የደቡቡ የክልል አደረጃጀት ጥናት ውጤትና ህገመንግስታዊ እውቅናው!!

የደቡብ ክልሉ መሪ ድርጅት ደህዴን ካለፈው አመት ጀምሮ በክልሉ የተነሱ የክልል የከፊል ራስገዝ ህገመንግስታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የነዚሁ የአደረጃጀት ጥያቄዎች መንስኤና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ጥናት አካሂጃለው ብሎ በሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል:: ከ20 አባላት በላይ ከተለያዩ የጥናት ዘርፎች (ከአንትሮፖሎጂ፣ ታሪክ፣ የህዝብ አስተዳደር፣ ፓለቲካ ሳይንስ እና ፌዴራሊዝም የጥናት መስኮች) የተውጣጡ ምሁራንን የያዘ ነው የተባለው የጥናት ቡድንም በነዚሁ ተመራማሪዎቹ ላለፉት 7 ወራት ከአንድ ዞን በስተቀር በሁሉም የደቡብ ክልል ዞኖች የተውጠጡ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ መረጃ ሰብስቦ ሲያጠናው የቆየው ጥናት ውጤት ነው ብሎ የሚከተሉትን ነጥብች አስቀምጧል::

1.) የ1987ቱን የደቡብ ክልል አወቃቀር በፌዴራል መንግስት ውሳኔ በዘፈቀደ ነው ወይስ የክልሉ ህዝብ ተሳትፏል በሚለው ጉዳይ ህዝብ የሰጠው ምላሽ የደቡብ ክልል በመንግስት ተጠፍጥፎ የተስራ አይደለም የሚል ሆኗል።
2.) የክልሉ ምሁራን ያለ መንግስት ተፅእኖ ክልሉ በደቡብ ክልልነት እንዲመሰረት ተስማምተው ክልሉ መመስረቱን ተናግረዋል።
3.) በጥናት ውጤቱ መስረት አብዛኛው የክልሉ ህዝብ አሁን ያለው የክልል አደረጃጀት ቢቀጥል የሚለውን አማራጭ መርጠዋል።
4.) ክልሉ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቢከፈል የሚለውም በሁለተኛ ደረጃነት በጥናቱ ተሳታፊዎች ተመርጧል።
5.) የክልል ምስረታ ጥያቄዎች ለጊዜው ቢቆይ እና በእርጋታ ቢታይ የሚለውም በጥናቱ በሶስተኛ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

እንግዲህ ይሄን “ሳይንሳዊ ጥናት” ውጤት መግለጫ እንበለው ሪፖርት ስናየው ደህዴን የተባለው የደቡቡ የኢህአዴግ እህት ድርጅት “ድርጅታዊ ህልውናውን ለማስቀጠል” ሲባል ከባለፈው የተድበዘበዘ መግለጫ ቀጥሎ የወሰደው ሁለተኛው (ይቅርታ ለካስ በመሀል ከሲዳማ ዞን ውጭ በክልሉ ግጭት በሌለባቸው ሰላማዊ አካባቢዎች በሙሉ የታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅም አለ) ርምጃ መሆኑን መረዳት አይከብድም:: የባለፈው ሳምንት መግለጫቸውም ሆነ ይህ ሪፖርት ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጣረዝ መሆኑን ወይ እስከ አሁን አልተረዱትም አሊያም ሊረዱት አልፈለጉም::

ሲጀምር በየዞኑ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በነቂስ ወጥቶ በሰላማዊ ሰልፍ የጠየቀውንና ህገመንግስታዊ መሰረት ያለው በከፊል የራስገዝ አስተዳደር የክልል አደረጃጀት ራስን በራስ የማስተዳደር የህዝቦች የህልውና ጥያቄ ህገመንግስቱ በ”ሳይንሳዊ ጥናት” ውጤት መሰረት ይመለሳል ብሎ ህገመንግስታዊ አካሄድ ባላስቀመጠበት ሁኔታ በቀጥታ ህገመንግስታዊ አካሄዱን በተፃረረ መልኩ እንደዚህ አይነት አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሞከሩ ግራ ያጋባል::

ሲቀጥል ደግሞ የክልልነት ጥያቄ ያነሱ ዞኖች በየዞኖቻቸው የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በአብላጫ ወይንም በሙሉ ድምፅ አስወስነው ወደ ክልላዊው ምክር ቤቱ በፅሁፍ መላካቸው እየታወቀ በምን ስሌት ነው በክልላዊው ማዕከላዊ ምክር ቤት ያንኑ የየዞናቸውን ምክር ቤት አቋም (ውሳኔ) ሽረው ከሲዳማ ውጭ ያሉት ዞኖች በአንድ ላይ ለመቀጠል የሚወስኑት?! ክልላዊው ድርጅት ደህዴን ለህልውናውም ቢሆን እንደ ሌሎቹ እህት ድርጅቶች የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ውሳኔ ወስኖ ለውጡን በህዝባዊ መሰረት በማስቀጠል የሚመጣውን በፀጋ መቀበል የሚሻለው ይመስላል:: ሰፊው ህዝብ ሁሌም ትክክል ነው (The People are Always Right) የሚለውን ታዋቂ (popular) አባባል ልብ ይሏል::

በመጨረሻም ሀገሪቱ ውስጥ ሁለት አይነት የፌዴራላዊው ስርአት አሰራር እንዳለ ልብ ይሏል:: ይኸውም የደቡብ ክልል አወቃቀርን ያየነው እንደሆነ ጂኦግራፊያዊ አከላለልን መሰረት ያደረገ ሲሆን የተቀሩት የሀገሪቱ ክልሎች አወቃቀር ደግሞ ብሔርና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው:: ለዚህ መሬት የወረደ እውነታ (the reality on the ground) ማሳያ ካስፈለገ ደግሞ በዛ ያሉ ማጣቀሻዎች ማቅረብ ይቻላል:: ዞሮ ዞሮ የሚያዋጣን አካሄድ የሚሆነው ግን ወይ ስራ ላይ ባለው ህገመንግስታዊና ህገመንግስታዊ መሰረት ባለው አካሄድ ብቻ የሁሉንም ህዝቦች ጥያቄዎች በእኩል አግባብ ማስተናገድ አሊያም ደግሞ ህገመንግስቱን በማሻሻል ወደ አዲስ ሀገር አቀፍ የአስተዳደር ወሰኖች አወቃቀር በመግባት በአዲስ አደረጃጀት እንደገና ማዋቀር ነው::

One thought on “የደቡቡ የክልል አደረጃጀት ጥናት ውጤትና ህገመንግስታዊ እውቅናው!!

  1. “ሀገሪቱ ውስጥ ሁለት አይነት የፌዴራላዊው ስርአት አሰራር እንዳለ ልብ ይሏል:: ይኸውም የደቡብ ክልል አወቃቀርን ያየነው እንደሆነ ጂኦግራፊያዊ አከላለልን መሰረት ያደረገ ሲሆን የተቀሩት የሀገሪቱ ክልሎች አወቃቀር ደግሞ ብሔርና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው::” የሚላው ሀሰብ ላይ በሀገራች ክልሎች አወቃቀር በተመለከተ አንተ እንደልካው በሀገራችን ያለው ፌደራሊዝም አወቃቀር በብሄር፣ በቋንቋ፣ በህል እና በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም አወቃቀር የመይወጥለቸው አካሎች ደቡብ ብ/ብ/ህዝቦች ብቻ በጂኦግራፊያዊ አወቃቀር የተቀረ ተደርጎ ማወሳድ የለበትም ለምሰሌ ልክ እንዳ ደቡብ አማራ፣ ትግራይ፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ ክልል በውስጡ ብዙ ብሄሮች መኖራቸው መዘንገት የለበትም።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡