በከርሞ በሬ አይታረስም፤ ሀገርም በለውጥ አትፈርስም!!

ኢትዮጵያ አሁን ፍሬን የበጠሰ ባቡር ነች! ፍሬን የበጠሰን ባቡር ደግሞ ወይ ‘derail’ ታደርጋለህ አሊያም እጅህን አጣጥፈህ የሚመጣውን በፀጋ ትቀበላለህ:: አሁን ላይ እንደ አገር በመላው ሀገሪቱ የተቀጣጠለው የለውጥ ፍላጎትን በአግባቡና በግዜ ሊያስተናግድ የሚችል ተቋማዊም ሆነ ሀገራዊ ብቃት ላይ አይደለንም:: ‘ፖለቲከኞቻችንም’ ቢሆኑ እንዲህ አይነት የህዝብ የለውጥ ፍላጎትን ለማስተናገድ የሚችል የእውቀትና የልምድ ዝግጅት ይሁን ተቋማዊ ጥንካሬ የላቸውም:: ይህ የሆነበትም ምክንያት የቀደመው ህወሓት መሩ ኢህአዴግ በሀገሪቱ የድርጅቱ አባልም ይሁን አጋር የሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችን ሲያደራጅ የወጠነው ፖለቲካል ሲስተም ማሽን እየሰራ እንዲቀጥል በታማኝነት ነዳጅ/ከሰል የሚጨምሩና በድርጅቱ ‘ቀኖና’ የሚያምኑ “ታማኝ ካድሬዎች” ስብስብ አድርጎ እንዲሁም ከድርጅቱ ህልውናም ይሁን ተለምዷዊ አሰራር ውጭ operate ማድረግ የሚችሉ independent thinkers ስብስብ እንዳይሆኑ by design የሰራበት ነገር በመሆኑ ነው::

Naturally የእኛ ሀገር የፖለቲካ ‘ምሁራን’ ዋነኛው ችግር ተምረው እውቀት ጨብጠውም ከቀደመው ታሪካችን አለመማራቸው ነው:: በእርግጥ በዋነኛዎቹ ርዕዮታዊ አደረጃጀት ባላቸው እንደ ኢህአዴግ ባሉ የፖለቲካ ተቋማት (within the establishment political institutions) ውስጥ ለአበልና ለስልጣንና እንዲሁም ተያይዘው ለሚመጡ ጥቅማጥቅሞች ብሎ ከተሰገሰገው ካድሬ ውጭ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ ፖለቲካን የሚያራምዱ ፖለቲከኞች (mainstream politicians) እጅግ ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ይታወቃል:: የፖለቲካ ምሁር ማለት በመሰረቱ ለህዝብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንዲሁም የፍትህ ጥያቄዎች የሀገሪቱን የዘርፉን ባለሙያዎች አስተባብሮ መፍትሄ መፈለግ የሚችል critical thinking ያዳበረ እንጂ ከየኮሌጆች ዲግሪ በገንዘብም ሆነ በራሱ ልፋት ያግበሰበሰ አይደለም:: የአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ እውነትም የተማሩ ምሁራን አሉት ሊባል የሚችለው ደግሞ ህዝብ ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎችን በህዝቡ ፍላጎት አቅጣጫ መፍትሄ እያበጀ ከጊዜ ወደ ግዜ ለሚነሱ የህዝቡ ጥያቄዎች ግዜውን የጠበቀ መፍትሄ መስጠት ሲችል ነው::

ኢህአዴግና የተቋማዊ ስር-ነቀል ‘ለውጥ’ ፍርሀቱ

ባለፈው አንድ አመት ከግማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ እየነፈሰ ያለውን የለውጥ ንፋስ ተከትሎ በደቡብ ክልል የተነሱ የተለያዩ የክልሉ ህዝቦች የክልል የአደረጃጀት ጥያቄዎች የአሀዳዊ ፖለቲካ አቀንቃኝ የፖለቲካ ‘ምሁራን’ ነን ባዮች ‘ሀገር ያፈርሳል’ በሚል ጭፍን ሎጂክ ተቃውሞ ማሰማት እና የክልሉ መሪ የፖለቲካ ድርጅት ጉዳዩን እስካሁን የያዘበት አግባብ የዚህ ሀገራዊና ስር-ነቀል ችግር አንዱ ማሳያ ነው:: ከቀድሞው ጠ/ሚር መለስ ዜናዊ ቀመር ውጭ የሚሞከር አስተዳደራዊ አማራጭ ሀገር ያፈርሳል ብሎ ማሰብ ለዘመኑ ታላላቅ የሀገራችን ምሁራን ስድብ ነው:: በእርግጥ መለስ ኢትዮጵያን ከቀድሞው ጠ/ሚር ሀይለማሪያም ደሳለኝና ዶ/ር አርከበ እቁባይን ከመሳሰሉ የሀገራችን ኢንዳስትሪ አብዮት ቀማሪዎችና ፋና ወጊዎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ወደ ኢንዳስትሪው አብዮት እንድትወነጨፍ የሰሩት ስራ አለም ያጨበጨበለት ነው:: በዛው ልክ ደግሞ ሀገሪቱ አሁን ለገባችበትም የተጠላለፈ የፖለቲካ አዘቅት የቀመሩ ባለቤት መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው::

ታዲያ የሰለጠነ ፖለቲካን ማራመድ ማለት ጥሩ የሰራውን (what worked well) ይዞ በማስቀጠል የተበላሸውን እያስተካከሉና በእድገት ከቀደሙ ሀገሮች ልምድ እየወሰዱ ወደፊት መቀጠል እንጂ በራሱ የተጠላለፈና የወደቀ ሲስተም (a failed and self-defeating system) ካላስቀጠልኩ ብሎ ሀገርን ከመፍረስ ቋፍ ማድረስ አይደለም:: ይህ የፖለቲካ ክፍተት በደቡብ ክልል የተነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች እስካሁን በተስተናገዱበት አግባብ በግልፅ ተንፀባርቋል:: እኔ በበኩሌ የኢትዮጵያን ህዝቦች ሁሉ እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግና ህዝቡ በነቂስ አምኖበትና ፍፁም ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ድጋፉን የለገሰውን የትኛውም ስርዓት ከመቀበልና ከመደገፍ አላመነታም:: ዋናው ጥያቄ ታዲያ አሁን ባለው የደቡብ የክልሉ አደረጃጀት ህዝቡ ተስማምቷል ወይ ከተስማማስ ለምን በየአከባቢው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በነቂስ ሰላማዊ ሰለፍ ወጥቶ የአደረጃጀት ለውጥ እንዲደረግ ወይም ራስን በራስ ለማስተዳደር ህገመንግስታዊ ጥያቄ አስነሳ የሚለው ነው?

የማያፈናፍነው የህዝቦች መሰረታዊ የለውጥ ጥያቄና መፍትሄው

ሀገራችን አሁንም ሆነ ባለፉት 28 አመታት ስትተዳደርበት በቆየችው ፌዴራላዊ ስርዓት በህገመንግስቱ “ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ተብለው የተፈረጁት ተማምነው የተፈራረሙበት የጋራ መተዳደሪያ ሰነድ የሆነው የሀገሪቱ ህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ይኸው ህገመንግስት ራስን በራስ ማስተዳደር ለመረጠና ለፈለገ የትኛውም ህገመንግስቱ እውቅና የሰጠው ህዝብ (እዚህ ጋር ይኸው ህገመንግስት ከመፈጠሩ ከሺህ ዘመናት በፊት ያው ህዝብ በሚኖርበት መሬት የራሱ ባህልና ስርዓት ኖሮት እራሱን በራሱ ሲያስተዳድር እንደኖረ ልብ ይሏል) መብቱን አስቀድሞ አክብሮለታል:: ይህ ማለት ደግሞ በማንኛውም ግዜ በነባራዊው የክልል አደረጃጀት መዋቅር ፍትሀዊ እና በህዝቦች እኩልነት ላይ በተመሰረተ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አልነበረኝምና በክልል ተደራጅቼ ራሴን በራሴ ላስተዳድር ባህሌንና ማንነቴን ላጎልብት ካለ ይኸው መብቱ ይኸንኑ ህገመንግስታዊ አካሄድ ተከትሎ by default ተግባራዊ ይደረጋል ማለት ነው::

በከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የዞኑን ህዝቦች የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ተከትሎ በጠ/ሚር አብይ አህመድ የተመራው የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት የያዘ ቡድን ለማወያየት በሄደበት ወቅት የወጣው የዞኑ ህዝብ

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ሀገሪቱ ውስጥ ከተፈጠሩና conventional የሆነውን establishment ፖለቲካችንን መሰረት ካናጉት ስር-ነቀል የለውጥ ፍላጎትና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች አንፃር የደቡቡ የኢትዮጵያ አካባቢ ዘግይቶም ቢሆን ተቀላቅሏል:: የክልሉ መሪ ድርጅት ደኢህዴንም ቢሆን ሀገሪቱ በከፍተኛ ትንቅንቅ በተወጠረችበት ሰአት ለ’ለውጡ’ ቡድን አብላጫ ድጋፉን በመስጠት ጎራ የመለየት ውሳኔ ወስዷል:: ይህም ውሳኔው በ’ለውጡ’ ሂደት የራሱ የሆነ አበርክቶት ቢኖረውም ካለፈው አንድ አመት ወዲህ በራሱ ክልል ከጫፍ እስከ ጫፍ የተቀጣጠሉ የክልሉ ህዝቦች ስር-ነቀል የለውጥ ፍላጎቶች አንፃር ነገሮችን የያዘበት አግባብ ግራ እንደተጋባና ድርጅቱ እራሱ ለስር-ነቀል ለለውጥ ዝግጁ እንዳልሆነ አሳብቆበታል::

በተለይም ሲዳማ ዞንና የክልሉ ዋና ከተማና መቀመጫ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ አካባቢ ነግሶ ከቆየው ስርዓት አልበኝነት ጋር በተያያዘ የሚያስተዳድራቸው የተለያዩ ዞኖች ተወላጆችን ደህንነትና ፍትህን ከማረጋገጥ እንዲሁም የህግ የበላይነትን ከማስፈን አንፃር ያሳየው ዳተኝነት በዚሁ ግዜ ውስጥ የክልልነት ጥያቄ ባነሱ ህዝቦች ዘንድ ቅቡልነትን እንዲያጣ አድርጎታል:: በእርግጥ ይህ አቅመ ቢስነት የተፈጠረው በድርጅቱ የአንድ ብሔር አንጃዎች የክልሉን ቁልፍ ተቋማት ስልጣን በመቆጣጠር የውሳኔዎች monopoly እንዲፈጠር በማድረጋቸው ነው:: ሆኖም በከርሞ በሬ አይታረስምና ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት የፖለቲካ እውነታ (political reality) የሚመጥን ተራማጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ በማምጣትና ከህዝቡ ፍላጎት ጋር በማጣጣም ማስኬድ የረፈደበት ውሳኔ ቢሆን እንጂ ሀገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት ብቸኛው አማራጭ ነው::

2 thoughts on “በከርሞ በሬ አይታረስም፤ ሀገርም በለውጥ አትፈርስም!!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡