የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ እና የልሂቃኑ አካሄድ

በቦጋለ ታከለ

አዋሳን ማዕከል ያደረገ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት መመስረትን ብቻ አልመው የተነሱት የሲዳማ ፖለቲከኞች ከእዚህ ሁኔታ በቀር በምንም እንደማይስማሙ አበከረው ይናገራሉ፡፡ የሲዳማ ክልልን ከመመስረት ፍላጎታቸው ይልቅ አዋሳን የግል የማድረግ እራስ ወዳድነት የበዛበት ፍላጎታቸው ዘለግ እንደሚል ባለፈው ፅሁፌ በደንብ አስረድቻለሁ፡፡ ይህንኑ ፍላጎታቸውን ገቢራዊ ለማድረግ ይህንኑ ጥያቄያቸውን ሲያፍን የኖረው ህወሃት ከመንበር እስከሚታጣ ጠብቀዋል፡፡ ህወሃት ከመሃል ወደ ዳር ሃገር መሄዱ እርግጥ ሲሆን የሲዳማ ፖለቲከኞች ኤጄቶ የሚባል የገጠር ጎረምሶች ቡድን አቋቁመው ገና እግሩን በደንብ ባልተከለውን የዶ/ር አብይ መንግስት ፋታ እንዲነሳ አድርገዋል፡፡ የሚገርመው ነገር ይህ ኤጄቶ የሚባለው የሲዳማ ጎረምሶች ቡድን የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሃትን የበላይነት ለመጣል ባደረው ትግል ወቅት ከነአካቴው ያልነበረ እና አንዳች አስተዋፅዖ ያላበረከተ መሆኑ ነው፡፡ ኤጄቶ ለያዥ ገራዥ ያስቸገረ ደራሽ ታጋይ የሆነው ታጋዮችን እስርቤት አስገብቶ ቁምስቅል የሚያሳየው ህወሃት ሄዶ ሰው አላስርም ሲል ቃል የገባው የዶ/ር አብይ መንግስት መንበሩን ከያዘ፣ታጋይ የሚፈተንበት ዘመን ካለፈ በኋላ ነው፡፡

ይህን ቡድን በማደራጀት እና አይዞህ በማለት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስን፣ አቶ ቴድሮስ ገቢባን እና አቶ ደሴ ዳልኬን ጨምሮ በኢህአዴግ መራሹ መንግስት የስልጣን መሰላል ላይ ያሉ የሲዳማ ልሂቃን አስተዋፅኦ እንደነበረ ባለስልጣናቱ በየመገናኛ ብዙሃኑ ከሚሰጡት ቃለምልልስም መረዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪ በአዋሳ ምድር ኤጄቶ በቀን በብርሃን ሲዳማ ያልሆነን ሰው በድንጋይ ቀጥቅጦ ሲገድል፣ሲዘርፍ እና በከተማዋ ከሲዳምኛ በቀር በሌላ ቋንቋ የተፃፉ ታፔላዎችን እያወረደ ሲሰባብር ክልሉን የሚዘውሩት የሲዳማ ባለስልጣናት ዝም ብለው መመልከታቸው አቶ ቴድሮስ ገቢባ እንደውም አፋቸውን ሞልተው ወጣቶቹ ልክ ናቸው እስከማለት መድረሳቸው የኤጄቶ ውንብድናው የበዛ አካሄድ በሲዳማ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር እንደሚታገዝ አስረጅ ነው፡፡

ሌላው አስገራሚ ነገር ኤጄቶ የተባለው የሲዳማ የገጠር ጎረምሶች ቡድን ረብሻ ለማስነሳት ባሰበበት ቀን አዋሳ የሚገባ እንጅ አዋሳ የሚኖር አለመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ከገጠራማ አካባቢዎች ገስግሰው መጥተው ውንብድና በተሞላበት አኳኋን የነዋሪውን ሰላም እያደፈረሱ፣ ንግድ እና የመንግስት ስራ መስራት እስከሚያስቸግር ድረስ አዋሳ የእኛ ነች ሲሉ አዋሳ ተወልዶ ያደገው ወጣት ዝም ብሎ ከመመልከት በቀር የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ የዚህ ምክንያቱ እነዚህን ጎረምሶች ከገጠር የማመላለሻ ትራንስፖርት ወጭን ከመሸፈን ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ገብተው የሚያደርጉትን ህገወጥ ስራ አይቶ እንዳላየ በማለፉ በኩል የመንግስት ባለስልጣናት ሚና በግልፅ የሚታይ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የከተማው ህዝብ ራሱን በመንግስት በኩል ህጋዊ ከለላ የሌለው አድርጎ ስለሚያስብ በዝምታ ማየትን መርጦ ኖሯል፡፡

ነገሩን ግልፅ ለማድረግ ራሴ በአይኔ ያየሁትን አጋጣሚ ባነሳ በአዋሳ ከተማ በወላይታ ዲቻ እና በአዋሳ ከነማ መሃከል የሚደረግ የእግር ኳስ ጨዋታ በሚስተናገድበት በአንዱ ቀን ከጨዋታው የሚመለሱ ኤጄቶዎች በመንገድ ላይ ያሉ ሱቆች በራቸው ላይ ያደረጉትን የሚሸጥ ነገር ሲያሻቸው በእግራቸው፣ሲፈልጉ በያዙት ዱላ እየመቱ ያልፋሉ፡፡ በዚህ መሃል የወንዶች ልብስ መሸጫ ሱቅ ውስጥ አንድ አራት ሆነው በቡድን ገብተው ነጋዴው አሻንጉሊት ላይ የሰቀላቸውን ልብሶች ለማውለቅ ሲታገሉ ባለሱቁ የሞትሞቱን አላስወልቅም ብሎ ሲታገል ትርምስ ተፈጠረ፡፡

ትርምሱን ሊያስቆሙ የመጡ ፖሊሶች ሲዳምኛ እየተናገሩ ኤጄቶዎቹ በር እንዲለቁ አደረጉ፡፡ ከዛም ፖሊስ ተብየዎቹ የሰው ሱቅ ገብተው የሚበጠብጡ ኤጄቶዎችን ትተው ንብረቴን አላዘርፍም ብሎ ለብቻው ከአራት ጎረምሶች ጋር የሚታገለው ነጋዴ ላይ አንዱ በተለይ አይኑን አጉረጥርጦ መቆጣት ጀመረ፣ እንደመማታት እየሞከረው ነጋዴው ቶሎ ሱቁን ዘግቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄድ ያዋክበው ጀመር፡፡ ነጋዴው ግራ በመጋባት “ደግሞ ጥፋተኛው እኔው ሆንኩኝ” እያለ ሱቁን ዘግቶ ከተቆጣው ፖሊስ ፊት ፊት ሲሄድ የሰው ሱቅ ዘው ያሉት ጎረምሶች እየተሳሳቁ ተረኛ ተበጥባጭ ፍለጋ ወደፊት ቀጠሉ፡፡ ይህ አንድ አጋጣሚ ነው፤ አዋሳ በርካታ እንዲህ ያሉ በህግ አካላት ጭምር የሚታገዙ ውንብድናዎችን ታስተናግዳለች፡፡

በአንድ በኩል የገጠር ጎረምሶችን አደራጅተው የአዋሳ ከተማን በእጅ አዙር የሚያምሳምሱ የሲዳማ ልሂቃን እና ባለስልጣናት የሚሰሩት ህገ-ወጥ ስራ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ በ11/11/11 በህግም ሆነ በጉልበት እንደሚያስፈፅሙ እርግጠኞች ስለነበሩ ከዛ ከሶስት ወራት በፊት ጀምሮ ሰላሳ ስምንት የሲዳማ ልሂቃንን የያዘ “የሲዳማ ክልል አስተዳደር ሴክሬታሪያት” የሚባል መዋቅር አወዋቅረዋል፡፡ እነዚህ ሰላሳ ስምንት ሰዎች ህዝብ የመረጣቸው አይደሉም፣ የክልሉ መንግስትም አያውቃቸውም፣ እነ አቶ ሚሊዮን ግን በግል አያማክሯቸውም አይደግፏቸውም ማለት አይደለም፡፡

ይህ ሰላሳ ስምንት ሰዎችን የያዘው ሴክሬታሪያት በመንግስት የማይታወቅ፣ በህዝብም ያልተመረጠ ህገወጥ ቢሆንም በሶሻል ሚዲያዎች በሚለቀቁ ቪዲዮዎች ሲመሰረት እና ስብሰባውን ሲያካሂድ ታይቷል፡፡ ህገ-ወጡ ሴክሬታሪያት የሚሰራቸው ስራዎች የሲዳማን ክልል ህገመንግስት ረቂቂ እስከ ማዘጋጀት እንደሚሄድ ነው “ሲዳማ ፔጅ” እና “ኤጀቶ ሲዳማ አፌርስ” በሚለው የማህበራዊ ድህረገፆች በሚለቃቸው ተከታታይ ፅሁፎች እ የቪዲዮ ምስሎች የሚገልፀው፡፡

ይህ ሴክሬታሪያት ኤጀቶ የተባለው ፅንፈኛ ቡድን በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የሚያደርሰው ጥፋት በማስተባበሩ በኩል እጁ የለበትም ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ይህ ሴክሬታሪያት ወይ ህጋዊ የሚሆንበትን እና ካጠፋ የሚጠየቅበትን መንገድ ሲያመቻች አለያም ህገወጡ ሴክሬታሪያት ከህገወጥ ተግባሩ እንዲታቀብ ሲያደርግ አልታየም፡፡

በአንፃሩ በህጋዊ መንገድ የሲቪክ ማህበርነት ፈቃድ ለማውጣት እየተንቀሳቀሰ ያለውን እና በተቻለ መጠን የአዲስ አበባን ህዘብ ውክልና ለማግኘት ህዝብን ሰብስቦ የመከረውን የባለ አደራው ምክርቤት መውጣት መግባቱ በከፍተኛ የመንግስት ተፅዕኖ ስር ከመውደቅ አልፎ መግለጫ መስጠት እና የመሰብሰብ መብቱ ሲረገጥ ይስተዋላል፡፡ መንግስት በአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ላይ ያለው ከልክ ያለፈ ክትትል እና ቁጥጥር በሲዳማ ፖለቲከኞች ላይም ቢያደርግ ኖሮ ዛሬ በደቡብ ክልል የታየው አሳዛኝ የህይወት እና የንብረት ውድመት ባልታየ ነበር፡፡
ይህ የሲዳማ እና የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች የተጣመሩበትን አደገኛ አካሄድ ዝም ብሎ የማየቱ ነገር ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን አጥብቆ በመያዙ እንከን የሌላቸውን ሌሎች የደቡብ ክልል ብሄረሰቦችን ክፉኛ ያስቆጣ ነው፡፡ የቁጣቸው ዋነኛ ማጠንጠኛ መንግስት ለፍተው ያስዋቧትን አዋሳን ለሲዳማ ፖለቲከኞች በገፀ-በረከትነት ሊያበረክት እስከ መቻል ይሄዳ የሚለው ጥርጣሬ ነው፡፡ ይህ ቁታ “በፍጥነት በብሄራችን የሚቀነበብ ክልል ይፈቀድልን” የሚል ጥያቄ እንዲያዥጎደጉጉ አድርጓቸዋል፡፡

ይህ ንዴት ወለድ ጥያቄ መንግስት የሲዳማ ፖለቲከኖችን እሹሩሩ ከማለቱ የተነሳ የመጣ እንጅ የደቡብ ክልል ብሄረሰቦች ከአንድ ክልል አልፎ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ለማደርም ጥበት እጅግም የማይፈትናቸው፣ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነትም ፅኑ ምሰሶ የሆኑ ክፍሎች ናቸው፡፡ የሲዳማ ልሂቃንን እራስ ወዳድነቱ ያመዘነ ጥያቄ መግራት ካልተቻለ ግን ይህ የኢትዮጵያዊነት ጠንካራ አዕማድ ሊወድቅ የማይችልበት ነገር የለም፡፡ የሲዳማ ብሄርተኞችን ጥያቄ ልጓም አስገብቶ በውል አለመያዝ ኢትዮጵያን ውድ ዋጋ የሚያስከፍል መዘዝ አለው፡፡ ይህ መዘዝ በምን ይገለፃል? የሲዳማ ፖለቲከስ እንዴት መያዝ አለበት? የሚለውን ለመዳሰስ ሳምንት ልመለስ፡፡

One thought on “የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ እና የልሂቃኑ አካሄድ

 1. What a nice view.
  Thank you.

  On Sat, Aug 3, 2019 at 10:25 AM Ethiopian Think Thank Group wrote:

  > Seyoum Teshome posted: “አዋሳን ማዕከል ያደረገ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት መመስረትን ብቻ አልመው
  > የተነሱት የሲዳማ ፖለቲከኞች ከእዚህ ሁኔታ በቀር በምንም እንደማይስማሙ አበከረው ይናገራሉ፡፡ የሲዳማ ክልልን ከመመስረት
  > ፍላጎታቸው ይልቅ አዋሳን የግል የማድረግ እራስ ወዳድነት የበዛበት ፍላጎታቸው ዘለግ እንደሚል ባለፈው ፅሁፌ በደንብ
  > አስረድቻለሁ፡፡ ይህንኑ ፍላጎታቸውን ገቢራዊ ለማድረግ ይህንኑ ጥያቄያቸውን ሲያፍን የኖረው ህወሃ”
  >

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡