ኢህአዴግ “አሃዳዊ” የሚሆነው በህወሓት ወይስ በውህደት ነው?

ህወሓት ከእሱ ውጪ ያሉትን ስርዓቶች በሙሉ “አህዳዊ” በማለት ይፈርጃል። በመሰረቱ “አሃዱ” የሚለው ቃል ፍቺ “አንድ” ማለት ሲሆን “አሃዳዊ” ማለት ደግሞ “አንድ-ዓይነት” እንደማለት ነው። ከዚህ አንፃር እንደ ህወሓት ያለ አህዳዊ በዓለም ላይ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም። ለዚህ ደግሞ የህወሓትን አመራርና አሰራር በጥሞና ማጤን ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ ደረጃ ህወሓት የሚመራው በአንድ አይነት መርህና አቅጣጫ ነው። እነሱም አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ናቸው። ህወሓት ከደደቢት ተነስቶ አዲስ አበባ የገባው፣ ከአዲስ አበባ ሸሽቶ መቀሌ የመሸገው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቅጣጫን ተከትሎ ነው። አሁንም ድረስ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጪ ሌላ አቅጣጫ መከተል ቀርቶ ማሰብ አይችሉም። ከዚህ በተጨማሪ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር መሰረት እያንዳንዱ አባል ለድርጅቱ ውሳኔ ተገዢ መሆን አለበት።

ሁለተኛ ላለፉት 27 አመታት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሲመሩበት የነበረው ህወሓቶች በነደፉት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቅጣጫ ነው። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውሳኔ አሰጣጥና አፈፃፀም በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ የተመሰረተ ነው። የኢህአዴግ ማዕከላዊ ወይም ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች ሁሉም አባል ድርጅቶች ተቀብለው ተግባራዊ የማድረግ ግዴታና ኃላፊነት አለባቸው። ስለዚህ ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የህወሓትን መርህና አቅጣጫ ይከተላሉ።

ሦስተኛ አምስቱን ክልሎች የሚያስተዳድሩት ድርጅቶች የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ “አጋራ” እንጂ “አባል” አይደሉም። በመሆኑም በጋራ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ስልጣን የላቸውም። ሆኖም ግን የአምስቱም ክልላዊ መስተዳደሮች የኢህአዴግ መንግስት የሚመራበትን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቅጣጫ ይከተላሉ፤ ገዢው ፓርቲ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ያስፈፅማሉ። ስዚህ አጋር ድርጅቶች ህወሓት በኢህአዴግ በኩል ያስቀመጠላቸውን አቅጣጫ ይከተላሉ፤ ለኢህአዴግ መንግስት ውሳኔ ተገዦ ይሆናሉ።

አራተኛ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በአንድ ለአምስት (1-ለ-5) አደረጃጀት አማካኝነት በፌደራል፣ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ፣ ጎጥና ሰፈር አድርጎ ከእያንዳንዱ ግለሰብ ቤት ይገባል። ከ1-ለ-5 አደረጃጀት የሚያፈነግጠው፤ ዘይት የሌለው ወጥ መብላት አሊያም ስኳር የሌለው ሻይ/ቡና መጠጣት የሚሻ ሰው ብቻ ነው። በዚህ መሰረት የህወሓት መርህና አቅጣጫ ከደደቢት ተነስቶ በእያንዳንዱ ሰው ቤት ይገባል። በመሆኑም ሁሉም ሰው ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተገዢ ይሆናል።

አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የህወሓቶች የተግባር መርህና መመሪያ እንደመሆናቸው መጠን፤ “ሁሉም ሰው ለህወሓት ተገዢ ሆኗል” ወይም “ህወሓት ሁሉንም ሰው ይገዛል” ማለት ነው። በዚህ መሰረት ህወሓት “አሃዱ” ሲሆን አገዛዙ ደግሞ “አሃዳዊ” መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ሁሉም በአንድ-ዓይነት አቅጣጫና መመሪያ የሚመሩ ቢሆኑም በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች፣ በፌደራል መንግስትና ክልሎች፣ በብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል አንድነት የለም። የአማርኛ መዝገበ ቃላት “አንድነት” የሚለውን ቃል “ህብረት” የሚል ፍቺ እንዳለው ይገልፃል። በዚህ መሰረት “አሃዳዊነት” በልዩነትና መለያየት ላይ የተመሰረተ የአንድ ወገን የበላይነት ነው። በሌላ በኩል “አንድነት” ደግሞ በልዩነት ውስጥ ህብረትን በመፍጠር በእኩልነት መኖር መቻል ነው።

ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ ያደረገው የህወሓትን የበላይነት ለማስወገድ በተደረገ ትግል ነው። በመጀመሪያ በታህሳስ 2008 ዓ.ም በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በአመቱ መጨረሻ አከባቢ የክልሉን መስተዳደር ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ይልቅ ለህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ተገዢ እንዲሆን አድርጎታል። በተመሳሳይ በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በተለያዩ የአማራ አከባቢዎች የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ የክልሉን መስተዳደር ለዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተገዢ እንዳይሆን አድርጎታል።

የኦህዴድ/ኦዴፓና ብአዴን/አዴፓ አመራሮች የህወሓትን ጫና ለመቋቋምና ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በሚያደርጉት ጥረት የኦሮማራ ጥምረትን መሰረቱ። የኦሮማራ ጥምረት እየተጠናከረ ሲሄድ ደህዴንን ከህወሓት እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት ጥረት ማድረግ ጀመረ። በመጨረሻ ህወሓት በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አማካኝነት ኢህአዴግን መቆጣጠር ሲሳነው የአመራር ለውጥ አደረገ። በዚህ ምክንያት ህወሓት መቀሌ ሄዶ መሸገ።

ከ2010 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ አጋር ድርጅቶችን ከህወሓት እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት ከፍተኛ ርብርብ ተደረገ። አሁን ላይ ከትግራይ ክልል በስተቀር አብዛኛው የሀገሪቱ አከባቢ ከህወሓት አህዳዊ አገዛዝና የበላይነት በከፊል ነፃ ወጥቷል ማለት ይቻላል። ነገር ግን ዘላቂ ለውጥና ሰላም ሊመጣ የሚችለው በልዩነትና መለያየት ላይ የተመሰረተውን የህወሓት የበላይነት ጨርሶ በማስወገድ በልዩነት ውስጥ ህብረትና እኩልነትን ማረጋገጥ ሲቻል ነው።

በዚህ ረገድ የህወሓት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ከሞላ ጎደል አብቅቶለታል። አሁን የቀረው በህወሓት መሪነት ለተዘረጋው አህዳዊ ስርዓት መሰረት የሆነውን “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ጨርሶ ማስወገድ ነው። ለዚህ ደግሞ የኢህአዴግ ውህደት የግድ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን የህወሓትን የበላይነትና አሃዳዊ ስርዓት ሙሉ በሙሉ በማስወገድ በህብረትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት መገንባት ይቻላል።