የገባንበት ብሔራዊ የፖለቲካ ቀውስና ምንጮቹ!!

ኢትዮጵያዊያን በዘመናት መሀከል እንደ ሀገርም ባይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ህዝቦች መሀከል ችግሮቻችንን በተለያዩ እድሜ ጠገብ ባህላዊ ሸንጎዎችና: በሀገር ሽማግሌዎች ጉባኤ በሰከነ መንፈስና በምክንያታዊነት እየተነጋገሩ ሲፈቱና በነፍስ በሚፈላለጉ መሀከል ሳይቀር ሰላምን ሲያሰፍኑ ኖረዋል:: ሌላው አለም ላይ ብዙም የማይታወቀው ይህ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ልዩነቶች በመነጋገር የመፍታት ሀገራዊ እሴት ከአለም ህዝቦች ለየት የሚያደርገን አንዱና ዋነኛው የአብሮነታችን እሴት ነው:: እንደ እኔ እይታ እነዚህ ውድ ሀገራዊ እሴቶች ባይኖሩን ኖሮ እንደ ፖለቲከኞቻችን አያያዝ እስካሁን እንደ ሀገር መቀጠል የምንችል አይመስለኝም:: ከዚህ በተረፈ ደግሞ ህዝባችን አንዳንድ ግለኝነትና አድርባይነት የተጠናወታቸው ፖለቲከኞቻችን የሀገራችን ሰው “ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች” እንዳለው ሊሰብኩን እንደሚሞክሩት በዘርና በጎሳ የተለያየን ህዝቦች ሳንሆን በባህል የተጋባን በአብሮነት የተሳለስን በወንድማማችነት የተፋቀርንና በዘመን እርዝመት በጋብቻ የተጋመድን አንድ የሆንን ህዝቦች ነን:: እውን እስኪ በዚህ ትውልድ የሚኖርና በቅርብ እርቀት በሚገኝ የዘር ግንዱ ቢያንስ ከአምስት የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች በጋብቻ ያልተዛመደ የዘር ሀረጉን ከሶስትና አራት ብሔሮች የማይመዝ ኢትዮጵያዊ አለ?! ይህን እውነት ለመረዳት የተለየ በጥናት ላይ የተደገፈ መረጃ ሳያስፈልገው ወደየቤተሰባችን የዘር ሀረግ ታሪክ መመልከት በቂ ይመስለኛል::

ያልጨረስነው የሀገረ መንግስት ግንባታና የስርዓተ መንግስት በየጊዜው መቀያየር

ሀገራችን ኢትዮጵያ እስከ አሁን በዛ ባሉና በተለያዩ የስርዓተ መንግስት ሂደቶች አልፋ ነው አሁን ላለንበት ስርዓተ መንግስት የበቃችው:: ታላቋን አሜሪካ እንኳ ብንወስድ በአንድ የስርዓተ መንግስት አወቃቀር ላለፉት ሁለት መቶ አመታት በላይ ወደተሻለች ታላቅ ሀገርነት ራሷን ስታዘምን ቆይታለች:: እኛን የወሰድን እንደሆነ ግን በዚህ ግዜ ውስጥ ብቻ በርከት ካሉ የግዜውን ገዥ የፖለቲካ አስተሳሰብ (the dominant political narrative or thinking of the day) ብቻ መሰረት ባደረገ አስተሳሰብ ላይ በተመሰረቱ መርሆዎች እየተነሳን የተለያዩ ይሆኑናል ያልናቸውን ስርዓተ መንግስቶች ሁሉ ስናስተናግድ ዛሬ ላይ ደርሰናል:: በእርግጥ በሀገረ መንግስት ምስረታ (state formation) ከአብዛኛው የአለም ክፍል አንፃር ስንታይ ቀደምት የሆንነውን ያክል የፖለቲካ ማህበረሰባችን አስተሳሰብ አብሮ ሊያድግ ባለመቻሉ እስከ አሁን ሀገረ መንግስት ግንባታውን (state building) መጨረስ አልቻልንም:: የዚህ እውነታ የቅርብ ግዜ ተፅዕኖ (short lived consequence) የሺህ አመታት ወንድማማች ህዝብ የሆነውንና በጋብቻ ሳይቀር ከቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለዘመናት የተሳሰረን የኤርትራን ህዝብ ያሳጣን ሲሆን አሁን ላለንበት ሀገራዊ የፖለቲካ ቀውስም (national political crisis) ቢሆን የዳረገን ይኸው በዘመናት መሀከል መጨረስ ያልቻልነው የሀገረ መንግስት ግንባታና ተያያዡ የብሔረ መንግስት ግንባታ (nation building) የጠራ አቅጣጫ አለመያዝና የዚሁ ውጤት የፈጠረው አንዱ ክፍተት ነው:: በተጨማሪም በነባራዊነት በትውልዳችን በተለይም ደግሞ የፖለቲካ ማህበረሰባችን ዘንድ በጉዳዩ ላይ የጠራ ግንዛቤ ያለመኖርና የፖለቲካ ልሂቃኖቻችንም (political elites) ከነበረባቸው ደካማ የማስረፅ አቅምና ዝንባሌ አንፃር በፖለቲካ ማህበረሰቡ ዘንድ በየጊዜው ከሚፈጠረውና ጎልቶ ከወጣው ጥራዝ ነጠቅ አመለካከትና እውቀት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር ይመስለኛል::

የአንድ ህዝብ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስነልቦና (sociopolitical psyche) እንደ ደራሽ ወንዝ መንገድ ላይ ያገኘውን ሁሉ እያዘለ በስተመጨረሻ በባዕድ ነገር መድረሻውን የሚሞላና የራሱን መንገድ የሚዘጋ ሳይሆን የማንነቱ መገለጫ የሆኑ ዋናና ማዕከላዊ የሆኑ እሴቶቹን (core values) ሳይጥል ወይም በባዕድ ነገሮች ሳይበርዝና ሳያዳፍን ጠብቆ ይልቁንም የበለጠ እያጎለበተ የሚዘልቅ ነው:: ይህ ማለት ደግሞ የአንድ ህዝብ ወይም ማህበረሰብ ዋና የማንነቱ መገለጫዎች (ለዚህም መሰረት የሆኑት ቋንቋውንና ባህሉን በዋናነት) በዘመናት መሀከል ብዙም ለውጥ የሚታይባቸው አይደሉም:: ከዚህ እውነታ አንፃር ይህን ለሺህ ዘመናት በተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እርስ በርሱ የተጋመደን ህዝብ አንድ ላይ በእኩል ሚዛንና በጋራ ተስፋና ጥቅም ላይ በተመሰረተ ስርዓተ መንግስት ለማስተዳደር በይበልጥ አካታች የሆነና ዘመን ተሻጋሪ ስርዓተ መንግስት ለመከተል መሰረት መሆን የነበረበት በዋነኛነት የማንነቱ ማዕከል የሆነው የየማህበረሰቡ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስነልቦና እንዲሁም ባህላዊ እሴቱ እንጂ በግዜው ገዥ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብና ትርክት መሆን አልነበረበትም:: ይህ በየዘመናቱ ሊቀያየር የሚችል ነገር በመሆኑና ከአንደኛው ትውልድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ወደ ሌላኛው ትውልድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የሚለያይ በመሆኑም ጭምር:: ለዚህም ነው በየጊዜው ከዜሮ መጀመር (starting from scratch) እንደ ሀገር የፖለቲካ ማህበረሰባችን አይነተኛ መገለጫ ሆኖ የቆየው::

ህገመንግስቱና የስርዓተ መንግስቱ ተያያዥ ችግሮች

ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የከረምንበትና ቅርፅና ይዘቱን እየቀያየረ ወደ ከፋ ደረጃ ሲሸጋገር የቆየው ብሔራዊ የፖለቲካ ቀውስ ችግሩ ከየት መጣ ብለን የጠየቅን እንደሆነ ብዙ ውስብስብና ተያያዥ መነሻ ምክንያቶች ሊኖሩት ቢችሉም በዋነኛነት አሁን ካለው ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ ስርዓት (Ethnic Federalism) የመነጨው ስርዓተ መንግስት የፈጠረው ክፍተት ውጤትና ላለፉት ሁለት አስርታት በማዕከላዊነት ሲዘወር የቆየው የኢኮኖሚ ስርዓት ውጤት ነው:: በተለያዩ ግዜዎች በሀገር ደረጃ ከተደረጉ የምሁራን ምክክሮች መገንዘብ እንደቻልነውም ቢሆን ፌዴራላዊ ስርዓተ መንግስት ለኢትዮጵያ የተሻለ አማራጭ ቢሆንም ብሔርን መሰረት ያደረገ መሆኑ ግን ሀገሪቱ አሁን ለገባችበት ብሔራዊ የፖለቲካ ቀውስ የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከቱ የማይካድና ገሀድ የወጣ ሀቅ ነው:: በፌዴራል ስርዓት ላይ የተመሰረተ ህገ መንግስት ያላቸውን እንደ አሜሪካ ያሉ ሌሎች ሀገሮች ህገመንግስቶችን ያየን እንደሆን የኛ ከነሱ ጋር እንኳ ሲነፃፀር የራሱ መሰረታዊ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል:: በተለይም ደግሞ በዚሁ ህገመንግስታችን እውቅና የተቸረው ብሔርን መሰረት ያደረገው ፖለቲካዊ አደረጃጀት:: በዋናነት ግን አሁን ላለንበት ሀገራዊ የፖለቲካ ቀውስ የህገመንግስቱ ሚና ለፖለቲካ ስርዓቱ (ለስርዓተ መንግስቱ) ባለፉት ሁለት አስርታት ውስጥ የተፈጠረውን የብሔር ፅንፈኝነት ኮትኩቶ አሁን ላለበት ደረጃ ለማድረስ በተዘዋዋሪነት ፈቃድ (indirect license) የሰጠበት ሁኔታ ይመስላል::

ያለንበት ስርዓተ መንግስት ያሉበት ውስብስብ ችግሮች መቀረፍ ካለባቸው ህገመንግስቱ ላይ መሻሻል ካለባቸው ክፍሎች ጀምሮ ህዝባዊ ፍላጎትንና የጋራ ሀገራዊ እሴቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ደረጃ በደረጃ ለህዝብ ውይይት በማቅረብ ህገመንግስቱ ራሱ ባስቀመጣቸው የማሻሻያ ህጎችና ህገመንግስታዊ አካሄዶች የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዱ አስፈላጊ ጉዳይ ይመስላል:: በእርግጥ አሁን ባለንበት ሀገራዊ ነባራዊ እውነታ (ሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት በማይታይበትና ከለውጡ ጋር በተያያዘ የጋራ ሀገራዊ ፍኖተ ካርታ በሌለበት ወይም ካለም ወደ ህዝቡ ባልደረሰበት ሁኔታ) ይህን ማድረግ ይቻላል ወይ የሚለው በውስብስብ ሀገራዊ ችግሮች ለተጠላለፈው የ’ለውጡ’ መንግስት ትልቅ ራስ ምታት ነው:: የዚህ ፅሁፍ ዋና ሀሳብም በእርግጥ የህገመንግስት ማሻሻያ አስፈላጊነትን ለመጠቆም ወይም ለማንሳት ባለመሆኑና ይኽም ጉዳይ ከዚህ ፅሁፍ ዳራ ውጭ (beyond the scope of this article) በመሆኑ ጉዳዩን እዚሁ ጋር ልቋጨው:: በአጠቃላይ አሁን ላይ መመለሻ የሌለው ጫፍ (no turning point) ላይ የደረስንበት የሚመስለውን የብሔር ፅንፈኝነት ግን የዜጎችን ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ከተሳነው የተወሳሰበ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ችግር የመነጨም ጭምር መሆኑን ለይተን ለማየት መሞከር እንደ ሀገር መፍትሄ ለማምጣት የምናደርገውን ጉዞ አላስፈላጊ በሆነ መልኩ ረጅም ያደርገዋል::

ብሔራዊ የፖለቲካ ቀውስና ነባራዊው ሀገራዊ የፖለቲካ እውነታ

አሁን ባለንበት የሀገራችን ፖለቲካዊ ምህዳር እውነታ በፖለቲካ ተቋማት ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች (politicians within the establishment) በህዝብ ዘንድ እውቅናቸውን ባያጡ እንኳ በአብዛኛው ተደማጭነት የሌላቸው (even if they haven’t lost their legitimacy they surely have very small public confidence if any) ሲሆን ህዝቡ በአብዛኛው የሚያዳምጠውና እምነት እየጣለበት ያለው የብሔር ‘አክቲቪስቶቹ’ ላይ እየሆነ የሄደበት እውነታ ነው እየተፈጠረ የመጣው:: በእርግጥ የዚህ አሉታዊ ተፅዕኖ በተፎካካሪም ሆነ በገዢው የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ ባሉ ‘የዳቦ ፖለቲከኞች’ ዘንድ ሲሆን ሲሆን የተሻለ ስልጣን መቆናጠጫነት አሊያም ደግሞ እንደ መሰንበቻነት መላ ተወስዶ ከሰሞኑ የብሔር ፅንፈኝነት ባህል (norm) እየሆነ የሄደበት እውነታ አሁን ለገባንበት ብሔራዊ የፖለቲካ ቀውስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል::

እኔ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም’ ብዬ ማመንን የምመርጥ አዎንታዊ አስተሳሰብ ያለኝ (Optimist) ነኝ:: ነገር ግን ዛሬ ላይ እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያ በጂኦግራፊያዊ ይዘትም ሆነ በህዝቦች (nations) ስብጥሯ የዛሬ 500 አመት የነበረች ኢትዮጵያ እንዳልሆነች ልብ ልንል ይገባል:: የዛሬ 30 አመትስ ቢሆን የነበረችው ኢትዮጵያ እኮ አሁን ያለችን ኢትዮጵያ አይደለችም:: ታሪክ በግልፅ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ባለፉት መቶዎች አመታት ብቻ በህዝቦች ስብጥሯ እየቀጨጨችና እና ጂኦግራፊያዊ ይዞታዋ እየጠበበች የመጣች መሆኑን ነው:: (History clearly shows us that Ethiopia has been shrinking in its geographic size and composition of nations over the past hundred years alone.) እናም እንደ ዳቦ ቅርጫ ተቆራርሳ ተቆራርሳ አሁን ወዳለን የባህር በር እንኳ የሌላት ቁራሽ ሀገርነት የተለወጠችው ኢትዮጵያችን የማትፈርሰው ‘መንግስተ-ሰማይ’ አይደለችም በዚሁ ከቀጠልን ማለቴ ነው:: ደግነቱ ግን ሁሌም ዘግይተንም ቢሆን ከወደ ቀልባችን ስለምንመለስ እየቆራረስናትም ቢሆን እስከዛሬ ቆይታለች:: ስለዚህ ተስፈኝነታችን ሁሌም ያለንበትን መሬት የወረደ እውነታ ከግንዛቤ ያስገባ ቢሆን መልካም ነው:: ቸር እንሰንብት!!