ ፌክ አርበኞች የተዘጋጀ እንዳልሆነ ቀደም ብዬ ጠቅሻለሁ፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ሁሉንም እውነት በደንብ ያውቁታል- እነርሱ ጋ ያለችው ጫወታ በፖለቲካ ተቋምሮ አንዱ ሌላውን መብላት ወይም ማትረፍ በመሆኑ አውቆ የተኛን በመቀስቀስ ጎረቤት አልረብሽም፡፡ ይህ ጽሁፍ ለጨዋ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እና የነጋዴዎቹ ንፋስ ለሚያንገዳግዳቸው ንጹህ የኦሮሞ ልጆች ነው፡፡ ከማህበረሰባዊ ጀግንነት እስከ ማህበረሰባዊ ውግዘት እና ጠላትነት ያለው ርቀት ምን ያህል ነው?፡፡ ትላንት ጩኸታችንን የጮኸልንን- ህመማችንን የታመመልንን- ስቃያችንን የተሰቃየልንን እና የዛሬዋ ጀምበር እንድትወጣ አሜሪካ ሳይሆን ኢትዮጵያ/ ዲሲ- ሚኒሶታ ሳይሆን ፊንፊኔ ላይ ሆኖ ሞትን የተጋፈጠልንን ጎበዝ ዛሬ በምን አግባብ እና በየትኛውስ ሞራል ነው በታሪካችን የተደራደረ ሰው አድርገን ልንጮህበት የምንችለው? የፊንፊኔ ጉዳይ፣ የልዩ ጥቅም ጣጣ፣ የማስተር ፕላን እሰጥ አገባ፣ የለገጣፎ የህግ ይከበራል አቋም፣ በፊንፊኔ የኦሮምኛ ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ ትግል፣ የጠቅላይ ሚነስትሩ ወደ መንበረ ስለጣን መምጣት እና የኦሮሞ ሀገር የመምራት እውነት ወስጥ አዲሱ ያለው ድርሻ፣… ብዙ- በጣም ብዙ፡፡ አዲሱ ቢሳሳት እንኳን እኛ ለአንድ ገጽ ስህተት ብለን አንድ ሺህ ገጽ መጽሀፍ የምንቀድ ጅሎች አይደለንም፡፡ በዚያ ጀምበር ደም በለበሰችበት ክፉ ጊዜ ከእኩያን ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ በጀግንነት የተዋደቀልንን ሰው ውለታ እንዘነጋ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? Nuuti ijoolee warra safuu bekuuti… እንላት ብሂላችንስ ወዴት አለች?

ማሳያ አራት

የአሮማራ ጥምረት- የመላ ኢትዮጵያውያን ጥምረት ነው፤ ይህ የሚያስፈራቸው ደግሞ ብዙ ናቸው፡፡ የአማራ ህዝብ ከኦሮሞ ህዝብ ቀጥሎ የቁጥር የበላይነት ያለው ታላቅ ህዝብ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ከየትኛውም ብሄር በላይ እነዚህ ሁለት ህዝቦች የመጋባት እና የመዋለድ ብልጫ አላቸው፡፡ አብሮነታቸው እና ታሪካዊ ትስስራቸው በተገቢው ቅኝት ታሽቶ ቅጥፈት ሳይሆን እውነት ያደመቀው ዚመት መፍጠር ከጀመረ ይህች ሀገር ሰላም ትሆናለች፡፡ የዚህች ሀገር ሰላም መሆን ማለት ደግሞ በፖለቲካ ደላሎች መዝገበ ቃላት ሲተረጎም የደላሎቹ ስራ ማጣት ማለት ነው፡፡ የቡርቃ ዝምታን የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ አድርገው የሚያቀርቡት እና ተስፋዬ ራሱ ልቦለድ ነው የሚለው መጽሀፍ በሁለቱ ህዝቦቸ መሀከል የተዘረጋ ጥቁር መጋረጃ ወይም እንደ ጅብራ የተገተረ የመከፋፈያ ግድግዳ ነው፡፡ ይህ ስትራቴጂ ረጅም ጊዜ ያገለገለ እና ለስትራቴጀስቶቹም ግብ ወጤታማ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ግን አይሰራም፡፡ ምክንያቱም የቡርቃ ዝምታ የኦሮሞ ታሪክ አልፋ እና ኦሜጋ አይደለም፡፡ ኦሮሙማ ከሁሉም ትርክት በላይ ነው፡፡

አቶ አዲሱ አረጋ አምቦ በነበረው የጋራ የውይይት መድረክ ላይ በተስፋዬ ገብረአብ በተጻፈው “የቡርቃ ዝምታ” መጽሃፍ ላይ ሂስ (Critique) አቅርበዋል። አቶ አዲሱ ባቀረቡት ሀሳብ ላይ አድማጭ የነበርነው ታዳሚዎች የሳቸውን ሂስ ከተዋጠልን መቀበል፣ ካልተዋጠልን ደግሞ የመተው ወይም በሃሳብ የመሞገት ሙሉ መብታችን የተከበረ ነው። የቀረበው የመጽሃፍ ሂስ ትክክል አይደለም የምንል ካለንም ስርዓትን ተከትሎ የቀረበ ወረቀት በመሆኑ ስርዓትን ተከትሎ የመከራከሪያ ተጠይቆችን በማቅረብ መገዳደርና ማሸነፍ መቻል የታላቅነት መገለጫ ነው።

ጥቆማ

በአሁኑ አዴፓ በቀድሞው ስሙ ብአዴን ውስጥ ቁልፍ ቦታ ላይ የነበረ እና አሁን ግን በጀርመን ሙኒክ የሚኖር ሰው ከአንድ አመት በፊት አውሮፓ ተገናኝተን ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ እርሱ አያውቀኝም እኔ ግን አወቀዋለሁ፡፡ ብዙ ካወራን በኋላ አንድ ጥራዝ ከመኪናው ውስጥ አወጥቶ እየዘረጋልኝ አንብበውና ስሜትህን አካፍለኝ አለኝ፡፡ ጥራዙ የአንድ መጽሀፍ ኮፒ ነው፤ ጽሁፉ የአማራ ህዝብ በባሌ ተራሮች ላይ እንዴት በግፍ እንደታረደ፣ በአሳሳ አና በኮፈሌ ብልቱ እንዴት እንደተሸለተ፣ በሲሬ እና በአርሲ ከነበትንብረቱ- ከነከብቶች ልጆቹ በጭካኔ እንዴት እንደ ጋየ…ወዘተ ፊልም በሚመስል የፈጠራ ትርክት የሚያስነብብ መሀከለኛ ጥራዝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ ደወልኩለት— መጽሀፉ በበረከት ትእዛዝ ተጽፎ በሜጋ ሊታተም የነበረ እዩት ተብሎ ብአዴን ጽ/ቤት ከመጣ በኋላ አዲሱ ለገሰ አይሆንም ብሎ ያስቀረው እንደሆነ አጫወተኝ፡፡ የተጻፈበት ጊዜ ከቡርቃ ዝምታ ጋር ተመሳሳይ ስለነበረ ወደ ኦሮሞው የተወረወረችው የቂም እና የጥላቻ ቦምብ ወደ አማራውም ተወርውራ እንደነበር የገባኝ ያኔ ነው፡፡ በምንም ሚዛን ተስፋዬ ገብረአብ ከአዲሱ አረጋ በላይ ለኦሮሞ ሊቆረቆርም ሆነ የኦሮሞ ህመም ሊያመው አይችልም፡፡ የሚበጀው መንቃት ነው፡፡


ፀሃፊው፦ ዶ/ር ነገራ ካባ ነው

3 thoughts on “የቡርቃ ዝምታ እና አዲሱ አረጋ

  1. ወያኔ ስልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ የቆጥሩ ማነስ ምክንያት ዲሞክራሲ በረጅሙ ያቀደውን የሺህ ዓመት የመግዛት ጥም እንደማይዋጣለት በደንብ ጠንክሮ ስለተገነዘበ ኦሮሞን የአማራን እንዲሁም የኢትዮጵያን አጥፊ አማራን ደግሞ ጭቆና የተናወጠው በጉልበት ሊገዛ የተነሳ ነፍጠኛ ነው በሚል ወያኔ ባሰለጠናቸው ኦሮም ተናጋሪዎች በሩ ተዘግቶበት ሲሰበክ 27 አመት አልፏል እነ ለማም ይህንን በጣጥሰው በመምጣታቸው ነው የኢትዮጵያን ህዝብ እምነት አግኝተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ዓለኝታ መሆን የቻሉት:: ተስፋዬም የወያኔን አላማ ለማሳካት ከፍተኛ ዓስተዋጾ ያደረግ ነገር ግን ወያኔ ወደ ሚወዳት ኤርትራ ሲመጣበት ብቻ የከዳ ጸረ ኢትዮያዊ ነው:: ስለዚህ አዲሱ ዓረጋ እውነቱን ይዞ ይህንን የሀሰስ ጭድ ስለደረመሰባቸው በታላቁ የኦሮም ህዝብ ለረጅም ግዜ ሊቸረችሩበት ያሰቡትን ከረንሲ ከጥቅም ውጭ ስላረገባቸው የይገደል ዘመቻ እያደረጉበት ነው ልክ የሚያመልኩበት የጣኦት እንደተሰበረበረ ያዙኝ ልቀቁን እያሉ ነው:: በዚህም ግዜ ነው እውነተኛ መሪ ማለት ምን እንደሆነ የምናየው ኦዲፒ ይህንን የተነፋ ባሉን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እውነትን ተጠቅሞ ማተንፈስ አለበት : በነጀዋር ጣት ንቅነቃ የሚደናብር ፓርቲ መሆንም የለበትም ይህም በቻ ነው ታላቁን የኦሮሞ ህዝብ በሳልነት ጀግንነት አርቆ አስተዋይነትን ና የኢትዮጵያን መስራች ከሆነ ጅግና ህዝብ የሚጠበቀው::
    ገለቱማ

    Like

  2. Good analysis and rejection of victim playing. This game of victim playing is the beginning of downgrading our pride as people. Even if the story is true we know it is not true , this is not the way to go since this kind of aproch helps not our purpose of peace and prosperity but the purpose of the enemy

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡