ይድረስ ለጠ/ሚ አብይ አህመድ፦ “የግብርና ሚኒስቴር የጋምቤላ ደን እንዲጨፍጨፍ ፍቃድና ብድር እንደሰጠ ያውቃሉ?”

በየትኛውም አከባቢ የሚፈፀም ኢ-ፍትሃዊ ተግባር የዜጎችን መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚፃረር በመሆኑ ብቻ ሊወገዝ ይገባል። ይህ ኢፍትሃዊ ተግባር የተፈፀመው እዚሁ ሀገራችን ውስጥ ከሆነ ደግሞ ይበልጥ ሊያሳስበን ይገባል። ድርጊቱ በደን መመናመን እና በአየር ፀባይ መዛባት ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ያጠላውን ተፈጥሯዊ አደጋ የሚያባብስ ከሆነ ችግሩ የአንድ ወረዳ ወይም ክልል ከመሆን አልፎ ሀገር-አቀፍ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ብቸኛ ተፈጥሯዊ ደን የመታደግ እና ያለመታደግ ሲሆን ደግሞ ጉዳዩ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ይሆናል። አዎ… ጉዳዩ በጋምቤላ ክልል በሚገኘው ልዩ የሆነ ተፈጥሯዊ ደን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ስለ መግታት ነው።

በእርግጥ እንደ ሀገር አንድ መሰረታዊ ችግር አለብን። ብዙዉን ግዜ በአንዱ አከባቢ የሚከሰት ችግርን እኛንም የሚመለከት፤ የራሳችን ወይም የጋራ ችግር አድርገን አንመለከትም። ከዚህ በፊት ከፈፀምናቸው የተሳሳቱ ተግባራት አንማርም። ከዚህ በተጨማሪ የዛሬ ተግባራችን ወደፊት በእኛ እና ሌሎች ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ወይም ጥቅም አርቀን አናስተውልም። ወያኔ የጋምቤላ ህዝብን ሲጨፈጭፍ እንዳልሰማ ሆንን። የክልሉን ህዝብ ጨፍጭፎ 65% የሚሆነውን የክልሉን መሬት በእርሻ ኢንቨስትመንት ስም ሲቀራመቱ አይተን እንዳላየ ሆንን። ከጋምቤላ ህዝብ ላይ የዘረፉትን መሬት ለማልማት በሚል ሰበብ ከልማት ባንክ 9.3 ቢሊዮን ብር ብድር ሲወስዱ በግድየሌሽነት ዝም አለን።

ህወሓቶች እና ጀሌዎቻቸው ከልማት ባንክ በወሰዱት ብድር፤ ግማሹ መቀሌ ላይ ህንፃ ሲገነባ ሌላው በዶላር ቀይሮ ወደ አሜሪካ ይዞት ሄደ። የተቀሩት ደግሞ በብድሩ ገንዘብ መኪናዎች እና ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገቡ መነገድ ጀመሩ። የጋምቤላ ህዝብ ሲጨፈጨፍ እና መሬቱ ሲዘረፍ ዝም ማለታችን የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብትና ንብረት በልማት ባንክ እና ጉሙሩክ በኩል በገፍ ተዘረፈ። የዶ/ር አብይ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ህወሓቶች የዘረፉትን ሃብትና ንብረት ይዘው መቀሌ ሲመሽጉ የተቀሩት ደግሞ ወደ ውጪ ሸሹ። ነገር ግን ከህወሓቶች ጋር አብረው ሲዘርፉ እና ሲያዘርፉ የነበሩት አካላት በሙሉ አሁንም አሉ።

This slideshow requires JavaScript.

ከህወሓቶች ጋር ተመሳጥረው የጋምቤላን ህዝብ መሬት በግፍ በመዝረፍ ረገድ የተሳተፉ የውጪ ሀገር ኩባንያዎች፣ በቢሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብትን ያለ አዋጭነት ጥናት አንስተው የሰጡት የልማት ባንክ ኃላፊዎች፣ የህዝብን ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ በሚያመች መልኩ የእርሻ ኢንቨስትመንት ፍቃድ የሰጡት የግብርና ሚኒስቴር እና የፌደራል ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ከእነዚህ ዘራፊዎች ጋር በመሆን የራሳቸውን ህዝብ ያስጨፈጨፉ እና ያዘረፉ የጋምቤላ ክልል ኃላፊዎች አሁንም በተለመደው የዘረፋ ተግባር በመፈፀም ላይ ናቸው።

የቨርዳብታ ሀርቨስት የተሰኘው የህንድ ኩባንያ በ2002 ዓ.ም ከህወሓቶች ጋር በመመሳጠር በጋምቤላ ከልል ከህዝብ በተዘረፈ 3012 ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ልማት ኢንቨስትመንት ፍቃድ አወጣ። የጋምቤላ ክልላዊ መስተዳደር ምክር ቤት በቀን 06/07/2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በፃፈው ደብዳቤ መሰረት ይህ ኩባንያ፤ አንደኛ፡- የምርት መጠቀሚያ ግብር ከፍሎ አያውቅም፣ ሁለተኛ፡- በተጭበረበረ መንገድ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ 70 ሚሊዮን ብር ብድር ወስዷል፣ ሦስተኛ፡- የ2011 ዓ.ም የመሬት መጠቀሚያ ግብር አልከፈለም፣ አራተኛ፡- በመንግስት አዋጅ መሰረት በማድረግ ለወረዳው የሦስት ወር የሥራ ግብር አልከፈለም፣ አምስተኛ፡- ኩባንያው የሻይ ችግኝ የተከለው በአከባቢው ያሉትን እድሜ ጠገብ የሆኑ ዛፎችን በማስወገድ እና ወንዞች የሚገኙበትን ቦታ በዶዘር በመደርመስ እና ምንጮችን በመድፈን በታችኛው ተፋሰስ አከባቢዎች ላይ የውሃ እጥረት አስከትሏል፣ ስድሰተኛ፡- በአከባቢው የሚገኙ እድሜ ተገብ የሆኑ ዛፎችን እና በኢትዮጵያ ልዩ የሆነውን የጋምቤላ የተፈጥሮ ደን በመጨፍጨፍ በምትኩ የባህር ዛፍ በመትከል በአከባቢው ስነ-ምህዳር ከፍተኛ መዛባት ከማስከተሉም በላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የከፋ ጉዳት እያስከተለ ነው።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር እና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን የቨርዳብታ ሀርቨስት የሻይ ልማት ጋር ተያይዞ ከአከባቢያዊ እና ማህበራዊ ጥበቃ አንፃር ለሚነሱ ጥያቄዎች የውሳኔ ሃሳብ ለመስጠት እንዲረዳ የፕሮጀክቱን የእስካሁን አፈፃፀም ኢኮኖሚያዊ፣ አከባቢያዊ፣ ማህበራዊ ጠቀሜታ እና ፋይዳውን አስመልክቶ ጥናት በማድረግ ከጥናቱ ግኝት በመነሳት የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ከኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅጣጫ ተሰጥቶት ነበር። በዚህ መሰረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ 3 አባላትና ከጋምቤላ ክልል 4 ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ ቡድን በማዋቀር በቨርዳብታ ሀርቨስት ኩባንያ የሥራ አፈፃፀም እና በአከባቢዊ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በዝርዝር አጥንቶ ያዘጋጀውን 72 ገፅ ሪፖርት በቀን 10/01/2011 ዓ.ም ለኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የላከ ሲሆን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ግልባጭ ተደርጓል። በዚህ መሰረት የተቋቋመው ኮሚቴ በተጠየቀው መሰረት የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።

  • አንደኛ፡- የቨርዳብታ ሀርቨስት ለሻይ ልማት ኢንቨስትመንት ከወሰደው 3012 ሄክታር መሬት ውስጥ አሁን ላይ በሻይ የተሸፈነው 320 ሄክታር ሲሆን የተመነጠረ ደግሞ 240 ሄክታር ነው። በቀጣይ ኩባንያው ለሻይ ልማት እና ለሻይ ማጠውለጊያ የሚውል የባህር ዛፍ ተከላ እንደሚካሄድበት ታሳቢ በማድረግ በጠቅላላ 560 ሄክታር መሬት ይዞ ተጨማሪ መሬት ሳይጨምር ልማቱን ቢቀጥል፣
  • ሁለተኛ፡- በልማቱ ምክንያት የተጎዳው አከባቢ መልሶ እንዲያገግም የማካካሻ የአከባቢ ልማት ስራ መስራት አለበት። ተጨማሪ የአከባቢ ውድመት መከሰት የለበትም።
  • ሦስተኛ፡- የቨርዳብታ ሀርቨስት ለሻይ ልማት ኢንቨስትመንት ከዚህ በፊት በ3012 ሄክታር የገባው ውል እንደገና በ560 ሄክታር መሻሻል ይኖርበታል።
  • አራተኛ፡- ኩባንያው ያሉበት ክፍተቶች አርሞ የሀገራችንን አከባቢያዊና ማህበራዊ ህጎች አክብሮ ስራውን እንዲያከናውን ቢደረግ።

This slideshow requires JavaScript.

ሆኖም ግን ከህወሓቶች ጋር በመሆን ከጋምቤላ ክልል ህዝብ ላይ በተዘረፈ 3012 ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ልማት ኢንቨስትመንት ፍቃድ ያወጣው ህንዳዊ ከግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች ለአስር አመታት የዘለቀ ጋር ጠንካራ የጥቅም ትስስር አለው። ከዚህ በፊት በተጭበረበረ መንገድ 70 ሚሊዮን ብር ብድር መውሰዱ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኃላፊዎች ጋር ተመሳሳይ የጥቅም ትስስር እንዳለው መገመት ይቻላል። ከእነዚህ ያለውን ጠንካራ ትስስር በመጠቀም የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር እና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን እና የጋምቤላ ክልል መስተዳደር በጋራ በመሆን ያቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አደረገ። በመቀጠል ተጨማሪ ባህር ዛፍ ለመትከል የሚሆን መሬት እና ብድር ጠየቀ።

በዚህ መሰረት የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሣኒ ረዲ አህመድ የጋምቤላ ክልል ኃላፊዎችን ከሁለት ወር በፊት በክልሉ ምክር ቤት በኩል የተላለፈውን ውሳኔ በማስቀየር አዲስ ሪፖርት እንዲያቀርቡ አስገደዷቸው። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ደግሞ ለኩባንያው ለባህር ዛፍ ተከላ የሚሆን ተጨማሪ ብድር እንዲሰጠው ትዕዛዝ አስተላለፉ። ይህን ውሳኔ የተቃወሙ የልማት ባንክ ሁለት ዳይሬክተሮች ባለፈው ሳምንት ከስራቸው ታገዱ። በመጨረሻም የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሣኒ ረዲ አህመድ በ12/9/2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በፃፉት ደብዳቤ ቨርዳብታ ሀርቨስት ኩባንያ ለባህር ዛፍ ተከላ የሚሆን ተጨማሪ መሬት እና ብድር እንዲሰጠው ወሰኑ። በዚህ መሰረት የግብርና ሚኒስቴር በጋምቤላ ክልል የሚገኝ የተፈጥሮ ደን እንዲጨፈጨፍ ፍቃድ የሰጡ ሲሆን ለደን ለጭፍጨፋ የሚውል ገንዘብ ደግሞ ከልማት ባንክ ብድር እንዲሰጠው መመሪያ ሰጥተዋል።