የኢህአዴግ የውስጥ ቁርሾ ሀገር ሳያፈራርስ በቤተሰብ ወግ በግልፅ እንወቃቀስ!!

አሁን ያለንበት ሀገራዊ እውነታ ለሀገራዊ መግባባት አስቸጋሪ ነው:: የክልል መንግስታት እንኳ እርስ በርሳቸው መተማመን የሌላቸው ከመሆኑ አልፎ በተወሰኑ ክልሎች መሀከል የፖለቲካ ፍጥጫ (political stalemate) የሚታይበት ሁኔታ ነው ያለው:: ከሰሞኑ ህወሓት እና አዴፓ ባወጧቸው መግለጫዎች አንዳቸው ሌላቸውን የወቀሱበት ድርጊት ከተራ ወቀሳ አልፎ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊትና መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ምስክር ሁኑልኝ በሚል የገቡበት ‘የመግለጫ ጦርነት’ አካሄድ የጦርነት ከበሮ ከመደለቅ አይተናነስም። አዴፓና ህወሓት/ትህነግ የንትርካቸው (escalated standoff) መነሻ በህወሓት መግለጫ የተጠቀሱት ወቅታዊ ክስተቶች (በሀገሪቱ በቅርቡ የተደረጉ የከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያዎች) ቢሆኑም በዋናነት ግን ከድሮውኑም ሳይወራረድ ተማዞ የመጣው ድርጅታዊ ቁርሾአቸው ነው ክላሽ-ቀረሽ የቃላት ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው:: ታዲያ ወደዚህ ረብየለሽ ንትርክ መግባታቸው በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ላይ የሚያመጣው አላስፈላጊ የሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መሻከር ሲያልፍም የሁለቱን ክልሎች ወንድማማች ህዝቦች ወደ አጠቃላይ ግጭት ሊያስገባ የሚችል ሁኔታ (scenario) መፍጠራቸው ደንታ የሰጣቸው አይመስልም::

የኦዴፓው የዶ/ር አብይ ማዕከላዊ መንግስት በበኩሉ የሁለቱን እሰጣ-ገባ ባላየ አልፎ በአንድ ጎኑ የመፍረስ ጫፍ ላይ ቢሆንም ለማዕከላዊ ስልጣኑ ማሰንበቻ ወሳኝ ድጋፍ የሚሆነውን የደቡብን ክልል ደህዴን በመታደግ በሌላ ጎኑ ደግሞ ለክልሉ የተለያዩ ህዝቦች በከፊል ራስገዝ አስተዳደር ህገመንግስታዊ ማዕቀፍ የሁሉንም ህዝቦች የክልል የመመስረት የህልውና ጥያቄዎች በእኩልነት የማስተናገድና ግዜውን የጠበቀ መልስ በመስጠት ሁለት አማራጮች የተወጠረ ይመስላል:: በዚህ ሁሉ ሀገር እሳት ላይ ተጥዳ መፃኢ እጣ ፈንታዋን በሰቀቀን በመጠባበቅ ላይ ነች:: አሁን ላይ ባለንበት የገራችን ነባራዊ የፖለቲካ እውነታ አንፃር ለሀገሪቱ ህልውና የሚያሰጋት የህዝቦችዋ እርስ በርስ አለመተማመን ሳይሆን ሀገሪቷን የሚመሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ለራሳቸው የድርጅት ህልውና ሲሉ ብቻ የህዝብን የህልውና ጥያቄዎች በፖለቲካ ሽረባ የማዳፈንና ሰፊውን ህዝብ እኔ አውቅልሀለው በሚል ንቀት የተሞላበት አምባገነናዊ ስሌት ወደ አላስፈላጊ ግጭት የመክተት አባዜ ነው::

አሁን ባለው ጠ/ሚር አብይ አህመድ የሽግግር መንግስት የተዋቀረ/የሚዋቀር ብሔራዊ መግባባትን (national concensus) በግንባር ቀደምትነት የሚያቀነቅን (champion የሚያደርግ) ከገዢው መንግስት ተፅዕኖ ነፃ የሆነ አካል ጠንክሮና ራሱን ችሎ ነጥሮ ባልወጣበት ሁኔታ የተፈጠረው ስልጣን ላይ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች መፋጠጥ (stand-off) ፍሬን በጥሶ በክልሎች መሀከል ወዳለ የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት እንዳይሸጋገር ያሰጋል:: በሌላ መልኩ ደግሞ ከፖለቲከኞቹ በተቃራኒ አቅጣጫ ሊባል በሚችል መልኩ የተሰለፉት የየብሔሩ አክቲቪስቶቻችንም ቢሆኑ በነፃነት እርስ በርስ ተነጋግረው ወደ ጋራ መግባባት ሊመጡ የሚችሉበት መድረክ (platform) ባለመፈጠሩ ሁሉም የየራሱን ብሔር ወደ ቀኝ ዘመም የፖለቲካ እይታ እየነዳና ሌላኛውን በጠላትነት እያስፈረጀ ያለበት ሁኔታ እየተፈጠረ ያለውን ክፍተት (the already widening rift) የበለጠ እንዳያሰፋው ያሰጋል:: ከዚህ ከገባንበት ብሔራዊ የፖለቲካ ቀውስ መውጫ ብቸኛው መንገድ ሳይረፍድብንና ግዜ ሳለ በ11ኛው ሰዓትም ቢሆን ለብሔራዊ መግባባት በሰከነ መንፈስ እንደ አዋቂ መነጋገር (having the adult conversation of the Eleventh hour) ብቻ ነው::

ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ግዜ የማይሰጥ አንገብጋቢ ጉዳይ ቢኖር በየራሳቸው ብሔር ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው አክቲቪስቶች: የታሪክ ምሁራን: የፖለቲካ ልሂቃን እና የሀገር ሽማግልዎችን በአንድ መድረክ አሰባስቦ ሀገር አቀፍ ስርጭት ባላቸው የብሮድካስት ሚዲያዎች (ቴሌቪዥንና ሬድዮ ጣቢያዎች) በቀጥታ ስርጭት በማወያየት መጀመር ነው:: እስከ አሁን ሲደረግ የነበረው ሁሉም የኢትዮጵያ ምሁራን መሆናቸው ተረስቶ የኦሮሞ ምሁራን: የአማራ ምሁራን: የትግራይ ምሁራን እየተባለ በአብዛኛው የዛኑ ብሔር ብሶት በሚያቀነቅኑ የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ለዛው ብሔር ‘ምሁር’ የአየር ሰዓት በመስጠት የተለመዱ ‘ምሁራዊ’ ትንተናቸውን ለህዝብ መጋት እንጂ ግልፅና ብሔራዊ መግባባትን አላማው ያደረገ አካታች ውይይቶች ሲደረጉ አላየንም:: ሁሉም በየራሱ ብሔር ሚዲያ ላይ እየወጣ ከማላዘን ውጭ ቆም ብሎ የጋራ መግባቢያ ነጥብ (common ground) ሲፈልግ ወይንም እንደዛ አይነት ጉዳይ ላይ ሲያተኩር አላየንም::

በመንግስት ደረጃም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ከተወሰኑ ወራት በፊት በመንግስት በአዋጅ የተቋቋመ ኮሚሽን ቢኖርም ጎልተው የወጡ ውጤቶች ብዙም እየታዩ አይመስልም:: በአጠቃላይ ግን ብሔራዊ እርቅና መግባባት ላይ የሚሰራ ነፃ ተቋም በማቋቁምና (ወይንም አሁን ላይ በስራ ላይ ያለ ተመሳሳይ አላማና ሀላፊነት የተሰጠው ተቋም ካለም ከፖለቲካ ተቋማት ነፃ በማድረግ) አስፈላጊው መንግስታዊ ድጋፍ ሁሉ እየተደረገለት ህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን መርህ ላይ በተመሰረተ አካሄድ ወደ ብሔራዊ እርቅና መግባባት እንዲያመሩ እንዲሰራ ማብቃት ግዜ የማያስቀጥር ጉዳይ ነው:: በዚህም ሂደት ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ቱባ ባህላዊ እሴቶቻችንን ተቋማዊ ይዘት ባለው መንገድ የሚያጎለብትና ከዘመናዊና ሳይንሳዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ጋር በማቆራኘት ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ የግጭት አይነቶችን ቀድሞ መተንበይ (predict ማድረግ): እንዲሁም በዘላቂነት የሚፈቱበትን ሂደት በህግ ማዕቀፍ በማካተት ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው (institutionalize) የማድረግ ስራዎችን መስራቱ ዘላቂ መፍትሄን ከማምጣት አንፃር ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል:: ቸር እንሰንብት!!

One thought on “የኢህአዴግ የውስጥ ቁርሾ ሀገር ሳያፈራርስ በቤተሰብ ወግ በግልፅ እንወቃቀስ!!

 1. Dange

  On Mon, Jul 15, 2019, 2:02 PM Ethiopian Think Thank Group wrote:

  > Raphael Addisu posted: ” አሁን ያለንበት ሀገራዊ እውነታ ለሀገራዊ መግባባት አስቸጋሪ ነው:: የክልል
  > መንግስታት እንኳ እርስ በርሳቸው መተማመን የሌላቸው ከመሆኑ አልፎ በተወሰኑ ክልሎች መሀከል የፖለቲካ ፍጥጫ
  > (political stalemate) የሚታይበት ሁኔታ ነው ያለው:: ከሰሞኑ ህወሓት እና አዴፓ ባወጧቸው መግለጫዎች
  > አንዳቸው ሌላቸውን የወቀሱበት ድርጊት ከተራ ወቀሳ አልፎ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊትና መላ”
  >

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡