በ2012 ምርጫ እንዲካሄድ የሚሹት የህወሓት አገልጋዮች እና የምርጫ አጭበርባሪዎች ናቸው!

በቀጣዩ 2012 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ይካሄዳል ወይስ አይካሄድም በሚለው ዙሪያ በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም። በቅርቡ የተቋቋመው ኢዜማ አመራሮች ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን በመጥቀስ የ2012ቱ ምርጫ መካሄድ የለበትም ይላሉ። በሌላ በኩል ህወሓት እና አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣዩ ምርጫ በታቀደለት ግዜ መካሄድ እንዳለበት በተደጋጋሚ ይገልፃሉ። በአንፃሩ ዋናዎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ኦዴፓ እና አዴፓ ደግሞ የ2012ቱ ምርጫ መካሄድ አለበት ወይም የለበትም በሚለው ላይ አቋማቸው ግልፅ አይደለም። ሆኖም ግን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በታቀደለት ግዜ ምርጫ ከማካሄድ ባለፈ ግዜውን የማራዘም ስልጣን እንደሌለው ገልጿል።

በመጀመሪያ ደረጃ ሀገር አቀፉ ምርጫ በ2012 ዓ.ም የሚካሄድበት ምክንያት ምንድነው? የ2012ቱ ምርጫ የሚካሄድበት መሰረታዊ ምክንያት በኢፊዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 54(1) እና አንቀፅ 58(3) መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት አመታት ስለሆነ እና የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቅ ስላለበት ነው። በዚህ መሰረት ሕገ መንግስቱ ተግባር ላይ ከዋለበት 1987 ዓ.ም ጀምሮ በ1992፣ 1997፣ 2002 እና 2007 ዓ.ም አመስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በቀጣዩ 2012 ዓ.ም ደግሞ 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ቀጣዩ ምርጫ በተመጠለት ግዜ መካሄድ አለበት ማለት ሕገ መንግስቱ ያለ ምንም መሸራረፍ ሊከበር ይገባል እንደማለት ነው። በሕገ መንግስቱ መሰረት ከ1987 እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በየአምስት አመቱ ምርጫ ተካሂዷል። በቀጣዩ 2012 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ የዚሁ ቀጣይ ክፍል ነው። በመሆኑም ቀጣዩን ምርጫ በተቀመጠለት ግዜ ማካሄድ ፋይዳው ያለፈውን የምርጫ ማስቀጠል ነው። በእርግጥ ከ1987 – 2007 ዓ.ም በየአምስት አመቱ ምርጫ ተካሂዷል። በተመሳሳይ በቀጣዩ 2012 ዓ.ም 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ ይገባል ብሎ ማሰብ ከሕገ መንግስቱ አንፃር ትክክልና አግባብ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሕገ መንግስቱ የሚወስነው ምርጫው የሚካሄድበትን ግዜ ብቻ አይደለም።

በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 54(1) መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁሉ አቀፍ፥ ነፃ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት አመቱ መመረጥ እንዳለባቸው ይጠቅሳል። በሕገ መንግስቱ መሰረት ምርጫ መካሄድ አለበት ሲባል “ሁሉ አቀፍ፥ ነፃ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክለኛ እና ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ መሆን አለበት። ከዚህ አንፃር ከ1987 – 2007 ድረስ በየአምስት አመቱ ምርጫ ተካሂዷል። ነገር ግን ያለፉት ምርጫዎች “በሕገ መንግስቱ መሰረት የተካሄዱ ናቸው” ለማለት “ሁሉ አቀፍ፥ ነፃ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክለኛ እና ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ” በየአምስት አመቱ መካሄድ አለባቸው።

ያለፉት ምርጫዎች በየአምስት አመቱ ከመካሄዳቸው በስተቀር ሕገ መንግስቱ ላይ በተጠቀሰው መሰረት “ሁሉ አቀፍ፥ ነፃ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክለኛ እና ሚስጥራዊ” አልነበሩም። በመሆኑም ከ1987 እስከ 2007 ዓ.ም የተካሄዱት ምርጫዎች በሙሉ በሕገ መንግስቱ መሰረት የተካሄዱ አይደሉም። ያለፉት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ሕገ መንግስቱን በሚጥስ መልኩ መካሄዳቸው እውነት ሆኖ ሳለ “ቀጣዩ አመት ምርጫ በተቀመጠለት ግዜ ይካሄድ” የሚሉ ወገኖች ልክ እንደ ቀድሞ የዜጎችን ድምፅ ለማጭበርበር የሚሹ ናቸው። ከዚህ አንፃር የምርጫ ቦርድ እየሄደ ያለው የእነዚህን ወገኖች የማጭበርበር ፍላጎት ሊያሳካ በሚችል መልኩ ነው።

በሕገ መንግስቱ መሰረት “ሁሉ አቀፍ፥ ነፃ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክለኛ እና ሚስጥራዊ” የሆነ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በሌለበት ምርጫ እንዲካሄድ የሚወተውቱ ቡድኖች ዓላማ የመራጮችን ድምፅ ማጭበርበር ነው። ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ተፅዕኖ እና ጣልቃ-ገብነት ነፃ በሆነ መልኩ ቀጥተኛ እና ገለልተኛ ምርጫ ለማድረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሊደረግ ይገባል። በዚህ መልኩ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ ማጭበርበርን ለመከላከል የሚያስችል ስርዓት እና አሰራር ይዘረጋል። በእርግጥ የዜጎች መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ የግድ ነው። ነገር ግን ነፃና ገለልተኛ ምርጫ መካሄድ ካለበት ከዚህ በፊት ከተካሄዱት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ፍፁም በተለየ መልኩ ነው። ስለዚህ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ለማካሄድ በቅድሚያ ራሳቸውን ካለፉት ምርጫዎች ጨርሶ ማላቀቅ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሁሉን አቀፍ የሆነ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ ከምርጫ በፊት አማራጭ ያስፈልጋል። ከምርጫ በፊት የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩች ላይ ያላቸውን አቋም እና ፕሮግራም ለመራጮች በማስረዳት፣ በሚወዳደሩበት አከባቢ የራሳቸውን አደረጃጀት መዘርጋት እና ያለ ምንም ስጋትና ፍርሃት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አለባቸው። ሰፊና አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ አደረጃጀት እና የምርጫ ቅስቀሳ በማህብረሰቡ ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል። መራጮች ከተፎካካሪዎች መካከል የተሻለ ፕሮግራም እና ዕቅድ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲና ተወካይ በቀላሉ መለየት እና ድምፅ መስጠት ይችላሉ።

በዚህ መሠረት ሕገ መንግስቱ ምርጫ ስለሚካሄድበት ሁኔታ “ሁሉ አቀፍ፥ ነፃ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክለኛ እና ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ በየአምስት አመቱ ይካሄዳል” በማለት ከዘረዘራቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ “በየአምስት አመቱ” የሚለውን ብቻ በመነጠል “በቀጣዩ አመት ምርጫ ሊካሄድ ይገባል” የሚሉት ወገኖች፤ አንደኛ፡- ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊ የሆነ ቅድመ-ዝግጅት እንዳይደረግ፣ ሁለተኛ፡- ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች በተደራጀ መልኩ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ራሳቸውንና ፕሮግራማቸውን ለመራጮች እንዳያስተዋውቁ፣ ሦስተኛ፡- መራጮች በቂ ግንዛቤና አማራጭ ኖራቸው ይበጀናል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲና ተወካይ እንዳይመርጡ በማድረግ የህዝብን ድምፅ የማጭበርበር ዓላማ ያላቸው ናቸው። ከዚህ አንፃር ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያለፉትን የተጭበረበሩ ምርጫዎች መነሻ በማድረግ በቀጣዩ አመት ያለ በቂ ቅድመ ዝግጅት እና ምቹ ሁኔታ ሌላ የተጭበረበረ ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 102 ከተቋቋመበት ዓላማና ግብ አንፃር ፍፁም ስህተት ነው፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 102 መሠረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከማንኛውም ተፅዕኖ እና ጣልቃ-ገብነት ነፃ በሆነ መልኩ በገለልተኝነት የተቋቋመ ነው፡፡ በእርጎጥ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 54 መሠረት የህዝብ ተወካዮች የሥራ ዘመን አምስት አመት እንደመሆኑ መጠን የምርጫ ቦርድ በየአምስት አመቱ ምርጫ የማካሄድ ግዴታና ሃላፊነት አለበት፡፡ በተመሣሣይ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 103 መሠረት የተቋቋመው የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን በየአስር አመቱ የህዝብና ቤት ቆጠራ የማካሄድ ግዴታና ሃላፊነት አለበት፡፡ ህገ መንግስቱ ከፀደቀበት ግዜ ጀምሮ ሁለት ግዜ ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ የተካሄደ ሲሆን 3ኛው ህዝብና ቤት ቆጠራ ከሶስት አመት በፊት በ2009 ዓ.ም መካሄድ ነበረበት፡፡ ህዝብና ቤት ቆጠራው በህገ መንግስቱ ከተቀመጠለት ግዜ ሁለት አመት ዘግይቶ ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ከተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች በቀረበ ተቃውሞና አቤቱታ ምክንያት ላልተወሰነ ግዜ ተላልፏል፡፡

ህገ መንግስቱ ምርጫ በየአምስት አመቱ፣ ህዝብና ቤት ቆጠራን ደግሞ በየአስር አመቱ ሊካሄዱ እንደሚገባ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ባለፉት የህዝብና ቤት ቆጠራዎች የህዝብን ቁጥር በመቀነስና በመጨመር ረገድ የተፈፀሙ ሸፍጦችና ደባዎች የፈጠሩትን ክፍተትና ተፅዕኖ በመቅረፍ ትክክለኛ የህዝብና ቤት ቆጠራ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እስካልተፈጠረ ደረስ መቋረጥ አለበት ተብሎ ተቋርጧል፡፡ በዚህ መሠረት፣

  • አንደኛ፦ በህገ መንግስቱ መሠረት በየአስር አመቱ መካሄድ ያለበት ህዝብና ቤት ቆጠራ ባለፉት ሁለት ቆጠራዎች የተፈፀሙትን ስህተቶች እና አሁን በተጨባጭ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ከተራዘመ ባለፉት አምስት ምርጫዎች የተፈፀመውን የድምፅ ማጭበርበርና አሁን ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ማራዘም የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡
  • ሁለተኛ፦ በህግ መንግስቱ አንቀፅ 103(5) መሠረት የምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልሎችን የሚወስነው ከህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን በሚያገኘው መረጃ መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ የህዝብና ቤት ቆጠራ በተቀመጠለት ግዜ ካልተካሄደ የምርጫ ክልሎችን መወሰን አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም የተካሄደው ህዝብና ቤት ቆጠራ ስህተት ከሆነ በዚህ የተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ የምርጫ ክልሎችን መወሰን አይቻልም፡፡ በመሆኑም የህዝብና ቤት ቆጠራ ሳይካሄድ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡
  • ሶስተኛ፦ ቀጣዮ የ2002 ምርጫ መካሄድ አለበት ከሚሉት የፖለቲካ ቡድኖች መካከል አብዛኞቹ የህዝብና ቤት ቆጠራ መራዘሙን የሚደግፉ ናቸው፡፡ ከሌሎች በተለየ መልኩ የህዝብና ቤት ቆጠራው ሆነ ምርጫው በህገ መንግስቱ በተደነገገው መሠረት ሊካሄዱ ይገባል የሚል አቋም ያለው ህወሓት ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ህወሓት የህዝብና ቤት ቆጠራው መራዘሙን አጥብቆ ይቃወም እንጂ ከሶስት አመት በፊት ያውም ፈላጭ-ቆራጭ በነበረበት ወቅት የህዝብና ቤት ቆጠራውን ያራዘመው ራሱ ህወሓት ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ የአማራ ክልል እና አዲስ አበባ ህዝብን ቁጥር በመቀነስ የዘመናት ቂምና ጥላቻውን በተግባር የተወጣው ህወሓት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ሁሉ መሠረት የሆነው ህገ መንግስት በህወሓት የፖለቲካ አቋም እና አመለካከት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ ደርሶ የህዝብና ቤት ቆጠራ እና የምርጫ ጠበቃ የሆነው ህወሓት የህዝብን ቁጥር በመቀነስ Genocide የፈፀመ፣ በምርጫ ማጭበርበር በኢትዮጵያ ላይ የጭቆና ቀንበር የጫነ ፋሽስት ነው፡፡

በአጠቃላይ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ፣ የምርጫ ክልሎችን ለመወሰን የሚያስችል ተዓማኒነት ያለው ህዝብና ቤት ቆጠራ ሳይደረግ፣ የህወሓትን ሌጋሲ (ህገ መንግስት) እና የምርጫ ማጭበርበር ለማስቀጠል ሲባል ብቻ የ2012ቱን ምርጫ ማካሄድ በሀገርና ህዝብ ላይ የለየለት ግፍና በደል እንደ መፈፀም ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግ የሚተጉ ሰዎች፣ ቡድኖችና ተቋማት፤ የህወሓት አገልጋዮች፣ የጭቆና ተባባሪዎች እና የምርጫ አጭበርባሪዎች መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሆነ ሌሎች ተቋማት ከዚህ አዝቅት ራሳቸውን ይታደጋሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

One thought on “በ2012 ምርጫ እንዲካሄድ የሚሹት የህወሓት አገልጋዮች እና የምርጫ አጭበርባሪዎች ናቸው!

  1. ምርጫውን ማን የማራዘም ስልጣን አለው ።ከተራዘመስ ሀገሪቷን ማን ይመራል አሁን
    ያሉ ተመራጮች ስራ ዘመናቸው አልቋል ።ስለዚህ ምርጫው እስኪደረግ መከላከያ ሊመራ ነው ማለት ነው?

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡