የጭንቅ ሰዓታት: ከሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች የተላከ!

በሐዋሳ ከተማ በአሁኑ ሰዓት ያለው ተጨባጭ ሁኔታ

መንስኤ፡ ከሲዳማ ዞን የክልል ልሁን ጥያቄ ጋር የተያያዘ

በአቶቴ ሠፈር (ዛየን ኮሌጅ አካባቢን ጨምሮ) ችግሩ የጀመረው ከጠዋቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ ነው፡፡

 • ወጣቶች በአቶቴ ካፌና በዛየን ኮሌጅ በኩል ወደ ውስጥ የሚወስዱትን የ”ኮብል ስቶን” የውስጥ መንገዶች በትልልቅ ድንጋይ መዝጋት ጀመሩ፤

 • በየደጃችን ለልዩ ልዩ አገልግሎት የምንጠቀምባቸውን ትልልቅ ድንጋዮች ተጠቅመዋል፤

 • ዕድሜአቸው 15 እና 16 የሚሆን ትንንሽ ሴቶችና ወንዶች ልጆች ሳይቀሩ ተሣታፊዎች ናቸው፤

 • ወደ 3 ሰዓት አካባቢ ጥቂት (6 -7 የሚሆኑ) የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደመንደሮቻችን ውስጥ መጥተው ወጣቶቹ የጣሉትን ድንጋይ እንዲያነሱና መንገዱ እንዲከፈት አድርገው ወጣቶቹን በትነው ሄዱ፤

 • በ10 – 15 ደቂቃ ልዩነት የተበተኑት ወጣቶች ተመልሰው በመሰባሰብ መንገዶቹን በድጋሚ ዘጉ፣ በዚህ ሁሉ መሐል በጣም የሚረብሽ ጩኸትና ዛቻ ያሰማሉ፤

 • 4 ሰዓት አካባቢ ሌሎች የልዩ ኃይል አባላት መጥተው በድጋሚ ወጣቶቹ ድንጋዮቹን እንዲያነሱ አድርገው ሄዱ፤

 • ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወጣቶቹ መንገዱን መልሰው ዘጉት፤ ይህን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው ወጣቶቹን ለመበተን ሞከሩ፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ለሌላ ግዳጅ ይመስላል መንደራችንን ለቀው ሄዱ፤

 • የወታደሮቹን መሄድ ጠብቀው ወጣቶቹ በመንደራችን ለመደበኛ የሠፈር ጸጥታ ጥበቃ ብለን ያሰራናቸውን 2/ 3 የጥበቃ ኮንቴይነሮች (በመስተዋት የተሸፈኑ ናቸው) በድንጋይ ሰባበሩ

 • አንደኛው የጥበቃ ኮንቴይነር የዚህ አጭር ዘገባ አዘጋጅ ከቆመበት 20 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፣

 • በ50 ሜትር ርቀት ላይ የሚታየው የአቶቴ ዋናው አስፋልት ላይ በብዛት የተከማቸ ጎማ እየተቃጠለ ነው፡፡ መላ አስፋልቱ በድንጋይ ተዘግቷል

 • በሌላ ሠፈሮች ካሉ ወዳጆቻችን በስልክ እንዳረጋገጥነው ችግሩ በመላ የሀዋሳ ከተማ ውስጥ እየታየ ነው፡፡ ልዩነቱ በርካታ የሲዳማ ነዋሪዎች በሚገኙባቸው እንደ አቶቴ፣ አሊቶ፣ አላሙራ ወዘተ አካባቢዎች የከፋ መሆኑ ነው፡፡ እንደ ሞቢል፣ አሮጌ ገበያ ሐረር ሠፈር / ጎድጓዳ ሠፈር የመሳሰሉት ሠፈሮች ውጥረቱ ቢኖርም ከላይ በተጠቀሰው መጠንና ስፋት አይደለም፤

 • ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ መግቢያ በር በሆነው ሞኖፖል በሚባለው ሠፈር ከልዩልዩ የሲዳማ ወረዳዎች ወደ ሀዋሳ ለመግባት የመጡ በርካታ ሰዎችና የጸጥታ ኃይሉ ተፋጠው እንደሚገኙ በስልክ መረጃ አግኝቻለሁ

 • ሁኔታው በአጠቃላይ እጅግ አስፈሪ ነው፣

 • መንግሥት በ10 ሺህዎች የሚቆጠር የጸጥታ ኃይል በሀዋሳ ማሰማራቱን ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ይህን ኃይል አጠናክሮና አስተባብሮ ሁኔታውን በፍጥነት ካልተቆጣጠረው ከዜጎች መጎዳት በእጅጉ ያለፈ መዘዝ ማስከተሉ አይቀርም፡፡

(በአሁኑ ሰዓት በኛ ሰፈር ያለው ጩኸትና ግርግር ጋብ ያለ ይመስላል፣ ቢሆንም ከኛ ሠፈር ቅርበት ርቀት ባሉ አካባቢዎች ወጣቶቹ ባደረጉት ጥቃት አስፋልት ዳር ያሉ በርካታ መኖሪያ ቤቶችና በተለይ የሱቆች መስተዋቶች ተሰብረዋል፤ ንብረት መውደሙንም አሁን ዘግይቶ ሰምቻለሁ)

 • የጥቃቱ ቀጥተኛ ዒላማና ተጠቂ የሆነውን (ጉዳዩም በቀጥታ የሚመለከተውን የሀዋሳ ነዋሪ ደህንነቱን አደጋ ላይ በማይጥል ስልት የመፍትሔው አካል ማድረግ ወሳኝ የሆነበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስለኛል፤

 • አሁን ተኩስ እየሰማሁ ነው …

 • አሁን ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ ወጣቶቹ በአቶቴ አካባቢ አይታዩም፡፡ የመከላከያ አባል ከርቀት አስፋልት ላይ ቆሞ ይታየናል፡፡

 • በሁኔታው አደገኛነትና አስፈሪነት ምክንያት ወደ ውጭ አንወጣም፤ የግቢ በራችንን ቆልፈን ተቀምጠናል፡፡ ቤተሰብ በጸሎት ረዥም ጊዜ አሳልፏል፡፡ እየተደረገ ያለውን ብዙውን ድርጊት የምንከታተለው በበር ቀዳዳ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ከደጃችን ያሉትን ወጣቶች የጸጥታ ኃይሎች ካበረሩልን በኃላ በሚኖር ጥቂት የጊዜ ክፍተት በራችንን በጥንቃቄ ከፍተን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሞክረናል፡፡ በር መክፈትና ደጅ ላይ ቆሞ መመልከት በጣም አደገኛ ነው፡፡ የምትፈራው ወጣቶቹን ብቻ ሣይሆን ጎረቤቶችህን ጭምር ነው፡፡ ብዙዎቹ ከሲዳማ የሆኑ ጎረቤቶቻችን ላይ ምንም ስጋት አናይባቸውም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ የኛ “የጎረቤቶቻቸው” ይሉኝታ ይዞአቸው በይፋ አይገልጹትም እንጂ የኤጆቶ ወጣቶችን ድርጊት እንደሚደግፉ የሚጠቁሙ ብዙ ምልክቶች ይታያሉ፡፡