የህወሓት ዓላማና ስልት አንድና ተመሳሳይ ነው!

ይህ ፅሁፍ ከአንድ አመት በፊት – ታህሳስ 14/2018 የተፃፈ ሲሆን የህወሓት ዓላማና ስልት አንድና ተመሳሳይ ስለመሆኑ ዓይነተኛ ማሳያ ነው!

ሀገርና ህዝብ የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት የፖለቲካ ቡድን በተወሰነ ደረጃ የሚታወቅ የተግባር መርህና አቋም ሊኖረው ይገባል። ህወሓት ግን በግልፅ የሚታወቅ ድርጅታዊ መርህና አቋም የለውም። በመሆኑም በቀጣይ ሊወስድ የሚችለውን የተግባር እርምጃ ሆነ ሊያደርግ የሚችለውን የአቋም ለውጥ ማወቅና መገመት አስቸጋሪ ነው። ባለፉት ሦስት አመታት የሀገራችን ህዝብ ሆነ የዓለም አቀፉ ማህብረሰብ የህወሓትን የተግባር መርህ እና እርምጃ ለመገመት ያላደረጉት ጥረት የለም። ሆኖም ግን ሌላው ቀርቶ የህወሓት አመራሮችና አባላት የድርጅታቸውን አቅጣጫና እርምጃ በእርግጠኝነት ማወቅ ሆነ መገመት የሚችሉ አይመስለኝም። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የትግራይ ሆኑ የኢትዮጵያ ልሂቃን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ የህወሓትን ትክክለኛ ባህሪና ዓላማ በግልፅ ማወቅ አለመቻላቸው ነው።

እንደ አንድ የፖለቲካ ቡድን ህወሓት የራሱ የሆነ አቋምና መርህ፣ ዓላማና ግብ፣ የወደፊት አቅጣጫና ዕቅድ አለው። እነዚህ ነገሮች ከሌሉት ህወሓት እንደ ድርጅት ራሱን በራሱ መምራት ሆነ የትግራይ ክልልና ህዝብን ማስተዳደር አይችልም። እንደ አንድ ድርጅት ወይም ቡድን የህወሓት ዓላማና ግብ፣ የሚከተለው አቅጣጫ እና በተግባር የሚመራበት መርህ ምንድነው? ይህን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ከተቻለ የህወሓትን ትክክለኛ ባህሪ እና የወደፊት እርምጃ በእርግጠኝነት ማወቅና መገመት ይቻላል። ስለዚህ ከህወሓት ጋር የሚደረገው ማንኛውም ግንኙነትና እንቅስቃሴ በተጨባጭ በግልፅ በሚታወቅ መርህና አቅጣጫ ላይ የተመሰረተ ይሆናል።

በግልፅ ተለይቶ የሚታወቅ ዓላማና የተግባር መርህ ከሌለው የፖለቲካ ቡድን ጋር የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት ያልተጠበቀ ውጤት ያስከትላል። ለምሳሌ የደርግ ውድቀትን ተከትሎ በተቋቋመው የሽግግር መንግስት ውስጥ ብዛት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንደነበሩ ይታወሳል። ከዚያ በኋላ ባሉት አስር አመታት ውስጥ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት እነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎች በወታደራዊ ጉልበትና ፖለቲካዊ አሻጥር ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል። በወቅቱ ብዙዎች የችግሩ መንስዔ የኢህአዴግ መንግስት አምባገነንነት እንደሆነ ሲገልጹ ነበር።

በ1997ቱ ምርጫ የኢህአዴግን አምባገነንነት እና ጭቆና በነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማስወገድ የተደረገው ሙከራ በምርጫ ማጭበርበር፣ እስራትና ግድያ ሳይሳካ ቀረ። ከዚያ በኋላ ባሉት አስር አመታት የኢህአዴግ ጭቆና እና አምባገነንነት ወደ የህወሓት የበላይነት የሰፈነበት የአፓርታይድ ስርዓት ተቀየረ። ባለፉት ሦስት አመታት የታየው ለውጥ የመጣው የመንግስታዊ ሰርዓቱን ትክክለኛ ባህሪና እንቅስቃሴ በግልፅ መለየት በመቻሉ ነው። አሁን ያለው ለውጥ የመጣው የሀገራችን መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር ከኢህአዴግ አምባገነንነት እና ጭቆና ይልቅ የህወሓት የበላይነት እና አፓርታይድ እንደሆነ በመለየትና በዚህ ላይ የተመሰረተ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ በመቻሉ ነው።የህወሓትን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ የተዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት ከሞላ-ጎደል ወድቋል። በመሆኑም የህወሓትን የበላይነት እና ሌብነት ማዕከል ባደረገ መልኩ የተደረገው ህዝባዊ ንቅናቄና ትግል ዓላማውን አሳክቷል። ይሁን እንጂ የህወሓት የበላይነት ያበቃው በፌደራል መንግስቱ ውስጥ እንጂ በትግራይ ክልል ላይ ከቀድሞ በበለጠ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በእርግጥ አብዛኞቹ የህወሓት አባላትና አመራሮች ወደ መቀሌ በመሄድ መሽገዋል። ነገር ግን በህወሓት የአፓርታይድ ዘመን በተለያዩ ጎሳዎች፥ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል የተዘራው ጥላቻና ቂም፣ አለመተማመን እና ጥርታሬ በየትኛውም ግዜና አጋጣሚ ወደ ግጭትና ብጥብጥ ሊቀየር ይችላል። በዚህ ረገድ የቀድሞ የህወሓት ጄኔራሎች እና ባለስልጣናት፣ የፀጥታና ደህንነት ኃላፊዎች ያላቸውን ልምድና የሙያ ዕውቀት በመጠቀም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የእርስ-በእርስ ግጭትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋሉ።

በሌላ በመንግስት ኃላፊዎች፣ ተቋማትና ዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት በመፈፀም የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማናጋት በፈጸሙት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች የትግራይ ክልልን መደበቂያ ያደርጋሉ። በመሆኑም የህግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ህወሓት ዋና እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ምንም ዓይነት የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲደረግ አይፈቅድም። በአንፃሩ የክልሉ ነዋሪዎች የሚያነሱትን የማንነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል። በመሆኑም የትግራይን ክልል ጨምሮ በሀገር-አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ በዘላቂነት ማስቀጠል፣ በዚህም የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ህወሓት ዋና እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል።

ህወሓት በፌደራል ስርዓቱ ላይ የራሱን የበላይነት ለማረጋገጥ የዘረጋውን የአፓርታይድ ስርዓት ለመታገል እና ለማስወገድ ያስቻለው ስልት ከዚህ በኋላ አዋጭ አይደለም። ምክንያቱም በፌደራል ደረጃ የነበረው የህወሓት የበላይነት ከሞላ ጎደል አብቋታል። ከዚህ በኋላ ህወሓት የለውጡን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚጠቀመው ስልት የወንጀል ተግባራትን በመፈፅም እና ለወንጀለኞች መሸሸጊያ በመሆን የህግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማስተጓጎል ነው። በትግራይ ክልል የለውጥ ጥያቄን በኃይል በማፈን እና በሌሎች ክልሎች ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋል። ከዚህ በኋላ የህወሓት ስልትና ተግባር ወንጀል በመስራት እና ወንጀለኞችን በማበረታታት የተጀመረውን ለውጥ ማስተጓጎልና መቀልበስ ይሆናል።

በዚህም መንግስትና ዜጎች ለውጡን ከማስቀጠል ይልቅ ፀረ-ለውጥ እንቅስቃሴዎችን በመከላከል ላይ እንዲወጠሩና በሂደት በለውጡ ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረግ ነው። የጸረ-ለውጡ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ሲመጣና የዜጎች ሰላምና ደህንነት፣ እንዲሁም የሀገሪቱ አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ መንግስትም በጸረ-ለውጡ ኃይሎች ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል። ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረገው ጥረት በፀረ-ለውጡ ወገን ላይ እልቂት ከመጋበዝ የዘለለ ፋይዳ የለውም። ይህን ተከትሎ ጸረ-ለውጡን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚወስደው የኃይል እርምጃ መንግስትን ይበልጥ አምባገነን ያደርገዋል። የለውጡን ደጋፊዎች ወደ ጦርነት ከማስገባት እና መንግስትን አምባገነን ከማድረግ በዘለለ የጸረ-ለውጡ ኃይል ተመልሶ ስልጣን የመያዝ እድል የለውም። ይህ ልክ እንደ ጸረ-ለውጡ ኃይል በፍፁም የማይቀየር ሃቅ ነው።