አስደንጋጭ ዜና፦ ከእነመልሱ የወጣው የ12ኛ ክፍል ፈተና!

የ12ኛ ክፍል ፈተና በዚህ መልኩ የተበላሸበት ምክንያት የተማሪዎች ኩረጃ ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ፈተናውን ያወጣው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትልቅ ስህተት በመፈፀሙ ምክንያት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የፈተናዎች ኤጀንሲ ከፍተኛ ባለሙያ አነጋግሬያለሁ። በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በተለያዩ ኮርሶች ከ95 – 100 ያመጡበትን ምክንያት አስመልክቶ በመጀመሪያ የነበረኝ ግምት፤ መምህራን መልሱን ሰርተው ለተማሪዎች ሰጥተዋል ወይም በፈተና ክፍል ውስጥ በቡድን እንዲሰሩ ፈቅደዋል የሚል ነበር። የኤጀንሲው ባለሙያ “ተማሪዎቹ በቡድን መስራታቸው እርግጥ ነው። ለተማሪዎቹ መልሱን አሳልፎ የሰጠው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንጂ መምህራኑ አይደሉም” አለኝ።

የኤጄንሲው ባለሙያ ሁኔታው እንዲያስረዳኝ ስጠይቀው “የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ማን ይባላል?” የሚለውን ጥያቄ እንደ ምሳሌ በመውሰድ አስረዳኝ። ይህ ጥያቄ ለምሳሌ በአራት የተለያዩ ኮዶች ላይ በተለያየ ተራ ቁጥር ላይ ይገኛል። በሁሉም ኮዶች ላይ ጥያቄው ተመሣሣይ ሲሆን የሚለያየው በጥያቄው ተራ ቁጥር እና ከA – D በተሰጡት አራት ምርጫዎች ቅደምተከተል ነው። በዚህ መሠረት፣

  • በኮድ19 “የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ማን ይባላል?” ለሚለው ጥያቄ ያሉት ምርጫዎች፤ A) አዲስ አበባ B) ድሬዳዋ C) ጅማ D) መቀሌ።
  • በኮድ20 ስር ለሚገኘው “የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ማን ይባላል?” ለሚለው ጥያቄ ምርጫዎቹ፤ A) ድሬዳዋ B) አዲስ አበባ C) ጅማ D) መቀሌ
  • በኮድ21 ስር ለሚገኘው “የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ማን ይባላል?” ለሚለው ጥያቄ ደግሞ ምርጫዎቹ፤ A) ድሬዳዋ B) ጅማ C) አዲስ አበባ D) መቀሌ
  • በኮድ22 ስር ለሚገኘው “የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ማን ይባላል?” ለሚለው ጥያቄ ምርጫዎቹ፤ A) ድሬዳዋ B) ጅማ C) መቀሌ D) አዲስ አበባ

ከላይ በቀረበው ምሳሌ መሠረት መልሱ በአራቱም ኮዶች ላይ ቦታው ይቀያየራል። ድሬዳዋ የሚለው ምርጫ ሶስቱ ኮዶች ላይ A እና አንዱ ላይ B ነው። ጅማ የሚለው ምርጫ ሁለቱ ኮዶች ላይ B፣ ሁለቱ ላይ ደግሞ C ነው። መቀሌ የሚለው ምርጫ ሶስቱ ኮዶች ላይ D እና አንዱ ላይ ደግሞ C ነው። አዲስ አበባ የሚለው ምርጫ (መልሱ) ግን አንደኛው ኮድ ላይ A፣ ሁለተኛው ኮድ ላይ B፣ ሶስተኛው ኮድ ላይ C፣ አራተኛው ኮድ ላይ ደግሞ D ነው። ስለዚህ አራት የተለያዩ ኮዶች ያላቸው የፈተና ወረቀቶች በተርታ አስቀምጣችሁ ብትመለከቱ የጥያቄው መልስ ከታች በምስሉ ላይ እንዳለው ቁልጭ ብሎ ይታያል።

አብዛኞቹ ተማሪዎች 90ና ከዚያ በላይ ውጤት ያመጡባቸው ፈተናዎች በመጨረሻ ሁለት ቀናት (ሰኞና ማክሰኞ) በወሰዷቸው ኮርሶች ነው። የመጀመሪያ ሁለት ቀናት (ሐሙስና አርብ) ከተፈተኑ በኋላ ቅዳሜና እሁድ እረፍት ላይ ነበሩ። በእነዚህ የእረፍት ቀናት ነው እንግዲህ የተለያየው ኮዶች ያላቸውን የፈተና ወረቀቶች አንድ ላይ ሰብስበው ሲያመሳክሩ የፈተናውን የመልስ ቁልፍ (Answer Key) ያገኙት። በአራቱም ኮዶች ላይ የሚቀያየረው ምርጫ መልስ ነው። በዚህ መሠረት ተማሪዎቹ በጭራሽ ፈተና ተፈትነዋል ማለት አይቻልም። ምክንያቱም የ12ኛ ክፍል ፈተና ከእነመልሱ የተሰጠ ነው።


ማሳሰቢያ

እነዚህ ጥያቄዎች የመልሱን ቁልፍ (Answer Key) በአራቱ ኮዶች ላይ ያለውን ስብጥር ወይም ተዋረድ (Pattern) ለማሳየት እንደ ማሳያ የተጠቀምኳቸው ምሳሌዎች እንጂ ከ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተወሰዱ ትክክለኛ ጥያቄዎች አይደሉም።