የደቡብ ክልል ህዝቦች የክልልነት ጥያቄዎችና አማራጮች!!

በደቡቡ ክልል በአንድ የክልል መዋቅር ስር ይተዳደሩ የነበሩ ህዝቦች (nations) የየራሳቸውን የክልል እንሁን ጥያቄዎች በየዞን ምክር ቤቶቻቸው በሙሉ ድምፅ አስወስነው ወደ ክልሉ ምክር ቤት ከላኩ ሰንበትበት ብለዋል:: ይህን ተከትሉ ክልሉን የሚመራው ደህዴን በክልሉ ዋና ከተማ ሀዋሳ የሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ‘ኢጄቶ’ ብሎ ራሱን በሚጠራው የሲዳማ ወጣቶች ስብስብ መበተን ከጀመረ በኋላ ለ10 ቀናት ያክል አዲስ አበባ ላይ ባደረገው ስብሰባ መግባባት ተስኖት እንደነበር የውስጥ አዋቂ ምንጮች ይጠቁማሉ:: ሆኖም ትላንት ድርጅቱ ስብሰባው ውጤታማ እንደነበር መግለጫ ቢያወጣም ይህንኑ ተከትሎ የደቡቡን ፖለቲካ በሚዘውሩት ወላይታ ሶዶ እና ሀዋሳ ከተማዎች ላይ የተለያዩ ድባቦች ተስተውለዋል:: ሀዋሳ ላይ ኢጄቶዎች ከተማዋ ውስጥ የደስታ ፈንጠዝያ አንደምታ የነበረው ድርጊቶች ሲያንፀባርቁ ከወደ ወላይታ አንዳንድ ከተሞችና የአከባቢው ተወላጅ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ የተለያዩ ተቃውሞዎች ተስተናግደዋል::

በእርግጥ የክልሉ መሪ ድርጅት የሆነው ደህዴን በመግለጫው “በክልል የመደራጀት ጥያቄን በተመለከተ የህዝቦች ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲነሳ የነበረው ከአንድ አካባቢ ብቻ ባይሆንም ጥያቄውን በጥናት ላይ ተመስርቶ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ድርጅቱ በአስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በወሰደው አቋም መሰረት በዝርዝር ህዝቡን ያሳተፈ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በጥናቱ የቀረቡ አማራጮችን በጥልቀት በመመርመር፣ የህዝቡን የጋራ ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጠውን አማራጭ በመውሰድ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች በሚመለሱበት አግባብ ላይ አቋም ተወስዷል። በክልላችን መላው ህዝብ ምክክርና ውይይት የሚያደርግበት ሆኖ በአንድ በኩል በጥናቱም የተገኘውን የክልሉ ህዝቦች አብሮ የመቀጠል ፍላጎትን ባከበረ በሌላ ጎኑ ደግሞ ጉባኤውን ውሳኔ ተግባራዊ ባደረገ መንገድ እና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የመምራት ኃላፊነት ለመወጣት ማዕከላዊ ኮሚቴው ተስማምቷል” ከማለቱ ውጭ ስለውሳኔው ዝርዝር መረጃ ለመስጠት አልፈለገም:: ሆኖም ግን ከነዚህ ክስተቶች የስብሰባውን አቅጣጫ መገመት አይከብድም:: የሆነ ሆኖ ግን እነዚህ የክልሉ ህዝቦች ጥያቄዎች በአንድ ስብሰባ ውሳኔ የሚያገኙ ሳይሆን ውስብስብና ምናልባትም ከሁለትና ሶስት አመታት በፊት ሊፈቱ የሚችሉ አይመስሉም::

ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ለማግኘት የኢትዮጵያን ህዝብ መጠየቅ ያለብን አንድ ጥያቄ ቢኖር ‘እውን በደቡብ ብሔራዊ ክልል ውስጥ በአንድ የክልል መዋቅር ስር ይተዳደሩ የነበሩና የራሳቸው ከፊል ራስገዝ ክልል የጠየቁ ህዝቦች ይኸው ህገመንግስቱ የቸራቸው መብት ቢከበርላቸው ለኢትዮጵያ አንድነት ስጋት ናቸውን?!’ የሚለውን ይመስለኛል::

በየትኛውም አለም የህዝብን ነፃ ፈቃድ በሀይል ጨፍልቆ አንድን ሀገር ሀገር የሚያደርጉ ህዝቦችዋን (nations) እኩልነት ሳያስከብሩና ሳያረጋግጡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሀገር እፈጥራለሁ ብሎ ማሰብ በአለም ላይ በታሪክ ሂደት ከተከሰቱ የሀገረመንግስት ምስረታና ቀጣይ ግንባታ ታሪካዊ ልምዶች ላይ ካለ የእውቀት ውስኑነት የሚመነጭ ነው:: እኛ ኢትዮጵያዊያን አንድ መሰረታዊ ችግር ያለብን ይመስለኛል – ከታሪካችን መማር አለመቻላችን ወይንም ደግሞ አለመፈለጋችን:: በእኔ እይታ የክልልነት ጥያቄ ያነሱ ህዝቦች አስተዳደራዊ የማንነት ጥያቄው በህዝቡ ፍላጎትና በህገመንግስቱ ማዕቀፍ (within the provisions of the constitution) ተመልሶላቸው በጠንካራ በከፊል ነፃ የሆኑ የጋራ የኢኮኖሚ ዞኖች (semi-independent common regional and sub-national economic zones) እንዲተሳሰሩ ቢደረግ የበለጠ ጠንካራ ሀገራዊ ኢኮኖሚና የበለጠ ጠንካራና አንድነቷ ከመቼውም ግዜ ይልቅ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን መገንባት ይቻላል::

የቅርብ ግዜ ታሪካችንን እንኳ የኋሊት ብንመለከት በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ወቅት የዛሬ 20 ዓመት ገደማ የተነሳውን የሲዳማ ህዝብን የክልልነት ጥያቄ በህገመንግስታዊ አካሄድና በፖለቲካ ድርድር የሁሉንም በጉዳዩ የሚነካ ወገን/ማህበረሰብ (populations affected) ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ያለመመለስ ውጤት ታፍኖ የቆየ ጥያቄ አቅጣጫውን በሳተ መልኩ ገንፍሎ ወጥቶ አምና ሀዋሳ ላይ በታሪካች አሳፋሪ የሆነ አሰቃቂ ክስተት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል:: አሁንም በታሪካችን ትንሽ ወደኋላ የሄድን እንደሆነ በአምባገነናዊውና ጨቋኝ የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ የህዝቦችዋ ጫንቃ ላይ የከበደው ቀንበር ኤርትራ ከቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የጋራ የሆነ future እንዳታይና በበቃኝ እንድትሰናበት ዋነኛው ምክንያት ነበር::

የአለማችንን በአንድ ወቅት ታላላቅና የብዙ ህዝቦች ስብጥር የነበሩ ሀገራት አሁን ላይ ግን ወደ ብዙ ትናንሽ ሀገርነት የተከፋፈሉ/የተሸነሸኑ ሀገራትን ታሪክ ስናይ በአብዛኛው የህዝቦቻቸውን እኩልነት ያረጋገጠ (ፍትሀዊና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ) የማዕከላዊ መንግስት ስርዓት ባለመኖሩና የተጨቆኑ የሀገራቸው ህዝቦች ከተቀረው የሀገሬው ህዝብ ጋር የጋራ future ማየት ስላልቻሉ የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን ራሳቸውን ችለው እንደ ራስገዝ ሀገር የመቀጠል አማራጭ ለመጠቀም መገደዳቸውን እናያለን:: ይህም የነዚህ ትላልቅ ሀገራት መጨረሻ ሆኗል::

በእርግጥ የትኛውም ህዝብ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር የአንድ ትልቅ ሀገር አካል ከመሆን ይልቅ ብዙም አቅም የሌለው ለማንኛውም የውጭ ጥቃትም ሆነ ጫና የተጋለጠ ትንሽ ሀገር መሆንን አይመርጥም:: ለዚህም ነው የአውሮጳ ሀገራት በእኛ የእድገትና ስልጣኔ ደረጃ እያሉ ተገነጣጥለውና ተለያይተው ሲያበቁ አሁን ወደ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብነት በአውሮጳ ህብረት ስር እየተሰባሰቡ የመጡት:: ይህንንም የመረጡት በአንድ ጠንካራ የጋራ ማዕቀፍ ስር በመሆን ከተቀረው አለም የሚመጡ አዳዲስና ነባራዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጫናዎችን በቀላሉ መቋቋም ስለሚችሉ ነው::

ወደ ሀገራችን አንገብጋቢ ጉዳይ ስንመለስ እኛ ብዙዎች ያላገኙት እድል አለን የዚህ ችግር ሰለባ ላለመሆን ከሌሎች የሰለጠኑ ሀገሮች የተሻሉ አሰራሮችን ልምድ በመውሰድ የተሻለች ሀገር የመገንባት:: ዋናው ሀገራዊ አንድነታችንን አስጠብቀን መቀጠል ነው:: ይህን ደግሞ በመርህ ላይ በተመሰረተና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የህዝቦችን የማንነት ጥያቄዎች በዘላቂነት የሚመልስ/የመለሰ ስርዓት በማረጋገጥ ነው:: ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው የተለያዩ ህዝቦችን የማንነት ጥያቄዎች በህገመንግስቱ አግባብ በማስተናገድ ሲሆን ህገመንግስቱ ይህን ለማድረግ በማያስችልበት አግባብ ደግሞ አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ አካታች የሆነና ለሁሉም ህዝቦች እኩል ዘብ የሚቆምና ፍትሀዊ የሆነ መጫወቻ ሜዳ (playfield) የሚፈጥር እንዲሆን በማድረግ ነው:: ምክንያቱ የየትኛውም ሀገር ህገመንግስት ህልውና መሰረት ህዝቦቿን በእኩል የህግ አግባብ ማገልገል ስለሆነ:: የኛው ደግሞ ይህን ማድረግ ያልቻልኩ እንደሆነ ብሎ ሊሻሻል የሚችልበትንም አግባብ አስቀምጦልናል:: ስለዚህ ከታሪካችን መማር ከቻልን የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት እንችላለን ባይ ነኝ::
ቸር እንሰንብት::