የፌደራል ፖሊስን ወደ “ማፊያነት” የሚቀይረው አዋጅ! ኮሚሽነር ጀኔራሉ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ዜጎችን ማገትና መሰለል ይችላል!

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ (ለአስተያያት የቀረበ – ረቂቅ አዋጁን ይህን ማያያዣ በመጫን ማውረድ ይቻላል)

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ለማዘጋጀት የሚከተሉት ሁኔታዎች በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፦

 • የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲሁም ህገ መንግስቱን መሠረት አድርገው የሚወጡ ሕጎችን እና ኢትዮዽያ የተቀበለቻቸውን አለምአቀፍ ስምምነቶች የማክበርና የማስከበር ተልዕኮውን በተሻለ ሁኔታና ብቃት በመወጣት የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር እንደገና ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ፤
 • በተለያዩ ተቋማት ሲሰሩ የነበሩትን ተልዕኮዎች ማለትም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የገቢዎች ሚኒስቴር፤ በፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ሲሰሩ የነበሩ የምርመራ ስራዎች ለአገልግሎት አሰጣጥና ለቁጥጥር አመች ይሆን ዘንድ በአንድ ማእከል ማለትም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲከናወኑ በመንግስት በመወሰኑ እና በኮሚሽኑ አዋጅ ማካተት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
 • የኮሚሽኑ ተልእኮ እየሰፋ በመምጣቱ እና በሀገራችንና በአካባቢው ሀገራት ያለውን ነፃ የገበያ ውድድር የሚያቀጭጨውን ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ የሚቆጣጠር የተጠናከረ የጉምሩክ፤የቱሪዝም፤ የድንበር ፖሊስ እንዲሁም የምድር ባቡርና የማዕድን ደህንነት ጥበቃ ለማረጋገጥ ይህንን የሚመጥን የፖሊስ ሀይል ማደራጀትአስፈላጊ በመሆኑ፤
 • የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ተጠሪነት ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሰላም ሚኒስቴር እንዲሆን በአዋጅ ቁጥር በ1097/2011 በመወሰኑ ይህንንም በኮሚሽኑ አዋጅ ማካተት አስፈላጊ በመሆኑ፤
 • እንዲሁም በሀገራችን የመጣውን ዙሪያ መለስ ለውጥ እና የደረስንበትን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ እድገት በሚመጥን መልኩ ሕብረተሰቡን በእኩልነት የሚያገለግል፣ በፖሊሳዊ ሥነ-ምግባሩ የታነፀ፤ ብቃትና ጥራት ያለው አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የፖሊስ ሰራዊት ለማደራጀትና ለማዘመን የተቋሙን ስልጣንና ሀላፊነት በዚያው ልክ ማሻሻልና ሊካተቱ የሚገባቸውን ማካተት አስፈላጊ በመሆኑ፤
 • በአጠቃላይ የሀገርና የህዝብ ደህንነትና ሠላምን ማስፈን፤ አገራዊ ልማትን ለማፋጠን ዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተቋሙን ህግና አደረጃጀት ከለውጡ ጋር ማስተካከል አስፈላጊ በመሆኑ፤
 • በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇ፡፡

በአዋጁ የመጀመሪያ ክፍል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር … “በኢትዮጵያ የግዛት ወሰን ሆኖ በፌደራል መንግስቱ ስልጣን ስር በሚወድቁ ፖሊሳዊ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል” ተብሎ ተደንግጓል። በአዋጁ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ “የኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ሊያቋቁም ይችላል” በሚል ይደነግጋል።

በአዋጁ አንቀፅ 7 ስር ኮሚሽኑ የህብረተሰቡን ፍላጎትና ተሳትፎ ያረጋገጠ መረጃ መር ወንጀል የመከላከል መርህን ተከትሎ የሚሰራ እንደሆነ በመጥቀስ ከዘረዘራቸው ሥልጣንና ተግባራት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

 • 14) የሽብርተኝነት ድርጊት ሊፈፀም እንደሚችል ለመጠርጠር በቂ ምክንያት ሲኖርና ድርጊቱንም ለመከላከል ድንገተኛ ፍተሻ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ሲታመንበት በተጠረጠረው አካባቢ የተገኙ ተሽከርካሪዎችና እግረኞችን በማስቆም ድንገተኛ ፍተሻ ያደርጋል፤ ተጠርጣሪ ሰዎችና ማስረጃዎችን በመያዝ ይመረምራል፤
 • 15) በሽብርተኝነትና ሌሎች በፌደራል ፍርድ ቤቶች ስር በሚወድቁ ወንጀሎች ድርጊት የተጠረጠሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በፍርድ ቤት ትእዛዝ በማንኛውም ክልል ገብቶ የመያዝ ስልጣን አለው፡፡
 • 16) የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመመርመር የሚረዳ መሆኑ የታመነበትን መረጃና ማስረጃ ከማንኛውም ሰውና ተቋም የመውሰድ ስልጣን ይኖረዋል፤
 • 29) በፌዴራሉ መንግሥት ሲታዘዝ በክልሎች ጣልቃ በመግባት ሕግና ሥርዓትን ያስከብራል ዝርዝሩ በመመሪያ ይወሰናል፤
 • 37) ለሥራ ክፍሎቹና ለፖሊስ አባላትና ሲቪል ሰራተኞች አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ቢሮዎች፤ ካምፖችና የመኖሪያ ቤቶች እንዲገነቡ ያደርጋል ዝርዝሩ በደንብ ይወሰናል፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራሉን ስልጣንና ተግባር በሚደነግገው አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀጽ (2) የሚከተሉት ይገኙበታል።

 • ሠ. በሽብርተኝነትና በሙስና ወንጀል እንዲሁም በሀገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ሚስጥር በማባከን የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የሂሳብ ስቴትመንት እንዲመረመር እንዲሁም ካለፍርድ ቤት ትእዛዝ ከ7 ቀናት ላልበጠ ጊዜ እንዲታገድ ትእዛዝ ይሰጣል፣ አስፈላጊውም ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እንዲጠለፉ ያደርጋል፣
 • ረ. አስፈላጊ በሆነ ወቅትና ሁኔታ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በአንድ አካባቢ ወይም በሁሉም አካባቢ ድንገተኛ ፍተሻ እንዲደረግ ሊያዝ ይችላል፣
 • ቸ. ኮሚሽኑ የወንጀል መከላከልና መመርመር ሀላፊነቱን እንዳይወጣ ሊያደናቅፍ የሚችል ሚስጥራዊ የሆኑ የሂሳብ መዛግብትና ሰነዶች፤ የክፍያ ማስረጃዎችን ለማንኛውም አካል እንዳይገለፁ ሊያደርግ ይችላል፤ ዝርዝሩ በመመሪያ ይወሰናል፤

የኮሚሽኑ አስተዳደር አስመልክቶ በአዋጁ ክፍል ሶስት ስር ከተደነገጉት መካከል በአንቀፅ 17 (ለ) እያንዳንዱ የፖሊስ አባል ከተመረቀበት ጀምሮ 7 አመት ለተቋሙ የማገልገል ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። በዚያው ክፍል አንቀፅ 18 መሠረት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፌደራል ፖሊስ ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚገኝ የፖሊስ አባል አግባብ ባለው የውስጥ ደንብ እና መመሪያ መሠረት ቀለብ፣ የመኖሪያ ቤት፤ የደንብ ልብስ፣ የመጓጓዣና የህክምና አገልግሎት በነፃ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡
ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር ስለሚኖር ግንኙነትን የሚደነግገው አንቀፅ 24 የሚከተሉትን ንዑስ አንቀፆች አካትቷል፦

 1. ኮሚሽኑ እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች የሚኖራቸው አደረጃጀት እንደተጠበቀ ሆኖ በመካከላቸው የሚኖረውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ጉባኤ ያቋቁማሉ፡፡
 2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት የሚቋቋመው የጋራ ጉባኤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ሰብሳቢነት ይመራል፡፡
 3. የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽኖች ተጠሪነታቸው ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤው አባል ይሆናሉ፡፡

በአንቀፅ 24 ንዑስ አንቀፅ 3 መሠረት የሚቋቋመው “የጋራ ጉባኤው” ያሉትን ሥልጣንና ተግባራት አስመልክቶ በአንቀፅ 25 ከተዘረዘሩት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

 • ሀ) በፖሊሳዊ ሙያና ሥነ-ምግባር የታነፁ አባላትን ያቀፈና በተገቢው ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የፖሊስ ተቋም በየክልሉ የሚገነባበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
 • ሐ) በክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ሊኖር የሚገባውን አደረጃጀት እና ትጥቅ በተመለከተ ይወስናል፣ ይከታተላል፣
 • ቀ. ከክልሎች አቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች ኮሚሽኑ በመንግሥት ውሳኔ መሠረት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ ገብቶ በሚሠራበት ወቅት የሚመለከታቸው የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ትብብር የማድረግ ግዴታቸውን በተገቢው መወጣታቸውን ይከታተላል፣ ውሳኔ በማስተላለፍ ለሚመለከተው አካል ያቀርባል፡፡
 • በ. በኮሚሽነሮች ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች በሁሉም የፖሊስ ኮሚሽኖች ተግባራዊ መደረጋቸውን ይገመግማል፣ በክፍተቶቹ ላይ አቅጣጫ ያስቀመጣል፣ ለሚመለከተው የመንግስት አካልም ያቀርባል፣

በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ በአንቀፅ 27 “ስለ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች” እንደሚከተለው ይደነግጋል፦

 1. የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽኖች ተጠሪነት ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሆኖ እንደገና በዚህ አዋጅ ተቋቁመዋል፤
 2. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ኮሚሽኑ በሚሰጠው ውክልና መሠረት ተጠሪነታቸው ለየከተሞቻቸው አስተዳደር እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል፡፡
 3. የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖቹ ዓመታዊ ዕቅዳቸውንና የሥራ አፈፃፀማቸውን ሪፖርት ለኮሚሽኑና ለየከተሞቻቸው አስተዳደር ያቀርባሉ፤ ሆኖም በጀታቸው በየከተሞቻቸው አስተዳደር ም/ቤቶች ይወሰናል፡፡
 4. የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች የበላይ ኃላፊዎች በሚኒስትሩ አቅራቢነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ ሆነው የሁለቱም ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች ምክትል ሀላፊዎች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል አቅራቢነት በሚኒስትሩ ይሾማሉ፡፡