“ኣይተ ጌታቸው ረዳ ሆይ! ‘ይቀሰፋልን’ ምን አመጣው?” አዲስ ዘመን

ቅዱስ መጽሀፍ ሰው በልቡ ያሰበውን አፉ ያወራል ይላል። የአፍህን ፍሬ ትበላለህና ስለምትናገረው ነገርም ተጠንቀቅ ሲል ይመክራል። እነዚህን ጥቅሶች ስመለከትም ሁሌ ትዝ የሚለኝ አንድ ቁም ነገር አዘል ቀልድ አለ። ሰውዬው በረሃ እያቋረጠ ሲጓዝ በመንገዱ ላይ አንድ ነብር ዛፍ ላይ ተቀምጦ ይመለከትና ፈርቶ ይቆማል። ይህን የተመለከተው ነብርም ለሰውየው “እለፍ አልበላህም” ሲለው ሰውየው ብልጥ ነበርና “አልበላህምን ምን አመጣው” ሲል መንገድ መሄዱን ትቶ ህይወቱን አተረፈ ይላል። አውነት ነው ነብሩ በልቡ የመግደልና ደም የመጠጣት ሃሳብ ባይኖር ኖሮ ይህቺ ቃል ከአፉ ባልወጣች ነበረና!

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ እንዲህ በቅዱስ መጽሀፍ ጥቅስና በቀልድ ዳር ዳር ያልኩት በጣም የማከብራውቸውና ንግግራቸው የሚመስጠኝ የህወሃቱ አይተ ጌታቸው ረዳ በአንድ ቃለመጠየቅ ወቅት ስለ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተጠይቀው ሲመልሱ “እንዳታስቀስፉት” የምትል እሬት የሆነች ቃል ወርውረው ስለተመለከትኩ ነው። ይህ ቃል ለዴሞክራሲ ሺዎችን ከሰዋ ድርጅት አባልና ከፍተኛ አመራር መውጣቱ ደግሞ በጣም ያማል። የዴሞክራሲና የህገ መንግስት ጥሰት አለ እያሉ ጠዋት ማታ የሚወተውቱት አቶ ጌታቸው የግለሰብን ዴሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብትን ጭምር የሚጋፋ ይህን መሰሉን ንግግር መናገራቸው በብዙዎች ዘንድ የነበራቸውን ክብር በእጅጉ እንደጎዳ ይሰማኛል።

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ጭቁን ወንድሞቹ ጋር በመሰለፍ ክቡር የአካልና የህይወት ዋጋ የከፈለው በአገራችን ምድር ዴሞክራሲ አብቦና የዜጎች ሰብዓዊ መብት ያለምንም መሸራረፍ ተከብሮ አንገታችንን ቀና አድርግን የምንኖርባትን አገር እውን ለማድረግ ነበር። ይሁንና ህወሃት የእነዚያን ክቡር ሰማዕታት መስዋዕትነት ወደጎን ብሎ በደርግ ዘመን አንኳ ያልተፈጸመ ጥፍር መንቀል፣ በክቡሩ የሰው ልጅ ላይ ሽንት መሽናት ጫካ ውስጥ መጣልን… የመሳሰሉ ዘግናኝ ድርጊቶችን ሲያከናውን መቆየቱ በህያው ምስክሮች መረጋገጡ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

አቶ ጌታቸው መቀመጫ ባደረጓት ትግራይ አረናና ትዴትን የመሳሰሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቁምስቅል ማየታቸውንም ዕለት ከዕለት የምንሰማው ዜና ሆኗል። ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት መከበር ብዙ ዋጋ በተከፈለባት በዚህች ክልል የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚኖሩበት ቤት እንኳን እንዳይከራዩ በማድረግ የሚደርስባቸው እንግልት እጅግ የሚያሳዝን ነው። የህወሃት አንጋፋ አመራሮች በተገኙበት ኑ ሃሳባችሁን አካፍሉ ተብለው ከተጠሩ ተቃዋሚዎች አንዱ በሆነው አምዶም ገብረ ስላሴ ላይ በጭብጨባ ሃሳቡን ለማፈን ሲደረግ የነበረውን ጫና ለተመለከተ ህወሃት እና ዴሞክራሲ ምን ያህል እንደተራራቁ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው ።

ህወሃት በተሰኘው የፓርቲው ስያሜ ውስጥ የሚገኘው “አርነት” የሚለው ቃል ለሰዎች በሁሉ መልኩ ነጻነታቸውን የማጎናጸፍ ዕቅድ እንዳለ ያመላክታል። ይሁንና በዚህ መርህ በሚሰራ ድርጅት በሚመራ ክልል ውስጥ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ መታገዱና ይህን መብት ለማስከበር የሚሰራ ድርጅት መሪን “ትቀሰፋለህ” ብሎ የሞት ድንጋጌ ማወጅ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ የሚል ብሂልን ያስታውሳል። የትግራይ ህዝብ ጨዋና ዴሞክራሲ የገባው ህዝብ ሆኖ እንጂ የአቶ ጌታቸው ንግግር እኮ ዶክተር አረጋዊ ትግራይ ክልል ቢመጣ ግደሉት እንደማለት ነው።

መከላከያ አገር እንጂ ብሄር የለውም በሚለው ምርጥ ንግግራቸው ዘላለም በሚታወሱት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን የቀብር ሥነስርዓት ወቅትም ዶክተር አረጋዊ በርሄ በጥቂት ጋጠወጥ ቡድኖች የመደብደብ ወንጀል ተፈጽሞባቸው እንደነበር ሲታወስ አይበለውና እኚህ ግለሰብ አሁን ወደ ትግራይ ክልል ቢያቀኑ የአቶ ጌታቸው ረዳ መልዕክት ታክሎበት ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል ማሰቡ በራሱ ይከብዳል።

አቶ ጌታቸው በተደጋጋሚ በአገሪቱ ህገወጥነት እየተስፋፋ ነው የመንጋ ፍርድም በየቦታው ተስፋቷል ሲሉ እንዳላወገዙት ሁሉ ዶክተር አረጋዊ ወደ ትግራይ ክልል ቢመጡ የመንጋ ፍርድ ሰለባ ይሆናሉ ማለታቸው በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሚያስብል ነው። ምክንያቱም አቶ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች የህወሃት አመራሮች ደግመው ደጋግመው ሲደሰኩሩ የነበሩት ሌሎች ክልሎች እንጂ ትግራይ ከመንጋ ፍርድ ነጻ ነች የሚል ነበርና።

ከሰሞኑ የትግራይ ክልል ተማሪዎች ጥቃት እየደረሰባቸው ነውና ወደ አማራ ክልል እንዳይሄዱ ሲል የወጣው መግለጫም ልክ እንደ አቶ ጌታቸው ንግግር በህወሃት ውስጥ ጣትን ወዳሌላ መቀሰር እንጂ ራስን መመልከት ብዙም እንዳልተለመደ ማሳያ ነው። ምክንያቱም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በደረሱ አላስፈላጊ ጥቃቶች ዜጎች ያለአግባብ የተገደሉት ትግራይ ክልልም ጭምር ነበርና። ይሁንና የክልል ተማሪዎች ትግራይ ክልል ውስጥ ተገድለዋልና ወደትግራይ እንዳትሄዱ ሲል ተማሪዎቹን ያቀበ አንድም ክልል አልሰማሁም። ስለዚህ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም ወደሌላ አካል ጣታቸውን ከመቀሰራቸው አስቀድሞ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ቢመለከቱ መልካም ነው እላለሁ።

አቶ ጌታቸው ረዳ ከዚህ ቀደም በቀረቡባቸው የመገናኛ ብዙሃን መድረኮች የሚያምኑበትን ሃሳብ ያስረዱልኛል በሚሏቸው መረጃዎች አስደግፈው በመናገር ነበር የማውቃቸው። ይሁንና በስሜት ሞቅታ ጣል የሚያድርጓቸው ንግግሮች ራሳቸውንም በወቅቱ የነበረውንም አመራር ዋጋ እንዳስከፈለም የሚረሱት አይመስለኝም።

የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር በነበሩበትም ወቅት ህዝቦች ኢፍትሃዊነትን በመቃወም ያደርጉት የነበረውን ትግል ያዳክምልኛል ብለው የወረወሯት ጥንቃቄ የጎደላት ንግግር ምን ያህል የህዝብን ቁጣ ቀስቅሶ ትግሉን እንዳቀጣጠለም የሚረሳቸው አይመስለኝም።
አስር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ እንደሚለው ብሂል በተለይም የፖለቲካ አመራር የሆኑ ግለሰቦች አንዴ ለሚናገሩት ንግግር ሺህ እና ሺህ ጊዜ ደጋግመው ማሰብ እንደሚኖርባቸው አምናለሁ። ምክንያቱም ንግግራችውን የሚዳያምጥ ብቻ ሳይሆን አዳምጦ ሳያገናዝብ ወደ እርምጃ የሚያመራ ብዙ የህብረተሰብ ክፍል አለና።

ከዚህ አንጻር ስመለከተው አቶ ጌታቸው ረዳ በሰሞኑ ቃለምልልሳቸው ላይ ሃይለኛ ፋውል ሰርተዋል ብዬ አስባለሁ። ካለፈው ስህተታቸውም እየታረሙ መሄድ ላይ አሁንም ችግር እንዳለባቸውም ያመለክተኛል።

አቶ ጌታቸው ከፍተኛ አመራር የሆኑበት ህወሃት ምርጫው ዘንድሮ ካልተካሄደ ሞቼ እገኛለሁ እያለ ሲናገር ደጋግመን ሰምተነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይን ያህል ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚታፈኑበትና የሚጨቆኑበት ክልል እንደሌለም ትግራይ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲዎች የሚገልጹት ጉዳይ ነው። እናስ ህወሃት ምን ምቹ ሁኔታን አዘጋጅቶ ነው ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ ይካሄድ እያለ የሚወተውተው የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ያጭርብኛል።

በእኔ አምነት ህወሃት ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ ይከናወን የሚልበት ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች አሉ። አንድም በአፈና በያዘው መዋቅር ህዝብና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አፍኖ የለመደውን የይስሙላ አሸናፊነት ለማወጅ አልያም ምርጫውን ተከትሎ ይመጣልኛል ብሎ በሚያስበው ሁከት የለውጥ ኃይሉ ችግር ውስጥ ገብቶ በዚህ አቋራጭ ጊዜ ያለፈበትን የስልጣን ጥማቴን የሚያስታግስ አንድ ነገር ይፈጠርልኛል በሚል የዋህ ህሳቤ!
እኔ ግን እላለሁ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ ሁሉም የህወሃት አመራሮች የአገሪቱና የህዝቡን ወቅታዊ ሁኔታ አጢኑ። ጊዜ ካለፈበትና ቆሞ ቀር ከሆነው የማስፈራራትና ሴራ ተግባራችሁም ታቅባችሁ ህዝቡ ላደረገላችሁ ይቅርታ ውለታውን አውነተኛ ዴሞክራሲን በማስፈን መልሱ!

ምንጭ ፦ አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2012 ነጻ ሃሳብ አምድ