የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች!

እስኪ ፖለቲካው ይቆየንና ስለ እውነት እንናገር። ለአንድ አፍታ፤ ሳናዳምጥ አናውራ፣ ሳናውቅ አንቃወም፣ ሳይገባን አንደግፍ። እስኪ ለአፍታ እንኳን ከግብታዊ ስሜት እንውጣ፣ በምክንያት እናስብ። የአንድ ሃሳብ ትክክለኝነት የሚመዘነው በተናጋሪው ስልጣንና ማንነት ሳይሆን በምክንያታዊ ዕውቀት ነው። ምክንያታዊ ዕውቀት የትላንቱን ጠንቅቆ ማወቅ፣ የዛሬን በዝርዝር መገንዘብ፣ የነገን በትክክል መገመት ያስችላል። የትላንቱን ታሪክ እና የወደፊቱን ሁኔታ መሰረት ያደረገ በሰዎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥና መሻሻል ሊያመጣ የሚችል ሃሳብ ትክክልና አግባብ ነው። እንዲህ ያለ ሃሳብን ላለመቀበል መቃወም ራስን ማታለል፣ ሌሎችን መበደል ነው። ስለዚህ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ስንል ቆም ብለን ማሰብ፣ በምክንያት መጠየቅና በተግባር መፈተሸ ያስፈልጋል።

እንደ ናጄሪያዊው ሎሬት “Wale Soyinka” አገላለፅ “አክራሪ ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል፤ ግን ደግሞ አንድ ላይ ያውራል!” ይላል። በዋናነት ከ50 አመት በፊት የተጀመረው የብሔርተኝነት ንቅናቄ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል። ዛሬ ላይ ብሔርተኝነት ህዝባዊ ንቅናቄ ከመፍጠር አልፎ የግጭትና ዕልቂት መሳሪያ ሆኗል። ነገሩ ከራስ ወዳድነትና ወገንተኝነት አልፎ ወደ ጦርነትና ዕልቂት ሊቀየር ጫፍ ላይ ደርሷል። ሁሉም ሰው በየራሱ ብሔር ስር ተወሽቋል። እድሜ ለሕገ መንግስቱ እና ፌደራሊዝም ስርዓት ሁሉም ሰው በየራሱ ብሔር ጉያ ስር ተወሽቋል። ሁሉም ሰው በብሔር ተደራጅቶ አንድነቱን አጠናክሯል። ነገር ግን አንድ ላይ ያስተሳሰረው ነገር አንድ ላይ አውሮታል። ብሔርተኝነት በተንሰራፋው ልክ የሰዎችን እይታ፣ የማስተዋል አቅም እና የግንዛቤ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

አዎ… ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል። የእያንዳንዱን ብሔር አንድነት ያጠናክራል፤ የብሔር መብትና እኩልነት ይከበራል። በብሔር መደራጀት፣ በብሔር መነቃነቅ፣ በብሔር መቃወም፣ በብሔር መጠየቅ፣ በብሔር መንጠቅ፣ በብሔር ማጥፋት፣ በብሔር መግደል ይቻል ይሆናል። ነገር ግን በብሔር ፖለቲካ በራስ ማየት፣ በራስ ማሰብ፣ በራስ ማስተዋል፣ በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ፣ በራስ አመዛዝኖ መወሰን፣ ራስን በራስ መምራት አይቻልም። ምክንያቱም ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል እንጂ አንድ ዓይን የለውም፤ የሚያስብ አዕምሮ፣ አስተዋይ ልቦና፣ የራሱ ፍላጎትና ምርጫ የለውም። በመሆኑም ብሔር በራሱ አመዛዝኖ መወሰን እና ራሱን በራሱ መምራት አይችልም።

“Wale Soyinka” እንዳለው አንድ ላይ ያስተሳሰረን ብሔርተኝነት እውነታን ከማየት ያግደናል። ነባራዊ እውነታን ማየትና መገንዘብ የማይችል በራሱ ማሰብና ማስተዋል አይችልም፤ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መወሰን፣ ራሱን በራሱ መምራትና መንቀሳቀስ ይሳነዋል። ስለዚህ በብሔርተኝነት አንድ ላይ የታሰረ ህዝብ እውነታን አይቶ የሚገነዘብለት፣ አስቦና አመዛዝኖ የሚወስንለት፣ እንዲሁም ከፊት ሆኖ እየመራ የሚያንቀሳቅሰው መሪ ያስፈልገዋል። አንድ ላይ የተሳሰረን ህዝብ መምራት የሚችለው አንድ ሰው ወይም ቡድን ነው። በመሆኑም አንድ ብሔር ከአንድ በላይ መሪ ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ አንድ መሪ በራሱ እውነታን ያያል፣ ያገናዝባል፣ አመዛዝኖ ይወስናል፣ ከፊት ሆኖ ይመራል። የተቀሩት የብሔሩ አባላት በመሪው ዓይን ያያሉ፣ እሱ ያዘዛቸውን ያደርጋሉ፣ እሱ በመራቸው መንገድ ይጓዛሉ።

በዚህ መልኩ አክራሪ ብሔርተኝነት የሰው ልጅን ከምክንያታዊነት ወደ ግዑዝ መንጋነት ይቀይራል። መሪው የተናገረው ውሸት እውነት ይሆናል፣ መሪው የካደው እውነት ወደ ውሸትነት ይቀየራል፣ የመሪው ጥፋት ሁሌም አግባብ ነው፣ የመሪው መንግድ ፍፁም ትክክል ነው። መንገዱ በጠላቶች የተሞላ ነው። በጠላት ላይ ሲሰበክ የኖረ ጥላቻ ሁሌም ጠላት ይፈልጋል። በመሆኑም አንዱ ጠላት ሲወገድ ሌላ መተካት የግድ ይላል። ጉዞው በህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመከላከል የሚካሄድ ትግል ነው። በህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመከላከል የሚደረገው ትግል መስዕዋትነት ይጠይቃል። የትግሉ ዓላማ ነፃነትን መቀዳጀት ነው። በመጨረሻ የትግሉ ውጤት ነፃነትና ሰማዕታት ይሆናሉ።

እንደ ካሜሮናዊው ምሁር አቺሌ ምቤምቤ አገላለፅ መሪው ያለው “የሙታን ኃይል” (Necropower) ነው፣ ፖለቲካውም “የሙታን ፖለቲካ” (Necropolitics” ይባላል። የሙታን ኃይል ማን መኖር፣ ማን መሞት እንዳለበት መወሰን የሚያስችል ስልጣን ነው። በሙታን ፖለቲካ ራስን በመከላከል እና በማጥፋት፣ በመመለስ እና ነመቅረት፣ በነፃነት እና ሰማዓት መካክል ግልፅ የሆነ መስመር የለም። የሙታን መሪዎች በትግል ከተገኘው ድል ይልቅ የተገደሉትን፣ ካገኙት ነፃነት ይልቅ ሰማዕታቱን ማሰብ ይመርጣሉ። ምክንያቱም ቂምና ጥላቻን ማራዘም ይሻሉ። ጠላትና ጦርነት ከሌለ ተከታይ አይኖራቸውም። ስለዚህ ስልጣናቸውን ለማራዘም ጥላቻ እየሰበኩ ጠላት ያፈራሉ፣ ቂም በመቆስቆስ ግጭት ይፈጥራሉ። ይህ ሲሆን ጭፍን ደጋፊዎች የሙታን መንገድን ይከተላሉ። በቂምና ጥላቻ ሌሎችን ይገድላሉ ወይም በሌሎች ይገደላሉ። በዚህ መልኩ የሙታን ኃይል ከሞት ይመነጫል፣ የሙታን ፖለቲካ በፍርሃት መርህ ይመራል።

ባለፉት አራት አስርት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የሙታን ፖለቲካ ነው። የፖለቲካ መሪዎቻችን ስልጣንም ከሞት የመነጨ ኃይል ነው። ከአብዮቱ ጀምሮ የሀገራችን ፖለቲካ በጅምላ መፈራረጅና መገዳደል የተሞላ መሆኑ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በተለይ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን አብዮትና ፀረ አብዮት፣ ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር፤ ኢትዮጵያ ወይም ሞት፣ የአንድነት ወታደር እና ገንጣይ ወንበዴ፤ ሰላምና ፀረ-ሰላም፣ ልማትና ፀረ-ልማት፣ ህገ መንግስትና ፀረ-ህገ መንግስት፣ ሽብርና ፀረ-ሽብር፣… ወዘተ በሚል የጅምላ ፍረጃ የአንድ ዘመን ትውልድ እርስ በእርሱ ለዕልቂት ተዳርጓል። ምክንያቱም ያ ትውልድ አብዮተኛ ነው። “አብዮት” ደግሞ ወረተኛ ነው። ወረቱ ሲያልቅ እርስ በእርስ መፈራረጅና መገዳደል የግድ ነው።

በመሰረቱ አብዮተኛ እና ፀረ-አብዮተኛ በሚል በጅምላ ከመከፋፈል በስተቀር በመካከላቸው መሰረታዊ የሆነ የአቋም ሆነ ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት አልነበረውም። ሁሉም አብዮተኛ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፣ የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ይጠይቃል። ከሞላ ጎደል ሁሉም አብዮተኞች የማርክሲስት/ሌኔኒስት ጥራዝ ነጠቆች ናቸው። ነገር ግን ሁሉም ራሳቸውን “አብዮተኛ” ሌሎችን “ፀረ-አብዮተኛ” ብለው በጅምላ ይፈራረጃሉ። ከጅምላ መፈራረጅ ቀጥሎ በጅምላ መገዳደል ይከተላል። ምክንያቱም የአብዮተኛው ድል የሚረጋገጠው ፀረ-አብዮቶችን በመግደል ነው። በሌላ በኩል አንድ ፀረ-አብዮተኛ የሚኖረው አብዮተኞች በሙሉ ሲወገዱ ነው። የአብዮቱ ስኬት ለፀረ አብዮቱ ሽንፈት ነው።

በሙታን ፖለቲካ የአንዱ ህይወት የሚገኘው በተቀናቃኙ ሞት ነው። ስለዚህ ጎራ ለይቶ መገዳደል የስርዓቱ መገለጫ ነው። ይህ በተለይ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ ኢትዮጵያ ስትመራበት የነበረ የፖለቲካ ስርዓት ነው። ለምሳሌ በደርግ የተጠለፈውን የተማሪዎች አብዮት ለማስመለስ የነጭ ሽብር ጥቃት ተፈፀመ። ነጭ ሽብርን ለመመከት ቀይ ሽብር ተፋፋመ። በዚህ ምክንያት አንድ ትውልድ በሙታን ፖለቲካ መከነ። እናት ልጇ ለተገደለበት ጥይት ከፈለች፣ አባት የልጁን ሬሳ ከመንገድ ላይ ማንሳት ተሳነው፣ ወዳጅ ዘመድ ከገዳዮች ፊት ማልቀስ ተከለከለ።

ከነጭ ሽብር ጥቃት የተረፉት ሶሻሊስት አብዮተኞች ደርግ እና መኢሶን በሚል ተከፋፍለው ተገዳደሉ። ደርግ ደግሞ “ቆራጥ አብዮተኛ” እና “ስርጎ-ገብ አድሃሪ” በሚል እርስ በእርስ ተከፋፍሎ ተገዳደለ። በዚህ መልኩ እነ ጄነራል ተፈሪ በንቲ እና ሺ/አለቃ አጥናፉ አባተን የመሳሰሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገደሉ። የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቀንቃኞች የነበሩት ኢህአፓ እና ህወሓት ደርግን ለመውጋት በመሸጉበት እርስ በእርስ ተዋጉ። ኢህአፓን ያስወጣው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በውስጡ የትግራይ ማርክሲስት ልኔኒስት ሊግ (ትማልሊ) የሚል ድርጅት በመፍጠር ለሁለት ተከፈለ። ይህን ተከትሎ የህወሓት ዋና ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ኢ/ር ግደይ ዘርዓፂዮንን ጨምሮ ሌሎች የድርጅቱ መስራቾች ተሰደዱ።

ደርግ እና ህወሓት በየፊናቸው እርስ በእርስ ተከፋፍለው ከተገዳደሉ በኋላ የሀገር አንድነት እና የብሔር እኩልነት በሚል እርስ በእርስ ውጊያ ገጠሙ። ደርግ ወድቆ ህወሓት ሲመጣ ከስም በቀር የትውልድ አሊያም የስርዓት ለውጥ አልተደረገም። ምክንያቱም ደርግና ህወሓት የ1960ዎቹ አብዮተኛ ትውልድ ናቸው። አብዮተኛ ትውልድ ደግሞ “የፀረ” ፖለቲካ አራማጅ ነው። ስልጣኑም ከሞት የመነጨ ነው። በመሆኑም ህወሓት ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት፤ ሰላምና ፀረ-ሰላም፣ ልማትና ፀረ-ልማት፣ ህገ መንግስትና ፀረ-ህገ መንግስት እያለ በጅምላ መፈረጅ፣ በጅምላ ማሰር፣ በጅምላ መግደልና ማሰቃየት ጀመረ። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ነገር በሽብርተኝነት የሚፈርጅ የፀረ-ሽብር አዋጅ አወጣ። በዚህ መልኩ የደርግ ቀይ ሽብር ዘመቻ በፀረ-ሽብር አዋጅ ተተካ።

አብዮተኛ ትውልድ የፀረ-ፖለቲካ አቀንቃኝ፣ የሙታን ፖለቲካ አራማጅ ነው። የአንድ ትውልድ አማካይ ዘመን 30 አመት ነው። በዚህ መሰረት የ1960ዎቹ ትውልድ ዘመን ያከተመው በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ነው። የ1997ቱ ምርጫ የአብዮተኛው ትውልድ ዘመን ማብቂያና የአዲሱ ትውልድ ዘመን መጀመሪያ ነበር። ነገር ግን አዲሱ ትውልድ ሀገሪቱን ለመረከብ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ያደረገው ግብግብ በአጋዚ ወታደሮች ተጨናገፈ። ከአስር አመት ትዕግስት በኋላ ለቀጣይ 50 አመታት ኢትዮጵያን ለመግዛት ሲያልሙ የነበሩትን አብዮተኞች በሦስት አመት ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ከስልጣን አስወገደ።

በአጠቃላይ ከደርግ መምጣት እስከ ህወሓት ውድቀት ድረስ ያለው ሁኔታ አንድና ተመሳሳይ ነው። አብዮተኞች ከሃሳብ የበላይነት ይልቅ በጉልበት የበላይነት፣ ከውይይት ይልቅ በጦርነት፣ ከመነጋገር ይልቅ በመገዳደል የሚያምኑ ስለመሆናቸው ከኢትዮጵያ በላይ እማኝ ምስክር የለም። በዚህ የጥሎ ማለፍ ፖለቲካ ውስጥ የአንዱ ስልጣን ሌላውን በመጣል፣ የአንዱ ድል ሌላውን በመግደል፣ የአንዱ ህይወት በሌላኛው ሞት ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ የተገነባችበት መሰረት ተሸርሽሮ አልቋል።

በእርግጥ የአብዮቱ ፖለቲካ የሚቀጥል ከሆነ በጥቂት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች። ስለዚህ አዲሱ ትውልድ እንኳን የሚመራው መንግስት የሚኖርበት ሀገር አይኖረውም። ኢትዮጵያ ከፈረሰች ደግሞ አሁን በውስጧ ያሉት ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ሀገር መስርተው በጉርብትና የሚኖሩ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። ከዚያ ይልቅ ሀገሪቱ ከፈረሰች ምስራቅ አፍሪካን የሚያጥለቀልቅ የደም ጎርፍ ይፈስሳል፣ ተቆጥሮ የማያልቅ ሬሳ በየስርቻው ይከመራል። ኢትዮጵያ ወደ ምድራዊ ሲዖል ትቀየራለች። ስለዚህ አዲሱ ትውልድ የትላንቱን ያረጀ የፖለቲካ አመለካከትና ዛሬ ላይ የሚስተዋለውን ጭፍን ብሔርተኝነት ማስወገድ አለበት።

በዚህ መሰረት የወደፊቱን አስከፊ እልቂትና ውድቀት ለማስቀረት አዲሱ ትውልድ አበክሮ ማሰብ፣ መስራትና መተባበር ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ ከፊት ለፊቱ ቆመው የዕልቂት ነጋሪት እየጎሰሙ ያሉትን የፖለቲካ ቡድኖች በግልጽ መጋፈጥ አለበት። እነዚህ የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች ህወሓት እና ጃዋር (ኦነግ) ናቸው። ለአዲሱ ትውልድ የሁለቱ ጥምረት ትክክለኝነት እና አግባብነት ፍፁም ሊያሳስበው አይገባም። ምክንያቱም የህወሓቶች ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ ባለፉት 27 አመታት በተግባር የታየ ነገር ነው። ህወሓቶች በ1997ቱ ምርጫ ደንግጠው ልክ እንደ አሁኑ ወደ መቀሌ ሸሽተው ከተመለሱ በኋላ በአስር አመት ውስጥ በህዝብ ላይ ያደረሱትን ስቃይ እና በሀገር ላይ የፈፀሙትን ዘረፋ ሁላችንም እናውቃለን።

አሁን ደግሞ ተመልሰው ከመጡ በምድር ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ አሰቃቂ ነገር ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ጥርጥር የለኝም። በሌላ በኩል እነ ጃዋር መሃመድ የሚያራግቡት አክራሪ ብሔርተኝነት እነ ሌንጮ ለታ እና ሌንጮ ባቲ እድሜ ልካቸውን ሞክረው እውን ሊሆን እንደማይችል በተግባር ያረጋገጡት ነገር ነው። ህወሓት እና ጃዋር/ኦነግ ጥምረት የፈጠሩበት ምክንያት፤ አንደኛ፡- ሁለቱም ስር የሰደደ የስልጣን ጥማት እና የቁሳዊ ኃብት ፍላጎት ስላላቸው፣ ሁለተኛ፡- ሁለቱም የሙታን ፖለቲካ የሚያራምዱ የአብዮቱ ትውልድ ርዘራዦች በመሆናቸው ነው። በአጠቃላይ የህወሓት እና ጃዋር/ኦነግ ቅንጅት ላለፉት አርባ አመታት የመጣንበትን በጥላቻነ ቂም የታጨቀ፣ በግጭትና ጦርነት፣ እንዲሁም በጅምላ ፍረጃና ግድያ የሚታመስ፣ ያን ያረጀና ያፈጀ የሙታን ፖለቲካ ለማስቀጠል ያለመ ነው። በዚህ ምክንያት ገፈት ቀማሽ የሚሆነው ደግሞ አዲሱ ትውልድ ነው! የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች የሁላችንም ስጋት ናቸው!

One thought on “የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች!

  1. አሃዳዊ ስርአት ለመገንባት የሚደረገው ሽርጉድ ድካም ቴተርፉ እንደሆነ እንጂ በፍፁም ሊሳካላቹ አይችልም። ስዩም አንተ ለራስህ ሞልቶ የሚፈሰው የጥላቻ በሽታህን ያበሽታክን በየ ፌስቡኩ እየዘራህ ሰውን ለማፋጀት ሊት ከቀን እየሰራህ ነው። ሆነም ቀረም በዝች አገር አንተና መሰሎችህ አብዬቱ ካልበላቹ በስተቅር አገራችን ሰላም አናገኝም በቅርቡም መበላታቹ አይቀርም።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡