የህወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሙሉ መግለጫ ምን ይላል?

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ. ም አጠናቆ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። መግለጫ የሚከተለው ነው።

ምንጭ:- BBC|አማርኛ

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐምሌ 2/2011 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ በቅርቡ ባጋጠመው የከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ግድያን መነሻ በማድረግ በአገራችን እያደገ እየመጣ ያለውን ሁለገብ ችግርና እሱን ተከትሎ ወደፊት ሊያጋጥም የሚችለው አጠቃላይ ሁኔታ፤ ለሀገራችን ና ለክልላችን ያለውን ትርጉም በመተንተን በአስቸኳይ ሊፈጸሙ ይቸባቸዋል ያላቸውን ወሳኝ አቅጣጫዎችን እና ውሳኔዎችን አስቀምጧል።

በአሁኑ ወቅት የአገራችንን ህልውና ከመጥፎው ወደ ባሰ ሁኔታ ሊወስድ የሚችል በመጠኑና ስፋቱ እጅጉን አሳሳቢ የሆነ ሁኔታ ላይ ደርሰናል።

በየጊዜው እየተከማቸ የመጣ፤ በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የአገራችንን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከት አደጋ እየተበራከተ፣ ከቀን ወደ ቀንም የዚህ አደጋ ፍጥነት እየጨመረ መጥቶ በቅርቡ የተቀነባበረና ረጅም ዝግጅት የተደረገበት በአገራችን ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችና የአማራ ክልል አመራሮችን በግፍ ወደ መግደል ደረጃ ላይ ደርሷል።

ትናንት የሀገራችንን ህልውናና ክብር አሳልፈው የሰጡ፤ የኢትዮጵያን መበታተን እውን ለማድረግ ቀንና ሌሊት አንቀላፍተው የማያውቁ ኃይሎች በለውጥ ስም ግንባር በመፍጠር አሰላለፍ በማይለይ ሁኔታ ሁሉም ተደበላልቆ አንድ ላይ እንዲኖር በመደረጉ፤ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተደራረበ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል።

በአንጻሩ ደግሞ፤ ለዚህች ሃገር ክብርና ህልውና ዕድሜ ልካቸውን የታገሉት የሚታደኑበት፣ የሚታሰሩበትና ጥላሸት የሚቀቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በሰላም እጦት ህዝቦች እንዲሰቃዩ፣ በማንነታቸው ምክንያት ዜጎች ህይወታቸውን እንዲያጡ፣ እንዲሳቀቁ፣ መጠለያ አጥተው ፀሐይና ብርድ ላይ እንዲጣሉ፣ በዚህች ሃገር ታሪክ ላይ ታይቶ የማይታወቅ ግጭትና በሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል የተበራከተበት፣ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ያልተቻለበት፣ ሃገር ጠባቂ አጥታ የጽንፈኞች መፈንጫ እየሆነች ፀረ ሕገ-መንግሥትና የፌደራል ሥርዓት የሆኑ ጫፍ የረገጡ የትምክህት ኃይሎች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ህወሓት የትምክህት ኃይል ሲል፤ የህዝብን መብትና ጥቅሞችን ረግጠው ስስታም ፍላጎቶቻቸውን ማስፈፀም የሚፈልጉ ኃይሎችን እንጂ የህዝብ ነው ብሎ አያውቅም ሊልም አይችልም። በማነኛውም መመዘኛ ትምክህተኛ የሚባል ህዝብ የለም። የሁሉም ህዝቦች ፍላጎትና ምኞት አንድ ነው።

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልImage copyrightANADOLU AGENCY

ወዳጅም ጠላትም ማወቅ የሚገባው ህወሓት ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ ለህዝብ ከፍተኛ ክብር የሚሰጥ ህዝባዊ እምነት ይዞ የሚታገል ድርጅት ነው። ባለፉት ጊዜያት ከአማራ ህዝብ ጋር ሆኖ ፀረ ትምክህትና ገዢዎችን በአንድነት የታገለና የበለጠ መስዋዕትነት የከፈለ ድርጅት ነው። ስለሆነም የአማራን ህዝብ ትምክህተኛ ማለት የሚችል ድርጅት አይደለም።

ነገር ግን፤ እነዚህ ፀረ ህዝብ የትምክህት ኃይሎች የሚፈልጉትን የድሮ ህልማቸውን ለማስፈፀም ሲሉ የአማራን ህዝብ ትምክህተኛ ተባልክ በማለት እያደናገሩ ነው። በአማራው ህዝብ ስም እየነገዱ ያልተባለውንና ያልሆነውን እንዲህ ተባልክ እያሉ እንደመዥገር ተጣብቀው ሊመጡት ጥረት እያደረጉ ነው። ቢሆንም ግን የአማራ ህዝብ እንደማነኛውም ህዝብ ለሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ ብሎ መስዋዕትነት በመክፈል አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና የነበረውና ያለው ህዝብ ነው።

ተጀምሮ የነበረው ተስፋ የሚሰጥ ልማትና እድገት አሁን መሪ አጥቶ ቁልቁል መውረድ የጀመረበትን ሁኔታ እያየን ነው። የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ከማንኛውም ጊዜ በላይ የዚህችን ሃገር ሰላምና ደህንነት መጠበቅ አልቻሉም። የእነዚህ መሪዎች ግድያ የሚያረጋግጠው ሃቅ ቢኖር፤ የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እየተቸገረ፣ በግፍና በጭካኔ የስልጣን ጥማታቸውን ማርካት የሚፈልጉ የትምክህት ኃይሎች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው የዚህች ሃገር ህዝቦች ዋስትና የሆነውን ሕገ መንግጅትና የፌደራል ሥርዓቱን ለማፍረስ በጠራራ ፀሐይየሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ እየታየ ነው።

በእንዲህ ያለ ሁኔታ፡ በየቀኑ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለመገመት በሚያስቸግር ደረጃ ላይ ተደርሷል። የአገራችን ሁኔታ እንዲህ ወዳለው ደረጃ መድረሱ እየታወቀ በግልጽ የተፈፀመውን የከፍተኛ መሪዎችን መግደልና በቀላሉ ሥርዓት የማፍረስ ተግባርን የመኮነንም ሆነ የጠራ አቋም በመያዝ ትግል እየተደረገ አይደለም።

ይልቁንም ሁሉም የለውጡ መሪዎች ነበሩ እየተባለ ይህን እኩይ ተግባር እንዲቀጥል የሚያደርግና እዚሁ ላይ እጅ የነበራቸው አካላት ተጠያቂ እንዳይሆኑ ሆን ተብሎ ለመሸፋፈን ካለሃፍረት ጥረት እየተደረገ ነው። ሌላው ቀርቶ የዚህችን ሃገር ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሐላፊነት የተሸከሙ የፀጥታና የደህንነት አካላት በተፈፀመው ጥቃት ላይ ያለባቸውን ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መንገድ እየተሰራበት አይደለም።

ይህ ሁኔታ የሃገራችንን ህልውና ወደከፋ አደጋ እያስገባ መሆኑን በመገንዘብ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀደም ብሎ ለይቶ ያስቀመጣቸውን የትግል አቅጣጫዎችን በማጠናከር በቅርቡ የተከሰተውን ሁኔታ መነሻ አድርጎ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

  • 1. በጀግኖቹ ከፍተኛ የሃገር መከላከያ አመራሮች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ከማሰብ እስከ መተግበር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የነበሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ሃገራዊ በሆነ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ፣ የጸጥታና ደህንነት አመራሮች በዚሁ ሴራ ላይ በነበራቸው ሚናም ሆነ ተገቢውን ሐላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ባጋጠመው ጥፋት ተጠያቂዎች እንዲሆኑ፣ የዚህ ምርመራ ሂደትና ውጤትም በየጊዜው ለኢትዮጵያ ህዝቦች ግልጽ እንዲሆን የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።

  • 2. በአሁኑ ወቅት ሀገር እየበተነ ያለው ከዚህም ከዚያም የተሰባሰበው የትምክህት ኃይል ነው። ይህ ኃይል ዕድል አግኝቶ እንደፈለገ እንዲፈነጭ እያደረገ ያለው ደግሞ አዴፓ ነው። በመሆኑም፤ አዴፓ ባጋጠመው ጥፋት ላይ በአጠቃላይ፣ በተለይም ደግሞ በድርጅቱ አመራሮች ላይ ባጋጠመው ግድያ ላይ በዝርዝር ገምግሞ ወደ ተጠያቂነት እንዲሸጋገር እንዲያደርግና አቋም እንዲይዝ ከዚህም ተነስቶ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል።

  • ከዚህ በተጨማሪም የውስጥ ችግርን ለመሸፈን ሲባል ጥፋቱ የሦስተኛ አካል እጅ አለበት፣ ረጃጅም እጆች ያሉበት ነው እያሉ ህዝብን ማደናገር ሊቆም ይገባል። እንዲህ እያሉ መኖር እንደማይቻል ህዝብም ተገንዝቦታል። ስለዚህም አዴፓ ሁሉንም ውስጣዊ ችግሮቹን በዝርዝር ገምግሞ ግልጽ አቋሙን እንዲያስታውቅ ጥሪ እናቀርባለን። ይህን ማድረግ ካልቻለ እንዲህ ካለው ኃይል ጋር አብሮ ለመስራትና ለመታገል እንደሚቸገር ሊታወቅ ይገባል።

  • 3. እስካሁን ድረስ ያጋጠመው መሰረታዊ ችግር በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የአሰላለፍ መደበላለቅና በጠራ ውግንና ላይ የተመሰረተ ትግል እየተተወ፤ ሁሉም ዓይነት ጥገኛ እና ደባል አመለካከቶችን ተሸክሞ የሚኖር ድርጅት እየሆነ በመምጣቱ ነው። ስለሆነም የሀገራችንን ህልውናና ደህንነት ለማስጠበቅ ኢህአዴግ ወደተለመደውና ወደሚታወቅበት ባህሪና እምነት ተመልሶ፤ ከጎራ መደበላለቅ የጠራና በግልጽ ውግንና ላይ የተመሰረተ ትግል እንዲያካሂድ እና በመጪው ዓመት በሕገ መንግሥታችን መሰረት እንዲካሄድ የሚገባውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ እንደ ግንባርና እንደ መንግሥት አቋሙን ለኢትዮጵያ ህዝቦች ግልጽ እንዲያደርግ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሳስባል።

  • 4. የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እና የሃገር ሉዓላዊነትን ከማነኛውም አደጋ ለመከላከልና ለመጠበቅ የተሰጣችሁን ሕገ መንግጅታዊ ኃላፊነት ከማነኛውም ግዜ በላይ ውስጣዊ አንድነታችሁን በማጠናከር የሃገራችሁን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ግዴታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እያቀረብን፤ ይህን ለመፈጸም በምታደርጉት ትግል ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አሁንም እንደ ሁልግዜው ከጎናችሁ በመሆን በጽናት እንደሚታገል ያረጋግጥላችኋል።

  • 5. ህወሐት እንደ አንድ ሕገ መንግሥታዊና ፌደራላዊ ኃይል ሕዝብንና ሀገርን ለማዳን ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ሕገ መንግሥታዊና ፌደራላዊ ኃይሎች ጋር ሰፊ መድረክ ፈጥሮ ለመታገልና በአስቸኳይ ወደ ተግባር ለመሸጋገር የህወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ ወስኗል።

  • 6. በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉት የክልል እንሁን ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሊፈቱ ይገባል። ከዚህ ውጪ የህዝብን ጥያቄ በኃይል ወይም በሌላ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ፍጹም ተቀባይነት የለውም።

  • 7. የፌደራሉ መንግሥት በዚህች ሀገር አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ሕግና የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጥ፣ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሳይሸራረፍ በጥብቅ እንዲተገበር የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አሁንም በድጋሚ ያሳስባል።