ዲፋክቶ ወይስ ድንፋታ: አንቀጽ 39 እና ሀገር ምሥረታ

ፀሓፊ:- ቢኒያም ነጋሽ
እ.ኤ.አ. ጥቅምት 27 2017 የካታሎኒያ ምክር ቤት ካታሎኒያ ነፃ አገር መሆኗን ያወጀበት ሥነ-ሥርዓት በትልልቆቹ የዓለም መገናኛ ብዙሀን በቀጥታ ጭምር የተላለፈ ነበር፡፡ ፓርላማው ይህን የመሰለ ቀልብ የሚይዝ ውሳኔ ያሳለፈው በአውራጃው ሥራ አስፈጻሚ የአንድ ወገን ውሳኔ በዚያው ወር መጀመሪያ ያካሄደውን የሕዝበ-ውሳኔ ውጤት መሠረት በማድረግ ነበር፡፡ የነፃ አገርነት እወጃውን ተከትሎም የስፔን ፌዴራል መንግሥት ማስጠንቀቂያው ጆሮ ዳባ ልበስ ያለውን የአውራጃ ፓርላማ በትኖ፣ ሥራ-አስፈጻሚውን አፍርሶ ከማድሪድ ቀጥታ ትዕዛዝ የሚቀበል ጊዜያዊ መንግሥት መሠረተ፡፡ ይህንን የመገንጠል እንቅስቃሴ ያስተባበሩ ሰዎችንም ፍርድ ቤት ቀርበው እስር እንዲከናነቡ አደረገ፡፡


የካታሎኒያ የሕዝብ ወሳኔ ከመካሄዱ ጥቂት ቀናት በፊት ተመሳሳይ የመገንጠል ሕዝበ-ውሳኔ በኢራቅ የኩርዲስታን ክልላዊ መንግሥት ተከናውኖ ነበር፡፡ የመገንጠል ሀሳቡ 93 በመቶ የኩርድ ሕዝብን ድጋፍ ማግኘቱ ቀድሞውንም ቢሆን የተገመተ ነበር፡፡ ይሁንና የሕዝበ-ውሳኔው ውጤት የኮረኮረው ደስታና ፈንጠዝያ ተኖ ለመጥፋት የቀናት ዕድሜ ብቻ ነበር የወሰደበት፡፡ የኢራቅና የሌሎች አገራትን ማስጠንቀቂያ ገሸሽ በማድረግ የአንድ ወገን ሕዝበ-ውሳኔ ያካሄደው የኩርዲስታን ክልላዊ መንግሥት፤ ከሕዝበ-ውሳኔው ማግሥት ወታደሮቹ በነዳጅ ከበለጸገችው የኪርኩክ ከተማ እንዲወጡ ተገደዱ፤ የአየር ክልሉም በኢራቅ መንግሥት ውሳኔ በኢራንና በቱርክ በመዘጋቱ ክልሉ የምድር ላይ ደሴት ሆነ፤ የወቅቱ የኩርዲስታን ፕሬዝዳንት የነበሩት ማሱድ ባርዛኒ በውርደት ሥልጣናቸውን ለቀቁ፡፡ የነፃ አገር ምሥረታው ጉዳይም ውሃ በልቶት ቀረ፡፡

ከኤርትራ እኩል እ.ኤ.አ. በ1991 ነፃነቷን ያወጀችው ሶማሌላንድ የራሷ ገንዘብ፣ ፖሊስና የተሻለ ዴሞክራሲያው አስተዳደር አሥፍና ለሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ ሰንብታለች፡፡ የራሷ የባህር በርና የተለየ የቅኝ ግዛት ታሪክ ያላት ሶማሌላንድ እንደ ‹‹አገር›› እውቅና ሊሠጣት የፈቀደ አንድም አገር ማግኘት አልተሳካለትም፡፡ የዋናው ሶማሊያ በጦርነት መታመሱ እንደ በጎ አጋጣሚ ሆኖላት ለሰላሳ ዓመት ጉልምስና የደረሰው ራስ-ገዝነቷም ከሌሎች አገሮች ጋር በወሳኝ ጉዳዮች ውል የመግባትና በተባበሩት መንግሥታትም ሆነ በሌሎች አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት የመሳተፍ ወግ ማዕረግ አላበቃትም፡፡

ዋናዋ ሶማሊያ ሰላሟ ተመልሶ፤ ጉልበቷም ፈርጥሞ ሶማሌላንድን ወደ ‹‹እናት አገሯ›› ለመመለስና የሶማሊያን ግዛታዊ አንድነት ለማስጠበቅ ብትሞክር ይህንን ከማድረግ የሚከለክላት አዲስ የሕግም የፖለቲካ እውነታም እስካሁን አልተፈጠረም፡፡
ከዚህ ሂደት ለየት ያሉ ሁለት ተሞክሮዎች እናንሳ፡፡ የካናዳዋ ኩቤክን ጉዳይ እናስቀድም፡፡ በ1995 የኩቤክ ክልል ነዋሪዎች ከካናዳ ጋር አዲስ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትብብር እንዲመሠረት መደበኛ ሀሳብ በቀረበበት ሁኔታ ኩቤክ ሉዓላዊ እንድትሆን ይስማሙ እንደሆነ ድምጽ እንዲሰጡ በኩቤክ ክልላዊ መንግሥት ተጠየቁ፡፡ 50.5 በመቶ የሚሆነው መራጭ ‹‹ሉዓላዊ›› መሆኑ ይቅርብን ብሎ ወሰነ፡፡ ሀሳቡ ውድቅ ሲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

የመገንጠል መብትን ባላካተተ ሕገ-መንግሥት በምትደዳረው ካናዳ እንዲህ ዓይነቱ ለጥቂት የወደቀ የአንድ ወገን የመገንጠል ሙከራ እንዲሁ በቀላሉ አልታለፈም፡፡ የተፈጠረው መደናገር የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአንድ ወገን የመገንጠል ሙከራውን በተመለከተ አስተያየቱን የሚያቀርብበት ሁኔታ ፈጠር፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባቀረበው ዝናው የናኘ ተጠቃሽ አስተያየትም የአንድ ወገን ህዝበ-ውሳኔው ሕጋዊ አለመሆኑን፣ ዓለማቀፉ የራስን ዕድል በራስ የመወስን መብትም ኩቤክን እንደማይመለከት፤ የኩቤክ ህዝብ በግልጽ የመገንጠል ሀሳቡን በማያወላውል ሁኔታ ከደገፈ ከዴሞክራሲ መርህ አንጻር የፌዴራል መንግሥቱ በግልጽ የቀረበውን የሕዝብ ፍላጎት ‹‹አላየሁም አልሰማሁም›› ብሎ እንደማያልፈው ተጠቀሰ፡፡ የፍርድ ቤቱ አስተያየት የሕዝቡ ውሳኔ መገንጠልን በቀጥታ ባያስከትልም በፌዴራሊዝም መርህ መሠረት የፌዴራል መንግሥቱና የፌዴሬሽኑ አባላት ወደ ድርድር እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑንም የጠቆመ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥቱ ባወጣው ሕግም ለሕዝበ-ውሳኔ የሚቀርበው ጥያቄ ግልጽና መገንጠልን ሳይቀባባ የሚያቀርብ እንዲሆን ይህም በፈዴራል ሕግ አውጭ ምክር ቤት እንዲረጋገጥ፣ የሕዝብ ድጋፍ 50 በመቶ መሙላቱ ብቻ በቂ ተደርጎ እንዳይወሰድ፣ የመገንጠል የመጨረሻ ውሳኔም ያለ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ እውን እንደማይሆን ተደነገገ፡፡ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በተለየ መልኩ የሚተረጉም ሕግ በኩቤክ ክልላዊ መንግሥት ቢወጣም ሌላ የህዝበ-ውሳኔ ባለመሞከሩ ምክንያት የሁለቱ ሕጎች መጣረስ ጉዳይ ሆኖ ሳይቀረብ ቀጥሏል፡፡ የአንድ ወገን የመገንጠል ውሳኔው ከ50 በመቶ በላይ ድጋፍ ቢያገኝ ኖሮ ኩቤክ ‹‹ነፃ ሉዓላዊ አገር›› ሊያደርጋት እንደማይችል ከፍርድ ቤቱ አስተያየትም ሆነ ከፌዴራል መንግሥቱ አቋም መረዳት ይቻላል፡፡ ነፃ አገርነቷን ዕውቅና ለመስጠት የሚከጅሉ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች ሊኖሩ ቢችሉ እንኳ የካናዳና የጎረቤቷ አሜሪካ ግፊት በኩቤካውያን በፌዴራል መንግሥቱ ያልተባረከ ፍች ላይ ቀዝቃዛ ውኃ የሚቸልስበት እንደሚሆን መገመት ስህተት አይሆንም፡፡

የስኮትላንድ ጉዳይ ለየት ካሉት ተሞክሮዎች የሚጠቀስ ነው፡፡ በመስከረም 2014 በተካሄደው የስኮትላንዳውያን ህዝበ-ውሳኔ የቀረበው ጥያቄ ቅልብጭ ያለ ነበር፡- ስኮትላንድ ራሷን የቻለች አገር ልትሆን ይገባል ወይ? ሕዝበ-ውሳኔው የተደራጀው በተደጋጋሚ የሚቀርብን የስኮትላንድ ብሔርተኛ ፓርቲ ፖለቲካዊ ጥያቄ ለማስተናገድና ጉዳዩን ከምርጫ መቅስቀሻ ነጥብነት ለመፋቅ ነው፡፡ በዩናይትድ ኪንግደምና በስኮትላንድ መካከል የተደረሰው ስምምነት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የስኮትላንድ ፓርላማ ከ2014 መጠናቀቅ በፊት ህዝበ-ውሳኔ ማደራጀት የሚያስችል ሕግ የማውጣት ሥልጣን በጊዜያዊነት የተሰጠበት ነው፡፡ ሕዝበ-ውሳኔው በ55 በመቶ ህዝብ ተቃውሞ ስለገጠመው ሳይሳካ ቀረ፡፡ የስኮትላንድ ፓርላማም በልዩ ሁኔታ ለአንድ ጊዜ የተሰጠው ሕዝበ-ውሳኔ የማደራጀት ሥልጣኑ 2014 ሲጋበደድ ተመልሶ ወደ ለንደን እጅ ገባ፡፡ በሕዝበ ውሳኔው በቂ ድጋፍ ተገኝቶ ቢሆንም እንኳ የስኮትላንድ አገርነት ከህዝበ-ውሳኔው ውጤት ባሻገር በብዙ ጉዳዮች የሚመሠረት ነበር፡፡ ለምሳሌ የራሷ ተገንጣይ ክልል የራስ ምታት የሆነባት ስፔን ስኮትላንድ ነፃ አገር የምትሆን ከሆነ የአውሮፓ ኅብረት አባል እንዳትሆን የማገድ መብቷን እንደምትጠቀምበት ማስታወቋ የሚነግረን የጉዳዩን ውስብስብነት ነው፡፡

ቀደም ብለው የቀረቡትና ሌሎች እጅግ በጣም ብዙ ምሣሌዎች የሚያሳዩት አንድ ነገር ቢኖር አሁን ባለው ዓለማዊ ሁኔታ መገንጠልና አገር መሆን እንዲሁ በቀላሉ የሚሳካ አለመሆኑን ነው፡፡ በአዲሱ ሚሊኒየም ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ጋር ባልተያያዘ ነፃ አገር ለመሆን የበቁትና እንደ አዲስ አገር ሰፊ ተቀባይነት ያገኙት አገራት ደቡብ ሱዳንና ምስራቅ ቲሞር ብቻ መሆናቸው የሚያስተላልፈው መልዕክት ጠንካራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ረገድ የሚካሄደው ውይይት የመገንጠልና የአዲስ አገር ምሥረታ ጉዳይን እጅግ አቃሎ የሚያቅርብና የ‹‹መቻሉን›› ጉዳይ ለአፍታ እንኳ ሳያነሳ ‹‹ይጠቅማልን/አይጠቅምምን›› የሚተነትን ሆኖ መገኘቱ እንግዳ ያደርገዋል፡፡ መገንጠልና አገር መሆንም እንደ በቀላሉ የሚሳካ መደበኛ የፖለቲካ ምርጫ ተደርጎ መቅረቡን ከተጠቀሰው ግልጽ ዓለምአቀፍ አጠቃላይ ዝንባሌ አንጻር ሲታይ ነገሩ ኮርኳሪ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ምናልባትም ይህ ዓይነቱ እንግዳ ተዋስኦ እንዲዳብር ምክንያት የሆኑ ሁለት ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ‹‹የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት›› ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የሀገራዊ አንድነት ችግር መፍትሔ ሆኖ ከተማሪዎቹ ንቅናቄ ጀምሮ በማርክሳዊ መንፈሱ በጥራዝነጥቅነት ሲቀነቀን መክረሙ፤ በሽግግሩ ቻርተርና በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት መካተቱ፤ ይህም አወዛጋቢው መርህ ከሌላው ዓለም በተነጠለ መልኩ ጥያቄ የማይነሳበት መደበኛ አሠራር ሆኖ የመታየት ዕድል እንዲያገኝ ማድረጉ ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት የኤርትራ መገንጠልንና የተሟላ አገር ሆና መውጣቷን በወሳኝነት ያሳኩት ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸው ተድበስብሶ (የኤርትራ የነፃነት ቀን የሚታሰበው በግንቦት 16 1983 መሆኑን ልብ ይሏል) አዲስ አገር ምሥረታው ለይስሙላ በተካሄደው የሕዝበ-ውሳኔና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተደርጎ መነገሩ፣ በቅርቡና በአቅራቢያችን ደቡብ ሱዳን አገር ሆና ብቅ ከማለቷ ጋር ተዳምሮ የፈጠረው ነው፡፡ በመቀጠልም በእርግጥ በአንቀጽ 39 መገንጠልና አገር ምሥረታ ዕውን የመሆን ዕድል ያለው አማራጭ ወይስ ሊተገበር የማይችል ‹‹ላም አለኝ በሰማይ›› ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቃል-ኪዳን መሆኑን መፈተሽ ነው፡፡
መገንጠል እንደ ‹‹መብት››?

የራስን ዕድል በራስ መወሰን መርህ (መገንጠልን የግድ ላያካት ይችላል/ውስጣዊ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ይሆናል ማለት ነው) ብዙ ውዝግቦችን የተሸከመ ጓዘ-ብዙ ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹መገንጠል›› የሚለው በግልጽ ሲታከልበት ደግሞ ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› ነው የሚሆነው፡፡ በዓለም ካሉ አገራት መካከል እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አፈጠጠር ያለው አንድም አገር የመገንጠል መብትን በግልጽ በሕገ-መንግሥቱ አካቶ አናገኘውም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን መብት በግልጽ ደንግገው የነበሩት አንድ ሁለት ኮሚኒስት አገራትንም ታሪክ ፈልጎ የሚያገኛቸው ከሙታን መንደር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመገንጠል መብትን በግልጽ ሕገ-መንግሥታዊ ዕውቅና በመስጠት ረገድ ከኛዋ ኢትዮጵያ በተጨማሪ የምትጠቀሰው ሌላ አገር የሁለት ሚጢጢ ደሴቶች ጥምረት የሆነችውና የሕዝብ ቁጥሯም አምሳ ሺህ ገደማ የሆነው ሴንት ኪቲስና ኔቪስ ብቻ ነች፡፡ በ2/3ኛ የሕዝብ ድምጽ ድጋፍ የሚፈጸመው ይህ መብት የተሰጠውም ከተጣማሪ ደሴቶች ለአንዷ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንዶች የመብት ሁሉ ቁንጮ፤ የዴሞክራሲያዊነትና የተራማጅነት ማንጠሪያ ፈተና ተደርጎ የሚቀርበው ‹‹የብሔረሰቦች የመገንጠል መብት›› እንደ ዋልያ በኢትዮጵያ ብቻ ተወስኖ የመገኘቱ ሁኔታ ርዕሰ-ጉዳዩን እንድናይበት የተገጠመልንን መነጽር አጽድተን በአዲስ ዕይታ በወፍ በረር የተወሰኑ ነጥቦችን እንድናነሳ የሚያደርግ ነው፡፡

‹‹የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት›› (People’s right to self-determination) የተ.መ.ድ. ቻርተርን ጨምሮ በተለያዩ ዝነኛ የዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት መሣሪያዎች ውስጥ የተካተተ ‹‹መብት›› መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ በአንጻሩ ይህንን መብት የደነገገው የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርና ሌሎች የድርጅቱ ውሳኔዎችም የአገራት የግዛት አንድነት (territorial integrity) የማይገስስና የዚህ መብት ትግበራም ከዚሁ በተቃራኒ በሆነ መልኩ እንደማይፈጸም ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም ከዚህ መርህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ቁልፍ ጥያቄ የመብቱ ባለቤት ተደርጎ የተጠቀሰው ‹‹ሕዝብ›› ማነው? የሚለው ነው፡፡

በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ የተዋወቀው የ‹‹ራስን ዕድል በራስ መወሰን›› በስታሊናዊ መንፈሱ የቀረበና ‹‹ህዝብ››ን ከ‹‹ብሔር/ብሔረሰብ›› ጋር ብቻ አጣብቆ የሚረዳ ይሁን እንጅ እንዲህ ዓይነቱ ጥብቅ ቁርኝት በሕግም በተግባርም ጎልቶ የምናየው አረዳድ አይደለም፡፡ በመሆኑም ‹‹የብሔር/ብሔረሰቦች›› ተብሎ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የተጠቀሰው መርህ ቢያንስ ስለዓለም አቀፍ ሕግ በምናወራበት ወቅት ‹‹የህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን›› መርህ ብለን ሰፋ ባለ መልኩ ዳግም ልንተዋወቀው ይገባል፡፡

መርሁ በዓለም አቀፍ ሕግ የያዘውን ግንባር ቦታ ያገኘበት ታሪካዊ ድባብና ዕድገትም ሌላው ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ የሚገባው ነጥብ ነው፡፡ መብቱ በዓለም አቀፍ ሕግ በመሠረቱ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ከተሸነፉ ትልልቅ ኢምፓየሮች ለተፈለፈሉ ትንንሽ አገሮች፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ከቅኝ ግዛት ነፃ ለሚውጡና በሌሎች አገራት አስገባሪነትና ብዝበዛ ሥር ለወደቁ ሕዝቦች ጋር የተያያዘ ቢሆንም በተወሰኑ እጅግ የተለዩ ሁኔታዎች በሌሎች አግባቦችም ተተግብሮ ያውቃል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ መርሁን የሻቱት ለመገንጠል ሳይሆን ላሳኩት መገንጠላቸው ምክንያት እንዲሆን ብቻ ነው፡፡

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ የፈረሱ ሶሻሊስት ኢምፓየሮች ስር የነበሩ ሪፐብሊኮች ነፃ የወጡበት ሁኔታ ከዚሁ መርህ ጋር ተያይዞ የሚነሳበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህም ሆኖ መርሁ ከላይ በቀዳሚነት ከተጠቀሱት ታሪካዊ አውዶች ውጭ ያለው ተፈጻሚነት በከፍተኛ ውዝግብ የተሞላ ነው፡፡ ዓለም ዓይነተኛ የሀገር-መንግሥታት ውቅር መሆኑም የአገራት ነባር ድንበር እንዲሁ በቀላሉ የማይለወጥ ሆኖ ከፍ ያለ ዋጋ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ የወላጅ አገሩ ሙሉ ፍቃድ ባልታከለበት ሁኔታ ሊደርግ የሚችል በመገንጠል የሚገለጽ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እንቅስቃሴ በስኬት የሚጠናቀቅበት ዕድል አነስተኛ ነው ብሎ ማለፍ ለሀሳቡ አጽንኦት መንፈግ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚሁ መርህ ጋር በተያያዘም ሆነ ሳይያዝ አዲስ አገር መመሥረትን ሙሉ በሙሉ ዝግ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ሕግ የዳበረ ባይመስልም ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ከባተ በኋላ ግን አዲስ አገር ምሥረታን ያረገዘው በራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ምትክ በአንድ አገር ውስጥ የውህዳንን መብት ዕውቅና የመስጠት ጉዳይ ተቀባይነቱ እያደገ መምጣቱ ግልጽ ነው፡፡

አገር መሆንንና አገር ሆኖ መታወቅን በተመለከተ ሁለት የታወቁ ኀልዮት አሉ፡፡ የመጀመሪያው አዲስ አገርን አገር የሚያደርገው ከሌሎች አገራት የሚያገኘው ዕውቅና ነው፤ በመሆኑም የአንድ አዲስ አገር አገርነት ከሱ ውጭ በሆኑ ነባር አገራት ችሮታ ላይ የተመሠረተ አድርጎ የሚያቀርብ ነው፡፡ ሁለተኛው ኀልዩት አገርነት መሬት ላይ ባለው ሀቅ አገር ሆኖ መገኘት ላይ የሚመሰረት መሆኑና ዕውቅና ማግኘትም ለዚህ እውነታ የሚሰጥ ይሁንታ ብቻ እንደሆነ የሚከራከር ነው፡፡ ግዛቱን በሚገባ የሚቆጣጠር፣ አስፈላጊውን መንግሥታዊ መዋቅር የዘረጋና አስፈላጊውን የህዝብ አገልግሎት ማቅረብ፣ ፀጥታን ማረጋገጥ መብትን ማስከበር የቻለ፣ ከውጭ ኃይል ተፅዕኖ የተላቀቀ የራሱ ነፃነት ያለው አካል እንደ አገር ሊቆጥር ይችላል እንደማለት ነው፡፡ የዕውቅና የማግኘት ሚናም የመባረክ ያህል ይሆናል፡፡ ምንም እንኳ አሁን አሁን የሁለተኛው አረዳድ በበርካታ የዓለም አቀፍ ሕግ ምሑራን ዘንድ የበለጠ ትክክል ሆኖ የሚታይበት አግባባ ጎልቶ ይታይ እንጅ በተግባራዊ ዓለም ግን የዕውቅና አስፈላጊነት ቁልፍ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩ አይካድም፡፡ ታይዋንን ከተባበሩት መንግሥታት የአምስቱ ኃያላን ወንበር አንስቶ ዲፋክቶ ሀገረመንግሥት ያደረጋት፤ ቤጅንግንም የቬቶ ፓወር ባለቤት ያላት ሉዓላዊ አገር ያደረጋት እውቅናና ፖለቲካ መሆኑ የዕውቅናን ሚና ዝቅ አድርገን እንዳናይ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረግ ሁሉ አቀፍ ዕውቅና መንፈግም የአገርነትን ወግ ማዕረግ ከማሳጣት የሚሻገሩ መዘዞችን የሚያስከትል መሆኑም የሚታበል አይደለም፡፡ የባህር በር አልባዋ ኢትዮጵያን፣ የቀንዱንና የአህጉሩን ፖለቲካ በሚገባ ለሚከታተል ሰው የዕውቅና ጉዳይ ምን ያህል ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው መታዘብ የሚቻል ነው፡፡

አንቀጽ 39 እና መገንጠል

መገንጠልን በቀላል ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸም የ‹‹ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› መብት አድርጎ የሚደነግገው አንቀጽ 39 ከሕገ-መንግሥታዊ ልማድ እጅግ ያፈነገጠ ከመሆኑ አንጻር አጨቃጫቂ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም፡፡ ይህ አንቀጽም ዝርዝር ሕግ ወጥቶለት፣ በተግባርም ተፈትሾ ስለማያውቅ በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ አንቀጽ 39ን ተማምነው ሰሞኑን በየሶሻል ሚዲያው ‹‹39›› ቁጥርን እየጻፉ ለሚዝቱት ዘማቾችም በእርግጥ አንቀጹ ሀጃቸውን የሚያወጣላቸው ለመሆኑ መልስ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በቅድሚያ ጉዳዩ የሕግ ጉዳይ የሆነውን ያህል ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መሆኑን ማውሳት ይገባል፡፡ አንቀጽ 39 በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት በቀላሉ የሚፈጸም መብት ሆኖ ይቅረብ እንጅ የፌዴራል መንግሥቱ የነቃ ድጋፍ ካልታከለበት መብቱ የሚተገበርበትም ሆነ አገር የሚመሠረትበት ዕድል ግመል በመርፌ ቀዳዳ የምትሾልክበትን ያሕል መሆኑ ጸሐፊው የሚጋራው የታወቀ እምነት ነው፤ የፌዴራል መንግሥቱ የነቃ ድጋፍ መኖሩ በራሱ ዕድሉን ሰፋ ያደርገው ይሆናል እንጅ በመሠረቱ ሁኔታውን ባይቀየረውም ቅሉ፡፡ በኢትዮጵያ የዳበረው ተዋስኦ በአንጸሩ ‹‹መብቱ›› አንዴ በሕገ-መንግሥት ከተካተተ በኋላ የአገር ክፋይ ሲገነጠል የፌዴራል መንግሥቱ በሀዘን ‹‹ግዴታ››ውን ከመወጣት በስተቀር ምንም ማድረግ አይችልም የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ ፌዴራል መንግሥቱ በሕገ-መንግሥቱ ያለበት ኃላፊነት በውስጣዊ ሉዓላዊነቱ የሚሸፈንና ዓለም አቀፍ ባህርይ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ቀለል ባለ አነጋገር የመገንጠል ጥያቄን መመለስ የክልል ጥያቄን ለመመለስ ከሚሰጠው ቦታ ያን ያሕል የከበደ አይደለም እንደማለት ነው፡፡

ጉዳዩ በመሠረቱ የውስጥ ጉዳይ ነው፡፡ በኩቤክ ጉዳይ እንደተጠቀሰውና የዓለም አቀፍ ሕግና ፖለቲካ እንደሚያሳየውም ከተወሰኑ በስተቀራዊ ሁኔታዎች ውጭ የታወቀ ግዛታዊ አንድነት ያለው የራሱን ዕድል በራሱ የወሰነ ነባር ሀገረ-መንግሥት ውስጥ አዲስ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መተግበር አለበት ተብሎ አይጠብቅም፤ ለዚህ ጠበቃም ሆኖ የሚቆም ደራሽ የውጭ ኃይል ሲኖር መነሻው ሕግ ሳይሆን ፖለቲካ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ የሚፈጠር ዓለም አቀፍ ግፊት የሚኖርበት አጋጣሚ አነስተኛ መሆኑን መጠበቅ ትክክል ነው፡፡

ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር የፌዴራል መንግሥቱ መገንጠሉን ለማስቀረት መብቱን በቀጥታ ሳይቃረን በተግባር ግን ሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፉን ጠብቆ መብቱ የማይተገበረትን ፖለቲካዊና ህጋዊ ሁኔታ መፍጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ብሔር ለመገንጠል ጥያቄ ቢያቀርብና ሌላ ጉረቤት ብሔር የግዛት ጥያቄ ቢያነሳ ይህን ጉዳይ በመፍታት ሂደት የመገንጠል ጉዳዩን ማዘግየት ይቻላል፡፡ መብቱ ለብሔር እንጅ ለክልል አለመሰጠቱን፣ የብሔር ‹‹ግዛታዊ አንድነት›› ጉዳይ ተቀባይነቱ አጠራጣሪ መሆኑም ሊነሳ እንሚችል ልብ ይሏል፡፡ የንብረት ክፍፍሉም በሀገር ቤት ሕግ የሚወሰን በመሆኑ መገንጠልን በተግባር በማይቻል መልኩ የንብረት ክፍፍል ህግ ማውጣት ይችላል፡፡ በቅርቡ በክልል ጥያቄ ላይ የተነሳውን የሕገ-መንግሥት አተረጓጎም በማንሳትም ይህን ጥያቄ ያቀረበው ስሙ በሕገ-መንግሥቱ ተጠቅሶ የሚገኝ ክልል (ብሔር ነኝ ብሎ መሆን አለበት ጥያቄውን የሚያቀርበው) ከሆነ ጉዳዩን የሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ አድርጎ በማቅረብ ጉዳዩን ቆልፎ በእንጥልጥል ማስቀረት ይቻላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅም (እንዲህ ዓይነት አዋጅ በቀጥታ አንቀጹን አይመለከትም)

ለመብቱ መተገበር በቅድሚያ መደረግ ያለባቸውን የመምረጥና መሰል መብቶች እንዲሁም የክልሉን ሥልጣኖች በማሟሸሽ የመገንጠል ሁኔታውን ማገት ይቻላል፡፡ አገር እሆናለሁ ያለው ብሔር አገር ከመሆኑ በፊት ጉዳዩን በሌሎች ፍርድ ቤቶች ወይም ገላጋዮች የሚያቀርብበት ዕድል ባለመኖሩ ጉዳዩን መልሶ ለፌዴራል መንግሥቱ ብቻ የሚያቀርብበት ሁኔታና ይህን መሰል ሁኔታ በገለልተኝነት የሚዳኝ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት አለመኖሩም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በመጠቀም ጉዳዩ በፖለቲካ ዓይን ለመጠዘዝ ይቻላል፡፡

የመገንጠል ጥያቄን የሚያነሳ ብሔር በቀላሉ ቅድመ-ሁኔታዎችን አሟልቶ የአገር ውስጡን ጣጣ በቀላሉ ሊፈጽም ቻለ ብለን ግምት ብንወስድ እንኳ የቀረው የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን አዲስ አካል እንደ አገር ዕውቅና የመስጠት ግዴታ የለበትም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የመወሰን መብት ለወላጅ አገሩ መንግሥትና ሕዝብ የተተወ ነው፡፡ የተፈጠረውን አዲስ አካል ዕውቅና የመንፈግና ሌሎች አካላትም ያንኑ እንዲያደርጉ የዲፕሎማሲ ጫና በማሳደር የአገርነት ህልሙን ማጨናገፍ የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ የኤርትራ ነፃ አገር በምትሆንበት ወቅት ከኢሳያስ በላይ ለኤርትራ ‹‹ነፃነት›› ቆሚያለሁ የሚል መንግሥት አዲስ አበባ ላይ ፊጥ ባይል ኖሮ ሁኔታው እንደሆነው አልጋ ባልጋ እንደማይሆን አንዳንድ ወሳኝ አገራት ከኢትዮጵያ ጎን ለመቆም ነበራቸው የተባለው ፍላጎት ጠቋሚ ነው፡፡ በታሪክ የመገንጠል መብትን አካተው የነበሩ አገራት የፈረሱትና አዳዲሶቹ አገራት የተወለዱበት ሁኔታ ከ‹መብቱ›› ይልቅ በሌሎች ወሳኝ የፖለቲካ ሂደቶች ምክንያት መሆኑም የመገንጠል አንቀጹን ፋይዳ የሚያጣጥል ነው፡፡

በተለይም በአዲሱ ሚሊኒየም አዲስ አገር የመቀበል አፒታይቱ ከተዘጋው የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ባሻገር ኢትዮጵያ ባለችበት ቀጠናና አህጉር ብሔርን መሠረት ያደረገ የመንገንጠል እንቅስቃሴ ካዘለው የአፍሪካ አህጉርን የሚያፈርስ የዶሚኖ ውጤት አንጻር እንደ ነውር የሚታይ መሆኑ በዚህ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሔሮች ወሰን ዘለለ መሆናቸውም እያንዳንዱ የሚፈጠር አገር ለጎረቤት አገራት ሌላ የግዛት ጥያቄ ስጋት የሚፈጥር መሆኑ ለአገር ምሥረታው ፊት መነሳት የራሱ ድርሻ አይጠፋውም፡፡ የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ የነበራቸው ወሰን ተከብሮ እንዲቆይ በመመሥረቻ ሰነዳቸው በማያወላውል ሁኔታ ማስቀመጣቸውም ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ነው፡፡

የደቡብ ሱዳንና ኤርትራ አገር ሆኖ መውጣት የቻሉበትን ሁኔታ የመረመሩት ካትሪና ሩዲንኮቫ የተሰኙ ምሑር በአፍሪካ ውስጥ ሉዓላዊ አገር ሆኖ ለመውጣት ሁለት ጉዳዮች ወሳኝ መሆናቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ እነሱም ከቅኝ ግዛት ወቅት ጋር የተያያዘ የግዛትነት ታሪክና የወላጅ አገር በጎ ፍቃድ ናቸው፡፡ የሁለቱ አገሮች አገርነት አህጉሩንም ሆነ ሰፊውን ዓለም ካማረረ ለአሥርት ዓመታት የዘለቀ ጦርነት በኋላ የተሳካ መሆኑና አገር መሆናቸው ያመጣል ተብሎ የተገመተው ሰላምና እረፍትም ለአገር ምሥረታው ያደረገው አስተዋጽኦ የሚናቅ አይደለም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ እንገንጠል የሚሉት አካላት ሁለቱንም ወሳኝ ቅድመ-ሁኔታዎች አሟልተው ሉዓላዊ አገር የሚሆኑበት ዕድል እንደሌለ ለማንኛውም ሚዛናዊ ታዛቢ የሚታይ ነው፡፡

ከቀደመው መረዳት እንደምንችለው በህወሓት የተፃፈው ሕገ-መንግሥት እንግዳ በሆነ መልኩ የመገንጠል አንቀጽን ያካተት ቢሆንም ይህ አንቀጽ አዲስ አገር ለመመሥረት ሕጋዊና ፖለቲካዊ መደላድልን በማመቻቸት ረገድ ያለው ፋይዳ በፌዴራል መንግሥቱ በጎ ፍቃድ የተመሠረተ መሆኑና ይህ በጎ ፍቃድ በተገኘበት ሁኔታም አሁን ባለው ዓለምአቀፍ ፖለቲካና የኢትዮጵያ መልካዓምድራዊ አቀማመጥ አንጻር የህልሙ መሳካት አጠያያቂ ነው፡፡ መገንጠልና አዲስ አገር ምሥረታ በመሠረቱ በአንድ አገር የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ብቻ የማይሳካ የመሆኑን እውነታ ይዘን ስንመለከተው ሕገ-መንግሥቱ የማይሰጠውን እሰጣለሁ የሚል ጉረኛ አንቀጽ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በመሆኑም አንቀጽ 39 ተገንጥሎ አገር በመሆን ቀቢጸ ተስፋ ተማምኖ ድንጋይ ሲወረወርም ርችት ሲተኮስም፣ በትንሹም በትልቁም ሰበብ እየፈለጉ ‹‹አንቀጽ 39››ን እየጠሩ ዘራፍ ከማለትና የመሳካት ዕደሉ ጠባብ ለሆነ የአገር ምሥረታ ፕሮጀክት ሀይልና ጉልበት ከማፍሰስ ይልቅ ከመገንጠል በመለስ ያሉ በርካታ ዕድሎችን አጣጥሞ ለመጠቀም ሙሉ ሀይልን ማዋል የብልህ ውሳኔ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የቀረበውን ሀተታ በመመሥረትም የትግራይ ዲ ፋክቶ ሀገረ-መንግሥትነት ‹‹ውጥን›› ጉዳይን በቀጣይ ጽሑፍ እንቃኛለን፡፡

2 thoughts on “ዲፋክቶ ወይስ ድንፋታ: አንቀጽ 39 እና ሀገር ምሥረታ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡