ከሁለት ቀናት በኋላ ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይወስናል!

ህወሓት መጋቢት 2011 ዓ.ም ወይን በተሰኘው የድርጀቱ የንድፈ ሃሳብ መፅሄት ላይ ባወጣው ባለ 43 ገፅ ፅሁፍ የኢህአዴግ ውህደት ቀጥተኛ የሆነ የህልውና አደጋ እንደጋረጠበት ገልጿል። በዚህ መሰረት ላለፉት ስድስት ወራት በውህደቱ የተደቀነበትን አደጋ ለመመከት ዝርዝር መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። መርሃ ግብሩ በዋናነት ሦስት ዓይነት የተግባር እርምጃዎችን ያካተተ ሲሆን ሦስቱም በተቀናጀ መልኩ ጎን ለጎን የሚተገበሩ ናቸው። በዚህ መልኩ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ የኢህአዴግን ውህዳት ለማስተጓጎል ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል።

ህወሓት በ2011 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረጋቸው ሦስቱ የተግባር እቅዶች የሚከተሉት ናቸው፡- 1ኛ) ኢህአዴግን እንደ አንድ መታገያ መድረክ መጠቀም፣ 2ኛ) ሕገ መንግስታዊ ወይም ህብረ ብሔራዊ የፌደራሊስቶች ግንባር መመስረት፣ እና 3ኛ) ለመጨረሻው ፍቺ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ናቸው። ሰሞኑን የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መቀሌ ላይ ስብሰባ እያደረገ ሲሆን ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ህወሓት የስብሰባውን መጀመር አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ማዕከላዊ ኮሚቴው “በህዝብ ህልውና” ላይ የተጋረጠውን አደጋ ገምግሞ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተገልጿል። በተጨባጭ በትግራይ ሆነ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተጋረጠ የህልውና አደጋ የለም። ከዚያ ይልቅ ቀጥተኛ የሆነ የህልውና አደጋ የተጋረጠበት ህወሓትና ህወሓት ብቻ ነው። ምክንያቱም ህወሓት ከሰባት ወራት በፊት ወይን መፅሄት ላይ ባወጣው ፅሁፍ መሰረት የኢህአዴግ ውህደት ቀጥተኛ የሆነ የህልውና አደጋ አንደሆነ ገልጿል። ስለዚህ በሰሞኑ ስብሰባ ማዕከላዊ ኮሚቴው ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት ዋና ዋና ተግባራት አፈፃፀምና ውጤት ገምግሞ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። “የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በቀጣይ ቀናት ምን ዓይነት ውሳኔዎች ሊያሳልፍ ይችላል?” ለሚለው ህወሓት የኢህአዴግን ውህደት ለመመከት ያስቀመጣቸውን ሦስት ዋና ዋና አቅጣጫዎች እና አፈፃፀም በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል።

1ኛ) ኢህአዴግን እንደ አንድ መታገያ መድረክ መጠቀም

ህወሓት ውህደቱን ለመመከት ያስቀመጠው የመጀመሪያ አቅጣጫ ኢህአዴግን እንደ መታገያ መድረክ መጠቀም ነው። ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ ካደረገበት ግዜ ጀምሮ ህወሓት እንደ አባል ድርጅት በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ውስጥ ተሳታፊ እንደሆነ ይታወቃል። በእርግጥ አብዛኞቹ የህወሓት አመራሮች የተጣለባቸውን ሥራና ኃላፊነት በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ የኢህአዴግን ውህደት በማደናቀፍ ተግባር የተሰማሩ ናቸው። በፌደራልና ክልል ደረጃ የሚገኙ የህወሓት አባላትና አመራሮች የኢህአዴግን ውህደት ለመመከት የሚከተሉትን አቅጣጫ አስመልክቶ ህወሓት ወይን በተሰኘው መፅሔት ባወጣው ፅሁፍ ገፅ 38 ላይ እንዲህ ገልፆታል፡-

“በአሁኑ ሰዓት በተነሳው ወሳኝ ጉዳይ ማለትም አንድ ውሁድ ፓርቲን በሚመለከትም እስከ ሄደበት ድረስ ሁለትና ሶስት የሚሆኑ መታገያ አቅጣጫዎች ይዘን እንደ መድረክ እንጠቀምበት፡፡ በዚህ መሰረት አንደኛው የኢህአዴግ ችግር በዋናነት የአደረጃጀት ችግር ሳይሆን የአስተሳሰብ ነው፣ በመሆኑም ይሄንን ማዕከል ያደረገ ትግልና ማስተካከያ ይኑረን፣ የአስተሳሰብ ሪፎርምን ዋናው ጉዳይ እናድርግ በሚል መስራት፡፡ አንድ ውሁድ ፓርቲን በሚመለከት ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ውህደት የራሱ ሳይንስ፣ መርህና አካሄድ እንዳለው፣ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይፈፀሙ የሚመሰረት ውህድ ፓርቲ የትም እንደማይደርስ መግለፅ ነው። ስለዚህ ወደዚህ አሰራር መግባትና መጀመር እንደሚያስፈልግ በመግለፅ ህወሓት ደግሞ ለዚህ ዝግጁ መሆኑን ማሳየት፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የያዝነውን አቋም ለመላ አባሎች፣ አመራርና የኢህአዴግ ካድሬ፣ ለመላ የህወሓት አባሎችና አመራሮች፣ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይ ደግሞ ለመላ የትግራይ ህዝብ እንዲሁም ለዓለም ለማሳወቅ በፅሑፎች ላይ የተመሰረተ ውይይት፣ ክርክር፣ በሚድያ በሁሉም ቋንቋዎች ይፋዊ የሆነ ትግል ማካሄድ፡፡
…..በሌላ በኩል ይህ በኢህአዴግ ውስጥ እየቀጠለ አጋር ድርጅቶች የየብሄራቸውና ብሄረሰባቸውን ፓርቲ ይዘው ድምፅ እንዲኖራቸው የሚያስችል መጠነኛ የሕገ ደንብ ማስተካከያ አድርገን “ይግቡ” ብለን ለማንነት ፖለቲካ በዋናነት ደግሞ ራስን በራስ ለመወሰን መብት የሚታገሉ፣ የዜግነት ፖለቲካን የሚቃወሙ ሃይሎችን አንድ ላይ ማሰባሰብ። ይህ ደግሞ የብሄርና የብሄረሰቦች የበላይነት ያለው ግንባር የምናደርግበት እድል የሚያሰፋ አቅጣጫ ይዘን እንታገል።”ከላይ በተገለፀው መሰረት መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ከሆነበት ግዜ አንስቶ ህወሓት መስራችና አባል የሆነበትን ኢህአዴግ እንደ መታገያ መድረክ በመጠቀም፤ በአባል ድርጅቶችና አመራሮች መካከል የአቋምና አመለካከት ልዩነት ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፣ ውህደቱ እውን እንዳይሆን በኢህአዴግ ካድሬዎች፣ በህወሓት አባላትና አመራሮች፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና የዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ አፍራሽ ቅስቀሳ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የውይይት መድረኮችና ሚዲያዎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ አድርጓል። በመጨረሻም ኢህአዴግን እንደ መታገያ መድረክ በመጠቀም በአዲሱ አመራርና አጋር ድርጅቶች መካከል ልዩነት በመፍጠር ውህደቱን ለማደናቀፍ ጥረት አድርጓል።

ህወሓት ይህን ሁሉ አፍራሽ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ኢህአዴግ ውህደቱን ለማጠናቀቅ ጫፍ ላይ ደርሷል። ስለዚህ ህወሓት ኢህአዴግን እንደ መታገያ መድረክ ሲያደርግ የነበረው አፍራሽ እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም። ኢህአዴግ ውስጥ የጌራቸው አሰፋ ጉዳይ አስፈፃሚ የሆነው ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ስለ ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ የሰጠው አስተያየት ይህን ያሳያል።

2ኛ) የፌደራሊስቶች ህብረት/ግንባር መፍጠር

የኢህአዴግን ውህደት ለማደናቀፍ ህወሓት የነደፈው ሁለተኛ ስልት ከፌደራሊስት ኃይሎች ጋር ህብረት መመስረት ነው። ወይን መፅሔት በወጣው ፅኁፍ ኢህአዴግን እንደ መታገያ መድረክ በመጠቀም የሚደረገው እንቅስቃሴ ውህደቱን ጨርሶ ሊያስቆመው እንደማይችል ይገልፃል። በመሆኑም ውህደቱ እውን ሲሆን ህወሓት ለብቻው ተነጥሎ እንዳይቀር የፌደራሊስት እና ሕገ መንግስቱን የሚቀበሉ ሃይሎችን በማጠናከር የኢህአዴግ ተቀናቃኝ ግንባር መፍጠር እንዳለበት እንዲህ ሲል አቅጣጫ አስቀምጧል፡-“ሁለተኛው እና ከዚህ ከላይ ከተገለጠው መታገያ አቅጣጫችን ጎን ለጎን በጥብቅ መስራት ያለብንና አሁንም ባለፈውም የወሰንነውንና ስራውም የተጀማመረውን፣ ፌደራሊስት እና ሕገ መንግስቱን የሚቀበሉ ሃይሎችን ጉዳይ ማጠናከር ነው፡፡ …ብሄራዊ አደረጃጀትን የሚያጠፋ የአገር አቀፍ ውሁድ ፓርቲ አደረጃጀት እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ ብሄርን መሰረት ካደረገ አገራዊ ጥምረት፣ ግንባር ወይም ህብረት ውጭ ውሁድ የሚባል ፓርቲ ሊኖር አይችልም፡፡ በመሆኑም በዚህ አገር እስካለን ድረስ ኢህአዴግ እየተቀበረ ስለሆነ ቶሎ ብለን በብሄራዊ ድርጅቶች ላይ መሰረት ያደረገ አገራዊ መድረክ፣ መታገል ይኖርብናል። በመሆኑም ከዚህ ውጭ በኢህአዴግ ስም የሚደረግ የአንድ አገር አቀፍ ውሁድ ፓርቲ ምስረታን ሙሉ በሙሉ ተቃውመን መቆም እና ለህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም ስኬት መዋጋት ብቻ ነው ያለብን፡፡
…[ይሁን እንጂ] ኢህአዴግን ወደ አንድ ውሁድ ፓርቲ ልቀይረው ነው’ እያለ ያለው ሃይል፣ ከላይ [አንደኛ] የተገለፀውን የመታገያ አቅጣጫ ይዘን ብንዋጋም የተወሰነ ጊዜ ቢሰጠን ነው እንጂ የያዘውን መደብ ይተገብራል፡፡ ያ በሚሆንበት ጊዜ እኛ ወደ ውሁዱ ፓርቲ ልንገባ አንችልም፡፡ [ውህደቱን ብንቀላቀል] ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ለህዝቦች በተለይ ደግሞ ለትግራይ ህዝብ ትግል ትልቅ ክህደት [ይሆናል]። ኢህአዴግ ሲቀበር የራሳችንን የተሟላ አማራጭ ይዘን ከውህደቱ ራሳችንን አግልለን ነው የምንቀጥለው፡፡ በዚህ ወቅት ቶሎ ግንባር ፈጥረን አማራጭ ፓርቲ ይዘን ልንቆይ ይገባናል፡፡ እነዚህ ሃይሎች ደግሞ ሕገ-መንግስቱን የሚቀበሉ ፌደራሊስት ሃይሎች ናቸው፡፡ ራስህን አግልለህ መቆየት ምናልባት የበለጠ የሚሆንበት ሁኔታ ካለ እየተከታተልን የሚታይ ይሆናል።”ቀደም ሲል አንደኛ ላይ በተገለፀው መሰረት ኢህአዴግን እንደ መታገያ መድረክ በመጠቀም ውህደቱን ለማደናቀፍ የተደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት አላመጣም። በተመሳሳይ ህዝባዊ ድጋፍና ተቀባይነት ቀርቶ በግልፅ የሚታወቅ አባላትና አመራሮች የሌላቸውን የይስሙላ “ፓርቲዎች” እና እንደ አየለ ጫሚሶ፣ ትግዕሰቱ አወል፣ በቀለ ገርባ እና የመሳሰሉ ሰዎችን መቀሌ ድረስ በመጥራት የፌደራሊስቶች ግንባር ለመመስረት ያደረገው ጥረት በህዝብ ዘንድ መሳቂያ-መሳለቂያ ለመሆን የዘለለ ውጤት አላመጣም። ስለዚህ ህወሓት ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ የኢህአዴግን ውህደት ለማስተጓጎል ሲከተላቸው የነበሩት ሁለት የመታገያ አቅጣጫዎች የሚፈለገውን ውጤት አላመጡም።

3ኛ) ለመጨረሻው ፍቺ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ

ወይን መፅሔት “በኢትዮጵያ አገር አቀፍ የተዋሃደ ፓርቲ ጥያቄ ለምን?” በሚል ርዕስ ባወጣው ፅሁፍ መሰረት ቀደም ሲል የተጠቀሱት የመታገያ አቅጣጫዎች ውጤት ካላመጡ የኢህአዴግ ውህደት ዕውን ይሆናል። በሌላ በኩል የኢህአዴግ ተልዕኮና ዓላማ ከፓርቲው አልፎ የኢትዮጵያን አንድነትና የህዝቦቿን ሰላም ይወስናል። በመሰረቱ እንደ ህወሓት አገላለፅ ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ እንደምትበታተን እና ህዝቦቿም በጦርነት ምክንያት ለዕልቂት እንደሚዳረጉ ከላይ በተጠቀሰው ፅሁፍ ገፅ 13 እና 29 ላይ በዝርዝር ተገልጿል።

በእርግጥ ይህ ህወሓት መቀሌ ከገባ በኋላ ያስቀመጠው አቅጣጫ ሳይሆን የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ከተመሰረተበት ዕለት አንስቶ ሲመራበት ነበር። በወይን መፅሔት ላይ የወጣው ፅሁፍ “የአብዮታዊ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ምንነት” የሚለውን መፅሃፍ ዋቢ በማድረግ የኢህአዴግ ዓላማና ተልዕኮ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በተለየ መልኩ የሀገርን ህልውና እና የህዝቦችን መፃኢ ዕድል የሚወስን እንደሆነ ይገልፃል። እንደ ህወሓት አገላለፅ፣ ኢትዮጵያን ከመበታተንና ህዝቦቿን ከመተላለቅ ሊታደጋቸው የሚችለው ኢህአዴግ ብቻ ነው። ስለዚህ የኢህአዴግ ውህደት እውን የሚሆን ከሆነ የሀገሪቱ መበታተን አይቀሬ ነው። በመሆኑም ህወሓት ያስቀመጠው ሦስተኛው አቅጣጫ የመጨረሻውን ፍቺ ለመፈፀም ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ነው፡-“ህዝባዊና አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ይህን አቋም ይዘን ፊት ለፊት ስንገጥማቸው ወይ ደግሞ ይሄ የመፍትሄ ሃሳብ ሳይሳካ ቀርቶ የአገር መበተን ካስከተለ ባለፉት ፅሑፎቻችንም የለየናቸው ከባድ ጫና፣ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ከዚያም ከፍ ብሎ የፀጥታ አደጋዎችም ከሁሉም አቅጣጫዎች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በተለይ የመጨረሻው ፍቺ ይህንን ጉዳይ ሊያፋጥነው ይችላል፡፡ አይሆንም ላለ ሁሉም “እምቢተኛ ነው፣ ሀገር በታኝ ነው…” ከሚል ጀምሮ እስከ ማገድ የሚሄድና ሌሎች አደጋዎችም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህ አደጋ ብቻ ግን አይሆንም፤ የትግል ዕድሎችም ይፈጠራሉ፡፡ በህዝባችንና በድርጅታችን ጉልህ መጠናከር በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተሻለ ተነፃፃሪ መነሳሳት፣ እንዲሁም በሕገ-መንግስትና ፌደራሊስት፣…ወዘተ ሰልፍ ለይቶ ትግልና መተናነቅ የሚፈጠርበት ሂደትም ይሆናል፡፡
….ያም ሆነ ይህ ግን ፈተናዎችንና አደጋዎችን ለመከላከል ዕድሎችን መጠቀምና ማስፋት አሁንም በጥንካሬያችን፣ በመርህ ላይ በተመሰረተ አንድነታችንና ፅናታችን ላይ ብቻ የሚንጠለጠል ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ዕድገቶች ግምት ውስጥ በማስገባት አጠቃላይ የፖለቲካዊ፣ የፀጥታና ኢኮኖሚያዊ ዝግጅቶቻችንን በተለይ ደግሞ በንቃት የሚቆም ወጣት ከመፍጠር ጎን ለጎን የፀጥታ ዝግጅታችንን መልሶ በጥልቀትና በዝርዝር መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡”የኢህአዴግን ውህደት በበላይነት ከሚመሩት አንድ ክፍተኛ ባለስልጣን በሰጡኝ መረጃ መሰረት አምስቱ አጋር ድርጅቶች እና ሦስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በመዋሃድ “የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ” ለመመስረት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ናቸው። የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ (ኢብፓ) ምስረታ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢህአዴግ) ሙሉ በሙሉ ያፈርሰዋል። ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ ፓርቲ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለውን አቅጣጫ ያለፈበት የህወሓቶች የጭቆና መሳሪያ እንደሆነ ከላይ የተጠቀሱት ባለስልጣን ነግረውኛል። በሌላ በኩል ህወሓቶች የውህደቱ አካል እንደማይሆኑ በፅሁፍ ጭምር መግለፃቸው ተሰምቷል።

በዚህ መሰረት አዴፓ፣ ኦዴፓ. ደህዴን እና አምስቱ አጋር ድርጅቶች ተዋህደው አዲሱን ፓርቲ ሲመሰርቱ የኢህአዴግ መስራችና ባለቤት የነበረው ህወሓት ለብቻው ተነጥሎ መቅረቱ እርግጥ ሆኗል። ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- ኢህአዴግን መታገያ መድረክ በመጠቀም ያደረገው ሙከራ ውጤት አላመጣም። ሁለተኛ፡- ከህገ መንግስት ወይም ፌደራሊስት ኃይሎች ጋር ግንባር መፍጠር አልቻሉም። ስለዚህ ህወሓት የቀረው ብቸኛ አማራጭ የመጨረሻውን ፍቺ ለመፈፀም ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት የትግራይ ክልልን መገንጠልና ይህን ተከትሎ ለሚመጣው አደጋ ራሱን ማዘጋጀት ነው።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መቀሌ ላይ ስብሰባ የተቀመጠው ድርጅቱ ካስቀመጣቸው ሦስት አማራጮች ውስጥ አንዱን ብቻ ይዞ ነው። ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ህወሓት የቀረው ብቸኛ አማራጭ ራሱንና የክልሉን ህዝብ አጠናክሮ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚገኙ የብሔር ቡድኖች በማነሳሳት “ትግልና መተናነቅ” ነው። በዚህ ምክንያት “የሀገር መበተን ካስከተለ” በሚል ከባድ ጫና፣ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ከዚያም አልፎ “ከሁሉም አቅጣጫ የፀጥታ አደጋዎች” ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመለየት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል። በአጠቃላይ ህወሓት ከኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም ጭምር የመጨረሻውን ፍቺ ለማድረግ ተዘጋጅቷል።

ህወሓት በሁሉም አቅጣጫ ሊያጋጥሙኝ ይችላሉ በሚል ከሚያደርጋቸው ቅድመ ዝግጅቶች አንዱ የቴሌኮሚኒኬሽን ግንኙነት መስመር ነው። በዚህ ረገድ ህወሓት ከኢትዮቴሌኮም ሰርቨር ጋር የሚያገናኘውን መስመር በመቀየር በሁመራ በኩል የፋይበር ኦፕቲክ ኬብል በመዘርጋት በሱዳን በኩል ከዓለም አቀፉ የኢንተርኔት ግንኙነት መስመር ጋር ለማገናኘት ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር። ሆኖም ግን በመጨረሻ ሰዓት የፌደራሉ ደህንነት መስሪያ ቤት ጉዳዩን ደርሶበት የግንኙነት መስመሩን እንደቆረጠው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመንግስት ኃላፊ በቅርቡ አጫውቶኛል። በተመሳሳይ የመጨረሻው ፍቺ ከተፈፀመ በኋላ የሚገጥመውን የውጪ ምንዛሬ ከግምት በማስገባት ዶላርና ዮሮ በከፍተኛ የምንዛሬ ዋጋ እየገዛ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በሌላ በኩል በአማራና የቅማንት ማህብረሰብ፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ማህብረሰብ በሚኖርባቸው አከባቢዎች፣ እንዲሁም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች የሚታዩ ህገወጥ ተግባራት በሙሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የህወሓት ቅድመ ዝግጅት አካል ናቸው።

በአጠቃላይ ህወሓት ከኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም ጋር የመጨረሻውን ፍቺ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱን ከሞላ ጎደል አጠናቅቋል። የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መቀሌ ላይ በሚያደርገው ስብሰባ ድርጅቱ ለመጨረሻው ፍቺ የተደረገውን ቅድመ ዝግጅት ገምግሞ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ህወሓት የመጨረሻውን ፍቺ ለመፈፀምና ከሁሉም አቅጣጫዎች የሚገጥሙትን አደጋዎች ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት አድርጓል ሲባል በአጭሩ “ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማተራመስ ዝግጅቱን ጨርሷል” እንደማለት ነው። የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ መሰረት ስብሰባው አራት ቀናት እንደሚፈጅ ተገልጿል። ስለዚህ ከሁለት ቀናት በኋላ ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይወስናል!