የህወሓት መግለጫ፦ “ከውሸት ክምር የጥላቻ ግንብ ይገነባል!”

እውነት እውነት እላችኋላሁ በዓለም ላይ እንደ ህወሓት የሚገርመኝ ነገር የለም። በተግባር እልም… ያለ ጨቋኝና ጨካኝ እንደሆነ እናውቃለን። መግለጫ ሲያወጣ ግን ፍፁም ጨዋና አዛኝ እንደሆነ ይናገራል። የሚመራውን ህዝብ የሚጠላ፣ የሚያስተዳድረውን ሀገር አሳልፎ የሚሸጥ፥ በነፃ የሚሰጥ እንደሆነ እኮ ከእኛ በላይ የአይን እማኝ የለም። ነገር ግን መግለጫ ባወጣ ቁጥር ለህዝብ ተቆርቋሪ፣ ለሀገር አሳቢ እንደሆነ ይናገራል። በእርግጥ ህወሓቶች የሚናገሩት ሁሉ ውሸት እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን። በመሆኑም እነሱ መግለጫ ባወጡ ቁጥር ምላሽ መስጠት አያስፈልግም ነበር። ነገር ግን ህወሓቶች ዳግመው የሚዋሹት “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” በሚል እሳቤ ነው። በጣም የሚገርመው ደግሞ ይህን አካሄድ ትክክልና አዋጭ እንደሆነ በተግባር አረጋግጠውታል።

በመጀመሪያ ደረጃ ህወሓት 27 አመት ሙሉ ኢትዮጵያ ላይ የጨፈረው ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል የሚናገሩትን ውሸት አምኖ ይቀበል ስለነበረ ነው። ዛሬም ልክ እንደ ትላንቱ ዓይን ያወጣ ውሸት የሚናገሩት ውሸትነቱ ጠፍቷቸው ሳይሆን “የሚያምነን የህብረተሰብ ክፍል አይጠፋም” በሚል ነው። ህወሓቶች የተናገሩትን ውሸት ሳያላምጡ የሚውጡ ብቻ ሳይሆን የወጡትን ውሸት መልሰው የሚተፉ ቱቦዎች እንዳሉም ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለምሳሌ “የእነ እከሌ መታሰር የህወሓት አገዛዝ የተሻለ እንደነበር ያሰል” የሚሉ አክቲቪስቶች፣ ትላንት አስረው ሲገርፉትና በግፍ ሲያሰቃዩት እንዳልነበር ዛሬ መቀሌ ድረስ ሄዶ “የእንትን መንገድ መዘጋቱ መንግስት እንደሌለ ያሳያል” የሚሉ “ፖለቲከኞች ህወሓቶች በገንዘብ ለውሰው የሰጧቸውን ውሸት መልሰው ቋንቋና ቦታ ቀይረው የሚያስተጋቡ ተላላኪ ጡርባዎች ናቸው።

በዚህ ምክንያት የህወሓቶች ውሸት ብዙ ርቀት ተጉዞ፣ ይዘትና ጭብጡን ቀይሮ፣ እውነት እንዲመስል በሃሜትና ጥላቻ ተሸፋፍኖ ሚሊዮኖች ጋር ይደርሳል። እየቆየ ሲሄድ ህወሓቶች ራሳቸው በፈጠሩት ውሸት እንደ ቅዱስ ቃል ይምሉበታል፤ ለተላላኪዎቻቸው የህወሓት ውሸት ዕውቀት ይመስላቸዋል፤ ይሄ ሚስኪን ህዝብ ደግሞ የሰማውን ውሸት “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው!” በሚል አምኖ ይቀበላል። በዚህ መሰረት ከውሸት ክምር ያለመተማመንና ጥላቻ ግንብ ይገነባል። በዜጎች መካከል ያለመተማመንና ጥላቻ ሲኖር የህወሓት ዓላማና ግብ እውን ይሆናል። ምክንያቱም በህዝቦች መካከል መተማመንና መግባባት ባለበት እንደ ህወሓት ያለ አፋኝና ዘራፊ ቡድን ፈፅሞ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ውሸትና ጥላቻ የህወሓት ነፍስና ስጋ ነው። ሁለቱ ከሌሉ የህወሓት ህልውና ያከትማል።

ለምሳሌ ህወሓት ዛሬ ያወጣው መግለጫ ማጠንጠኛው “በትግራይ ህዝብ ላይ የተጋረጠውን የህልውና፣ ደህንነትና ዋስትና አደጋ መመከት” የሚል ነው። በአንድ ህዝብ ላይ የህልውና አደጋ (existential threat) መመከት ማለት በህዝቡ ላይ በግልፅ የተቃጣ “የዘር ማጥፋት ጥቃት አለ” ማለት ነው። የህልውና አደጋ የተጋረጠበት ህዝብ ደግሞ የማንም ድጋፍና ማበረታቻ ራሱን ለመከላከል ይታገላል። ነገር ግን በትግራይ ህዝብ ሆነ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተጋረጠ የህልውና አደጋ የለም። ይሁን እንጂ ህወሓት አሁን ላይ “በትግራይ ህዝብ ላይ የተጋረጠውን የህልውና፣ ደህንነትና ዋስትና አደጋ መመከት” እያለ በህዝብና ሀገር ላይ መዓት የሚጠራው ሲጀመር ወደ ስልጣን የመጣው ይሄንኑ ስልት በመጠቀም እንደሆነና ዳግም ተመልሶ ሊመጣ የሚችለውም በተመሣሣይ መንገድ እንደሆነ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የቀድሞው የብዓዴን መስራች የነበረው አቶ ያሬድ ጥበቡን ጠይቄው የመለሰልኝ ይሄን የሚያረጋግጥ ነው። አቶ ያሬድ በወቅቱ አክሱም አከባቢ ቤተክርስቲያን ውስጥ ቅስቀሳ ሲያደርግ የነበረን አንድየህወሓት ካድሬ “የትግራይ ህዝብ ሆይ፦ ባህልህን የሚያጠፋ፣ ሃይማኖትህን የሚቀይር፣ ሀገርና ሚስትህን የሚቀማ ጠላት መጥቶብሃል” እያለ ሲቀሰቅስ በመስማቱ በጣም ግራ መጋባቱን አስታውሶ አጫውቶኛል።

የዛሬው መግለጫ የሚያስታውሰን ነገር ቢኖር የህወሓትን ውሸትና ስልት ነው። ከ45 አመት በፊት በትግራይ ህዝብ ውስጥ የዘራው ውሸትና ጥላቻ ከ17 አመታት በኋላ ለስልጣን አብቅቷል። በተመሣሣይ ለ27 አመታት የፈፀመው ዘረፋና ውሸት በመጨረሻ ለውድቀት ዳርገውታል። ከውድቀታቸው ለማገገምና ተመልሰው ለመምጣት እየተጠቀሙት ያለው መንገድ ደግሞ ከ27 አመት በፊት ወደ ስልጣን የመጡበትንና ከአንድ አመት በፊት ለውድቀት የዳረጋቸውን መንገድ ነው። በዚህ መሠረት ህወሓት የባህሪ፣ አመለካከት፣ አካሄድ ሆነ የመንገድ ለውጥ አያደርግም። ከዚህ አንፃር አስገራሚው ነገር ከህወሓቶች ይልቅ የእኛ አለማሰብ፣ አለመረዳትና አለመቀየር ነው።

ለምሳሌ ህወሓት “አህዳዊነት ያወግዛል፣ ህብረ ብሔራዊነትን ያወድሳል፤ ህገመንግስቱን እያደነቀ ቀጣዩ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት አበክሮ ይጠይቃል” ግን ለመሆኑ “አህዳዊነት” ማለት ራስን በራስ የማስተዳደር እድል የሌለበት፣ ወጥ በሆነ አንድ አይነት አስተዳደር መመራት ነው። ህወሓት በዚህ ሀገር ላይ አድራጊና ፈጣሪ በነበረበት 27 አመታት ውስጥ አሁን እሱ በሚያደርገው ልክ የፌደራሉን መንግስት የሚገዳደር፣ የሚወዳደርና የሚፎካከር የክልል መንግስት ቀርቶ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ወጣ ያለ ነገር ትንፍሽ የሚል ባለስልጣን አልነበረም። ይሄን ማወቅ የሚሻ ደግሞ አልማዝ መኮ፣ አባተ ኪሾ፣ ታምራት ላይኔ፣…ወዘተ የመሳሰሉትን ሰዎች አፈላልጎ ይጠይቅ። አህዳዊ ስርዓት ቢኖር ኖሮ የዛሬውን የህወሓት መግለጫ ያወጡት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መሰብሰቢያቸው እስር ቤት ውስጥ እንጂ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አልነበረም። ስለዚህ ህወሓቶች አሁን ያለውን አመራር በአህዳዊነት ለመውቀስ የቻሉት በስልጣን ላይ ቡድን ህወሓቶች አንሸዋርረው የዘረጉትን ፖለቲካዊ ስርዓትና አደረጃጀት አክብሮ እየሰራ የመሆኑ ማሳያ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ህወሓቶች “ቀጣዩ ምርጫ ካልተካሄደ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ህጋዊ መሠረትና ተቀባይነት የለውም” ሲሉ እኮ ላለፉት 27 አመታት ህዝቡ ላይ ተጭነው ሀገሪቱን የዘረፉት በህዝባዊ ድጋፍና ህጋዊ መሠረት ያስመስሉታል። ብዙዎች ይሄን ውሸት ደጋግመው ስለሰሙት እውነት ሊመስላቸው ይችላል። ነገር ግን ህወሓት የሚባለው ቡድን ሌላው ቢቀር “ምርጭ” የሚለውን ቃል ፈፅሞ መጥራት የለበትም። ምክንያቱም ስለቀጣዩ ምርጫ ለመናገር በቅድሚያ ያለፈውን ምርጫ ትክክለኛነትና አግባብነት ማረጋገጥ አለበት። ያለፈው ምርጫ ደግሞ 100% ነው። ይሄ ምርጫ ሳይሆን ቅሌት ነው!!! ወዳጄ “ህወሓቶች አያፍሩም፣ አይቀየሩም!” የምልህ ለዚህ ነው!!