ከግብረሰዶሞች ጉብኝት በስተጀርባ ያለው ማን ነው?

ኣይተ ፍፁም ብርሃኔ ለቶቶ ቱርስ ለተባለው የግብረሰዶማዊያን አስጎብኚ ድርጅት ሃላፊ በኢሜል ላቀረብኩለት ጥያቄ “ተጨባጭ ካለው አስጊ ሁኔታ አንፃር በቀጣይ አመት ጥቅምት ወር ላይ በኢትዮጵያ ሊያደርጉት ያቀዱትን ጉብኝት ማድረግ እንደማይቻል ገልጿል። ሆኖም ግን ወደፊት ተመሳሳይ ጥላቻ በሌለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዱን ተናግሯል።” በእርግጥ ድርጅቱ በማስታወቂያው ላይ በተጠቀሰው መርሃ ግብር መሰረት በኢትዮጵያ በሚገኙ የሃይማኖት ስፍራዎች ላይ ጉብኝት ለማድረግ ቢመጣ ኖሮ ሊከሰት ይችል የነበረው አደጋ በጣም የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ሆኖም ግን ድርጅቱ በብዙሃኑ የሀገሪቱ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለውና በሀገሪቱ ህግ ወንጀል የሆነን ተግባር በዚህ ልክ በይፋ ለማድረግ የተነሳሳበት ምክንያት ምንድን ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘ ያለኝን የግል ምልከታና ግምት በጥርጣሬ የተሞላ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ግብረሰዶማዊነት ወንጀል በሆነበት እና በማህብረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት በሌለበት ሀገር ላይ፣ ያውም ደግሞ በተለይ ለክርስትና እምነት ተከታዮች እንደ ቅዱስ የሚወሰዱ ገዳማት እና ቤተ ክርስትያናትን “አስጎበኛለሁ” ብሎ በይፋ መለፈፍ ለምን አስፈለገ? ግብረሰዶም የሆኑ የውጪ ሀገር ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር፣ ሌላው ቀርቶ የላሊበላ ውቅር ቤተ ክርስቲያናትን እንደጎበኙ ከሰሞኑ ሰምተናል። እነዚህ ሰዎች ስለ ፆታዊ ባህሪያቸው በይፋ ሳይለፍፉ በፀባይ መጥተው ቅዱስ የተባለን ስፍራ ጎብኝተው በሰላም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ከዚህ በኋላ ግን እነዚህ ሰዎች ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚችሉ አይመስለኝም። ተመልሰው ቢመጡም በሰላም ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ አይመስለኝም። ስለዚህ ቶቶ የተባለው የግብረሰዶማዊያን አስጎብኚ ድርጅት የሌለን ችግር በራሱ ፈጥሮ ከማህብረሰቡ ጋር አጉል መቃቃር ውስጥ የገባበት ምክንያት ምንድን ነው?

ይህ አስጎብኚ ድርጅት የሌለን ችግር ከመፍጠሩም በላይ ተጨማሪ ችግሮች ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ለምሳሌ ትላንት የድርጅቱ ኃላፊ ለቢቢሲ አማርኛ ፕሮግራም ክፍል በሰጠው አስተያየት በኢትዮጵያ ሊያደርግ ያቀደውን ጉብኝት ፈፅሞ እንደማይሰርዝ ተናግሮ ነበረ። በዕቅዱ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ አንዳች ችግር ቢገጥማቸው ጉዳዩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት እንደሚስብ እና የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ እንደሚያጠለሽ እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ክፉኛ እንደሚጎዳ ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ጉዳዩን አስመልክቶ ለአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አቤቱታ እንደሚያቀርብ መግለፁ ይታወሳል። ትላንት ይህን ብሎ ዛሬ ደግሞ በኢትዮጵያ ሊያደርግ የነበረውን ጉብኝት መሰረዙን ገልጿል።

በእርግጥ ድርጅቱ ያደረገው እንቅስቃሴ በተጨባጭ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ አይሄድም። በኢትዮጵያ ጉብኝት የማድረግ ዕቅድ እንዳለው ማሳወቅ እና በኢትዮጵያ ማህብረሰብ ዘንድ ቁጣና ተቃውሞ መቀስቀስ እንጂ በተግባር ጉብኝቱን የማድረግ ፍላጎት የለውም። ለዚህ ደግሞ ጉዳዩን አስመልክቶ የለቀቀው ማስታወቂያ እና የተፈጠረው እሰጣ-ገባ አንዱ ማሳያ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የቶቶ ቱርስ ድርጅት ኃላፊ ትላንት ለቢቢሲ ከተናገሩት እንደምንረዳው፣ መሰረታዊ ዓላማቸው የኢትዮጵያን ገፅታ በማጠልሸት፣ የቱሪዝም ኢኮኖሚውን በመጉዳት እና በዲፕሎማሳዊ ጫና አማካኝነት በሀገሪቱ ህዝብና መንግስት አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ ነው። ይህን እያሰብኩ ሳለ ደግሞ በቅርቡ የደረሰኝ አንድ መረጃ ወደ አዕምሮዬ መጣ።

ሰሞኑን ደርሶኝ የነበረና ብዙም ትኩረት ያልሰጠሁት መረጃ፤ “ህወሓቶች በቀጣይ ምን ሊያደርጉ እንደሆነ ባይታወቅም በአሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ የሀገሪቱን ባለስልጣናት የሚያማልዱ ሰዎች (lobbyists) በሚገኙበት ሰፈር በስፋት በታየት ጀምረዋል” የሚል ነበር። በእርግጠኝነት መናገር ቢከብድም ከዚህ ጉዳይ በስተጀርባ የህወሓት ክፋት እና ደባ እንዳለ መገመት አይከብድም። የድርጁቱ “ፀብ የለሽ በዳቦ” ዓይነት እንቅስቃሴ ከኋላው አንድ ሃይል እንዳለ ጠቋሚ ነው፡፡ የፖለቲካ እስረኞችን ለማሰቃየት ግብረሰዶሞችን ቀጥሮ ሲያሰራ የነበረው ህወሓት አሁንም እገዛቸውን ፈልጎ እነሱ ጋር መሄዱ አያስገርምም፡፡

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የተገደለውን ተማሪ አስመልክቶ በኢሜል ማብራሪያ ያልጠየቀው ፍፁም ብርሄኔ የቶቶ ቱርስ ጉዳይ ይህን ያህል አሳስቦት ማብራሪያ መጠየቁ ጥርጣሬዬን ይበልጥ ያጠናክረዋል፡፡ ምክንያቱም ከታላቅ ወንድሙ ዳንኤል ብርሃኔ ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ በአካል የተገናኘን ግዜ ምሳ ልጋብዝህ ብሎ የወሰደኝ ፒያሳ በሚገኝ ሆቴል ነበር፡፡ ይህ ሆቴል ንብረትነቱ የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ መስሪያ ቤት ሲሆን በሆቴሉ ውስጥ የሚደረግ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በድብቅ ይቀረፃል፡፡ ተጠቃሚው ከሆቴሉ ከወጣም በኋላ በደህንነት ሰራተኞች ክትትል ይደረግበታል፡፡ በቀላል አማርኛ ዳንኤል እዚያ ሆቴል ወስዶ ለአቶ ጌታቸው አሰፋ አሳልፎ ሰጠኝ፡፡ ከዚያ ወዲህ የጌታቸውን ሃሳብ ለማወቅና ለመገመት ስፈልግ የዳንኤል ብርሃኔን እንቅስቃሴ እከታተላለሁ፡፡ የዳንኤልን ሃሳብ ለመገመት ደግሞ የእሱን ድቀ መዝሙር ማየት በቂ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከቶቶ ቱርስ ጋር ተያይዞ የተሸረበው ሸርና አሻጥር ጫፉ እዚሁ ያለ ይመስለኛል ለማለት ነው!!!

One thought on “ከግብረሰዶሞች ጉብኝት በስተጀርባ ያለው ማን ነው?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡