የሽንፈት ሙሾ: ህወሓት በፖል ካጋሜ አንገት ላይ የጌታቸው አሰፋን ፊት ቀጠለበት!!!  

በትላንትናው ዕለት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ መጀመሩን አስመልክቶ የወጣውን የፎቶ ምስል ስመለከት ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የሆነ የፊት ገፅታ ማየቴ ትዝ አለኝ። ከዚያ “ይሄን የፊት ገፅታ ያየሁት መቼ ነበር?” እያልኩ ማሰላሰል ጀመርኩ። ግዜና ቦታው ጠፋኝ እንጂ በህወሓት አመራሮች ላይ ተመሳሳይ ገፅታ ማየቴ ትዝ ይለኛል። ነገር ግን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የውህደቱ ጉዳይ የውይይት አጀንዳ ይሁን ወይስ አይሁን በሚለው ላይ ውሳኔ ማሳለፉን የሚጠቁም መረጃ ስለደረሰኝ ትኩረቴን ወደዚያ አዞርኩ። አብዛኛው የፌስቡክ ተጠቃሚ በምስሉ ላይ ባለው የህወሓቶች የፊት ገፅታ መሳቅና መሳለቅ ጀምሯል። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ባሳለፈው ውሳኔ ክፉኛ ተበሳጭተው የወጡት የህወሓት አመራሮች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሳቂያና መሳለቂያ መሆናቸውን ሲመለከቱ የባሰ ጨሱ።

በዚህ ምክንያት ከደረሰባቸው የፖለቲካ ኪሳራ ለማገገም በሥራ አስፈፃሚ ኮሚተው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ አመራሮች ፎቶ በህወሓት የፌስቡክ ገፅ ላይ እንዲወጣ ቀጭን መመሪያ የሰጣሉ። የፌስቡክ ገፁ የሚያወጣቸው የፎቶ ምስሎችም በፈገግታ የተሞላና የአመራሮቹን የፊት ገፅታ በጥሩ ሁኔታ የሚያሳይ መሆን እንዳለበት ታምኗል። ሆኖም የህወሓት ፌስቡክ ገፅ ያወጣቸው ፎቶዎች የታሰበውን አይነት ውጤት የሚያመጡ አይደሉም። ከዚያ ይልቅ አመራሮቹን የባሰ መሳቂያና መሳለቂያ የሚያደርጋቸው ሆኖ ተገኘ።

የህወሓት ፌስቡክ ገፅ ባወጣው ፎቶ የዘጠኝ ሰዎች ምስል ያለበት ነው። መሃል ላይ ዶ/ር ደብረፂዮን ፎቶ አለ። የቢሮ ወንበር ላይ ወደኋላ ደገፍ ብሎ ተቀምጧል። ልክ የቡጢ ግጥሚያ ላይ ያለ ይመስል ሁለት እጆቹን ጨብጦ ወደ አፍና አፍንጫው አስጠግቷቸዋል። አያያዙን ሲያዩት በግራ እጁ ቡጢ ሊሰነዝር የተዘጋጀ ይመስላል። ግን ደግሞ ወንበሩ ላይ ወደኋላ ተለጥጧል። ከአቀማመጡ አንፃር ሲታይ በአንድ ቡጢ ይዘረራል። ተሸንፏል ብለው እንዳይተውት ደግሞ በድንገት በግራ እጁ ቡጢ ሊሰነዝር ይችላል። በዚህ ምክንያት ተጋጣሚውን መዘረር ባይችል እንኳን ማቁሰል አይሳነውም። በደብረፂዮን የፊት ገፅታ ላይ የሚታየው ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይከብዳል። ፊቱ ላይ የሚታየው የደስታ ድሜት ነው እንዳይባል ቅንጣት ያህል ፈገግታ አይታይም። ፊቱ ላይ የመከፋት ስሜት ይታያል እንዳይባል ደግሞ የአፉና ዓይኑ አከፋፈት የሞቀ ጨዋታ ላይ እንዳለ ያስታውቃል።

Photo© Tigray People’s Liberation Front/TPLF Official

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሳቂያና መሳለቂያ መሆናቸውን ለማስቀረት በህወሓት የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣው የዶ/ር ደብረፂዮን ምስል ትክክለኛ ባህሪውን የሚያሳይ ነው። ልክ እንደ ዶ/ር ደብረፂዮን ፎቶው ላይ ያለው ገፅታ ይወላውላል። በአንድ በኩል የቢሮ ወንበር ላይ ተቀምጧል ሲሉት በሌላ በኩል ደግሞ ልክ እንደ ቦክሰኛ ቡጢ ሊሰነዝር ያቆበቆበ ይመስላል። የፊት ገፅታው ላይ በአንድ ግዜ የደስታና መከፋት ስሜት ማንፀባረቅ የሚችል ሰው አለ ከተባለ ዶ/ር ደብረፂዮን እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም።

በሌላ በኩል አቶ ጌታቸው ረዳ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ ፀሐይ የመታው ጎመን ይመስል ፊቱ ጠውልጎ፣ ስሜቱ ዝሏል።ማታ ላይ የበህወሓት የፌስቡክ ገፅ የወጣው ምስል ደግሞ ጌቾ ከምንግዜው ፕላኔት ሆቴል ደረሰ ያሰኛል። ምክንያቱም በዚህ ፎቶ ላይም የጌታቸው ፊት ጠውልጓል፣ ስሜቱም ዝሏል። ለፎቶ ሲባል ዓይንና አፉን በግድ የፈለቀቁት ይመስላል። የፊት ገፅታውን በማየት ሳቅ ላይ ይሁን ሲቃ ላይ መለየት አይቻልም። ከዚህ በተረፈ አቶ አዲስ ዓለም ባሌማ፣ ኬሪያ፣ አስመላሽ እና የመሳሰሉት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባላት በኩልና በጥቁር ምንፅር ደምቀው የሚታዩበት ፎቶ ተመርጦ ተለጥፏል። ሞንጆሪኖ የህወሓት/ኢህአዴግን ቀይ ኮፍያን አድርጋ ከአንገት በላይ ትታያለች። ከእሷ ጎን ደግሞ አንድ ማንነቱ በግልፅ ተለይቶ የማይታወቅ የህወሓት ታጋይ የጦር መሳሪያ፣ የድል ችቦ፣ ባንዲራ እና የራዲዮ መገናኛ ይዞ ሸብረክ ብሎ ቆሟል። እንግዲህ ከዘጠኙ የህወሓት/ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ውስጥ የቀረው አቶ ጌታቸው አሰፋ ነው። ስለዚህ ይህ የፖስተር ስዕል ጌታቸው አሰፋ ነው ማለት ነው?

በሌላ በኩል ከፎቶዎቹ ጋር አብሮ የወጣው ፅሁፍ መደምደሚያ “ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለሰማዕታት! ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ” የሚል ነው። ይህ አባባል ላለፉት አርባ አምስት አመታት ያለ አግባብ ጥቅም ላይ በመዋሉ ምክንያት ትርጉምና ለዛ አጥቷል። በእንዲህ ያለ ባዶ መፈክር በኢህአዴግ ውህደት የደሰባቸውን ሽንፈትና በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰነዘረባቸው ላለው ትችት አጸፋ ሊሆን አይችልም። በአጠቃላይ የህወሓት ፌስቡክ ገጽ ያወጣቸው የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባላት ፎቶ ምስሎች ሆኑ ከምስሉ ጋር የወጣው ፅሁፍ ውጤታማ አልሆነም። በዚህ መሰረት ለ40 ደቂቃ በኋላ ከሥራ አስፈፃሚው አባላት ይሁን ከድርጅቶ መስራቾች አሊያም ደግሞ ከገጹ ተከታዮች በተሰጠ ጥቆማ ከላይ በተጠቀሱት የፎቶ ምስሎችና የፅሁፉ ይዘት ሙሉ በሙሉ ተለውጠዋል።

በፅሁፉ ይዘት ላይ ከተደረገው ለውጥ በተጨማሪ የክልሉን ምክትል ፕረዜዳንት ስም በመጥቀስ ለዶ/ር ደብረፂዮን ግልባጭ ተደርጓል። ከዚህ አንፃር ለገፁ አዘጋጆች ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሰጠው ዶ/ር ደብረፂዮን እንደሆነ መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ የፎቶ ምስሎቹን ስትመለከቱ ደግሞ ግምታችሁ ፍፁም ስህተት እንደሆነ ይገባችኋል። ምክንያቱም የመጀመሪያው ላይ የዶ/ር ደብረፂዮን ፎቶ ምስል መሃል ላይ የነበረ ሲሆን በሁለተኛው ላይ ግን ፎቶው ተነስቶ የህወሓት ሎጎ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ቀድሞ በነበረው የግራ የገባው ፎቶ ምትክ ዶ/ር ደብረፂዮን ገና ታጋይ እያለ በተነሳው ፎቶ ተተክቷል። ይህን የድሮ ጥቁርና ነጭ ፎቶ ከዛሬው የዶ/ር ደብረፂዮን የፊት ገፅታ ጋር መመሳሰል ቀርቶ ለንፅፅር እንኳን አይቀርብም። በቅርብ የተነሳው ፎቶ ላይ ያለው የፊት ገፅታ ግራ የገባው ከተባለ በጥቁርና ነጩ ፎቶ ላይ የሚታየው የፊት ገፅታ ወስፌ የሚባል ዓይነት ነው።

Photo© Tigray People’s Liberation Front/TPLF Official

በመጀመሪያው ፅሁፍ የህወሓት/ኢህአዴግን ኮፍያ አድርጋ ዘመን ተሸጋሪ የሆነድንቡሽ ያለ ጉንጭና ከንፈር የነበረው የሞንጆሪኖ ፎቶ ተነስቷል። በምትኩ ደግሞ ገና ጫካ እያለች ፀጉሯን የጭራሮ መጥረጊያ አስመስላ የተነሳችው ጥቁርና ነጭ ፎቶ ገብቷል። በመጀመሪያው ፅሁፍ ላይ ጥቁር ምንፅር አድርጎ በማይክራፎን ሲናገር የሚያሳይ ፎቶ የነበረው ዓለም ገብረዋሃድ እሱ መሆኑን በሚያጠራጥር መልኩ በጭራሮ ስታይል በተነሳ ጥቁርና ነጭ ፎቶ ተተክቷል። ወ/ሮ ኬሪያ ሂጃብ ከመቀየር በዘለለ በፎቶው ቀለምና ዓይነት ላይ ብዙም ለውጥ አልተደረገም። በተመሳሳይ አቶ አዲስዓለም ባሌማ ደግሞ በሁለቱ ምስሎች ላይ ያለው ልዩነት አንድ ጥቁር ምንፅር ብቻ ነው። መጀመሪያ ላይ የጠወለገ ጎመን ይመስል የነበረው ጌታቸው ረዳ ጥቁር ምንፅር አድርጎ ከአቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ጋር ጎን ለጎን ቆመው ይታያሉ።

በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተነሳው ሆነ በህወሓት የፌስቡክ ገፅ ላይ በወጣው ፎቶ የድብርት ስሜት ጫኚና አውራጭ ይመስል የነበረው ጌታቸው ረዳ በሁለተኛው ፅሁፍ ላይ ዘናጭ ፍሪክ መስሎ መታዬቱ ያስጠረጥራል። በእርግጥ አቶ ጌታቸው ረዳ በስብሰባው ላይ ሆነ በመጀመሪያው ምስል ላይ የነበረውን የፊት ገፅታ ለሦስተኛ ግዜ ቢደግመው ኖሮ ፌስቡክ ራሱ አስፈሪ ምስል በሚል ይፈርጀውና ወይ ፅሁፉን ያጠፋዋል አሊያም ይሸፍነዋል የሚል እምነት አለኝ። ከሁሉም ከሁሉም የሚገርመው ግን ማንነቱ ባልታወቀው የህወሓት ታጋይ ቦታ የገባው ፎቶ ነው። በፌስቡክ ገፁ ላይ በወጣው የመጀመሪያ ፅሁፍ ስምንቱ የህወሓት/ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና አንድ ማንነቱ ተለይቶ ያልታወቀ የቀድሞ የህወሓት ታጋይ ምስል እንደነበር ቀደምሲል ተገልጿል። በሁለተኛው ፅሁፍ ላይ ግን በታጋዩ ቦታ ወታደራዊ ሬንጀር ልብስ የለበሰ ሰው ምስል ተተክቷል። ይህ በታጋዩ ምትክ የገባው ፎቶ ምስል ዘጠንኛው የህወሓት/ኢህአዴግ ስራ አስፈፀፃሚ ኮሚቴ አባል የአቶ ጌታቸው አሰፋ ምስል ነው።

አንድ ወዳጄ ሁለተኛ ላይ የወጣው ምስል ፌስቡክ ላይ ለጥፎ እንደተመለከትኩ ወዲያው ወደ ህወሓት ፌስቡክ ገፅ ሄጄ ስክሪንሾት አነሳሁት። በገፁ ላይ ወደ ታች ዝቅ ስል ደግሞ የመጀመሪያውን ፅሁፍ አገኘሁት። በመቀጠል በሁለቱ ፅሁፎችና ምስሎች መካከል ያለውን ልዩነት በጥሞና ማጤን ጀመርኩኝ። ከወትሮ በተለየ የአቶ ጌታቸው አሰፋ ምስል ከተቀሩት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባላት ጋር አብሮ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መለቀቅ የተጀመረው ከመቼ ወዲህ ነው? አቶ ጌታቸው አሰፋ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ መሆኑ ተረስቶ ወይስ ሰውዬ ያለበት ፍርሃት ለቅቆት ነው? ሰውዬው የፎቶ ምስሉ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲወጣ ቢፈቅድ እንኳን እንዲህ ያለ ወታደራዊ ልብስ ለብሶ ፎቶ የተነሳው መቼና የት ነው?

Photo© Tigray People’s Liberation Front/TPLF Official (Cropped Image)

ከላይ የተነሱትንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ለመመለስ በቅድሚያ የፎቶ ምስሉን ትክክለኝነት ማረጋገጥ ተገቢ ነው። በዚህ መሰረት በሁለተኛው ፅሁፍ ላይ የአቶ ጌታቸው አሰፋ እንደሆነ ተደርጎ የወጣውን የፎቶ ምስል ስፈልገው የሩዋንዳው ፕረዜዳንት ፖል ካጋሜ ሆነው አገኘኋቸው። በእርግጥ የፊት ገፅታው የአቶ ጌታቸው አሰፋ ነው። ከዚያ በተረፈ ያለው ግን ፕረዜዳንት ፖል ካጋሜ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ባለፈው አመት 2018 ዓ፣ም ላይ የተነሱት ፎቶ ነው። ስለዚህ የህወሓት ፌስቡክ ገፅ ላይ በወጣው ፅሁፍ የአቶ ጌታቸው አሰፋ ምስል እንደሆነ ተደርጎ የወጣው ፎቶ የጌታቸው አሰፋን የፊት ምስል ቆርጦ በፖል ካጋሜ አንገት ላይ በመቀጠል የተሰረ ሃሰተኛ ምስል ነው።

Photo© edge.ug

ህወሓቶች “’እኛ ራሳችን አይተነው አናውቅም’ እያሉ የሚያቆላምጡት የሰው አውሬን ወታደራዊ ልብስ የለበሰ አስመስሎ ማውጣት ለምን አስፈለገ?” የሚለውን ስናይ ደግሞ የኢህአዴግ ውህደት በህወሓት ላይ ያደረሰውን ሽንፈትና አቅመ-ቢስነት ይጠቁመናል። በትላንቱ ስብሰባ ላይ የደሰበት ሽንፈት፣ ከስብሰባው በኋላ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች የወረደበት ትችትና ሽሙጥ ህወሓትን እንደ ሳማ ለብልቦታል። ሽንፈትና አቅመ-ቢስነት ውስጡን እንደ አሲድ አቃጥሎታል። በተለይ የዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል፣ የጌታቸው ረዳ፣ የአስመላሽ ወልደስላሴ እና የሞንጆሪኖ የፊት ገፅታ የኢህአዴግ ውህደት የፈጠረባቸው የውርደትና ሽንፈት ስሜት እንደ ቋያ እሳት ውስጣቸውን እያነደደው እንደሆነ በግልፅ ያሳያል።

በህወሓቶች የፊት ገፅታ ላይ እንዲህ ያለ የሽንፈትና ውርደት ስሜት ስመለከት ይሄ ለሁለተኛ ግዜዬ ነው። የመጀመሪያውን የሽንፈት ፅዋ የተጎነጩት በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ነበር። ምርጫና አማራጭ በሌለበት እንደ እንቆቆ የሚመርረውን ሽንፈት ጭልጥ ሲያደርጉ፣ ከዚያ በኋላ በውስጣቸው የውርደትና ተሸናፊነት ስሜት አንጀታቸው እንደ ንፍሮ ሲቀቀል፣ በብስጭት ብዛት ጨቋራቸው የአሲድ ማቆሪያ ሲሆን፣ በዚህ መልኩ በውስጣቸው የፈነዳው እሳተ ገሞራ እየገነፈለ ፊታቸው ማዲያት ሲያወጣ፣ በእብሪት ሲሳደቡ የነበረው ሰዎች አንገታቸውን አቀርቅረው ሃፍረትን ሲከናነቡ አስታውሳሉ። አምባገነን ሲወድቅ፣ ጨቋኝ ሲሸነፍ፣ አፓርታይድ ሲሞት ፊቱ ላይ የሚታየውን ስቃይ አውቀዋለሁ፣ ጣር ይዞት የሚያሰማውን የሲቃ ድምጽ እንደ ጥዑም ዜማ አዳምጠዋለሁ።

ትላንት ህወሓቶች ላይ ያየሁት የፊት ገፅታ ከሁለት አመት በፊት መጋቢት 2010 ዓ.ም ላይ አይቼው እንደነበር ትዝ ያለኝ ለዚህ ነው። እኔ የህወሓትን ስሜት የማጠናው በዕውቀትና ማስረጃ ነው። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የፃፍኳቸው ከአንድ ሺህ በላይ ጦማሮች በግምት ወደ 20ና 30 ጥናታዊ ፅሁፍ ይወጣዋል። ህወሓት ሲሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሲያሸንፍም አውቃለሁ፤ አከርክሪው ሲመታና ቆስሎ ሲድን፣ ሸሽቶ ሲሄድና አድብቶ ሲመጣ የጎሪጥ አየዋለሁ። ምክንያቱም የተናገሩትን ሳይሆን ለምን እንደተናገሩት በጥሞና አጤናለሁ። ካደረጉት ክፋት ይልቅ ያደረጉበት እኩይ ዓላማ አስባለሁ። በዚህ ላይ ደግሞ ያሰቡትንና ያደረጉትን የሚያሳዩ ያፈተለኩ መረጃዎችን በጥንቃቄ አያለሁ። ለምሳሌ ብዙዎች ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ያደረኩት ትላንት ማታ ህወሓት በፌስቡክ ገፁ ላይ ያወጣው ፅሁፍ ሊመስላቸው ይችላል።

PHOTO © Ethio Wiki Leaks

በእርግጥ እሱ ራሱን የቻለ ግብዓት ነው። ነገር ግን ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ የዶ/ር አብይን መመረጥ ተከትሎ ወ/ሮ ገሊላ ሚካኤል የተባለች ግለሰብ ለዶ/ር ደብረፂዮን የላከችው ምክረ ሃሳብ ነው። በዚህ የኢሜይል መልዕክት ህወሓት በዶ/ር አብይ መመረጥ ምክንያት የደረሰበትን ውርደትና ተሸናፊነት በግልፅ መረዳት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ጠ/ሚ አብይ በመቀሌ ከተማ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የተደረገላቸው አቀባበል፣ ከተሰብሳቢዎች የተነሱላቸው ጥያቄዎች፣ የህወሓት ካድሬዎች የነገሯቸው፣ በስብሰባ አዳራሹ የነበሩት እንግዶች፣ ሌላው ቀርቶ የተሸለሙት ባህላዊ አልባሳት እና አየር ማረፊያ ላይ የተበረከተላቸው እቅፍ አበባ እንኳን ሽንፈት በወለደው አስመሳይነት የታጨቀ ነው። ህወሓቶች በዚያን ወቅት ሰሞን የተሰማቸውን የሽንፈትና ውርደት ስሜት ከትላንት ጀምሮ ዳግም እያጣጣሙት ነው። መቼም ሰው ናቸውና ብርታቱን ይስጣቸው!!!!

One thought on “የሽንፈት ሙሾ: ህወሓት በፖል ካጋሜ አንገት ላይ የጌታቸው አሰፋን ፊት ቀጠለበት!!!  

  1. መረጃዎቻችሁ በጣም ማራኪና ትኩረት የተሰጣቸው አንኳር ክስተቶች ናቸውና በርቱልን!!!

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡