በደቡብ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና አንድምታዎቹ!

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በደቡብ ክልል እየታዩ የመጡ ለውጦች ክልሉን ይመራ የነበረውን (ይቅርታ የሚመራውን ለማለት ነው) ድርጅት ደህዴንን ግራ ያጋባው ይመስላል:: በተለይ በያዝነው አመት በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ህዝቦች የተነሱ የክልል አደረጃጀት ህገመንግስታዊ ጥያቄዎችን ተከትሎ የክልሉ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉዳዩን የያዘበት አግባብ በተለያዩ ‘የክልል ይገባኛል’ ጥያቄዎች ባነሱ የክልሉ ዞኖች ህዝቦች ከፍተኛ ተቃውሞዎች አስነስቶበታል:: በተለይም ደግሞ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ ባደረገው 11ኛ መደበኛ ጉባኤው ማገባደጃ ላይ ከገዳዩ ጋር በተያያዘ የሰጠው ግልፅ ያልሆነ መግለጫ ነገሮች ያልተጠበቁ አቅጣጫዎችን እንዲይዙ አድርጓቸዋል::

እነዚህ ለዘመናት በፖለቲካዊ ድርድሮች ተዳፍነው የቆዩ የህዝቡ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፈው አመት ጀምሮ ሀገራችን ውስጥ እየነፈሰ ካለው የለውጥ ንፋስ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ (magnitude) አንድ ላይ መገንፈላቸው ክልላዊውን የመንግስት አስተዳደር የያዘው መሪ ድርጅት ለነዚህ ተደራራቢ የህዝቡ ጥያቄዎች ወቅቱን የጠበቀ መልስ ከመስጠት አቅሙ ጋር ተያይዞ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል:: ለዚህም ይመስላል መንግስት ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣታቸው በፊት ከሐምሌ 15 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ ሁሉም የደቡብ ክልል ዞኖች ከተማ አስተዳደርና ልዩ ወረዳዎች ላይ ላልተወሰነ ግዜ በኮማንድ ፖስት ስር እንደሚተዳደሩ ሲል ግዚያዊ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጁን የገለፀው::

ካለፈው አመት ጀምሮ ሀዋሳና አከባቢዋ ላይ እየተስፋፋ የመጣው ስርዓት አልበኝነትና የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መታወጅ አስገዳጅ ሁኔታዎች ከፈጠሩ ሰነባብተዋል:: ነገር ግን የክልሉን ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች የአከባቢው ተወላጆች የተቆናጠጡበት ሁኔታና የስርዓት አልበኝነቱ በአከባቢው ያሉ የመንጋ ቡድኖችን ጫናን ተጠቅመው የራሳቸውን አጀንዳ ማስፈፀሚያ ጥሩ መንገድ ስለነበር ከመጀመሪያውም ቢሆን አስቸኳይ አዋጁ ተግባራዊ እንዳይሆን ያዘገየውም ይኸው ይመስላል::

ይህ ሁኔታ በተለይም የሀዋሳ ከተማና በአጠቃላይ የክልሉ ስልጣን የውሳኔ አቅም ሌሎችን የክልሉ ዞኖች ባገለለ መልኩ በአንድ ብሔር የአንጃ ቡድን ዘዋሪነት ቁጥጥር ስር ወድቆ የቆየበት ሁኔታ በጊዜ ሂደት በክልሉ ዞኖችና በክልሉ አስተዳደር መሀል እየሰፋ የሄደ መቃቃርና አለመግባባት የፈጠረበት ክስተት የክልሉን አስተዳደር አቅመ ቢስ (non-functional) አድርጎታል:: ለዚህ ደግሞ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በክልሉና በዞኖች መሀከል ያለው መዋቅራዊ የአስተዳዳር መስመር በአብዛኛው እየተቋረጠ (እየተበጠሰ) መምጣቱና ክልሉ አንድም የአብላጫ ድጋፍ ያለውና ተፈፃሚ የሆነ ውሳኔ መውሰድ: ቢወሰኑም እስከ ወረዳና ቀበሌዎች ተግባራዊ ማድረግ ያልቻለበት ሁኔታ አንዱ ማሳያው ነው::

በእርግጥ ከክልሉ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መግለጫ በኋላ በሲዳማ ዞን ውስጥ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ የተፈጠረውና የሲዳማ ብሔር አባል ያልሆኑ (non-ethnic Sidamas) የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የደረሰው የብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና ያደረሰው አላስፈላጊ የዜጎች የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ዋነኛ ምክንያት እንደሆኑ ይታወቃል:: ሆኖም ሌሎች ዞኖች ላይ ከመግለጫው ጋር በተያያዘ የታዩት ትላልቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችም የፈጠሩት ስጋት ለዚሁ ውሳኔ ምክንያት ነበሩ::

ዋናው ጥያቄ ‘ሌሎች ዞኖች ላይ የታዩት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ስጋት የፈጠሩት ለማን ነው?’ የሚለው ነው:: እነዚህ ሰላማዊ ሰልፎች በየዞኖቹ ህዝቦች የተነሱ ህገመንግስታዊ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች በህገመንግስቱ በተቀመጠላቸው ማዕቀፍ እንዲመለሱ ያላቸውን ፅኑ አቋም የገለፁበት ነበሩ:: በተጨማሪም በሲዳማ ዞን እንደታየው ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችም ሆኑ ንብረት የማውደምና የአካባቢውን ነዋሪ የቀን ተቀን ሰላማዊ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ የጣሉ እንዳልነበሩ ከየአካባቢዎ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ:: በእርግጥ ሰላማዊ ሰልፎቹ ፍቃድ ያላቸው ነበሩ ወይስ አልነበሩም የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው::

ስለዚህ እነዚህ ከሲዳማ ዞን ውጭ ያሉ ሌሎች የክልሉ ሰላማዊ አካባቢዎች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጣለበት አግባብ እንደ ቀድሞው ጊዜ የኢህአዴግ ስርዓት የህዝብ ሰላማዊና ህገመንግስታዊ ጥያቄዎች በድርጅታዊ አካሄድ በሀይል የማፈን (የመጨፍለቅ) ዝንባሌ ካለው ክልሉን ወዳልተፈለገ የቀውስ ቀጠና እንዳይቀይረው ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው:: በተጨማሪም በየአካባቢው በመንጋ ቡድኖች የታገዙ የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉና የስርዓት አልበኝነት አካሄዶች እንዲሁም ለተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች ጥቅም ሲባል ብቻ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት አዝማሚያ ያላቸውና የህግ የበላይነትን አደጋ ውስጥ የሚከቱ አካሄዶች ወደ አጠቃላይ ሀገራዊ ግጭት መፍጠር እንዳይሸጋገሩ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በኮማንድ ፖስት መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በዚህ ግዜ ሀገራችንን ብዙ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ከህዝብ ፍላጎት ጋር የሚጋጩ እርምጃዎችን ከመውሰድ መቆጠብ አስፈላጊ ነው::

One thought on “በደቡብ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና አንድምታዎቹ!

 1. ሰይቃጠል በቅጠል!

  ሕገመንግስታዊው የክልሎች አወቃቀር ብሔረሰብን ፣ ብሔርን፣ እና ሕዝብን ማዐከል ያደረገ ነው። የነዚህ ዋና መለያ ደግሞ ” ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው” ሲል አንቀጽ 39 ደንግጓል። በአንቀጽ 47 መሠረት አንድ ክልል ለአንድ ዘር ነው።

  ታዲያ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ብሎ ብሔረሰብ አለ? ተመዝግቦስ ያውቃል? ከ85 ብሔር ብሔረሰብ ወይም ህዝቦች መካከል ማለቴ ነው። ይህ ሁሉ ብሔረሰብ በ 9 ክልሎች መታጨቁ ከሕገመንግሥታቸው አንፃር ትክክል አይደለም። ፌደራሊዝሙ ሕገመንግሥቱን ጥሷል። 85 ፌደራል መነግሥታት መመሥረታቸው አይቀርም። ያበደ ሕገመንግሥት!
  ካፋ፣ ሻካ ወዘተ ዞኖቾ የእንከለል ጥያቄ አቅርበዋል። ነገ የመፈረካከስ እጣ ይጠብቃቸዋል። ለምን ቢባል የብሔረሰቦች ጥምረት ናቸውና ነገ ጥምረቱን አፍርሰው በየራሳቸው ክልል መጠየቅ ሕገመንግስታዊ መብታቸው ነው። የቤንሻንጉል የጋምቤላ የትግራይ የአማራ ክልሎችም ችግር ውስጥ ይገባሉ።
  ወደ ደማቸው ወይም ዘራቸው መገኛ ክልል መካለል የ፣ ሚፈልጉ በሁለተኛ ዜግነት በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ በሚደርስባቸው ግፍ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለማፈን በሚደረግ ጫና እና በነርሱ ወገን ክልሎች በሚፈጠረው ቅሬታ የሚጠብቀን ጣጣ ብዙ ነው። ከሁሉ በላይ እንኳን የትላንቶቹ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ይቅርና የዛሬ 400 አመት በኦሮሞ የተወሰዱ የአማራ እና የደቡብ አካባቢዎችን ታሪክ ማሰላሰል ተጀምሮአል። የሶማሌዎች እስከ አዋሽ ይሁን ደብረዘይት የነበራቸውን ጥያቄ ማስታወስም አይከፋም። እስከዚያው ግን የሽግግር መንግሥቱ ዘመን ክልሎች እየተመለሱ ነውና ክልል 14 የነበረው አዲስ አበባም ወደ ክልልነቱ ይመለስ። እነሲዳማ ከተመለሰላቸው አዲስ አበባም ግድ ነው። ካልሆነ አገሪቱን ከእርስበርስ ውድመት ለመታደግ ሕገመንግሥቱን እና ፌደራል አከላለሉን ተነጋግረንባቸው እናሻሽላቸው።

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡