ከደህዴን የተድበዘበዘ መግለጫ በስተጀርባ የተሸረበው የፖለቲካ ሴራ ሲገለጥ!

የህወሓት ‘የጡት ልጅ’ የሆነው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብሔራዊ ክልል መሪ ድርጅት ደህዴን በአዲስ አበባ በባለቀይ ቦኔት የሪፐብሊኩ ልዩ ሀይሎች ጥበቃ መሽጎ ያካሄደው ስብሰባ በመጀመሪያ በደህዴን ስም በተለያዩ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ስልጣን የተቆናጠጡ ባለስልጣናትን ቀጣይ የስልጣን ገመድ እንዳይበጠስ የማድረግ ሲቀጥል ደግሞ የድርጅቱን ህልውና የማስጠበቅ ተልዕኮ ያነገበ እንጂ እወክለዋለው የሚለውን የክልሉን ህዝቦች መብት ማስጠበቅ እንዳልነበር ከውስጥ አዋቂ ምንጮች መረዳት ተችሏል::

ድርጅቱ ለ10 ቀናት ባደረገው ስብሰባው በክልሉ ባሉ የተለያዩ ህዝቦች የቀረቡ የክልል አደረጃጀት ህገመንግስታዊ ጥያቄዎችን በተለመደ የፖለቲካ ሽረባው ለመቀልበስ ጥረት እያደረገ መሆኑ ታውቋል:: ከሲዳማ ህዝብ ውጭ ያሉ ሌሎች የክልሉ ህዝቦች ህገመንግስቱ ባጎናፀፋቸውና በከፊል ራስገዝ የክልል አስተዳደር መዋቅር የመደራጀት መብታቸውን ተጠቅመው ያቀረቡት በክልል የመደራጀት ህገመንግስታዊ የህዝብ ጥያቄ ችላ በማለትና አማራጭ የፖለቲካ ውሳኔዎች በመጫን የስልጣን ገመዳቸውን የማስቀጠልና ተያያዥ ጥቅማቸውን የማስጠበቅ ህቡዕ አላማ ባነገበ ተልዕኳቸው የህዝቦችን የህልውና ጥያቄዎች እስከመጨፍለቅ ለመሄድ ያለማመንታታቸው የፖለቲካ ድርጅቱ ህልውናውን ለማስቀጠል ሲል ብቻ ምን ያህል ከህገመንግስታዊ አካሄድ ያፈነገጠ አምባገነናዊና ለህዝብ ጥቅም ያልቆመ እየሆነ እንደሄደ አሳብቆበታል::

ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ብለን የጠየቅን እንደሆነ ቀድሞውንም የክልሉን ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ተቆናጠው የነበሩት የሲዳማ ባለስልጣናት ከራሱ ከሲዳማ ዞን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ በመቀጠል በአንድ ወር ልዩነት ውስጥ የክልሉ ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ ልኮ ጥያቄውን ባነሳው የክልሉ ህዝብ ህዝበ-ውሳኔ እንዲያስደርግበት በሌሎች የክልሉ ህዝቦች በፅሁፍ የቀረቡ ጥያቄዎችን በተለያዩ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ስልጣኖችን የተቆናጠጡ የሲዳማ ብሔር ተወላጆችን የፖለቲካ ተፅዕኖና ጫና በመጠቀም አፍነው ሲያበቁ በህዳር ወር 2011 ዓ.ም. ለክልሉ ምክር ቤት የቀረበውን የሲዳማውን ጥያቄ ለህዝበ ውሳኔ በዛኑ በቀረበበት ወቅት ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሄድ በማድረጋቸው ነው:: ይህም የተቀሩት ከታህሳስ ወር ጀምሮ በሌሎች የክልሉ ህዝቦች (ዎላይታ: ጋሞ: ከንባታ: ሀዲያ: ጉራጌን ጨምሮ በሌሎች ህዝቦች) የቀረቡ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እዛው ክልሉ ላይ ታፍነው እንዲቀሩ የተደረገበት የፖለቲካ ሴራ መጀመሪያውኑም አሁን በክልላዊው ድርጅት ደህዴን የክልሉ ህዝቦች ህገመንግስታዊ መብት ላይ የተቃጣ የመጨፍለቅ ውሳኔ ሴራ አካል እንደሆነ መገመት አያዳግትም::

በሌላ ጎኑ ደግሞ ከሲዳማው የክልል ጥያቄ ጀርባ የእነ ኦቦ ጃዋር በግንባር ቀደም አቀንቃኝነት መሰለፍን ስናስተውል ከመጀመሪያውኑ የእነርሱ ‘የኩሽቲክ ስርወ-መንግስት (Dynasty)’ ቀመር ያለችባት ሽረባ እንደሆነች መገመት አይከብድም:: ኦዴፖም ቢሆን ለማዕከላዊ መንግስቱ ስልጣን ማደላደያ የደህዴን ጠንካራ ድጋፍ ስለሚያስፈልገው የደህዴንን ‘የአሸናፊ ደጋፊነት’ ህልውና ከምንም ግዜ በላይ ይፈልገዋል:: ከዚህ በተረፈ ደግሞ በፌደራልና ክልል ደረጃ ቁንጮ ስልጣኖችን በደህዴን ስም የተቆናጠጡ የክልሉ ባለስልጣናትም ቢሆኑ የደህዴንን ቀጣይ ህልውና ማረጋገጥ የስልጣን ገመዳቸውን አስጠብቆ ለማስቀጠል ብቸኛ አማራጫቸው ነው:: ጉዳዩን ከማዕከላዊው መንግስት የአስተዳደር ፍላጎት (interest) አንፃር ያየነው እንደሆነ ደግሞ ለሲዳማ ክልል ሰጥቶ የተቀረውን የደቡብ ክልል ህዝብ እንደነበረ ዋና ከተማውን ሀዋሳ: ሶዶ: አርባምንጭ ወይንም ሆሳና ላይ ባደረገ የደቡብ ክልል መዋቅር ማስቀጠል ለማዕከላዊ መንግስቱ እጅግ የተሻለ የአስተዳደር መዋቅር ነው:: ከዚህ የአደረጃጀት መዋቅር አንፃር ተጨማሪ 4 ወይንም 5 ክልሎች መፈጠር ለማዕከላዊ መንግስቱም ቢሆን ትንሽ አስቸጋሪ (less ideal) የሆነ የአስተዳደር ምቹነትን (ease of governance) ይፈጥርበታል::

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ቢሆን የተለያዩ ምክንያቶችን ሲያቀርብ ቆይቶ በደህዴንን ማዕከላዊ ምክር ቤት የከትናንት ወዲያ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎችን በተመለከተ የተሰጠ የውሳኔ መግለጫ ተከትሎ በአንድ ሌሊት (overnight) ሊባል በሚችል መልኩ ተጨማሪ አባላትን መርጫለው ብሎ የሲዳማውን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ በተመለከተ ስለ ህዝበ-ውሳኔው አካሄድ ትናንት ምሽት መግለጫ መስጠቱ ከዚሁ የተሳሰረና ሰንሰለታማ ይዘት ከሚታይበት በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ የተለያዩ ህዝቦች ያቀረቡትን በከፊል ራስገዝ ክልል የመደራጀት ህገመንግስታዊ ጥያቄዎችን የማፈን የፖለቲካ ሴራ ሰንሰለት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ንክኪ ሊኖረው እንደሚችል አመላካች ፍንጮች ይሰጣል::