4 ቢሊዮን ችግኞችን ለማፍላት 40 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል!

ከጥቂት ቀናት በፊት በተካሄደው የችግኝ መትከል ዘመቻ ላይ ከ23 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ኢትዮጵያ እስከ ጳጉሜ መጨረሻ በምታደርገው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ 4.7 ቢሊዮን ችግኞችም መፈላታቸው ተገልጿል።

በአጠቃላይ ችግኞቹን ለማፍላት ወደ አርባ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብም መውጣቱን የብሔራዊ ደን ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ተፈራ መንግሥቱ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የዘንድሮውን የችግኝ ተከላው ፕሮግራም ባለፉት ሶስት ወራት መርኃ ግብር ተዘርግቶ እንደተሰራ ጠቅሰው፤ ዝግጅቱ ግን አመቱን ሙሉ ነው ተሰርቷል ብለዋል።

ለዚህ ተከላ ሲባል አዳዲስ አይነት ችግኞች ያልተፈሉ ሲሆን ተከላው የተከናወነው ባለው ክምችት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ 200 ሚሊዮን ችግኞች

በአስር ወራት አማርኛ ማንበብና መፃፍ የቻለው ጀርመናዊ

በኃገሪቱ ካሉ የችግኝ ጣቢያ ክምችት ችግኞቹ ከመሰራጨታቸው አንፃር ለእያንዳንዱ ስነ ምህዳር፣ አካባቢ የትኛው ይጠቅማል የሚል ጥናት አለመደረጉንም አቶ ተፈራ ጠቅሰዋል።

ይህ ማለት ግን ችግኞቹ የጎንዮሽ ችግር አለባቸው ማለት እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

“ለኢትዮጵያ መልክአ ምድር የማይሆኑ ችግኞች አልተፈሉም።” የሚሉት አቶ ተፈራ አንዳንድ ችግኞች ግን ካላቸው የአካባቢ መስተጋብር ጋር የተሻለ የሚፀድቁበት ሁኔታ ይኖራል ይላሉ።

ችግኞቹን ከሰሜን ወደ ደቡብ በማሰባጠርና በሚስማማባቸው አካባቢ ለመትከል በቂ ጊዜም እንዳልነበረ አስረድተዋል።

ካሉት ችግኞች ሁሉም ይፀድቃሉ ተብለው የማይጠበቁ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ተፈራ እስካሁን ባለው ልምድ ከአምሳ ፐርሰንት በታች የፀደቀበት ሁኔታም ስለነበር አሁን ባለው እስከ 70% የሚሆነው ከፀደቀ ትልቅ ውጤት ነው ብለው ያስባሉ።

ተከላው በበቂ ዝግጅት ካለመሆኑ፣ በስፋትና፣ በዘመቻ ከመሆኑ አንፃር፤ የህዝቡን መነቃቃት መፍጠር፣ ተቋማት በተቀናጀ ሁኔታ መምራታቸው የዘንድሮው ተከላ ሂደት ትርፉ መሆኑን ይናገራሉ።

የክትትል ስርአት ለመዘርጋት ጥረት መደረጉ እስካሁን ከነበረው የተሻለ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አቶ ተፈራ ያምናሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የተተከሉት ዛፎች ሃገር በቀል እና የውጪ ዝርያ ያላቸው ችግኞች እንደሚገኙበት የጠቀሱ ሲሆን ዝርዝር የችግኞቹ አይነት ወደፊት ይገለጻል ብለዋል።

ሰኞ ዕለት የተተከሉት ችግኞች በሙሉ በሃገር ውስጥ የተፈሉ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተፈራ ከሰኔ 26 ወዲህ 3.5 ቢሊዮን ችግኞች በመላው ሃገሪቱ መተከሉን ጨምረው ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው ይህ ዘመቻ ባሳለፍነው ሰኞ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ በዕለቱ አመሻሽ ላይ መንግሥት በመላው ሃገሪቱ የተተከሉት የችግኞች ብዛት ከ350 ሚሊዮን በላይ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

አንዳንድ ቦታዎች የሚተከሉ ችግኞች እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ቢነገርም ዶ/ር ተፈራ ግን “ዝግጁ የተደረጉት የችግኞች ብዛት 4.7 ቢሊዮን ስለነበሩ የችግኝ እጥረት አላጋጠመም” በማለት የክልል መንግሥታት ለዘመቻው ከፍተኛ ዝግጅት በማድረጋቸው ከተጠበቀው በላይ ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን አብራርተዋል።

“በኤችአይቪ የምሞት መስሎኝ ልጄን ለጉዲፈቻ ሰጠሁ”

የተተከሉት ችግኞች እንዴት ተቆጠሩ?

በአንድ ቀን ብዙ ችግኞችን በመትከል በህንድ ተይዞ የነበረው ክብረ ወሰን መሰበሩን እየተነገረ ሲሆን፤ ይህም በጊነስ በይፋ ስለመመዝገቡ የተጠየቁት ዶ/ር ተፈራ ይህን ጉዳይ የሚከታተለው የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስለጉዳዩ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃም ትክክለኛው ቁጥር የሚረጋገጥበት ሥርዓት እንዳለው አመልክቶ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ የማስመዝገቡ ሥራ በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ባለፈው ሰኞ በመላዋ ሃገሪቱ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ሁለት ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን መንግሥት አሳውቋል። በዚህም በዓለም በተመሳሳይ ተግባር ተይዞ የነበረው ክብረ ወሰን ወደ ስድስት እጥፍ በሚደርስ ቁጥር ተሻሽሏል።

ምንጭ፦ BBC|አማርኛ