የደቡብ ክልልን ለፖለቲካዊ ቀውስ የዳረጉት መዋቅራዊ ችግሮች!!

ጸሀፊ|ጌታሁን ካሳ

የደቡብ ክልል ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ እየታመሰበት ያለውን ሁኔታ የፈጠሩ ብዙ ውስብስብና ስር-ነቀል ችግሮች ቢኖሩትም በአጠቃላይ በመርህ ላይ የተመሰረተ ፍትሀዊ የስልጣን ክፍፍልና የሀብት አጠቃቀም ያለመኖር ችግሮች ሲሆኑ የሚከተሉት ከችግሩ መሰረታዊ ምንጮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው::

  • ከአገልግሎት ተደራሽነት ይልቅ የበጀት ክፍፍልን መሰረት ያደረገ አስተዳደራዊ መዋቅር መኖር

በክልሉ አስተዳደራዊ መዋቅር (ዞን፣ ወረዳ፣ ከተማ አስተዳደር፣ ልዮ ወረዳ) ሲሰራ ተገልጋዩ ማህበረሰብ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ ሳይሆን ቀጥታ ከበጀት ጋር መያያዙ የጊዜ ጉዳይ እንጂ አሁን ክልሉን የገጠመው ችግር እንደሚገጥመው ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡ ዛሬ የመዋቅር ጥያቄ እየተነሳባቸው ያሉ የክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ዋነኛ መንስኤው የተሻለ በጀት ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በወረዳና በልዩ ወረዳ መሀከል የበጀት ልዩነት መኖሩ፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደር መሀከል የበጀት ተመሳሳይነት መኖሩ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

ለዚህ ችግር ሌላው ጥሩ ማሳያው ለምሳሌ የከፋ ዞን ጨና ወረዳን የወሰድን እንደሆነ በመዋቅር ጥያቄ ምክንያት ከአመት በፊት የአንድ ብሄር ተወላጆችን በትውልድ መንደር ለያይቶ ለመፈነቃቀል፣ ለመገዳደል እና ትዳር እስከማፍረስ የደረሰ ግጭት መከሰቱ፤ ችግሩም የተፈታበት መንገድ የቀደመውን ወረዳ ለሁለት ከፍሎ አዲስ ወረዳና አዲስ የከተማ አስተዳደር በመመስረት ነበር:: “The Torn apart region” በሚል ርዕስ አንድ አሜሪካዊት የፌደራሊዝም ተመራማሪ የጻፈችው ጥናታዊ ጽሑፍ ከላይ የተጠቀሰውን ችግር በሚገባ ያብራራል፡፡

  • በክልሉ የአስተዳደር መዋቅር ፍትሀዊነት የጎደለው የፖለታካ ውክልና መኖር

ክልሉ ከአመሰራረቱ ጀምሮ በክልሉ ብሄረሰቦች እና አስተዳደራዊ መዋቅሮች መካከል ኢፍትሀዊ የፖለቲካ ውክልና እና የልማት ተጠቃሚነት መንገሱ ዛሬ ለተፈጠረው ችግር ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ለማሳያነት ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ክልሉን ከመሩ 5 የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሮች ውስጥ አራቱ የሲዳማ ብሄር ተወላጆች መሆናቸው የአንድ ብሄር የበላይነት የነገሰበት (Sidama hegemony) ክልል እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የልማት ኢፍትሀዊነትን ማሳያ እንደምሳሌ ከወሰድን ሀዋሳ ከተማን ብቻ የሚረዱ ወደ 159 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መኖራቸው ሌላው ክልሉ ውስጥ ያለውን ኢፍትሃዊነት አንጸባራቂ ነው፡፡ ወርቅ፣ የጫካ ቡና፣ ማር እና ልዩ ልዩ የሰብልና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ የሚመረትባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ምን ያህል በልማት ወደኋላ የቀሩ እንደሆኑ ማየቱ ተጨማሪ የኢፍትሃዊነት ማመሳከሪያ ነው፡፡ ደቡብ ምዕራብ ማለትም ቤንች፣ ከፋና ሸካን ዞኖች ሁሉንም ወረዳዎች ለምርምር ስራ እየወጣሁ የማየት እድሉ ስለገጠመኝ እማኝ የአይን ምስክር ነኝ፡፡ አካባቢው ላይ የተገነቡ አብዛኞቹ የአፈር ጥርጊያ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ኬላዎች በብዛት በደርግ ዘመን የተሰሩ ናቸው፡፡ ድልድይ የሌላቸው ብዙ ወንዞች የአካባቢውን መረሳት ተጨማሪ አሳባቂዎች ናቸው::

  • የጋራ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስርና የፖለቲካ አጀንዳ ያለው ማህበረሰብ መፍጠር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ትስስር ያለመኖር

ክልሉን በበላይነት ለአመታት ያስተዳደረው ድርጅት (ደኢህዴን) ደቡብን እንደ ክልል የጋራ የሆነ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ትስስር (infrastructural integration) የሌለው እና የጋራ የሆነ የፖለቲካ አጀንዳ (common political interest) ያለው ማህበረሰብ መፍጠር ባለመቻሉ ዛሬ ለመፍረክረክ ቢንደረደር ብዙም አስደናቂ አይሆንም፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ከአመት በፊት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በነበረው ተከታታይ የፖለቲካ ተቃውሞ እንቅስቃሴ መንገድ በተዘጋ ቁጥር ከክልሉ መዲና (ሀዋሳ) ርቀው የተቀመጡ የተለያዩ ዞኖች አመራሮች ወደ ሀዋሳ ሲጓዙ መንገድ ላይ የመታገት እና ከህዝቤ እንደራሴነት ስራቸውም የመስተጓጎል ችግር ይገጥማቸው እንደነበር የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡

  • ዞኖች የክልል መቀመጫ ተደርጎ በሚመረጥ ከተማ ላይ ከሚኖራቸው የሀብት ፈሰስ ጋር በተያያዘ የባለቤትነት ህጋዊ ማዕቀፍ ያለመኖር

የክልሉ መቀመጫ የሆነችው ሀዋሳ ከተማ ለክልል መዲናነት የተመረጠችበት እና የከተማዋ የአስተዳደራዊ ሁኔታ የሁሉም የክልሉ ብሔረሰቦች የጋራ መኖሪያ እንደመሆንዋ የነዋሪዎችዋን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና አስተዳደራዊ ተሳታፊነት ያረጋገጠ ሕጋዊ ማዕቀፍ (Legal framework) ሳይበጅለት ለዋና ከተማነት መመረጧ እና ክልሉ የመፍረስ አደጋ ቢያጋጥመው የከተማዋ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ በሕግ አግባብ የሚፈታበት ህጋዊ ማዕቀፍ ሳይኖር እያንዳንዱ ዞን እና ልዩ ወረዳዎች ከበጀታቸው በየአመቱ ለሀዋሳ ከተማ 20% በጀት እንዲቆርጡ መገደዳቸው ሌላው የክልሉን ችግር ማሳያ ነበር፡፡

በተጨማሪም ፌደራል መንግስት ለክልሉ ከሚመድበው በጀት ላይ እስከ (20%?) ለክልል ማዕከል ተብሎ በክልሉ ይመደባል፡፡ እናም ዛሬ የሲዳማ የክልል ጥያቄ ገፍቶ ሲመጣ ሌሎችም የየራሳችንን ክልል እንመሰርታለን ብለው እንቅስቃሴ ማድረጋቸው አንድም ሀዋሳ ከተማ ላይ ያደረጉትን ኢንቨስትመንት እንደ ከሰረ ኢንቨስትመንት ቆጥረውት በቁጭት እያዩት ስለሆነ፤ ሲቀጥልም ነገ በጋራ የሚያሳድጉት አዲስ የክልል ከተማ ተመሳሳይ ኪሳራና ቁጭት እንዳያስከትልባቸው በመስጋትም ጭምር ነው፡፡

  • የፖለቲካ ምህዳሩ አሳታፊነት የጎደለውና አግላይ የፉክክር ፖለቲካ መሰረት መያዙ

ክልሉ ከጅምሩ ጀምሮ በዋናነት የሲዳማ እና የወላይታ ፖለቲከኞች የትብብር ሳይሆን የፉክክር መድረክ መተወኛ መሆኑ እና ዛሬም ከለውጡ በኋላ የሁለቱ ፉክክር ማየሉ ክልሉ እንዲፈርስ ሌላኛው ገፊ ምክንያት ነበር፡፡ ሌሎቹ የክልሉ ብሄረሰቦች የተገፉና የተረሱ መሆናቸው (neglected counterparts) ከበፊትም ጀምሮ የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸውና የራሳቸውን አስተዳደር ስለመመስረት እያለሙ እንዲኖሩ አድርጓቸው ከርሟል፡፡

(ጌታሁን ካሳ በቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሀብት ኢኮኖሚክስ ረዳትፕሮፌሰር ሲሆኑ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ሀሳባቸውን በማካፈል ይታወቃሉ::)

2 thoughts on “የደቡብ ክልልን ለፖለቲካዊ ቀውስ የዳረጉት መዋቅራዊ ችግሮች!!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡