የወላይታው 35,000 የመከላከያ ተቀናሾችና ያልፈነዳው የግዜ ቦንብ ጉዳይ!!

በወላይታ ሶዶ ከተማ ስታዲየም የዞኑን የክልልነት ጥያቄና ሌሎች የፍትህ እንዲሁም ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመጠየቅ የወጣ ህዝብ

በወላይታ ሶዶ ከተማ የተካሄደውና በሀገሪቱ የተለያዩ ሚዲያዎች የተዘገበው ሰላማዊ ሰልፍ ከወትሮው የተለየ ስጋት የሚያጭር አንደምታ የተስተዋለበት ነበር:: በርግጥ ሰላማዊ ሰልፉ ሌሎች አካባቢዎች ላይ እንደታየው የማንነትና የክልል ራስን በራስ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ ጥያቄዎች: ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ያስተጋባ: እንዲሁም በፌዴራል መንግስቱ በኩል የሚደረጉ የልማት ድጎማዎች ከበቂ በታች መሆንና በሀዋሳና ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች በብሔሩ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ብሔር ተኮር ጥቃቶችን ለመከላከል በፌዴራል መንግስቱ በኩል የተደረገው ህገመንግስታዊ ከለላ በቂ ያልሆነና የዘገየ መሆኑን ያወገዙ መልዕክቶችን ያዘለ እንደነበር ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተ የወጡ የሚዲያ ዘገባዎች ያጠቁማሉ::

የደቡብ ብሔራዊ ክልል የመፈራረስ አደጋ ከተጋረጠበት በኋላ ከሲዳማ ዞን ቀጥሎ የዞኑ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ወስኖ የክልልነት ጥያቄ ያቀረበበት አንዱ ዞን ይኸው የወላይታ ዞን ነበር:: እንደ ታሪክ አዋቂዎች ትንተናም የሀገሩ ገዥ ከነበሩት ከንጉስ ጦና ዘመን በፊት ጀምሮ የራስ ገዝ አስተዳደር የነበረውና በስልጣኔም ቀደምት ከነበሩ ሀገራትና ከአፄ ሚኒሊክ ዘመን ጀምሮ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ትርክት ጉልህ ድርሻ ካላቸው የሀገራችን ክፍሎች አንዱ እንደሆነ ይጠቀሳል:: ሆኖም በዚህ ጠለቅ ያለ ጉዳይ ላይ ሁኔታዎች ከፈቀዱልኝ ሌላ ጊዜ ልመለስ ብችልም የዚህች መጣጥፌ አትኩሮት ይህ ጉዳይ አይደለም: ይልቁንም እግረ መንገዴን የወላይታ ህዝብ ምን ያህል የሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ የማንነት: የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቹን ማንሳት የሚችልና ከጥንታዊ ስልጣኔው ባሻገር ዘመኑ ከደረሰበት የአስተሳሰብ ስልጣኔ ጋር እራሱን አብሮ ማራመድ የቻለና በሰላማዊ አካሄድ የሚያምን መሆኑን ሳላደንቅ ማለፍ ስላልቻልኩ ነው:: ወደፊት እድሉን ሳገኝም የዚህን የጀግኖች ሀገር ህዝብ የኑሮ ዘይቤና ባህላዊ እሴቶች በጥቂቱም ቢሆን ለመረዳት የሚያስችለኝን ጉብኝት ባደርግ ደስ ይለኛል::

ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመለስ ታዲያ የሀገራትን የመከላከያ አቅም በየአመቱ ከሚመዝነው ግሎባል ፋየር ፓወር (Global Fire Power) የ2019 የፈረንጆች አመት ዘገባ ማየት እንደሚቻለው በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ብዛት (in active service) 140,000 ሲሆን ከዚህም ውስጥ ወደ 5,000 የሚደርሰው የአየር ሀይል አባላት ሲሆኑ የተቀረው 135,000 የምድር ጦር አባላት እንደሆኑ ይገመታል:: ይህ ተጠባባቂ የጦሩን አባላት (reserve army personnel) ሳይጨምር መሆኑ ነው እንግዲህ:: በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተሳተፉ የሚነገረው ወደ 35,000 የሚደርሰውና በህጋዊ ማህበር የተደራጀው በክብር ተቀናሽ የመከላከያ ሰራዊት አባል ቁጥር ታዲያ አሁን ያለውን የሀገሪቱን ጠቅላላ የመከላከያ ሰራዊት 1/4ኛ (25%) መሆኑ ነው:: ይህ እጅግ ትልቅ ቁጥር ነው:: ይህ ማለት የኬንያ እና የካሜሩን ጦር አንድ ላይ ተደምሮ ወይንም የቱኒዝያ አጠቃላይ ጦር ሀይል ብዛት ማለት ነው::

ታዲያ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ተቀናሽ የሰራዊቱ ጦር “የተዋደቅንላት ኢትዮጵያ አልተከላከለችልንም” የሚል ጠንከር ያለ የተቃውሞ ጭብጥ ያለው ቅሬታ አዘል እሮሮ ይዞ ነው ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው:: ከዚህ የሰራዊቱ አባላት ቅነሳ ጋር በተያያዘና በሶዶው ሰላማዊ ሰልፍ ከተራ ወታደር እስከ የከፍተኛ ማዕረግ አዛዥና በርካታ የልዩ ኮማንዶ (special operations force) አባላትን ጭምር ያካተተ የሁለት ወይም ሶስት ሀገራት የጦር ሀይል ቁጥር የማይተናነስ ቁጥር ያለው በተለያዩ የጦር ሀይሉ ክፍሎች ውስጥ ከፍተኛ ስልጠና የወሰደና በተለያየ አውደ ውጊያ ከፍተኛ ልምድ የቀሰመ 35,000 የሚሆን ተቀናሽ የሰራዊቱ አባል ከነሙሉ ወታደራዊ መለዮው ሰላማዊ ሰልፍ መውጣቱ ምን አይነት ሀገራዊ አንደምታ አለው የሚለውን ለማየት ነው ዋናው ትኩረቴ:: ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት ግን እነዚህ ተቀናሽ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከነሙሉ መለዮአቸው የዞኑ ህዝብ የፖለቲካ ጥያቄዎች በተነሱበት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ መገኘቱ አግባብ አይመስለኝም:: ይልቁንም ተቃውሟቸውን ራሱን በቻለ ሌላ መድረክ ማሰማት ነበረባቸው:: ቀጥሎ ከታች ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት እንሞክር::

.) መከላከያ በምን ምክንያት የአንድ አካባቢ ተወላጅ ብቻ የሆኑና የሀገሪቱን ጠቅላላ ጦር 1/4ኛ የሚሆኑ ወታደሮች ሊቀንስ ቻለ?

የኢትዮጵያን የምድር ጦር ብቃትን በተመለከተ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት አንድ የአሜሪካ ጦር ሀይል አድሚራል (በአለም ትልቁና የመጨረሻው የጦር መሪ ማዕረግ ነው) ሲገልፁት “በአለም ምርጥ ከሚባሉት የምድር ጦሮች አንዱ ነው (Ethiopia’s ground forces are one of the finest ground forces in the World)” ብለው መግለፃቸው ትዝ ይለኛል:: ይህ ማለት በአጭሩ ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ “Elite” ሊባል የሚችል የምድር ጦር ነው ያላት ማለት ነው:: ይህ አይነቱ ብቃት የሚመጣው ደግሞ በውግያ ዝግጁነት (combat readiness): በሎጂስቲክስ ማኔጅመንት: በታክቲካል የበላይነት (tactical superiority): እና በጦር ሜዳ ውጤታማነትን (battle effectiveness) ጨምሮ በሌሎች በውግያ ልምድ (through battle hardeness) በሚመጡ ብቃቶች ብቻ ናቸው::

እንደዚህ አይነት የውጊያ ዲሲፕሊን ያለው ሰራዊት መገንባት ደግሞ እጅግ ፈታኝና በአብዛኛው የአለም ሀገራት ዘንድ ሊታሰብ እንኳ የማይችል (near impossible) ነገር ነው:: ታዲያ እንዲህ አይነት ብቃት ያለው ጦር እንደዋዛ አሰናብተህ ሌላ የተሻለም ባይሆን እንኳ ተመሳሳይ ብቃት ያለው ጦር ለመገንባት ምናልባትም በአስርት የሚቆጠሩ አመታትና እጅግ ብዙ የሀገር ሀብት ይፈልጋል (It simply costs a furtune) በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በለች የደሀ ደሀ ሀገር:: ከዚህ በተጨማሪስ ይህን ያህል ቁጥር ያለውና ከፍተኛ ስልጠናና የውጊያ ልምድ ያለው (battle hardened) ከአንድ አካባቢ ብቻ የተውጣጣ ሀይል ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህዝብ ደህንነት ከከፈለው ውድ ዋጋ አንፃር ወደ ህብረተሰቡን ሲቀላቀል የተረጋጋ ህይወት የሚመራበት መንገድ ተመቻችቶለት ነው ወይ የተሰናበተው? ከሆነስ ከዚህ ተቀናሽ የሰራዊቱ አካል “የተዋደቅንላት ኢትዮጵያ አልተከላከለችልንም” የሚል እሮሮ ለምን ይሰማል? ከአንድ አከባቢ ተወላጆችስ ይህን ያህል ጦር ማሰናበት በቀጣይነት ለሀገሪቱ ዘላቂ መረጋጋትና ደህንነት አደጋ አይደቅንም ወይ? የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት በሌለበት ሁኔታና የጥቁር ገበያን የጦር መሳሪያ ሽያጭ መንግስት መቆጣጠር ባልቻለበት ሁኔታ ማለቴ ነው::

ለ.) ለፖለቲካ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መልስ ከመስጠት ይልቅ 35,000 ተቀናሽ የጦር ሀይል አባላት የያዘን አካባቢስ ሀገሪቱን ወደ ማይፈለግ መስመር ውስጥ ሊከት ወደሚችል ጥግ መግፋት ምን ያህል በሳል ፖለቲካዊ አካሄድ ነው?

ኢትዮጵያ አሁን ካለንበት ክፉ የታሪክ አጋጣሚም እንበል እውነታ አንፃር ሀገሪቱ ስትከተለው የቆየችው የተሳሳተ የፖለቲካ መስመር በፈጠረው ቀውስ የተነሳ ከጫፍ እስከ ጫፍ ስር የሰደደ የብሔር ፅንፈኝነትና የፖለቲካ ዋልታ ረገጥነት የሚታይበት ወቅት ላይ ነች:: ይህም ሁኔታ በታሪካችን ከመቼውም በላይ የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ያጠላበትና የመፈራረስ ስጋት የደቀነበት ሆኗል:: ይህ ገሀዳዊ እውነታ የሚንፀባረቅበት የፖለቲካ ክፍተት ባለበት ሁኔታ ታዲያ መሰረታዊ ህገመንግስታዊ አካሄዶችን ተከትሎ ለፖለቲካዊ እና የፍትህ ጥያቄዎች ፈጣንና አግባብ ያላቸው ህገመንግስታዊ ሂደቶችን (due constitutional processes) ጠብቆ ለህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት ችላ እየተባለ የተለመደው የዉሱን የፖለቲካ ቡድኖችን የበላይነት የማረጋገጥ እሩጫ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ይመስላል::

የፖለታካ የማንነት ጥያቄዎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚነሱ ተመሳሳይ ጥያቄዎች አግባብነት ባለው ህገመንግስታዊ አካሄድ ተገቢው የፖለቲካ ምላሽ የሚሰጠው ጉዳይ ነው:: ሆኖም ግን እንደ ህዝብ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተጨቋኝነት ብሶት ትርክት የበላይነቱን በያዘበት እንዲሁም ከሁሉም በላይ ደግሞ በብሔሩ ተወላጆች ላይ በተለያዩ አካባቢዎች በተቃጡ ብሔር ተኮር ጥቃት አደጋዎች በፌዴራሉም ሆነ በክልሉ መንግስት በቂና ፈጣን ህገመንግስታዊ ከለላ አልተሰጠም የሚል እሮሮ ባለበት ሁኔታ ይህን ያክል የሰራዊት አባል ያለምንም አማራጭ የማህበራዊ ዋስትና ሽፋን ማሰናበት በተለይም ሀገሪቱ ከምን ግዜውም በላይ በብሔር ፅንፈኝነት እየተናጠች ባለችበት ወቅት ለሰደድ እሳት ማገዶ ከማቀበል አይተናነስም:: ምናልባት በሀገሪቱ የሚቀጥለውን “የነፃ አውጪ ጦር” ቀጠና እንደመፍጠር ነው:: የደቡቡንም የሀገሪቱ ክፍል በቀጣይነት እንደቀደመው የሰሜኑ ክፍል የጦርነት አውድማ ሊያደርገው የሚችል አደገኛ ቅድመ ሁኔታ (dangerous precedent) እንዳይፈጥር እሰጋለው::

አሁን ባለበት ሁኔታ የወላይታው የፖለቲካ ቀውስ ሳይፈነዳ መክሸፍ ያለበት አደገኛ ቀጣይ የግዜ ቦንብ (the next time bomb to be defused) ይመስላል:: በዚህ ረገድ የጠ/ሚ አብይ አህመድ አስተዳደር የቀደሙ ስህተቶችን በማረም የህዝብ ጥያቄዎችን በአፋጣኝ ለመመለስ በመንቀሳቀስ በጥንቃቄ ሊይዘው የሚገባው ጉዳይ ነው:: የወላይታ ህዝብም ሆነ ይህ ተቀናሽ የመከላከያ ሀይል እስካሁን ያሳየው ታላቅ ትእግስትን የተላበሰ ሰላማዊ አካሄድ ኢትዮጵያዊ ክብር የሚቸረው ቢሆንም እስከ መቼ በዚህ ትዕግስት የተሞላበትና የሰለጠነ አካሄድ ይቀጥላል የሚለው እርግጠኛ መልስ ሊገኝለት የማይችል ጥያቄ ነው::

በወላይታ ሶዶ ከተማ “የተዋደቅንላት ኢትዮጵያ አልተከላከለችልንም” በሚል ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ 35,000 ተቀናሽ የመከላከያ ሰራዊት አባላት

A disgruntled soldier armed or unarmed poses a serious threat to national security. It even more dangerously presents an imminent and present or future threat when it meets with an unanswered ethnic identity (self-governance), economic and political question of the public from its own ethnic origin, in a time when a country is deeply polarized along ethnic lines.

One thought on “የወላይታው 35,000 የመከላከያ ተቀናሾችና ያልፈነዳው የግዜ ቦንብ ጉዳይ!!

 1. እነዚህ ሰራዊቶች የተቀነሱት በሪፎርም ስም የብሄር ምጠና ለመከወን ነው። እዚህ ጋር ሲሆን ወታደርም ብሄር አለው! (ጠሚው በተደጋጋሚ ወታደር ብሄር የለውም ሲሉን ነበር)
  ከዚህ በፊት በነበረው መረጃ መሰረት የእግረኛ ሰራዊቱ (ከየበታች የመሰመር መኮንኖች በታች) በብሄር ስብጥር
  1ኛ አማራ
  2ኛ ደቡብ (አበዛኛው ወላይታ መሆኑ ነው)
  3ኛ ኦሮምያና ትግራይ የተውጣጣ ነው ይባላል።
  ሲባል የሚሰማው፥ምክንያቱ ደግሞ፦
  ክልሎች ኮታ ሲሰጣቸው እነደ ብሄር መጠናቸው ነበር በዙህም ሂሳብ ኦሮሚያ ሲቀድም አማራ ሊከተል ይገባ ነበር። ለኦሮምያም ለይምሰል ኮፍተኛው ኮታ ይሰጠው ነበር፥ ነገር ግን ኮታውን አያሟላም፥ በተመልማይ ፍላጎት ሊሆን ይችላል፥ ወይም ልክ አማራ ክልል ይደረግበት እንደነበረው ኮታ የማሟላት ግፊት አይደረግበትም። ወሰጠ ምክንያቱ ለኦነግ አሰልጥን አናዘጋጅም ይመስል ነበር። የኦሮምያን ኮታ ብዛቱን ወደ ደቡብ ክልልና አማራም ይጫን ስለነበር ነው። እስቲ አስቡት የወላይታ ህዝብ ቁጥር በመጨረሻው የህዝ ቆጠራ ወቅት 1.7 ሚሊየን አካባቢ ነው። የአካባቢውን የኢኮኖሚ ሁኔታ የመሬት ጥበት፥ የሰስራ አጥ ወጣቱ ቁጥርን ግነዛቤ ውስጥ ስንከተው፥ ለብሄሩ ወጣቶች ክፍት የመሸሸጊያ ቦታ እንደ ፈደራል ፖሊስና መከላከያው ብቻ ነው። ከዚህ የተረፈው በዜና ስንሰማ እነደነበረው ስደት ወደ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች አካባቢ ነው። ስለዚህ ወጣቱ የጣለትን ኮታ ብቻ ሳይሆን ሲራዊታቸው እንዲበዛ የማይፈለጉት፥ ወይም መከላከያውን መቀላቀል የማይፈልጉ ብሄሮችን ኮታ መሙያ ሆኖ ኖሯል።

  አሁን ታሪክ የተቀየረ ሲመስል፥ የተዛባውን ኮታ ወላይታውን ቀንሶ አሰናብቶ፥ ሌላ ምልመላ ሊካሄድ ታሰቦሰ ቢሆን?
  በቅርብ የምናየው ይሆናል።

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡