የሲዳማ ጥያቄ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ፖለቲካ

በቦጋለ ታከለ
የሲዳማ ዞንን ወደ ክልልነት ለማሳደግ እታገላላሁ የሚለው የሲዳማ ልሂቃን ጥያቄ ውስጠ ሚስጥሩ ሲገለጥ የደቡብ ህዝቦች ሁሉ ተባብረው ያቀኗትን ውቧን የአዋሳ ከተማን ለሲዳማ ብቻ የማድረግ አምሮት ነው፡፡ ይህ አምሮት የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ተባብረው ያሳመሯትን አዲስ አበባን የኦሮሚያ ንብረት ለማድረግ በሚቋምጡ የኦሮሞ ብሄርተኛ ቢጤዎቻቸው ይደገፋል፡፡

የኦሮሞ ልሂቃን የሲዳማ ፖለቲከኞችን የክልል አምሮት አጥብቀው የሚደግፉበት ዋነኛው ምክንያት እነሱ እንደሚሉት የሲዳማ ህዝብ እና የኦሮሞ ህዝብ በሲአን እና በኦነግ በኩል ተቃቅፈው ሲታገሉ ስለኖሩ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ እና የሲዳማ ህዝብ እንደማንኛውም ማህበረሰብ የጠብም የፍቅርም ታሪክ ያላቸው ህዝቦች እንደሆኑ አሰበ ረጋሳ …በሚል ርዕስ የሰራው ጥናት ያመለክታል፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ የኦሮሞ ህዝብ በአመዛኙ ሰላማዊ ግንኙነት ያለው ከጌዲኦ ህዝብ ጋር ሲሆን ከሲዳማ ጎረቤቱ ጋር ጦር መማዘዙ የበዛ ታሪክ እንዳለው ነው፡፡

ከታሪክ አለፍ ብለን የቅርቡን ዘመን መስተጋብር ብናይ ደግሞ የሲዳማ እና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ወንዶ ገነት በተባለችው ለምለም ወረዳ ላይ ያላቸው ረዥም ጊዜ የወሰደ ቁርቁስ ጋብ ያለው የአቶ መለስ ኢህአዴግ አካሄድኩት ባለው ሪፈረንደም ነው፡፡ ሪፈረንደሙ በሲዳማ ክልል ከሚገኘው ለሙ የወንዶገነት ወረዳ ግዛት ውስጥ የተወሰነውን ለኦሮሚያ ክልል ጀባ ብሏል፡፡ እነዚህ ለኦሮሚያ ክልል የተሰጡ ግዛቶች የጆግራፊ አቀማመጥ በመሃል ሲዳማ ዞን ውስጥ እንደ ደሴት የተበጣጠሱ የኦሮሚያ ቀበሌዎችን የፈጠረ ነው፡፡ እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሚመራው የሲዳማ እና አባዱላ በሚመሩት የኦሮሞ ፖለቲከኞች መሃከል የሰውን ህይወት ጭምር ያስከፈለ ትልቅ ቁርቁስ ነበረ፡፡

ከዚህ እውነታ ባፈነገጠ መልኩ አሁን አሁን የኦሮሞ እና የሲዳማ ህዝቦች በፍቅር ብቻ የኖሩ አስመስሎ የመተረኩ ነገር እየበረከተ መጥቷል፡፡ ይህ ተረክ ከኦዴፓ ጋር ተዋሃድኩ ያለው የቀድሞው ኦዴግ አመራሮችን (ዶ/ር ዲማ ነገዎን) እና የኦነግ አመራሮችን አዋሳ አብርሮ አምጥቶ “የኤጄቶ እና የቄሮ ህብረት” በሚል ስብሰባ ላይ አስቀምጦ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ እውነቱ እየተጋነነ አንዳንዴ የሌለውም እየተፈጠረ የሲዳማ እና የኦሮሞ ህዝቦች ትግል የመንትዮች ትግል እንደሆነ ተወርቷል፡፡ እነ ዶ/ር ዲማ ነገዎን ከመሰሉ ከጉምቱ የኦሮሞ ብሄርተኞች እስከ ጃዋር እና ፀጋየ አራርሳን የመሰሉ ዱላ ተቀባዮቻቸው ድረስ የኦሮሞ ብሄርተኞች የሲዳማን ክልል በማዋለድ በኩል ከሲዳማ ፖለቲከኞች ጎን ቆመናል ባዮች ናቸው፣ አማካሪም ሆነው ታይተዋል፣ እንደ ትግል ስትራቴጅስትም ሲቃጣቸው ይስተዋላል፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች በዚህ ልክ ለሲዳማ ክልልነት እውን መሆን ቆመን እንደር የማለታቸውን ምስጢር መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡

ምክንያት አንድ

የመጀመሪያው ምስጢር የአዋሳ እና የአዲስ አበባ ጥያቄ ተመሳስሎሽ ነው፡፡ አዋሳን የግሉ ለማድረግ የሚሰግረው የሲዳማ ልሂቃን ምኞት አዲስ አበባን የራሱ ለማድረግ ከሚንገላታው የኦሮሞ ልሂቃን ፍላጎት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን አዲስ አበባ የኦሮሞ ተፈጥሯዊ ርስት ነች እንደሚሉት ሁሉ የሲዳማ ልሂቃንም አዋሳ ለሲዳማ ህዝብ እንደዛው ነች ይላሉ፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ከተማ ከመሆኗ እና በህገመንግስቱም የራሷአስተዳደር ያላት እንጅ በኦሮሚያ ግዛት ስር አለመሆኗ ግልፅ በሆነ ሁኔታ በመደንገጉ የኦሮሞ ልሂቃን አዲስ አበባን የራሳቸው የማድረግ ምኞታቸው ዕለቱን ሊሆን የማይችል፣ አስቸጋሪ እና ውስብስብ ሆኖታይቷቸዋል፡፡ በዚህ ላይ አዲስ አበባን የእኔ የሚያስብላቸው ከባድ ፍቅር አዲስ አበባን የጋራ መዲናው አድርጎ ከሚያስበው መላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሁሉ የሚያላትማቸው፣ ባለጋራቸውን የሚያበዛባቸው ብርቱ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ስለዚህ በተባበረ ክንድ የለሙ ከተሞች በስተመጨረሻው በአቅራቢያቸው ባለ አንድ ብሄር በባለቤትነት ሊጠቀለሉ እንደሚችሉ በአዋሳ በማስለመድ (እንደ “political pilot test” በመውሰድ) ቀጥሎ ወደ አዲስ አበባ መምጣት የኦሮሞ ልሂቃን ጥበብ ቢጤ አካሄድ ነው በሲዳማ ክልል ናፋቂ ፖለቲከኞች ዙሪያ የሚያዞራቸው፡፡ ባይሆን ኖሮ የኦሮሞ ልሂቃን የወላይታ፣ ከንባታ፣ ሃድያ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ከፋ፣ ጉራጌ ወዘተ ክልል ጠያቂዎችምን ለሲዳማ ክልል ጠያቂዎች በሚያደርጉት መጠን ሲያበረታቱ መታየት ነበረባቸው፡፡

ምክንያት ሁለት

ደቡብ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ብሄርተኞች ዘወትር በሚረግሙት እና ዛሬ እንደተደረገ ሁሉ በሚንገሸገሹበት የአፄ ምኒልክ መስፋት ወደ ኢትዮጵያ የተጨመረ ግዛት ነው፡፡ ቢሆንም የደቡብ ኢትዮጵያ ምሁራን አፄ ምኒልክን በመርገሙም ሆነ ኢትዮጵያ ለምትባል ሃገር ህልውና ምንግዴ በመሆን ከኦሮሞ ልሂቃን ጎን የሚቆሙ አይደሉም፡፡ በአንፃሩ የኦሮሞ ልሂቃን የደቡብ ምሁራን የተበድየ ፖለቲካቸው እየየ እድርተኛ እንዲሆኗቸው አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ከደቡብ ኢትዮጵያ ምድር የዘውግ ማንነቱን አስቀድሞ ኢትዮጵያዊነቱን ሁለተኛ አድርጎ ደረት የሚደቃ የተበድየ ፖለቲካው አልቃሽ ምሁርም ሆነ ፖለቲከኛ የማግኘቱ ነገር ግን በመሻታቸው ልክ አልተሳካላቸውም፡፡ ይህ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ብግን የሚያደርጋቸው ሃቅ ነው፡፡ ከዚህ ብስጭታቸው ተንፈስ የሚያደርጋቸው፣ የተበዳይ ማህበር የመመስረቱን አምሮታቸውን ለማስታገስ ዘንበል የሚልላቸው የሲዳማ ክልል ጠያቂ ልሂቅ ነው፡፡ የሲዳማ ልሂቃንም ቢሆኑ አዋሳ ከተማን ይዘን ክልል እንሁን ይበሉ እንጅ የኦሮሞ ብሄር ፖለቲከኞች በሚፈልጉት ልክ ኢትዮጵያዊነታቸውን ጠሎች አይደሉም፡፡

የኦሮሞ ልሂቃን የደቡብ ምሁራንን እና ፖለቲከኞችን ኢትዮጵያዊ ማንነትን እና እንደባንዲራ ያሉ ሃገራዊ ምልክትን በመጥላቱ ረገድ እንደ እነሱ ለማድረግ የሚፋትሩት መፋተር በሲዳማ ልሂቃን በኩል በር ያገኘ መስሏል፡፡ ይህ በር የኦሮሞ ልሂቃን በደቡብ ክልል ላይ ሲያዩት የሚጠሉትን ኢትዮጵያዊ ማንነትን የማጥበቅ ነገር የሚፈረካክሱበት ሁነኛ መግቢያ ነው፡፡ የሲዳማ ልሂቃንን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ እየተግተለተለ ያለው ወደ አስር የሚጠጉ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ አዲስ በሚመሰረቱ ክልሎች ትኩስ ብሄርተኝነትን የሚያመጣ እና የቀደመውን የደቡብ ልሂቃን የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የሚፈታተን ነገር ነው፡፡ ይህ ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር ክፉ ጠብ ላላቸው የኦሮሞ ብሄርተኘነት ፖለቲከኞች ሰርግ እና መልስ ነው፡፡

የኦሮሞ ልሂቃን ለበርካታ አመታት ምኒልክን የመርገም ተረክ በመተረኩ ስልት ማግኘት ያልቻሉትን የደቡብ ልሂቃን የተበድየ ፖለቲካ አጋርነት በሲዳማ ልሂቃን በኩል ገብተው በሚያደርጉት እጅግ የረቀቀ የፖለቲካ ስራ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የደቡብ ኢትዮጵያ ልሂቃንን በሚፈልጉት (ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ሁለተኛ አድርጎ በጎሳ ማንነት ላይ በማተኮሩ) መንገድ ለማስኬድ ይችላሉ፡፡

ምክንያት ሶስት

ከላይ በምክንያት ሁለት የተጠቀሰው የኦሮሞ ልሂቃን በደቡብ ክልል ፖለቲካ ውስጥ ያለ ፍላጎት ወደ ሶስተኛው እና የመጨሻው ምክንያት (ውጤትም ሊባል ይችላል) የሚያደርስ ነው፡፡ ይህ ሶስተኛው ምክንያት የደቡብ ኢትዮጵያ ልሂቃንን የቀደመ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አስጥሎ በኩሽ ህብረት ጥላ ውስጥ የመውደቅ ፍላጎት የመተካት ስልት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በተደጋጋሚ እየተቀነቀነ ያለው የኩሽ ህብረት ዝንባሌ የኦሮሞ ብሄርተኞች አጥብቀው የሚጠሉትን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከደቡብ ኢትዮጵያ ምድር ነቅለው እነርሱ በሚመሩት አዲስ ኩሻዊ ማንነት የመተካት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ዋነኛ አላማው በኦሮሞ ብሄርቶች ዘንድ የኢትዮጵያ ፈጣሪ የሚባለውን የአማራ ብሄር ማግለል ነው፡፡

ይህን ሲሉ ያልተረዷቸው ነጥቦች አሉ፡፡ አንደኛው የዘውግ ፖለቲካው የክርስትና አባት የሆነው እና አማራውን በመጥላት እና በማግለሉ በኩል ዋነኛ አጋር የሆነው ህወሃት መራሹ የትግራይ ምድር በኩሽ ህብረት ውስጥ ሊገባ የማይችል ሴማዊ መሆኑ ነው፡፡ በዋነኝነት አማራውን ለማግለል የተወጠነው የኩሽ ማንነት ከደቡብ ክልልም የጉራጌን እና የስልጤን ብሎም የኦሞቲክ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነውን የወላይታ፣ ዳዋሮ፣ ጋሞ፣ ጎፋ የመሳሰሉትን ህዝቦች የሚያገል ነው፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የኩሽ ህብረት በደቡብ ኢትዮጵያ ስር የሰደደውን የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ነቅሎ በሌላ ለመተካት ያለመ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ፈተና ነው፡፡ እውነት ማድረጊያው እና መግቢያው መንገድ ደግሞ የሲዳማ ልሂቃን የክልልነት ጥያቄ እንቅስቃሴ ሲሆን ፊት አውራሪዎቹም የሲዳማ እና የኦሮሞ ብሄርተኞች ናቸው፡፡

One thought on “የሲዳማ ጥያቄ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ፖለቲካ

  1. አይ ስዩሜ ሁሉም ፓስቶችህ ላይ ኦሮሞ ና ቄሮ፣ ሲዳማና ኤጄቶ፣ አዲሳባና ሀዋሳ አሉበት። አይዞን ደሴት የሆኑ ከተሞች ስለለሉን አትፍራ።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡