ሁለተኛ ደረጃ መሃይምነትን የማስወገድ ጉዞ እና የመምህራን ክብር

ትምህርትና ምሁራን ትላንትና ዛሬ…

በ1730 ዓ.ም ስልጣነ መንበሩን የተቆናጠጠው ቋረኛው ንጉስ ዳግማዊ እያሱ ለትምህርትና ለሳይንስ ታላቅ ቦታ ነበራቸው ይባላል፡፡ እኚህ ንጉስ በሀገሪቱ ትምህርት እንዲስፋፋና የተማረ ሰው በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲኖረው የጣሩና በተግባርም ያሳየ ታልቅ መሪ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይዠክራሉ፡፡

ንግሱ በኢትዮጲያ ትምህርት ተስፋፍቶ ለማየት ካለቸው ፍላጎት የተነሳ ትምህርትን እና የተማረን ለማበረታታት ልዩ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ንጉሱ በዘመናቸው ትምህርትን ለማበረታታት አዋጅ አወጣ፡፡ አዋጁም የተማረ ሰውን የሚያበረታታና ማንኛውም በትምህርት አለም ያለ ሰው የትምህርት ደረጃው በጨመረ ቁጥር በቤተ-መንግስቱ፣ በህብረተሰቡና በሀገሪቱ የሚኖረውን የክብር ቦታ የሚጨምር አዋጅ ነበር፡፡

በንጉሱ አዋጅ መሰረት በህዝቡም ዝቅተኛ ግምት፤ በቤተ መንግስቱም ተራ ምግብ የሚሰጣቸው ማንበብም ሆነ መጻፍ ለማይችሉ ሰዎች ነበር፡፡ ነገር ግን በሳይንሳዊ ጥናት ውስጥ ላለ ሰው ከምግቡ ጋር አብሮ ጠላ ይቀርብለታል በህብረተሰቡም ውስጥ ክብሩ ይጨምራል፡፡ ከዚህ ላቅ ብሎ በትምህርቱ ከገፋ ለምሳሌ ቅኔ ከተቀኘ ከምግቡ ጋር አብሮ ጠጅ ይቀርብለታል (በዚያን ዘመን በህብረተሰቡ ከፍ ያለ ቦታ ያላቸው እና የተከበሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ ጠጅ የሚጠጡት)፡፡ ከዚያም ቅኔን ጨርሶ ወደ መጻህፍት ጥናት የተሻገረ ሰው ሁሉ በህብረተሰቡ የመጨረሻው ትልቅ ክብርና በቤተ መንግስቱም የመጨረሻው ምርጥ ምግብ ይቀርብለታል፡፡

ትምህርት እና የተማረ ሰው እንዲከበር ሲባል የወጣውን የኢትዮጲያ የመጀመሪያው የትምህርት አዋጅን ተከትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዳግማዊ እያሱ ቤተ መንግስት የብዙ ተማሪዎች መሰብሰቢያ ሆነ ብዙ ምሁራንም ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ በዚህ ዘመንም ብዙ መጻህፍት ከአረብኛ ወደ ግዕዝ ተተርጉመው የትምህርቱና የመጻህፍቱ መናኸሪያ እንዲሆን ወደተመረጠውና ጣና ወደሚገኘው የቅዱስ ገብርሄል ገዳም መጓዝ ተጀመረ፡፡ በዮሀናና አንድሬዝ ተጽፎ “የኢትዮጲ ታሪክ” በሚል ርዕስ በአለማየሁ አበበ ተተርጉሞ  በ2003 ለህትመት የበቃው መጽሀፍ እንደሚያትተው የአጼ እያሱን አዋጅ ተከትለው የተሰበሰቡት መጻህፍት እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ እስከ ዛሬ ድረስ ያልተነበቡ መጽሀፍት በጣና የቅዱስ ገብርሄል ገዳም ይገኛሉ፡፡

እኚህ ለጥበብና ለትምህርት ትልቅ ቦታ የነበራቸው ታላቅ መሪ ዛሬ ከ280 አመታት በኃላ አንድ ግዜ ቀና ብለው ሀገራቸው ለትምህርት እና ለተማረ ሰው ያላትን ቦታ ቢያዩት ምን ይሉ ይሆን?፡፡ እኚህ መመራመርንና መጠየቅን የሚወድ ትውልድን ለመፈጠር ይጥሩ የነበሩ የትምህርት አርበኛ ዛሬ ከአንድ አሳብ ውጪ የሚያቀነቅንን ሰው በእናት ሀገሩ የእንጀራ ልጅ መሆኑን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን?፡፡

ይህች ሀገር ያጣችው የተማረ ሰው ብቻ ሳይሆን የተማረም ሀሳቢ እና ለሀገር ተቆርቋሪ ጭምር ነው፡፡ በየዩኒቨርስቲና ኮሌጁ የሚገኘው ከአጠቃላይ ህዝብም “የተሻለ” ነው የሚባለው ተማሪም ሆነ መምህራ ህዝቡን በትክክል አድምጦ ለችግሩ ከመድረስ ይልቅ ለጥቂት ስግብግብ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ በመሆን እራሱን ቆላና ደጋ ብሎ ከፋፍሎ ለእድገቷ ጋሬጣ ሆኖባታል፡፡ ስንቶች ለክብሯ እና ለማንነቷ የሞቱላትን ሀገር የተሻለ ነገር ማድረግ ሲገባው እሱም የልጅ ጠላት ሆኖባታል፡፡ ታዲ ይህንን ትውልድ ያኚ የሀገሬን ችግር በተማረ ሰው እፈታለው ብለው አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ ንጉስ አንድ ግዜ ቀና ብለው ቢያዩት ምን ይሉት ይሆን?፡፡

ከ280 አመታት በፊት የተለያዩ ገዳማት በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ገዳማቱ የእውቀት መሰረቶች ናቸውና በእያንዳንዳቸው ግቢ አንድ አንድ ዛፍ እንዲተከል በሚል አዋጅ ያወጡት እኚህ የትምህርት ወዳጅ ንጉስ ዛሬ የእውቀት መሰረት የሆኑት ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሎጆች በእውቀት እንዶድ የታጠበ ጭንቅላትና ትውልድ ከመፍጠር ይልቅ እውቀትን፣ ማንበብንና መመራመርን የሚፈራና መጠየቅን እንደ ነውር የሚያይ የወረቀት (ምርቃት) ተኮር ትውልድ ማምረቻዎች መሆናቸውን፣ አስመርቀው የሚያስወጧቸው “ተመራቂዎችም” አብዛኛዎቹ ጠንከር ያለ አሳብ ላይ መወያየትን የሚፈሩ፣ መጻህፍትን እና ጋዜጣን ከሽፋኑ በዘለለ የመመልከት ሞራል የሌላቸውና የፌስቡክ ወታደሮች  መሆናቸውን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን?፡፡

ሁለተኛ ደረጃ መሃይምነትን የማስወገድ ጉዞ

የ20ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓን የትምህርት ታሪክ መሰረት በማድረግ ሀገራት በሁለት ደረጃ የሚታይ መሀይምነት እንደሚያስተናግዱ ጆርጅ ኢሊዮት የተባሉ ጸሀፊ ይጠቁማሉ፡፡ የመጀመሪያው ደረጃ መሀይምነት የሚከሰተው አብዛኛው ማህበረሰብ የመማሪያ ትምህርት ቤቶች ከማጣቱ የተነሳ ሲሆን በዚህም ሳቢያ መጻፍም ሆነ ማንበብ ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ የዚህን ደረጃ መሀይምነት ማስወገድ የሚቻለው ትምህርት ቤቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግና በብዛት ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ነው፡፡ ይህንን ደረጃ መሀይምነት ለማስወገድ ደርግ “እድገት በህብረት” በሚል መፈክር ብዙዎቹን የገጠርና ከተማ ነዋሪዎችን ለማስተማር፣ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ የኢህአዴግ መንግስትም “አንድም ህጻን ከትምህርት እንዳይቀር” በሚል መፈክር ለጎልማሶች ጨምሮ ትምህርት ቤቶችን በየቀበሌውና መንደሩ በመክፈት ሁሉም ህጻንም ሆነ ጎልማሳ እንዲማር አድርጓል፡፡ ይህንን ደረጃ መሀይምነት በማስወገዱ ረገድ ሀገራችን ስኬታማ ነች ማለት ይቻላል፡፡

ጆርጅ ኢሊዮት እንደሚሉት ሁለተኛው ደረጃ መሀይምነት እጅጉን የከፋ እና የመጀመሪያ ደረጃ መሀይምነትን ለማስወገድ በተደረገው ጥረት (ተደራሽነት ላይ ብቻ ትኩረት በመደረጉ) የተነሳ የሚከሰት ነው፡፡ በሀገሪቱ የሚታየው መሀይምነት መገለጫዎችም አስደንጋጭና ፈጣን እርምጃን የሚሹ ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች ከማንበብና ከመጻፍ የዘለለ ጠንከር ያለ ቁም ነገር ለማድረግ ይከብዳቸዋል፡፡ ተማሪዎች ምንም እንኳን የተማሩ እና በትምህርት ደረጃ ላቅ ያለ ቦታ (ለምሳሌ ዩኒቨርስቲ የጨረሱ) ቢሆኑም ያላቸው እውቀት ግን ዝቅተኛ እና ከተባለው ደረጃ ጋር የማይመጣጠን ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ያለውን መሀይምነት ማስወገድ የሚከብደው ተማሪዎቹን የመጀመሪያውን ደረጃ መሀይምነት ለማስወገድ ስንል አውቃቹዋል ብለናቸው እዚህ ደረጃ ላይ  ሲደርሱ አታውቁም ማለቱ በተማሪዎቹም ሆነ በመንግስት ላይ የሚያመጣው ቀውስ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ደረጃ መሀይምነት በሀገራችን አሁን ላይ እየታየ እንደሚገኝ ለመታዘብ ቀላል ይመስላል፡፡

እንግሊዛዊቷ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ገጣሚና ሀያሲ ጆርጅ ኢሊዮት በ1860 በጻፉትና ስለ አውሮፓ ትምህርት በሚያወራው The Mill in the Folss በተሰኘው ልበ-ወለድ ነክ መጽሀፋቸው ሀገራት ሁለተኛ ደረጀውን መሀይምነት ማጥፋት የሚችሉትና አዋቂና ተመራማሪ ትውልድን የመፍጠር ህልማቸውን የሚያሳኩትም ሆነ የትምህርትን ጥራት ማስጠበቅ የሚችሉት ለምሁራን ተገቢውን ክብርና ትኩረት መስጠት ሲችሉና ይህንንም የማይደራደሩበት የፖሊሲ ሀቅ ሲሆን ነው ይላሉ፡፡ በትምህርት ጥራት አንቱ የተባሉ ሀገራትን የትምህርት ሂደት ስንመረምር የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ አጼ እያሱ ግን ይህንን እውነታ ከጆርጅ ኢሊዮትና ከአውሮፓውያኑ በፊት ቀድመው ከ100 አመታት በፊት የተረዱት ይመስላሉ፡፡

ኢህአዴግ መራሹ መንግስትም ከ50 በላይ ዩኒቨርስቲዎችን ከፍቶ ካበቃ በኃላ ቀጣዩ እቅዴ ከተደራሽነት ወደ ትምህርት ጥራት (ሁለተኛ ደረጃውን መሀይምነት ወደ ማጥፋቱ) መዞር ነው እያለ ይገኛል ፡፡ ምንም እንኳን እንቅስቃሴው ከጊዜያዊ የፖለቲካ ቁማር የዘለለ ባይሆንም በ2008 ዓ.ም “የመምህራንን ክብር በመመለስ” የትምህርት ጥራትን አስጠብቃለው በማለት የደሞዝ ጭማሬና ሌሎች ጥቅማ ጥቅም ለመስጠት ጥረት አድርጓል;; የሌሎች ሀገራት ትምህርትን ስንመረምርም ሆነ የሀገራችንን የኃላ የትምህርት ታሪክ ስናይ የትምህርት ጥራት የሚጠበቀው በደሞዝ ጭማሬና ለቤት መስሪያ መሬት በመስጠት ብቻ አይደለም፡፡

“ትምህርት” ሰፊ ነው በውስጡም ብዙ ተዋንያን አሉ ለእነዚህ ተዋንያን ልክ እንደ ዳግማዊ እያሱ ተገቢውን ክብር እና ቦታ ስንሰጥና ተስማሚና የተጠና ፖሊሲ ሲታከልበት ያኔ ጥራት ትመጣለች፡፡

3 thoughts on “ሁለተኛ ደረጃ መሃይምነትን የማስወገድ ጉዞ እና የመምህራን ክብር

  1. በጣም ጥሩ በጥናት ላይ የተመሰረተ የበሰለ ፅሁፍ በመሆኑ ወድጀዋለሁ…!

    በዝህ የአፃፃፍ ክህሎትዎ ሰሞኑን እያንጫጫ ስለሚገኘ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ያልዎትን ምልከታ እንዲሁ ቢያጋሩን ሙሉ ምስል ብንይዝ መልካም ነው።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡