የብሔርተኞች የተቃርኖ ፖለቲካ እና ህልውናቸው!!

አንድ ሀገር በመርህና በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት ከሌላት ሁሌም የተፋርሶ የፖለቲካ መስመር ላይ (in a constant state of deconstructive political path) እንደሆነች ትቀጥላለች:: ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁሉን አቃፊነት የጎደለው ስርዓት (non-inclusive system) ተጠቂ ትሆናለች:: የፖለቲካ ስርዓቱን ፌዴራልም በለው ሌላ ስልጣን የምትይዘው ያንተን ብሔር ልዩ የስርዓቱ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስለሚሆንና ይህ ደግሞ መርህ ላይ የተመሰረተ እስካልሆነ ሁሌም በሌላው ተጎጂነት (at the expense of the other) እወክለዋለው የምትለውን ብሔር ለመጥቀም ከቻልክም የበላይነቱን ለማስጠበቅ መሄድ ያለብህ አስገዳጅ ሁኔታዎች ስለሚፈጥር የእንደዚህ አይነት አካሄዶች ተዛማች ተፅእኖ (ripple effect) በአጠቃላይ ፍትሀዊነት የሌለበት ስርዓትን ይፈጥራል::

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የህልውናቸው መሰረት የብሔር ፅንፈኝነት ነው:: ለዚህም ነው የሆነ ሰዓት ላይ በስልጣን የመቆየት ወይም እወክለዋለው በሚሉት ህዝብ ዘንድ የተደማጭነት ህልውናቸው አደጋ የተጋረጠበት ሲመስላቸው ያቺን “የብሔር ካርድ” መዘዝ እያደረጉ ይህን ጨዋ ህዝብ እርስ በርሱ እያጋጩ ደርሶ አለሁልህ ባይ ወይም ገላጋይ እየሆኑ የሚሰነብቱት (‘survive’ የሚያደርጉት):: የሚገርመኝ ግን የዚህች “የብሔር ካርድ” የፖለቲካ የመሰንበቻ ብልሀት (survival tactic) ሁሌም የመስራቷና የመጨረሻ አማራጭ (last resort) የመሆኗ ጉዳይ ሳይሆን በህዝቡ ዘንድ ሁሌም ተቀባይ (relevant) የመሆኗ ጉዳይ ነው:: ፖለቲከኞቹ ይማሩም አይማሩም: በሙሰኝነት እወክለዋለው የሚሉትን ህዝብ ይዝረፉም አይዝረፉም: ወንጀለኛ ይሁኑም አይሁኑም ሁሌም በራሳቸው ብሔር ዘንድ ከህግ በላይ ሆነው “በብሔር ዋሻቸው” የመሸሸግ መብታቸው ይጠበቅላቸዋል:: ይህ ነባራዊ እውነታ እንደ ሀገር የፖለቲካ ስነልቦናችን ያለበትን ዝቅታ (the depth of our political psyche) በግልፅ አመላካች ነው::

የዜጎች በገዛ ሀገራቸው ባለ የትኛውም አይነት ስርዓት ውስጥ ሊኖር ለሚገባው እኩል ተጠቃሚነት በመርህ ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ውል (social contrat) መሰረት ነው: የስርዓቱም ፍትሀዊነት ዋንኛውና አይነተኛ መገለጫ ነው:: በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ማህበራዊ ህልውና መሰረት በሁሉም የዚያ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ማህበራዊ ውል (negotiated social contract) መኖሩ ሲሆን ይህም በአንደኛው ወገን ሌላኛው ላይ በሀይል የተጫነ (super-imposed) ሳይሆን በነፃ ፈቃድ ላይ በተመሰረተ አካሄድ ቅቡልነት ያለው መሆኑ ነው:: ይህ ደግሞ በየትኛውም ወቅት ሊቀየር የሚችል እንጂ እንደ መፅሐፍ-ቅዱስ ከሰማይ የወረደና የማይቀየር ቀኖናዊ ህግ አይደለም:: አሁን ሀገራችን ላይ እየታየ ያለው መሰረታዊ ችግር የሚመነጨው ከዚሁ አይነት የስርዓቱ ክፍተት ነው::

አሁን ላይ እንደ ሀገር ለውጥ ላይ መሆናችን የማይካድ ሀቅ ነው:: ነገር ግን ፖለቲከኞቻችን ህዝቡ ለሚፈልገው አይነት የለውጥ አቅጣጫ ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ቢያንስ ለህዝቡ ለውይይት ሊቀርብ የሚችል የለውጡን አቅጣጫዎች የሚጠቁም መርህ ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ ፍኖተ ካርታ እንኳ የላቸውም:: ይህን ስል ታዲያ የለውጡን የፊት መስመር መሪዎች (the public faces of the reform) ማለቴ አይደለም: ይልቁንም ከለውጡ የጫጉላ ግዜ በኋላ የለውጡን መሪዎች እጅ የኋሊት ጠምዝዘው በጭፍን ብሔርተኝነት አካሄዳቸው ለውጡን ወደ መጨናገፍ አፋፍ ላይ አድርሰውት የነበሩትን ማለቴ እንጅ:: በአጠቃላይ በለውጡ ሂደት ህዝቡ ለመረዳት የሚቸገረው አንድ ቁልፍ ነገር ቢኖር በሀገሪቱ ከለውጡ ጋር በተያያዘ እየተፈጠሩ ላሉ የለውጡ ውጤታማነት ማነቆዎች ተጠያቂ የሚያደርገው የለውጡን መሪዎች ጠ/ሚሩንና የኦቦ ለማን ቡድን መሆኑ ነው:: ነገር ግን እነዚህ ሁለት ሰዎችና የቅርብ አጋሮቻቸው ከወጡበትና ከሁለት አስርታት በላይ ስር ከሰደደው የፖለቲካ ስርዓት መስመር አንፃር በራሳቸው ብቻቸውን በህዝቡ ዘንድ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ቀላል ፈተና አይደለም የተጋረጠባቸውም ሆነ እያለፉበት ያለው::

የለውጡ የፊት መስመር መሪዎች የራሳቸው ድርጅት አባላቱ ከቀደመው ኢህአዴግ ውስጥ የወጡ ቢሆኑም በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ለውጡ መከተል ካለበት አቅጣጫ አንፃር በፅንፈኛ ብሔርተኞች ተጠልፏል ወይም ደግሞ በነዚሁ ቡድኖች ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ስር ወድቀዋል:: ይህን ደግሞ በለውጡ ሁለተኛ ግማሽ አመት ውስጥ በውል በተግባራዊ እርምጃዎቻቸው ያየነው ነው:: ይህ አካሄድ ከለውጡ አጋሮች በኩል ተመሳሳይ የፅንፈኛ ብሔርተኞች ተፅዕኖ አልፈጠረም ማለት አይቻልም:: የነዚህ የለውጡ ሁለት ክንፎች ውስጣዊ ተቃርኖአዊ አካሄድ ሶስተኛውን የደቡቡን የለውጡ አጋር ጥርስ አልባ ያደረገውን ተፅዕኖ ውጤትም በአደባባይ ያየነው ጉዳይ ነው:: ይልቁንም በ’እነሱ’ (ለውጡን ከፊት መስመር መሪዎቹ ጀርባ በሚዘውሩት ፅንፈኛ ብሔርተኞች) አመለካከት “ለውጡ” የቀደመውን የአንድ ብሔር ‘የበላይ ጠባቂ’ ከስልጣን ሸኝቶ ባለግዜ ተረኛ የሌላ ብሔር ‘የበላይ ጠባቂን’ ስልጣን ማደላደልና በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገዶች ማመቻቸት ነው:: ይህ ዘመኑ የደረሰበትን አለም አቀፋዊ የፖለቲካ መርህ ካለመረዳት አሊያም ለመቀበል ዝግጁ ካለመሆን የሚመነጭ ነው:: በተጨማሪም ተረኛነት ከተጠናወተው የፖለቲካ ዝንባሌ ውጭ ከአማራጭ ሀሳብ ድርቀት የሚመጣ ሌላውን ሁሉ ‘እኔ አውቅልኋለው’ የሚል አግላይና የተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት ውጤት ነው::

የፖለቲካ መስመርህ አስተሳሰብ መሰረትም ሆነ ልቀት (highlight) የራስህን ብሔር ልዩ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ ከሆነ መጀመሪያውኑም አድማስህን አጥብበህ ስለምትነሳ የትኛውንም ያህል ብትጠበብ ሙሉ አቃፊነት ያለው ስርዓት ልትፈጥር አትችልም:: እንደ አንድ መሪና ግለሰብ እጅግ ብሩህ አስተሳሰቦችን የምታራምድ ልትሆን ትችላለህ: የፖለቲካ መሰረትህ (political base) ግን “በብሔር ቅርጫት” የጠበበ ከሆነና ከዚህም የመነጨውና የምትንቀሳቀስበት ስርዓት (the resultant political system you operate in) ለሀሳብ ልዕልና በቂ ቦታ(room) ከሌለው የአሰራር ለውጥ ከማምጣት ባለፈ መሰረታዊ የሆነ: ሁሉን አቃፊና ግዜን ተሻጋሪ የሆነ የስርዓት ለውጥ ልታመጣ አትችልም:: ይህን ጠጣር እውነታ (hard reality) በግዜ መረዳት እንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብም ሆነ እንደ ሀገር ወደምንፈልግበት ትክክለኛ መስመር በግዜ እንድንገባ ይረዳናል:: ፈጣሪ መንገዳችንን ቀና ያድርግልን::
ቸር እንሰንብት::