በኢህአዴግ ውህደት የሚፈርሰው ህወሓት ወይስ ኢትዮጵያ?

“የኢህአዴግ ውህደት እና የህወሓት አጥፍቶ መጥፋት” በሚለው ፅሁፍ ለመግለፅ እንደተሞከረው ህወሓት የህወሓት አጥፍቶ መጥፋት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል። ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ የወሰዳቸውን ዝርዝር ተግባራት፣ እንዲሁም የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መቀሌ ላይ እያደረገ ባለው ስብሰባ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች መመልከት ከመጀመራችን በፊት ባለፉት አራት አመታት የታዩትን ለውጦች በአጭሩ እንመልከት።

በጥቅሉ ከ2008 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በመላ ሀገሪቱ ተስፋፋ። ከ2009 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ ኦህዴድ እና ብአዴን በኦሮማራ ጥምረት አማካኝነት ራሳቸውን ከህወሐት አገልጋይነት ነፃ አወጡ። በ2010 አጋማሽ ላይ የህወሓት የስልጣን የበላይነት ተወግዶ አዲስ አመራር ወደ ስልጣን መጣ። አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣበት ግዜ ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ አምስቱን አጋር ድርጅቶች እና ደህዴንን ከህወሓት ተፅዕኖ እና መገልገያነት ነፃ አወጣ። በዚህ ረገድ የአብዲ ኢሌ ከስልጣን መወገድ፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ግሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ አፋርና ድሬዳዋ የተደረጉት የአመራር ለውጦች ይጠቀሳሉ።

ፎቶ፦ Tigrai Online

በአንፃሩ ህወሓት እስከ 2011 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶችን በመጠቀም እድሜውን የማራዘም ተስፋ ነበረው። ለዚህ ደግሞ የኦሮሞና አማራ ልሂቃን ከስልጣን ክፍፍል ጋር በተያያዘ በመካከላቸው አለመግባባት ይፈጠራል። በዚህም የህወሓትን አከርካሪ የሰበረው የኦሮማራ ጥምረት በራሱ ግዜ ይሰበራል የሚል ተስፋ ነበራቸው። በሌላ በኩል አጋር ድርጅቶች በሀገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ የባለቤት ስሜት እና የመወሰን ስልጣን እስከሌላቸው ድረስ ከፌደራሉ መንግስት ጋር ተቀራርበው አይሰሩም የሚል እምነት ነበራቸው።

በዚህ መሰረት ኢህአዴግን እንደ አንድ መታገያ መድረክ በመጠቀም በተለይ በኦህዴድ/ኦዴፓ እና ብአዴን/አዴፓ መካከል ያለውን ልዩነትና ክፍተት ይበልጥ በማስፋት የኦሮማራን ጥምረት ለማዳከም ሞክሯል። ከዚህ በተጨማሪ የኦሮማራ ጥምረት ፍፁም ዘረኛ እና አግላይ እንደሆነ በመግለፅ ለደህዴንና አጋር ድርጅቶች ስጋት መሆኑን ለማሳየት ተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል። በዚህ መልኩ ህወሓት በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል፣ እንዲሁም በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች መካከል ያሉትን ክፍተቶች በማስፋትና በመጠቀም ወደ ስልጣን ለመመለስ አሊያም እድሜውን ለማራዘም ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ምክንያቱ ደግሞ ህወሓት በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች መካከል ልዩነት ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት ልክ የኢህአዴግ ውህደት እየተፋጠነ መምጣቱ ነው።

ህወሓት የግንባሩ መስራች እንደመሆኑ መጠን የኢህአዴግን ውህደት የሚቃወምበት ምክንያት ለብዙዎች ግልፅ አይደለም። አንዳንዶች ይህን የአጥፍቶ መጥፋት ባህሪ ጠንቅቀው የሚያውቁ ቢሆንም ህወሓት በፌደራሉ መንግስት ላይ የነበረውን የስልጣን የበላይነት በማጣቱ አደጋው የቀነሰ ወይም ያለፈ መስሏቸዋል። ሌሎች ደግሞ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመራውን ህዝብና ሀገር አጥፍቶ የሚጠፋበት ምክንያት ሊታያቸው አይችልም። ስለዚህ “ኢህአዴግ ከተዋሃደ ህወሓት ህዝብና ሀገርን አጥፍቶ ይጠፋል” ሲባል ለአብዛኞቻችን እውነት ላይመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ሁለቱም እሳቤ የህወሓትን ትክክለኛ ባህሪና እንቅስቃሴ ካለመገንዘብ የመነጨ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ህወሓት የፖለቲካ ቡድን ሳይሆን ጥገኛ የማፊያ ቡድን ነው። በመሆኑም እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ራሱን ችሎ መቆም፣ ለህዝብ ጥቅምና ተጠቃሚነት መስራት አይችልም። ከዚያ ይልቅ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖችን በመጠቀም የፖለቲካ ስልጣን በበላይነት መቆጣጠርና ህዝብን አፍኖ ሀገርን የሚዘርፍ ነው። የመንግስትን ስልጣንና መዋቅርን ተጠቅሞ ህገወጥ አፈና እና ዘረፋ የሚፈጽም ቡድን የማፊያ መንግስት ይባላል። ይህ የማፊያ ቡድን የመንግስታዊ ስርዓቱ መስራችና ባለቤት ሲሆን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የእሱ አገልጋይ፣ አጋር ድርጅቶች የህወሓት መገልገያዎች ነበሩ። የመንግስት ስልጣን የሌላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ደግሞ የህወሓት ተላላኪና አጋሮች ነበሩ ማለት ይቻላል።

ከላይ በተገለፀው መሰረት ህወሓት ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችነና እንቅስቃሴ በበላይነት መቆጣጠር መፈለጉ በራሱ የማፊያነት ሌላኛው መገለጫ ነው። ህዝብን በማፈን ሀገርን የመዝረፍ ዓላማና ተልዕኮ ያለው ቡድን ህዝባዊ መሰረትና ቅቡልነት የለውም። በመሆኑም ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በሃሳብ ተወዳድሮ ተመራጭ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ለህዝብ ጥቅምና መብት የቆሙ የፖለቲካ ቡድኖች በሀገር ውስጥ በነፃነት እንዳይደራጁና እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ ህዝቡን ምርጫና አማራጭ ማሳጣት አለበት። በእነዚህ ምትክ ደግሞ ከህዝብ ይልቅ ለእሱ አገልጋይና ተላላኪ የሆኑ የፖለቲካ ቡድኖችን ራሱ አደራጅቶ የፖለቲካ ስልጣን እንዲይዙ ያደርጋል።

ሆኖም ግን ይህ የማፍያ ቡድን በራሱ አደራጅቶ ስልጣንና ኃላፊነት የሰጣቸው ቡድኖች በድንገት ከቁጥጥር ውጪ ከወጡ የሚያስከትለው አደጋ ከባድ ነው። ምክንያቱም የዚህ ጥገኛ ቡድን ጥቅምና ህልውና የተመሰረተው ከራሱ ይልቅ በሌሎች አገልግሎትና ተገዢነት ላይ ነው። ከእነሱ አገልግሎትና ድጋፍ ውጪ በራሱ መቆምና መንቀሳቀስ አይችልም። በተመሳሳይ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እና አጋር ድርጅቶች ለህወሓት ተገዢና አገልጋይ ካልሆኑ ህልውናው ያከትማል። ስለዚህ ይህን ስጋትና አደጋ ለማስወገድ የራሱን ህልውና ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ከሆነ ነገር ጋር ማቆራኘት አለበት። ህወሓት “በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚመራ ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ትፈርሳለች፣ ህዝቦቿን በጦርነት ያልቃሉ” የሚል አቋም የሚያራምደው ጥገኛ ማፊያ ስለሆነ ነው። የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ሆነ በብሔር ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ አደረጃጀት መሰረታዊ ዓላማው “እኔ ከሌለሁ ሀገሪቱ የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቡም በጦርነት ለዕልቂት ይዳረጋል” በሚል የራሱን ህልውና ከህዝብና ሀገር ጋር ለማቆራኘት እንዲያስችለው ነው።

በእርግጥ የአንዱ መኖርና አለመኖር በሌላው ሕይወት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል። “እኔ ከሌለሁ አንተ አትኖርም” በሚለው እሳቤ ግን ከሁለት አንዳችን ወይም ሁለታችንም ጥገኛ መሆናችንን ያሳያል። የትግራይ ህዝብ ለሶስት ሺህ አመታት ያለና የነበረ ከሆነ የዛሬ 45 አመት የተፈጠረው ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ የበቀለ ጥገኛ አረም እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ለዘመናት የነበረች ሀገር እንደመሆኗ መጠን የዛሬ 30 አመት የመጣው ኢህአዴግ በሀገሪቱ ላይ የበቀለ ጥገኛ አረም ነው። ስለዚህ የህወሓት ሆነ ኢህአዴግ መወገድ ለትግራይና ኢትዮጵያ ህዝብ የህልውና አደጋ ሊሆን አይችልም።

ይሁን እንጂ ህወሓት መጋቢት 2011 ዓ.ም ወይን መፅሔት ላይ ያወጣው ባለ 43 ገፅ ፅሁፍ መነሻ ምክንያቱ የኢህአዴግ ውህደት እንደሆነ ይገልፃል። ፀኃፊው “አሁን በአገራችን ያጋጠመው ውስብስብ ፖለቲካ አንድ ውሁድ ፓርቲን በሚመለከት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ጥበብና ቆራጥነት ሊመራ ይገባል” በማለት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይገልፃል። አያይዞም “እየተቀበረ ያለውን ኢህአዴግ አልቅሰን እንሸኘው ወይስ ሙሉና የተጨበጠ አማራጫችንን ይዘን ቀርበን ትግላችንን እናጋግል?” በማለት ይጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪ በተጠቀሰው የህወሓት ፅሁፍ ገፅ 29 ላይ እንዲህ ይላል፡-

“አሁን ኢህአዴግንና በርሱ የሚመራውን ልማታዊ ዴሞክራሲ መንግስት በመምራት ላይ ያለው ኢህአዴግና የገዥ መደብ ቡድን መለያው ፀረ- አብዮት፣ ፀረ- ልማትና ፀረ-ዴሞክራሲ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ ሙስናና ብልሹ አሰራር ገዥ የሆነበት በውጤቱም አገር በመበታተን ጫፍ ላይ የደረሰበት ወቅት ላይ የሚቀነቀን “ውህደት” የሚባል ተረት ተረት ሊታለም አይችልም።”
ለህወሓት የኢህአዴግ ውህደት በአንድ በኩል ጣዕረ-ሞት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተረት ተረት የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? በመሰረቱ የኢህአዴግ ውህደት ከሚያስከትላቸው ለውጦች መካከል ዋና ዋናዎቹ፡- በኦዴፓና አዴፓ መካከል የነበረውን ያለመተማመን ስሜት ያስወግዳል፣ በኦሮማራ ጥምረት እና ደህዴን መካከል የነበረውን ክፍተት ይደፍናል፣ በኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች መካከል የነበረው ልዩነት ያስወግዳል፣ በሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የነበረውን ኢፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል ያስቀራል፣ በክልልና ብሔሮች መካከል የነበረውን የጠላትነትና ባላንጣነት ስሜት ያስቀራል፣ እንዲሁም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጥራዝ ነጠቅ መርህን ጨርሶ ለማስወገድ ያስችላል የሚሉት ናቸው።

ከላይ የተዘረዘሩት በሙሉ በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች ላይ የነበረውን ያልተገባ ስልጣንና የበላይነት የሚያስወግዱ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመበታተንና በህዝቦች መካከል ግጭትና ዕልቂት ለመፍጠር የሚጠቀምባቸውን ክፍተቶች የሚደፍኑ መሆናቸው እርግጥ ነው። በመሆኑም የኢህአዴግ ውህደት የህወሓትን የበላይነት እና ሀገሪቷን ለማፍረስና ለማተራመስ የነበረው አቅምና እድል ተመናምኖ ያልቃል። በዚህ ምክንያት ህወሓት ተመልሶ ወደ ስልጣን በመምጣት እንደ ቀድሞ ለእሱ አገልጋይና ተገዢ የሆኑ የፖለቲካ ቡድኖችን በማደራጀት የኢትዮጵያን ህዝብ ማፈንና መዝረፍ አይችልም። ስለዚህ በውህደቱ ምክንያት ሞቶ የሚቀበረው ኢህአዴግ ሳይሆን ራሱ ህወሓት ነው። በኢህአዴግ ውህደት ምክንያት የሚፈርሰው ሀገር ሳይሆን የህወሓት ማፊያ ቡድን ነው።

One thought on “በኢህአዴግ ውህደት የሚፈርሰው ህወሓት ወይስ ኢትዮጵያ?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡