ብሔርተኛ ቸግር እንጂ መፍትሄ የለውም! የፈተና ወረቀት በፌስቡክ ማውጣት የጀመረው ማን ነበር?

ባለፉት ቀናት በመላ ሀገሪቱ ኢንተርኔት ተቋረጠ። በኢንተርኔቱ ላይ የመብራት ፈረቃ ሲታከልበት ደግሞ ሁሉም ነገር ጭለማ ሆነ ማለት ይቻላል። ሌላው ቀርቶ ኢንተርኔቱ እንኳን ለምን እንደተቋረጠ የነገረን አካል የለም። ባለፉት ቀናት የኢንተርኔት አገልግሎት የነበራቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአሜሪካ ኢምባሲ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ባንኮች እና ሌሎች ጥቂት መስሪያ ቤቶች ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያ ሶስቱ የሳተላይት ኢንተርኔት ስለሚጠቀሙ እንደሆነ ሰምቼያለሁ።

የኢንተርኔት አገልግሎትን በመላ ሀገሪቱ ማቋረጥ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ግንኙነት ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንዳሳረፈ ለመረዳት ጥናት ሰርቶ የሚያቀርብ አካል አለመኖሩ ችግሩን በቸልታ ለማለፍ አመቺ ነው። ባለፉት ጥቂት ቀናት የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ቢተመን ግን በጣም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ጉዳዩን አስመልክቶ ከሀገር ውስጥ ሚዲያ አልፎ እንደ ቢቢሲ ባሉ ዓለም-አቀፍ ሚዲያዎች መዘገቡ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ ብቸኛው የኢንተርኔት አገልግሎቱ አቅራቢ የሆነው ኢትዮቴሌኮም የኢንተርኔት ግንኙነት የተቋረጠበትን ምክንያት “አላውቅም” ማለቱን ስሰማ በጣም ነው የገረመኝ። ምንአልባት ኢትዮቴሌኮም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት በመላ ሀገሪቱ ኢንተርኔት የተቋረጠበትን ምክንያት ለህዝብ የማሳወቅ ግዴታ አለበት። በእርግጥ በአንዳንድ የውጪ ሚዲያዎች የ10ኛ ክፍል ፈተና ተሰርቆ ስለወጣና እንደ ቴሌግራም ባሉ የማህበራዊ ሚዲያዎች ስለተሰራጨ እንደሆነ መዘገባቸውን ሰምቼያለሁ። ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ አከባቢዎች ደግሞ የጥያቄ መልስ በሞባይል አጭር የፅሁፍ መልዕክት መላኩን ተከትሎ አገልግሎቱ መቋረጡን ለማወቅ ችያለሁ።

ፎቶ © ኢዜጋ

በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ተማሪዎችን ቀጣይ እጣ-ፈንታ እና የትምህርት ዕድል በሚወስን ሀገር አቀፍ ጉዳይ ላይ እንዲህ ያለ ኃላፊነት የጎደለው ወራዳ ተግባር መፈፀም ፍፁም ድንቁርና ነው። ይሄ ጥቂቶችን ያለ አግባብ፣ በህገወጥ መንገድ ለመጥቀም ተብሎ በሀገሪቱ ቀጣይ ትውልድ ላይ ቁማር መጫወት ነው። እንዲህ ያለን እኩይ ተግባር ለማስቆም ወይም በአጭሩ ለመግታት ማንኛውም ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።

ቀጣዩን ትውልድ ለማጨናገፍ የሚደረግን እንቅስቃሴ ለመግታት እስከሆነ ድረስ ኢንተርኔት ቀርቶ መብራት እና መንገድ ቢዘጋ፣ አጠቃላይ የሀገሪቱ እንቅስቃሴ ለተወሰኑ ቀናት ቀጥ ብሎ ቢቆም አይደንቀኝም። ምክንያቱም ቀጣይ ትውልድ ከሌለ እንደ ሀገር ሆነ ህዝብ ወደፊት መቀጠል አንችልም። ወደፊት ለመራመድ ዛሬ ላይ መቆም የግድ ነው። ነገ ላይ መልካም ትውልድ ለማፍራት ዛሬ ላይ ለገጠመን ችግር ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አለብን። የዛሬውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የችግሩን መንስዔ ወደ ትላንት ተመልሰን መፈለግና መገንዘብ ይኖርብናል።

ሰሞኑን የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው የ10ኛ እና 12ኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚወስዱት ሀገር አቀፍ ፈተና በማህበራዊ ሚዲያዎች እና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት አማካኝነት እንዳይወጣ ለመከላከል መሆኑ እሙን ነው። ሀገር አቀፍ ፈተና በመጣ ቁጥር በመላ ሀገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚቻል አይመስለኝም። እዚህ ሀገር የኢንተርኔት ከተጀመረ ሁለት አስርት አመታት ሆኖታል። ከኢንተርኔት መምጣት በፊት ሆነ በኋላ አሁን ባለው መልኩ የፈተና ወረቀቶችን የማውጣት ችግር አልነበረም። ይህ ችግር የተከሰተው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ይህን ደግሞ ያደረጉት እነ ጃዋር መሃመድ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ይህን ጉዳይ ያነሳሁት እነ ጃዋር የፈተና ወረቀቶቹን በኢንተርኔት ማውጣታቸው “አግባብ ነው ወይስ አይደለም?” በሚለው ላይ ጉንጭ አልፋ ክርክር ለማድረግ አይደለም። በወቅቱ የፈተና ወረቀቱ ተሰርቆ እንዳይወጣ መንግስት የፈተና ግዜውን እንዲያራዝም በተለያዩ ሚዲያዎች ስወተውት ነበር። በሌላ በኩል እነ ጃዋር ፈተናውን በማውጣት በተማሪዎች የትምህርት እድል ላይ ቁማር ከመጫወት እንዲታቀቡ ስማፀን ነበር። ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች ጉዳዩን ቆም ብለው አስበው መፍትሄ ለመሻት ጥረት አላደረጉም። በመሆኑም የፈተና ወረቀቶቹ በኢንተርኔት ተለቀቀ፣ መንግስትም የፈተናውን ግዜ ለማራዘም ተገደደ።

ሆኖም ግን ችግሩ እንዲህ በቀላሉ ትላንት ላይ አልቆመም። ይሄው ዛሬ ድረስ ተከትሎን በመምጣት ከሰሞኑ እንደታየው በመላ ሀገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጥ የግድ ሆኗል። “ወደፊትም በተመሳሳይ መንገድ መቀጠል ይቻላል ወይ?” የሚለው በጣም አሳሳቢ ነው። “ችግሩን እንዴት በዘላቂነት መቅረፍ ይቻላል?” ለሚለው ጥያቄም እኔ መልስ የለኝም። ከእኔ ይልቅ ይህን ጥያቄ መመለስ ያለባቸው ድርጊቱን የጀመሩት አካላት ናቸው።

ስለዚህ ጥያቄው “ከሁለት አመት በፊት የፈተና ወረቀቱን ኢንተርኔት ላይ ያወጡት እነ ጃዋር ዛሬ ላይ ችግሩን ለመግታት ወይም ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሄ ሃሳብ አላቸው ወይ?” የሚለው ነው። በተግባር እንዳየነው መልሱ በአጭሩ “የላቸውም!” ነው። አያችሁ… “ብሔርተኝነት የማይቆጣጠሩትን ውሻ ማሳደግ ነው!” የምለው ለዚህ ነው። “ተው! ይሄ ነገር ከተጀመረ መጨረሻው የከፋ ነው!” እያልን ስንለምናቸው በማንአለብኝነት የጀመሩት ጣጣ ይሄው ዛሬም ድረስ ተከትሎን መጥቷል። ችግሩን በመፍጠር ረገድ ግንባር ቀደም የነበሩት ሰዎች ይሄው ዛሬ ጥጋቸውን ይዘው ተቀምጠዋል።