የፖለቲካው አዙሪት ጭምብል የጋረደው የሀገራችን ኢኮኖሚ!

በሽመልስ አርአያ

አሁን ሃገራችን ከገጠማት ፖለቲካዊ ተግዳሮት ለማገገም ከማህበራዊ ድረ-ገፆች እስከ መደበኛ የመገናኛ አውታሮች ትኩረት እየሳበ ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን እንዳለበት የሚወተውቱ ሃሳቦች መብዛት ነው። እርግጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የሰላም እጦትና የዜጎች መፈናቀል የወቅቱ የሃገራችን አንገብጋቢ ችግር እንደሆነ የአደባባይ ሃቅ ነው። ነገር ግን ለዚህ ለተጋረጠብን ፈተና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የፖለቲካ ሪፎርም በማካሄድና ዴሞክራሲን በማስፈን ብቻ ከችግሩ እንወጣለን ካልን የችግሩ ምንጭ እንዲሁም ጥልቀት በሚገባ እንዳልተረዳን ይጠቁማል። በመሆኑም የፖለቲካ ሜዳውን ለማስተካከል መፍትሄዎች እየቀረቡ እንዳሉት ሁሉ ለኢኮኖሚ ተግዳሮቶች አይነተኛ መፍትሄ የሚጠቁሙ መድረኮች እምብዛም አይስተዋሉም። የመንግስት ባለስልጣናት ከሚያቀርቡት ወቅታዊ ኢኮኖሚ ነክ ሪፖርት መነሻነት የሚኖር ውስን ሽፋን ካልሆነ በስተቀር ሃገሪቷ የተደቀነባት ፖለቲካዊ ተግዳሮት ብቻ ይመስል ሁሉም እዛው ላይ ሲረባረብ ይስተዋላል።

ከፍተኛ ስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት እና የመሳሰሉት የተጋረጠባቸው ሃገራት ፖለቲካዊ ቁመናቸው ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በመሆኑም አሁን የምንገኝበትን ምስቅልቅል ሁኔታ ላስተዋለ ከችግሩ ዋነኛ ምንጮች አንዱ ኢኮኖሚያዊ መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው። አንዳንድ ሃገራት (ለምሳሌ ቻይና) ዴሞክራሲን በሚፈለገው ልክ ባይፈቅዱም ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ወይም ከሞላ ጎደል በመመለሳቸው የተነሳ ለረጅም ዘመናት ሃገር ሳይናጋና እንደኛ የፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ ሳይገቡ መቆየት እንደቻሉ ማየት ይቻላል። A regime that succeeds in providing bread and butter for its people is guaranteed for long rule with political stability እንዲሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች እንደ የህዝብ ቁጥር እድገትና የአየር ንብረት ለውጥ (population growth(boom) and climate change) ያሉ ተግዳሮቶች ሲጨመሩ ሁኔታው ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንደሚባለው ይሆናል።

1.) አንገብጋቢና ወቅታዊ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች

ከነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ግብርና መር የኢንደስትሪ ፖሊሲ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ቢተገበርም እንደታሰበው ሽግግሩ ወደ ኢንደስትሪው መሆኑ ቀርቶ ባልታሰበ መልኩ የአገልግሎት ዘርፉ (service sector) ከግብርና መሪነቱን እንደተረከበ የሀገራዊ እድገቱን የሚተነትኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህን የተገነዘበው መንግስትም የተፋለሰውን ሽግግር ለማስተካከልና ኢንዲስትሪው የመሪነት ሚናውን እንዲረከብ ለማስቻል የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (Growth and Transformation Plan) ይዞ ብቅ አለ።

በቅርቡ የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለህዝብ ተወካዮችምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት “መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በየዓመቱ ከሃያ በመቶ (20%) ያላነሰ ዕድገት እንዲያስመዘግብ በእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተመለከተ ቢሆንም፣ በተለይም ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚጠበቀው እሴት የመጨመርና የኤክስፖርት ዘርፉን የመደገፍ ግብ መሻሻል ባለማሳየቱ በኢኮኖሚው የሚጠበቀው መዋቅራዊ ሽግግር ሳይሳካ ቀርቷል” ሲሉም ተደምጠዋል። ሌላው በሪፖርታቸው እንዳወሱት ምንም እንኳን ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት ቢሰጥም በሃገር ውስጥ ምርት ዜጎችን መመገብ እንዳልቻልን ነው የጠቆሙት። በመሆኑም በአቅርቦት እጥረት የተነሳ የምግብ ዋጋ ንረትን ለማስተካከል የውጭ ምንዛሪ በመመደብ የዳቦ ስንዴ እንዲሁም ለጨርቃ ጨርቅ ኢንደስትሪው በዋና ግብዓትነት የሚያገለግለው ጥጥ ሳይቀር ከውጭ እየገባ እንደሆነ አውስተዋል። ስለዚህ በፖሊሲው እንደተመለከተው ግብርናችን አድጎ የኢንዱስትሪ ዘርፉን መግቦ እንደታቀደው መዋቅራዊ ሽግግር ሊያደርግ ይቅርና አርሶ አደሩ እስካሁንም የዘመናዊ የእርሻ ግብዓት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንዳልሆነና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አቅም መፍጠር አለመቻሉን ስናይ ምን ያክል ወደኋላ እንደቀረን ከዚህ በላይ ማሳያ የለም።

የወጪ ንግድን በተመለከተ በዘመኑ ያጋጠመው ተግዳሮት ሲያብራሩ “የወጪ ሸቀጦች ገቢ ማሽቆልቆል ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈታኝ የሆነው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳይቀረፍ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የውጭ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ፍላጎት በሚጠበቀው ደረጃ ማሟላት አልተቻለም። በተጨማሪም በኤክስፖርት ገቢው መዳከም የተነሳም ሃገሪቱ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ላይ እራሱን የቻለ ተፅዕኖ በማሳደሩና የሃገሪቱ የውጭ ዕዳ ጫና ስጋት እንዲጨምር በማድረጉ፣ ተጨማሪ የልማት ብድር ለማግኘት እንዳልተቻለና በዚህም የተነሳ መንግስት የጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ተስተጓጉሏል” ብለዋል። ከዚሁ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተገናኘም የገቢ ዕቃዎች መጠንና የመንግሥት ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ በማድረጉ ኢኮኖሚው እንደተቀዛቀዘ አብራርተዋል።

2.) እንደ ሀገር ወዴትእያመራን ነው (Quo Vadis)?

አሁን ሀገሪቱ ከገባችበት የኢኮኖሚ አዙሪት ለመውጣት ይጠቅማሉ የተባሉና በተለያዩ ባለሞያዎች የተሰነዘሩ አንዴንዴም እርስ በርሳቸው ሲቃረኑ የሚስተዋሉ የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦች ከዚህ በታች በተደረገው የዳሰሳ ምልከታ እንደሚከተለው ተነስተዋል::

ሀ.) የኢኮኖሚው አውታር የሆኑ የመንግስት የልማት ተቋማትን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዘዋወርን (Privatization of major SOEs) ሀሳብ የሚያቀነቅኑ ምክረ ሀሳቦች

ከላይ የወቅቱ ተግዳሮት እንደሆነ በተገለፀው መሰረት የተፈጠረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ እንዲቻል በስራ ፈጣሪነቱ የሚታወቀው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከሚገኝበት ወህኒ ቤት “Ethiopia-Tipping Point (2019)” በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሃፉ አብራርቷል። በዚህ በ11 ምዕራፎች በተከፋፈለው ባለ 224 ገፅ ጥራዝ ውስጥ በዋናነት ትኩረት የሰጠው አምስት ትላልቆቹ (big fives) ብሎ የሰየማቸውን የመንግስት የልማት ድርጅቶች (State Owned Enterprises) ማለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ መርከብ እና ሎጂስቲክ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢቻል ሙሉ ለሙሉ ካልሆነም በከፊል ቢሸጡ የሚል ምክረ-ሃሳቡን ሰንዝሯል።

ከነዚህ አምስት ግዙፍ ተቋማት ጋር በተያያዘ በቅርቡ ስዊዘርላንድ ዳቮስ በአለም የኢኮኖሚ ፎረም (World Economic Forum) ላይ የተሳተፉት ዶ/ር አብይ አህመድ ቁልፍ የመንግስት የልማት ተቋማትን (SOEs) ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዛወር እቅድ እንዳላቸው የሚያሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል። የግሉን ዘርፍ ለማበረታታትና እድገቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል አስተዳደራቸው የፖሊሲ ለውጥ እንደሚያደርግ በተናገሩት መሰረት ቃላቸውን እንዲጠብቁ፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለው ኢኮኖሚ ለቀቅ ሊደረግ እንደሚገባ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት የምዕራቡ አለም ሚድያዎች (sponsored by multinational corporations) መንግስትን እየወተወቱ ይገኛሉ። በዚህም መሰረት የሰኔ 15ቱ የባህር ዳርና አዲስ አበባው ክስተት እንደመነሻ በማድረግ ፋይናንሺያል ታምስ (Financial Times) ሐምሌ 4/2019 “Ethiopia’s Abiy should stick to his liberal instincts” በሚል ርዕስ ባሰፈረው የኢዲቶሪያል አቋሙ የሃገሪቷ ፖለቲካና ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ከገባበት አጣብቂኝ ጠ/ሚንስትሩ እንዴት ሊታደጊት እንደሚገባ ባስተላለፈው ምክረ ሀሳቡ ኢኮኖሚውን በተመለከተ “For the most part, Mr. Abiy’s instincts have been right. To maintain the country’s imperative economic performance, the state’s grip should be loosened, including through the gradual and careful liberalization of the economy” ሲል ነበር በማሞካሸት ጀምሮ ማሳሰቢያውን ያሰፈረው።

.) የኢኮኖሚው አውታር የሆኑ የመንግስት የልማት ተቋማትን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዘዋወርን (Privatization of major SOEs) ሀሳብ የሚቃወሙ ምክረ ሀሳቦች

መንግስት አማራጭ ፖሊሲ ለመከተል እያማተረ ባለበት በዚህ ወቅት ይህንን ጅማሮው አጠናክሮ እንዲገፋበት የሚወተውቱ እንዳሉ ሁሉ የጠ/ሚሩ አስተዳደር በዚህ ዙሪያ በሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች ላይ ችኮላ ውስጥ መግባት እንደሌለበትና ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ስጋታቸውን የሚገልፁ እንዲሁ ብዙ ናቸው። መንግስት የጀመረው የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ በድጋሚ እንዲያጤነው “Is Ethiopia’s departure from state-led economy feasible?” በሚል ርዕስ በNew Business Ethiopia ላይ ሃሳባቸውን ካሰፈሩት መካከል አንዷለም ሲሳይ እንዳሉት “diminishing government intervention may not sustain the economic growth achieved so far. Liberalization ultimately results in millions of unemployed youth and poor farmers at the mercy of the free market” ሲሉ ድምዳሜያቸውን አስቀምጠዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ክቡር ገና “Deconstructing the privatization scam: A very British disease” በሚል ርዕስ የኬንያ ቴሌኮም ተሞክሮን ታሳቢ በማድረግ ባሰፈሩት ፅሁፍ እንዲሁ ስጋታቸውን አንፀባርቀዋል:: በከፊልም ቢሆን ለግሉ ዘርፍ ከማዛወር ይልቅ ድርጅቱ ያለበትን የማኔጅመንት ችግር በመቅረፍና በማሻሻል እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማገዝ የበለጠ አዋጭ እንደሚሆን መክረዋል። ለዚህም በምክንያትነት ያቀረቡት ቀድሞውኑም ለትርፍ ተብሎ በግሉ ዘርፍ ያልተመሰረቱ፣ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲባል በህዝብ ሃብት የተገነቡ እንደመሆናቸው ወደ ንግድ ቀጠና ማስገባት ለህዝቡ አይጠቅመውም ከሚል እሳቤ ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል። በነገራችን ላይ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወደ ግሉ ዘርፍ ተዛውሮ የነበረው የኬንያ አየር መንገድ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉን ምክንያት በማድረግ መንግስት መልሶ እንዲወርሰው የሃገሪቱ ፓርላማ ውሳኔ እስከማሳለፍ ደርሷል።

የሆነው ሆኖ የጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ምን አይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊከተል እንደሚችል ጠ/ሚሩ በዙሪያቸው የከበቡዋቸው አማካሪዎቻቸው ቀደም ብለው ይሰሩበት ከነበረው ተቋም አሰራር በመነሳት መገመት ይቻላል። የወቅቱ አማካሪዎችና የፖሊሲ ተቋማት በመምራት ላይ የሚገኙት (ለምሳሌ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፣ አቶ አበበ አበባየሁ ወ.ዘ.ተ.) ቀደም ብለው በአለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋማት (World Bank Group) ውስጥ ባሉ ተቋማት የሰሩ እንደመሆናቸው የቀደሞ ቀጣሪያቸው ሊያስፈፅመው ከተቋቋመበትና ከሚታወቅበት የአሰራር ባህል (advocating the dogmatic free-market policy) መሰረት የፖሊሲ ለውጥ እንደሚኖረን ግምታችን ቢያመላክትም ጠ/ሚሩን ወዴት ይዘዋቸው እንደሚጓዙ በሂደት የምናየው ይሆናል።

(ሽመልስ አርአያ /Shimelis Araya is a post graduate doctoral candidate at University of Giessen, Germany and can be reached via the following email: araya.gedam@gmail.com)

2 thoughts on “የፖለቲካው አዙሪት ጭምብል የጋረደው የሀገራችን ኢኮኖሚ!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡