ጌታቸው አሰፋ “በሌለበት” የተከሰሰው ሀገር ጥሎ ጠፍቶ ነው? ወይስ በመንግስት ላይ ሸፍቶ ነው?

የፌደራል አቃቤ ህግ ትላንት ባወጣው መግለጫ “ክስ ከተመሠረተባቸው 26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች 22ቱ ተከሳሾች በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ የቀድሞ የአገልግሎቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሠፋ በላይ እና አቶ ሽሻይ ልዑል በተባሉ የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎች “በሌሉበት” ክስ ተመስርቶባቸዋል” ይላል። በመገለጫው ዙሪያ በወጣው ዘገባ መሠረት “አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በአራቱ ተከሳሾች ላይ በሌሉበት ክስ ሊመሰረት የቻለው ደግሞ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 42/1/ለ እና 161/2/ሀ መሰረት ተከሳሾች የቀረቡባቸው ክሶች ከባድ በመሆናቸው በህጉ መሰረት በሌሉበት ክስ ሊቀርብባቸው የሚገባ በመሆኑ ነው” ተብሏል፡፡እኔ የህግ ባለሙያ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በሌለበት ክስ የሚመሰረተው በክሱ ላይ በተጠቀሰው የመኖሪያ አድራሻ ሳይገኝ ወይም በፖሊስ ተይዞ ሊቀርብ ባለመቻሉ ነው፡፡ ተከሳሹ ሀገር ውስጥ እያለ “በሌለበት” ሊከሰስ የሚችልበት የህግ አግባብ ያለ አይመስለኝም፡፡ “አንድ ተጠርጣሪ በሀገር ውስጥ እያለ እና የመኖሪያ አድራሻው እየታወቀ “በሌለበት” ሊከሰስ ይችላል” የሚል ህግ አንቀፅ መኖሩን ሰምቼ አላውቅም፡፡በእርግጥ የተቀሩት ሦስት ተከሳሾች ሀገር ወስጥ ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም። አቶ ጌታቸው አሰፋ ግን ትግራይ መቀሌ እንደሚኖር እርግጠኛ ነኝ። ስለዚህ የፌደራል አቃቤ ህግ በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ በሌለበት ህስ ከመመስረቱ በፊት በቅድሚያ ተጠርጣሪው “ሀገር ጥሎ ጠፍቷል” ወይም “ከመኖሪያ አድራሻው ጠፍቷል” አሊያም “በመንግስት ላይ ሸፍቷል” ብለው በይፋ መናገር አለባቸው። ይህ ባልሆነበት በሀገር ውስጥ ያለ እና የመኖሪያ አድራሻው እየታወቀ “በሌለበት” ብሎ ክስ ሊመሰርቱ የሚችሉበት አግባብ ያለ አይመስለኝም።በፕ/ር መረራ ጉዲና፣ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ጃዋር መሃመድ፣ ኢሳት እና ኦ.ኤም.ኤን ላይ ተመስርቶ የነበረውን ክስ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። 1ኛ ተከሳሽ ፕ/ር መረራ ጉዲና ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ ተይዘው መታሰራቸው ይታወሳል። የተቀሩት ከ2ኛ – 5ኛ ባሉት ላይ ደግሞ ክስ ከመመስረቱ በፊት ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ በጋዜጣ ጥሪ ቀርቧል። በተባለው ቀን ፍርድ ቤት የማይቀርቡ ከሆነ “በሌሉበት” ክስ እንደሚመሰረት በተገለፀው መሰረት ክስ ተመስርቷል።በዚህ መሠረት በአቶ ጌታቸው ላይ በሌለበት ክስ ከመመስረቱ በፊት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በጋዜጣ ጥሪ ሊቀርብለት ይገባል፡፡ በጋዜጣ ጥሪ ካልቀረበበት ደግሞ በተፈለገ ግዜ ተይዞ ሊቀርብ ይችላል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በጋዜጣ ጥሪ የሚቀርበው የመኖሪያ አድራሻው የማይታወቅ እና/ወይም በመጥሪያው መሠረት ፍርድ ቤት የማይቀርብ ከሆነና በሌሎች ተመሣሣይ ሁኔታዎች ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ አቶ ጌታቸው ላይ በሌለበት ክስ ከመመስረት በፊት በመኖሪያ አድራሻው ተፈልጎ ያልተገኘ ወይም በፖሊስ (ኢንተርፖልን ጨምሮ) ተይዞ ሊቀርብ ካልቻለ ብቻ ነው፡፡ ቀደም ሲል በተጠቀሰው ምሳሌ መሠረት አቶ ጌታቸው አሰፋ፤ እንደ ዶ/ር ብርሃኑ እና ጀዋር መሃመድ በመንግስት ቁጥጥረ ስር ላለመውደቅ ቀድሞ ሀገር ጥሎ የሸሸ ወይም ሀገር ውስጥ ሆኖ በመንግስት ላይ ከሸፈተ በጋዜጣ ላይ በሚወጣው ጥሪ መሠረት በተባለው ቀን የማይቀርብ ከሆነ “በሌለበት” እንደሚከሰስ በይፋ ይገለፃል፡፡ ነገር ግን ደረጃ አቶ ጌታቸው አሰፋ ወደ መቀሌ የሄደው ሸሽቶ እንጂ ሸፍቶ አይደለም። በፌደራሉ መንግስት ላይ ሸፍቶ ከሆነ አቃቤ ህግ ክስ ከመመስረቱ በፊት ተከሳሹ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በጋዜጣ ጥሪ ማቅረብ አለበት። ፍርድ ቤት አልቀርብም ብሎ ከቀጠለ ደግሞ ሽፍታው ብቻ ሳይሆን ለእሱ እገዛና ድጋፍ የሚያደርጉት አካላት በሙሉ፤ ተፈላጊ ወንጀለኛን በመደበቅ፥ ከህግ አካላት በመሰወር፣ ለተጠርጣሪ ወንጀለኛ ድጋፍና ትብብር በማድረግ፣ እንዲሁም የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ባለመቀበል ወይም የህግ አስከባሪ አካላትን ሥራ በማስተጓጎል፣…ወዘተ ወንጀል ሊከሰሱ ይገባል።ለሀገሪቱ ህግና መንግስት አልገዛም ብሎ ጫካ ከገባ “የጫካ ሽፍታ”፣ ከተማ ከገባ ደግሞ “የከተማ ሽፍታ” ነው። ለሀገሪቱ ህግና መንግስት ተገዢ ያልሆነ ሽፍታ እና ተባባሪዎቹ፤ ሀገር ውስጥ ካሉ በፌደራል ፖሊስ፣ ውጪ ሀገር ካሉ ደግሞ በኢንተርፖል አማካኝነት ታድነው ሊያዙ ይገባል። በሀገር ውስጥ ያለ ተጠርጣሪና ተባባሪዎቹን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋል ካልተቻለ የትግራይ ክልል መስተዳደር የሀገሪቱን ህግ ማስከበር አልቻለም። ስለዚህ የፌደራሉ መንግስት በክልሉ ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማወጅ ህግና ስርዓትን ማስከበር ይኖርበታል። የፌደራሉ መንግስት ህግና ስርዓትን እንዳያስከብር የክልሉ መስተዳደር እንቅፋት የሚሆን ከሆነ ግን በፌደራሉ መንግስት ላይ አምጿል ወይም ሸፍቷል ማለት ነው። በፌደራሉ መንግስት ላይ ያመፁ የክልል መስተዳደር አካላት፦ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከሚኖርበት ቀበሌ ሊቀመንበር እስከ ክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል።በእርግጥ በአንድ ሰው ምክንያት በክልሉ ላይ የመከላከያ ሰራዊት ማዝመት አዋጭ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ለምሳሌ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ቁጭ ብለው በፌደራሉ መንግስት ሥራዎች ላይ የመወሰን ስልጣን ሊኖራቸው አይገባም። በፌደራሉ መንግስት ሥራና አሰራር ላይ ለመወሰን አዲስ አበባ ወይም በሌላ አከባቢ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመጣስ ወይም በወንጀል ተባባሪነት ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር ሊውሉ ይገባል። ኢህአዴግ በራሱ የወስጥ ጉዳይ ላይ እንደፈለገው ሊወስን ይችል ይሆናል። ነገር ግን ለሀገሪቱ ህግና መንግስት ተገዢ ላልሆነ የክልል መስተዳደር የፌደራሉ መንግስት የበጀት ድጎማ የሚያደርግበት አግባብ አይታየኝም። ብቻ ዋናው ጥያቄ አቶ ጌታቸው አሰፋ በሌለበት የተከሰሰው “ሀገር ጥሎ ጠፍቶ ነው” ወይስ “በመንግስት ላይ ሸፍቶ ነው” የሚለው ነው? ሀገር ጥሎ ከጠፋ በጋዜጣ ይፋ ይውጣ፡፡ በመንግስት ላይ ሸፍቶ ጫካ ከገባ “ሽፋታ” የሚል ስም ይዉጣለት፡፡ ሀገር ጥሎ ሳይሸሽ ወይም ሳይሸፍት “በሌለበት” ብሎ መክሰስ “ሽንፈት” ነው፡፡

One thought on “ጌታቸው አሰፋ “በሌለበት” የተከሰሰው ሀገር ጥሎ ጠፍቶ ነው? ወይስ በመንግስት ላይ ሸፍቶ ነው?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡