ህወሓት በቀጣይ የሚወስዳቸው እርምጃዎች እና አማራጭ መንገዶች

ከውህድ ፓርቲው ምስረታና ቀጣይ ተግባራት ጋር በተያያዘ ህወሓት የለመደውን የበላይነት፣ ይሁንታና ስልጣን መልሶ ለማግኘት የተለያዩ ነገሮችን በመተግበር እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። እንደሚታወቀው የውህድ ፓርቲው ምስረታ እንደ ጣዖት የሚያመልኩት መለስ ዜናዊ በህይወት በነበረ ወቅት በተካሄዱት የኢህአዴግ ጉባኤዎች የተመከረበትና በራሳቸው በህወሓት ሰዎች ጥያቄው የቀረበና እነ ስዩም መስፍን ሳይቀር ፍላጎታቸውን ያንፀባረቁበት ነበር። ይሁንና ከመለስ ሞት በኋላ በነበሩ የድርጅቱ አካሄዶች ቀደም ሲል ጀምረው የታቀዱና የተተገበሩት መተካካትን ጨምሮ ሌሎች አንዳንድ የድርጅት አቅጣጫወች ውሀ በልቷቸው ቀረ። መተካካቱንም ከመለስ ሞት በኋላ የራሱ የህወሓት ሽማግሌወች ጥሰውት ከፊት ተሰለፉ፤ የተጀመረው የውህደት ሀሳብም በየጉባኤው እየተነሳ ሳይፈጸም በጠ/ሚ ዓቢይ ዘመን ወደ አፈጻፀም ተቀይሮ ዛሬ ላይ ለመድረስ በቃ።

ፀሃፊ:- ብሩክ ሲሳይ

መረዳት እንደሚቻለው ከመለስ ሞት በኋላ ቀደም ብለው የተቀመጡ ድርጅታዊ አቅጣጫወች ውሀ የበላቸው፤ ከድርጅት አባላቱ ፍላጎት ይልቅ በግለሰቡ አምባገነናዊ ባህርይ ተጸእኖ ምክንያት የራሱን ፍላጎት ሲጭንባቸው ሳያምኑበት ስለተቀበሉት ለመሆኑ ይጠቁማል። የሆኖ ሆኖ መተካካቱ በተለይ በህወሓት ቤት ውሀ ቢበላውም ግን የአንድ ወጥና ኅብረ ብሄራዊ ፓርቲው ምስረታ ግን በአዲሱ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ብርታትና በአጋር ፓርቲወች ድጋፍ እውን ለመሆን ችሏል። ህወሓት ድሮ ከራሱ ፍላጎት ጥያቄ ሲያቀርብበት የቆየውን የአንድ ፓርቲ ምስረታ ጉዳይ አሁን የሚቃወምበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን በእኛ ፍላጎት፣ በእኛ የበላይነት፣ በእኛ መልካም ፍቃድና አቅጣጫ መሆን አለበት የሚል የእብሪትና የተለመደ አምባገነናዊ ሁሉን አድራጊ ባህርያቸው የተነሳ ነው።
.
የህወሓት አመራሮች የትግራይን ሕዝብም ሆነ ሌላውን በማስመሰል ለማታለል አርባ ምክንያት ቢያቀርቡም ውህደቱና የኅብረ ብሄራዊ ፓርቲው ምስረታ ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያመጣው ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። እነሱም ሰበብና ውሸት ከማብዛት በቀር ይህ ነው የሚባል ውሀ የሚቋጥር አንድ ተጨባጭ ምክንያት የላቸውም። በእርግጥ በአሁኑ ሠዓት ህወሓት ከአባሉና ከማዕከላዊ ኮሚቴው በተጨማሪ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ጭምር የውህደቱን ሀሳብና የኅብረ ብሄራዊ ፓርቲ ምስረታውን በተመለከተ ደፍረው ፊት ለፊት ወጥተው መናገር ባይችሉም የሚደግፉት እንዳሉ የተረጋገጠ ነው። ፊት ለፊት ወጥተው ደፍረው እንዳይናገሩ ያደረጋቸውም የድርጅቱ አባላቱ ጫና ሳይሆን እንደ ጌታቸው አሰፋ፣ ስብሀት ነጋ ዓይነት ግለሰቦችን በመፍራት ነው።
.
ህወሓት በአሁኑ እየተንቀሳቀሰ ያለው እንደ ድርጅት በአመራሩ፣ በደጋፊውና አባሉ ፍላጎትና አቅጣጫ ሳይሆን በግለሰቦች በተለይም ደግሞ በጌታቸው አሰፋ ፍላጎትና አቅጣጫ ብቻ ነው። ጌታቸው አሰፋ ደግሞ ለምን ከሥልጣኔ ተነሳሁ፣ ለምን ላለፉት ዓመታት ጥፋቶች ሁሉ ተጠያቂ ወንጀለኛ ተብዬ ለምን ተከሰስኩ፣ ለምንስ የለመድነውን ነገር እናጣለን የሚል ነው። የሚያሳዝነው ነገር መላው የትግራይ ሕዝብ በአንድ ፈላጭ ቆራጭ ግለሰብ ፍላጎት ምክንያት ብቻ እየታመሰ መቆየቱ ነው። የሆኖ ሆኖ በአንድ ሰው ፍላጎትና ሀሳብ እስከ መቼ ሌላው ሳያምንበት ሊቀጥል ይችላል የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም በግለሰቦች መዳፍ ስር የገባው ህወሓትና የትግራይ ክልል መንግስት ግን በቀጣይነት ሊያደርጓቸው የሚችሉ ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴወችን ጨምሮ ሊከሰቱ የሚችሉ ሁነቶችና የህወሓት አማራጮች ምንድን ናቸው የሚለውን እንደሚከተለው አብራራለሁ።
.

☞ ህወሓት ከሁለት የመሰንጠቅ አደጋ ይገጥመዋል

እንግዲህ በድርጅት ውስጥ ያሉ ሰወች በሙሉ ሁሉም በአንድ ሳምባ የሚተነፍሱና ተመሳሳይ እሳቤ ያላቸው አይደሉም። አይደለም በድርጅት ውስጥ ያሉ ሰወች ይቅርና ወንድማማቾቹ አውአሎም ወልዱና አባይ ወልዱ በ1993ቱ የህወሓት ክፍፍል በተቃራኒ ቆመው እስከ መጠፋፋት ሁሉ የሚፈላለጉ ነበሩ። በመሆኑም ህወሓት እንደ ድርጅት ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ በእነ ጌታቸው አሰፋ፣ ስብሀት ነጋና በሌሎች ተስፋ የቆረጡ ሰወች ፍላጎት ብቻ ተወስኖ መንቀሳቀሱ አልዋጥላቸው ያሉ አመራሮች እንደ ድርጅት በህወሓት እንደ ክልል ደግሞ በክልሉ መንግስት ላይ ሊመጣ የሚችለው አደጋና ኪሳራ አርቅው በመመልከት በማዕከላዊ መንግስትና በውህዱ ፓርቲ ድጋፍ ከእነዚህ አድራጊ ፈጣሪ ግለሰቦች ተጽእኖ ነጻ ወጥተው ድጋፍ አሰባስበው ድርጅቱን ሊታደጉ ይችላሉ።
.
በዚህም ምክንያት የቡድንና የጎራ መለያየት ስለሚፈጠር ማዕከላዊ መንግስቱም ዝም ብሎ ስለማይመለከት ሁለት የህወሓት አንጃ ይፈጠራል። አንደኛው አንጃ የማዕከላዊ መንግስትና የውህድ ፓርቲው ድጋፍ ስለሚኖረው መጀመሪያ ላይ ደፍሮ ለመውጣት ቢከብደውም በሂደት ግን ድጋፍ እስካገኘ ድረስ አሸናፊ መሆኑ አይቀርም። ሁኔታውን በአስተውሎትና በጥሞና የሚመለከተው ሌላው አመራር፣ አባልና ደጋፊውም በሂደት አዲሱን ቡድን መደገፉ አይቀርም። ይህ እንደሚከሰት ደግሞ ከወዲሁ ጠቋሚ ምልክቶች ያሉ ሲሆን ከህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮምቴወች በግልጽ ባይሆንም በግለሰብ ደረጃ የውህደቱን ሀሳብና የጠሚ ዓቢይን የለውጥ እርምጃ የደገፉ ሰወች እንዳሉ ከታማኝ የመረጃ ምንጭ ሰምቻለሁ። በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ሀሳብ ያላቸው ሰወች ካሉ ወደታች ስንወርድ ደግሞ በርካታ ሰው እንደሚገኝ ምንም አያጠራጥርም። በመሆኑም የዋናው የአዲሱን ፓርቲ ድጋፍና በማዕከላዊ መንግስት ደረጃ የሚኖረውን ተጽእኖ በመጠቀም አልለወጥም ያለውን አፋራሹን ቡድን አሸንፎ በመውጣት ወይም ደግሞ በድርድር የውህድ ፓርቲውን ሀሳብ እንዲቀበሉ በማድረግና በሰጥቶ መቀበል ሂደት ህወሓት የብልጽግና ፓርቲን ይዋሃዳል። በዚህ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ለብቻው መተንተን የሚቻል ቢሆንም ለአሁኑ ልለፈው።
.

☞ የ defacto statehood ጉዳይን አጠናክሮ በተለመደው አፍራሽ መንገድ መሄድ፣ ከኤርትራ ጋር ጦርነት መግጠም

Defacto statehood የሚባለው ነገር ቅዠት ካልሆነ በቀር ከህግ አንጻር በህገ መንግስቱም ሆነ በዓለም አቀፍ ህግጋቶች አልያም ደግሞ በትግራይ ሕዝብ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም ከተቃዋሚ የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲወች ፍላጎት አንጻር የማይሳካና ለወሬ የማይበቃ ነገር ነው። የፖለቲካ ነገር የሚሆነው አይታወቅምና ህግም ባይፈቅድ፣ ሕዝቡም ባይፈልግ አሁን እያደረጉት እንዳለው ከፍተኛ የሆነ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት በወኪሎቻቸው በኩልና በራሳቸው እንቅስቃሴ በመላ አገራችን ግጭትና ትርምስ በመፍጠር የማዕከላዊ መንግስቱን ቅቡልነት ለማሳጣት በርትተው ይሰራሉ። ይህን ትርምስና ግጭት ሊያስቆም የሚችለውንና ለአገር አንድነት ዋስትና የሆነውን መከላከያ ሰራዊቱን ደግሞ በወኪሎቻቸውና በራሳቸው ሰወች አማካኝነት በብሄር በመከፋፈል ውጥረት ፈጥረው የተለያዩ አደጋወችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ይኼ ትርምስና ግጭት ከመከላከያ ሠራዊቱ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን በማድረግ ዓለም አቀፍ ሰላም አስጠባቂ ሰራዊት እንዲገባና ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት እስከ መጠየቅ የሚያደርሱ ነገሮችና ሴራወችን ይተገብራሉ። በተለይም የአዲሱ ፓርቲ አመራር እንዲከፋፈል ለማድረግ አማራና ኦሮሞውን፣ አፋርና ሶማሌውን የሚያጋጭ ብሄር ተኮር ትርምሶችና ግጭቶችን ይፈጥራሉ። ይሄንም ያላቸውን ሀብትና ገንዘብ በመጠቀም በየአካባቢው በሚገኙ ወኪሎቻቸውና የአጀንዳ ተጋሪወቻቸው በኩል በደምብ ያስፈጽማሉ።
.
የዓለምአቀፍ ትኩረት እንዲሰብና ጣልቃ ገብነት ጭምር እንዲኖር እንደ ታላቅ ስጋት ከሚቆጥሩትና ከሚፈሩት በኤርትራ መንግስት ላይ ጦርነት ይከፍታሉ። የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄን መንግስት ለመጣልና የእነሱ ደጋፊ የሆነ መንግስት በኤርትራ ለመፍጠር ከወዲሁ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ አዛዦችን በገንዘብና በሀብት እየደለሉ እንደሆነ መረጃወች ይጠቁማሉ። ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በተለያየ ምክንያቶች ቅሬታ ያለባቸውን ወታደራዊ አዛዦችና የደህንነት ሰወች እንዲሁም ሌሎች ለውጥ በመፈለግ ብቻ የተስማሙ ወታደራዊ ሰወችን በገንዘብ የመደለልና ከእነሱ ጎን የማሰለፉን ሥራ በስፋት ሲንቀሳቀሱበት የነበረ ጉዳይ ሲሆን ያመጣላቸውን ውጤት ለማወቅ አይቻልም። በአንጻሩ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግስት እንቅስቃሴያቸውን በትኩረት ስለሚከታተልና ስለሚያውቅ ምልክት ያየባቸውን ነገሮች በየጊዜው እያስተካከለና እርምጃ እየወሰደ በመሆኑ በዚህ በኩል የሚሳካላቸው ለመሆኑ አጠራጣሪ ነው። የሆኖ ሆኖ ወጣም ወረደ በኤርትራ ላይ ጦርነት መክፈትና በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ በመላ አገሪቱ ትርምስና የእርስበርስ ግጭት በማድረግ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ አስፈላጊነት በመረዳት ጣልቃ እንዲገባና ድርድር አልያም ሌላ እነሱን ሊጠቅም የሚችል ነገር እንዲያደርግ ጫና ይፈጥራሉ።
.

☞ ውህድ ፓርቲው በህግ ቅቡልነት እንዳይኖረውና አጋሮችም እንዲያፈነግጡ ማድረግ ፤ ከመስከረም በኋላ ኢህአዴግመወ ጠቅላይ ሚኒስተሩም ስልጣናቸው ስለሚያበቃ ህጋዊ አይደሉም ሊሉ ይችላሉ

አዲሱ የብልጽግና ፓርቲን ህጋዊ ቅቡልነት ለማሳጣት የህግ አግባቦችን እንደምንም በመፍጠርና የክስ ሂደቶችን በማስቀጠል በማዕከላዊ መንግስቱና በአዲሱ ፓርቲ አመራር ላይ ጫና የመፈወጠር እንቅስቃሴወችን ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት በአንድ በኩል ጊዜ በመግዛት አሁን ስምምነት ላይ የደረሱት አጋሮችና የኢህአዴግ ግምባር እንዲፈራቀቁ የተለያዩ ፖለቲካዊ ሴራወችንና ክፍፍሎችን ለመፍጠር ነው። ከህግ አንጻር ውህዱ ፓርቲ የቅቡልነት ጉዳይ የሚያሰጋው ነገር ባይሆንም ህወሓት ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ ከአዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ደኢህዴንና ከአጋሮቹ በእያንዳንዱ የውህደቱ ተቃዋሚ ቡድን በመፍጠር የህግ ጉዳይን በማንሳት የክስ ሂደት እንዲጀምሩ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። ውህዱ ፓርቲ አገር ለመምራት ህጋዊነት የለውም፤ በምርጫ የተመረጠው ኢህአዴግ እንጂ አዲሱ ፓርቲ አይደለም በማለት ኢህአዴግ ደግሞ ከግንቦት በኋላ ስልጣን ስለሌለው ጠሚ ዓቢይ ህጋዊ ጠቅላይ ሚኒስተር አይደሉም። በህግ ዘንድም ተቀባይነት የላቸውም፤ ህጋዊነታቸውም አብቅቷል ይላል። ይሁንና እነዚህ ነገሮች ከህግ አንጻር አሳሳቢ ባይሆኑም ለጠቅላይ ሚኒስተሩ የሚያሰጋ ባይሆንም ለጊዜው ግን ከፕሮፖጋንዳ ጋር ትርምስ ይፈጥሩበታል።
.
እነዚህን ሁሉ ተግባራት የሚያደርጉት በጎን ትርምስና ግጭቶችን በመፍጠር፣ በመላ አገሪቱ አስቀያሚ ድባብ እንዲፈጠር በማደረግ፣ የማዕከላዊ መንግስቱ አቅምየለሽ ወይም ደግሞ የአንድ ወገን ጉዳይ አስፈጻሚ እንደሆነ ቅስቀሳ በመስራት፣ ሕዝቡ ከሚፈልገው ወሳኝ የፖለቲካ ሽግግርና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ይልቅ ተስፋ ቆርጦ የሰላምና የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ብቻ እንዲያሳስበው በማድረግ ያለፈውን የ27 ዓመት የህወሓት የበላይነት ዘመን እንዲመኝና የታሰበው የፖለቲካ ሽግግር በአፍንጫዬ ይውጣ እስከማለት ድረስ እንዲሰማው በማድረግ ነው። ሕዝቡ በዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ሲገባላቸው ከተለያዩ አካላትና ከድርጅቶችም ጭምር ሰወችን በቀላሉ ለመደለል፣ በገንዘብ ለመግዛት አመቺ ሁኔታና እነሱ ይሻላሉ የሚል ሁኔታ እንዲፈጠር ይረዳል። ይኼ ከቀጠለም ለዘመናት ሲፈጽሙት የነበሩት ወንጀል፣ ሴራ፣ ሌብነትና ዘረፋ ተረስቶ ከእነሱ ጋር መስራትና መንቀሳቀስ ከነውርነት ይልቅ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችል ሁኔታ ስለሚፈጥር በቀላሉ ዓላማቸውን ያሳካሉ። ይህም ያለፈው ዘመን የፖለቲካ፣ የፓርቲ፣ የመንግስት አደረጃጀት ለውጥ ሳይኖረው እንዲቀጥል በር ይከፍታል። ምርጫውንም እነሱ በሚፈልጉት መልኩ ሊያስኬዱት ይችላሉ።
.

☞ ህወሓት ከሌሎች ፓርቲወች ጋር ግምባር በምፍጠር፤ በትግራይ ክልል ብቻ ምርጫ አደርጋለሁ ሊል ይችላል

ህወሓት አንድ ዕቅድ ብቻ ሳይሆን በርካታ ዕቅዶችና አማራጮችን ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው። ከእነዚህ እቅዶቹ አንደኛው ከዚህ በፊት መቀለ ላይ ሰብስቦ ጉባኤ በማድረግ አብረው ለመስራት አስተባባሪ ኮሚቴ መርጦ ከተለያየው ድርጅቶችና ቡድኖች ሌሎች በሂደት የሚጨመሩትን በመጨምር ሌላ ግምባር ፓርቲ መፍጠር ነው። በእርግጥ በዚህ ረገድ ሊመሰርቱት ያሰቡትን የፓርቲውን ፕሮግራምና ደምብ አዘጋጅተው ጨርሰዋል። ይሄን ግምባር ከመሰረቱ በኃላ ማዕከላዊ መንግስቱ ላይ ጫና በመፍጠር ምርጫውን እንዲካሄድ ግፊት በማድረግ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ሥራ ይሰራሉ። በዚህ ረገድ ከተለያየ ብሄር አክትቪስቶችና አክራሪ ቡድኖችን አብረው በማሰለፍ የመረጃ ልውውጥ ጦርነቱ ላይ ብልጫ ለማግኘት ወጥረው ይሰራሉ። ማዕከላዊ መንግስቱ በብዙ መልኩ ከህግ አንጻር ቅቡልነትና ስጋት የማይፈጥሩበት ዕድሎች ስለሚኖሩት ምርጫውን በተፈለገወወ ጊዜ የማያካሂድ ከሆነ ህወሓት በትግራይ ክልል ብቻ እንደ ተቃዋሚ አድርጋ ከፈጠረቻቸው ከመሰሎቿ ባይቶናና ሌሎች መሰል ፓርቲወችን ሰብስቦ በትግራይ ክልል ብቻ ምርጫ አደርጋለሁ ብላ መንቀሳቀሷ የማይቀር ይሆናል። ይህን ለማድረግም ከወዲሁ እየተዘጋጁበትና ምልክት እያሳዩበት ነገር ነው። ከህግ አንፃር እንደማያስኬዳቸው ቢታወቅም ሌሎች ጫናወችን በተጓዳኝ በመፍጠር ፈተና እና መሰናክሎችን በማብዛት የሚችሉትን ሁሉ አቅም ተጠቅመው ይሞክሩታል።

እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ሊያደርጓቸው የሚችሉ እንቅስቃሴወች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አነጣጥረው ያሉት አንድ ዓላማ ላይ ነው። ይኼውም ለአለፉት 27 ዓመታት ያለ ተጠያቂነት ፈላጭ ቆራጭ ሆነው እንደፈለጉ ሊዘርፉ፣ ሊመዘብሩ፣ ሊገድሉ፣ ሊያስሩ፣ ሊያፈናቅሉ፣ ሊያሰደዱ ያስቻላቸውን የበላይነት ሊያስገኝላቸው የቻለውን ስልጣን መልሰው መቆጣጠር ነው። ስልጣኑን መልሰው ካልተቆጣጠሩት እንኳን በድርድር፣ ስጋት በመሆን፣ በጫና ለእነሱ የሚጠቅመው አሮጌው የጥፋት መንገዳቸው መዋቅሩ፣ አደረጃጀቱ፣ አስተሳሰቡ እንዲቀጥል ማድረግና ሳይታሰሩ፣ ተጠያቂ ሳይሆኑ ጥቅማቸውን አስጠብቀው መቆየት ነው። እነዚህን ከላይ የተቀመጡትን አካሄዶች በተናጠል፣ ጎን ለጎን አልያም ሁሉንም በአንድ ላይ ሊተገብሯቸውና ሊሞክሯቸው የሚችሉት ነገሮች ናቸው።