የደኢህዴን “አዲስ ግኝት”፦ የደቡባዊ ማንነት እና ስነ-ልቦና!!

ከሰሞኑ ለአራት ቀናት በተለያዩ ሶስት ከተሞች ደኢህዴን በክልሉ ህዝቦች በተነሱ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች ዙሪያ የተደረጉ ድርጅታዊ የምክክር መድረኮችን አጠናቆ መግለጫ አውጥቷል:: በአዲስ አበባ የተደረገውን ውይይት በሚኒስትር ማዕረግ የኢሕአዴግ የዴሞክራሲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለስ ዓለሙ፤ የአዳማውን የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ የሐዋሳውን የደኢሕዴን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ነበሩ የመሩት። በመግለጫው ድርጅታዊ ህልውናውን ለማስጠበቅ ካለመ የአቋም መግለጫ ውጭ አሁን በክልሉ እየተነሱ ላሉ የህዝብ የአደረጃጀት ህገመንግስታዊ ጥያቄዎች መልስ ሊሆን የሚችል ነገርም ሆነ ፍንጭ በግሌ ባላይበትም ግን ቀልቤን የሳበውንና ከስር ያለውን ዐረፍተ ነገርና በጉዳዩ ላይ ያለኝን ስጋት ላካፍላችሁ::

“ደኢህዴን በመሪነት በቆየባቸው ዓመታት ብዝሃነት የልዩነት እና የግጭት ሰበብ እንዳይሆን በማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ብዝሃነትን በብቃት መምራት እንደሚቻል፤ እንዲሁም ህብረብሄራዊ ክልል በመመስረት በተሞክሮነት የሚጠቀስ ስራ የሰራ፤ ህዝቦችን ለአንድ የልማት አላማ በማንቀሳቀስና በማሰለፍ “ደቡባዊ የሆነ አዲስ ማንነትና ስነልቦና” በመገንባት ሂደት በክልሉ አያሌ የልማት፤ የሰላም፤ የዴሞክራሲ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡” ~ ደኢህዴን

ከላይ ባለው የመግለጫው ዐረፍተ ነገር የተጠቀሱትን ድርጅቱ ለሀገራዊው ሀገረ-መንግስት ግንባታ እንዲሁም ለክልሉ ህዝቦች ህብረ-ብሔራዊነትና አብሮነት ያበረከተው አስተዋፅኦ የሚያስመሰግነውና ለአጠቃላይ ሀገሪቱ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንደ ሞዴልም ሊወሰድ የሚችል ነው:: ሆኖም ሀገሪቱ አሁን ላይ እየተጠቀመችበት ያለውና የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው የኢፌድሪ ህገመንግስት በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ እና ሕዝቦች” ብሎ የፈረጃቸው ከጥንት ጀምሮ የራሳቸው ‘ማንነት’ ያላቸው ግን ደግሞ በአስተዳደራዊ መዋቅር ህገመንግስቱን እንደ ‘የጋራ’ መተዳደሪያ ሰነድ አድርገው ተቀብለው ‘በኢትዮጵያዊ’ የጋራ ማንነት ተሳስረው በአብሮነት የሚኖሩና የኖሩም ህዝቦችን እንጂ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የራሱን ድርጅታዊ ህልውና ለማስቀጠል ሲባል “‘ደቡባዊየሆነ አዲስ ማንነትን” “በሳይንሳዊጥናት” ያገኘሁት አዲስ ግኝት ነው ብሎ እነዚህ ህገመንግስቱ እውቅና የሰጣቸው የህዝቦች ማንነቶች ላይ የሚለጥፍባቸው ምናባዊ ህዝቦች” አይደሉም::

በዋናነት (ultimately) ደግሞ የኢፌድሪ ህገመንግስት በክልሎች አስተዳደራዊ አወቃቀር ደረጃ እውቅና የሰጠውና ከዘጠኙ የሀገሪቱ ክልሎች አንዱ የሆነው የተለያዩ ህዝቦች: ብሔሮችና ብሔረሰቦች ስብስብ የሆነው ‘የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል‘ እንጂ በ“ደቡባዊ ማንነት” እውቅና የሰጠው (recognize ያደረገው) ህዝብ የለም: ቢያንስ እስከ አሁን ሀገሪቱ እየተተዳደረችበት ባለው ህገመንግስት ማለቴ ነው:: እንግዲህ ከዚህ እውነታ አንፃር ደኢህዴን በክልሉ የሚከሰቱ “ችግሮችን” በ‘ሳይንሳዊ ጥናት‘ (informed decision) ላይ ተመርኩዞ ለመፍታት የሞከረበት አግባብ አበራታችና ምሳሌያዊ መሆኑ በጀ የሚያስብል ሆኖ ሳለ ይህ የህገመንግስቱን ልዕልና የሚጋፋና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ራሱን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነገር በሆኑ ቆም ብሎ በሰከነ መንፈስ ህዝባዊ መሠረት ያላቸውን በሳል አማራጮችን ማየቱ መልካም ይመስለኛል – ያው ድርጅቱንም ቢሆን የሚገዛው ይኸው አንድ ህገመንግስት እስከሆነ ማለቴ ነው::

ይህ አይነት የህዝብ ማንነትን ለመጨፍለቅ የሚደረግ እሩጫ ለህዝብ ተተናኳሽ (offensive) ከመሆኑም አልፎ በቀጣይነት ነገሮች ወደ ከፋ አቅጣጫ እንዲያመሩ ሊያደርግ የሚችልና ድርጅቱንም የበለጠ አደጋ ውስጥ የሚከተው አካሄድ ይመስለኛል:: ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በክልሉ በ1992 ዓ.ም. በቀደመው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ፊታውራሪነት አራት የተለያዩ ህዝቦችን (ወላይታ: ጋሞ: ጎፋ እና ዳውሮ ህዝቦች) ቋንቋዎች ጨፍልቆ አዲስና “ወጋጎዳ” የሚባል የጋራ ቋንቋ በ’ሳይንሳዊ ጥናት’ ላይ ተንተርሶ ለመፍጠር የተሞከረበት አካሄድ የፈጠረው ግጭት የብዙ ንፁሀን ዜጎችን ህይወት የቀጠፈበትና በሚሊዮኖች የሚገመት ንብረት የወደመበት ሁኔታ ነው:: …’ሳይቃጠል በቅጠል’ ያለው የሀገሬ ጠቢብ ማን ነበር??

3 thoughts on “የደኢህዴን “አዲስ ግኝት”፦ የደቡባዊ ማንነት እና ስነ-ልቦና!!

  1. አመሰግናለሁ በግል በደቡብ ኢትዮጵያ እየተሰራ ያለውን ደኢህዴን ወለድ የፓለቲካ ድራማ በማጋለጥ እያደረክ ያለው ተግባር አከብራለሁ ። ለድምፅ አልባ ድምፅ መሆን ያስከብራል ዋጋውንም ከምንጊዜውም በለይ የህሊና ዕረፍት ነው።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡