ለውጥ እና የፖለቲካ ሽኩቻ!

ፀሃፊ፦ መሀመድ ይማም እንድሪስ ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ

(ይህ ፅሁፍ መጀመሪያ የታተመው ፍትህ መፅሔት ላይ ነው)

ለለውጥ የተከፈለው መስዕዋትነት ፍሬ ወደ ማፍራቱ መሸጋገሩን ያበሰረው በጥቅምት 2010 የተካሄደው የኦሮሞ እና አማራ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ በባህር ዳር የተካሄደ ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በፖለቲከኞቹ መካከል ጥሩ መናበብ እና መግባባት መኖሩን ያሳየ ነበር፡፡ በወቅቱ ፍቅር አዋቂ እና እንግዳ አክባሪ የሆኑት ጎጃሞች ከደጀን አባይ ጀምረው እንግዶቹን እንኳን ወደ አገራችሁ ወደ ቤታችሁ መጣችሁ እያሉ ደማቅ አቀባበል እና መስተንግዶ አድርገውላቸዋል፡፡ በባህር ዳር በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ ኦቦ ለማ መገርሳ እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ያደረጉት ንግግር ሀሴት በልብ ውስጥ አጭሮ የብዙዎች እንባ በጉንጫቸው ላይ ፈስሶ ነበር፡፡ አቦ ለማም አትዮጵያዊነት “ሱስ” ነው፤ ኢትዮጵያዊነት በደም እና በልብ ውስጥ የታተመ በነጻነት ሲኖሩት የሚያምር ማንነት ነው አሉ፡፡ አቶ ገዱም በየቦታው ላለው ችግር ስር መሰረቱ በፖለቲካችን ውስጥ የሰፈነው ከፋፋይ የሆነ ነቀርሳ አስተሳብ ነው፤ እርሱ ነው መነቀል ያለበት ብለው ታዳሚውን አስደመሙት፤ ጭበጫበው ቀለጠ፡፡ በዚያን ቀን ብዙ ሰዎች ላይ የታየው ደስታ እና ተስፋ ወደር አልነበረውም፡፡ ከዚህ ሁነት በኋላ በታህሳስ ወር ኢህአዴግ የአስራ ሰባት ቀን የዝጉብኝ ስብሰባ አካሂዶ የአራቱ ፓርቲዎች መሪዎችች መግለጫ ሰጡ፤እንዲህ እንዲህ እያለ ሐይለማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቂያ አሰገብተው፤ ከዚያ ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ካመጥተው ለውጡ በአዲስ መንፈስ ሀ ብሉ የተጀመረ መሰለ፡፡ የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስቴር ንግግር ብዙዎቻችን አደነቅነው፤ ችግራችን፣ መሻኮታችን እና የወየበው የፖለቲካ አስተሳሰባችን ብን ብሎ ሲጠፋ ታዬን፤ ህልም የሚመስል ነገር ተከስቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የሴራ ፖለቲካ እና ትንታኔ አየሩን ሲቆጣጠሩት ግን ጊዜ አልወሰደባቸውም፤ የመስቀል አደባባይ ክስተት፣ የእንጂነር ሰመኘው ግድያ እና ጫፍ ረገጥ የፖለቲካ ሀይሎች የፖለቲካውን ምህዳር ሲቆጣጠሩት የለውጡ ሂደት ብልሽት እንደገጠመው በግልጽ መታየት ጀመረ፡፡ የለውጡ ፊት አውራሪ ያልናቸው ሰዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ፤ በኦሮሚያ ኦነግ እና ደጋፊዎቹ የበላይነቱን የያዙ ሲመስል፤ አማራው ደግም የቀድሞ የአማራ ነገስታትን የአይበገሬነት እና የድል ተምሳሌት አደርጎ ብሄርተኝነቱን አሟሟቀ፡፡አማራ የኢትዮጵ ፈጣሪ ስለሆነ ኢትዮጵያ ልታከብረው የሚገባ ህዝብ ነው፤ አሁን ግን ኢትዮጵያዊነት አትዮጵያዊነት የምትለዋ ነገር አማራን ዳግም ለማደንዘዝ የተዘየደች ናት፤ ብቸኛ መዳኛችን ኦሮማራ ሳይሆን በራሳችን መደራጀት ነው የሚሉ እና ሌሎች ድምጾችም ተሰሙ፡፡ እነ አቶ ገዱንም ሕወሐት ላነበረው ጭቆና ተባባሪ ነበራችሁ የሚለው ወቀሳ ከክልሉ ስልጣን አራቃቸው፡፡ በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ የተሰበከው አማራ ጠል ፖለቲካ በአማራ ህዝብ ላይ የሕልውና ስጋት ደቅኗል የሚለው ሀሳብ የአማራ ፖለቲካ የሚዘወርበት አንጓ ተደርጎ ተወሰደ፡፡

በመስከረም/ጥቅምት 2011 የተካሄደው የሚንስትሮች ሹመትን ተከትሎ ደግሞ አደፓ ተመቷል፤ አማራ ተገልሏል እና አጠቃላይ ለውጡ ወደ አንድ ወገን አዘንብሎ የአሮሞ የበላይነትን እና ተረኝነትን ለማስፈን መደላድል እየተሰራ ነው የሚለው ሀሳብ የተንታኞችን ቀልብ ሳበ፡፡ በሂደቱም ልሂቃንን አባድኖ ለጦፈ ክርክር እና ጥርጣሬ በሩን ወለል አድርጎ ከፍቶ የለውጥ ሀዋሪያዎቹ ድምጽ እና ፍላጎት ከነመፈጠሩ ከመድረኩ ጠፋ፡፡ የህግ በላይነት ተሸረሸረ፤መንግስት ርምጃ መውሰድ አቃተው፣ አድሎአዊነት ማቆጥቆጡ እና ፖለቲካውም መያዣ መጨበጫው አልታወቅ ማለቱ ብዙዎች ግራ አጋባ፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ፣ የሰኔ 15/2011 የአማራ ክልል አማራሮች እና የመከላከያ ጀኔራሎቹ ግዲያ ለውጡ ባለበት ቆሞ ወይም ወደ ኋላ ተመልሶ ኢትዮጵያችን ቋፍ ላይ ያለች መሰለች፡፡ ይህ ክስተት ግን መቀሌ ላይ ለመሸገው ሕወሀት ጉልበት የሰጠ መሰለ::

የኦሮሞ እና አማራ ልሂቃን ከትብበር ይልቅ ወደ ፉክክር እና ሴራ ውስጥ ለምን ገቡ? በለውጡ ሂደት ከፊት ካሉት መካከል ናቸው ያልናቸው ሰዎች በኢሬቻ በአል ዋዜማ ላይ መስከረም 23/2012 “ፊንፊኔ ላይ የሰበረንን ነፍጠኛ ሰብረነዋል፤ አሸንፈናል” ሲሉ ተደመጡ፡፡ በርግጥ ነፍጠኛ ሚለው ቃል ብሄር ባይኖረመውም በተለምዶ ስለሚታወቅ የአማራ ልጆች ነፍጠኞች ‘ውለታ ይገባቸዋል’ የሚሉ እና በሌሎች ቃላትም ምላሽ ሰጡ፡፡ ይህንንም ልሂቃን እና ፖለተከኞች ሆድ ለሆድ መራራቃቸውን ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ጥልቅ ምልከታ የማጠይቀው ጉዳይ ደግሞ ከቀርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ፖለቲከኞች እና አንቂዎች (activists) የንግግራቸው እና ትንታኔያቸው ማድመቂያ እና ማሳመሪያ አማራን የሚነኩ ነገሮች መሆናቸው ነው፡፡ የሚነሱ እና የሚጣሉ የፖለቲካ አጀንዳዎች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ አማራን ሳይነኩ አያልፉም፡፡አማራን መነካካት የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኝ ስትራቴጅ የሚመስል ነገር እንዳለው በግልጽ ይታያል፡፡ በድምር ስናየው ኦሮማራ ብሎ የጀመረው የለውጥ ንፋስ ነጻነት የታወጀበት መሆኑ ቀርቶ የምንሸነጋገልበት እና የምንገፋፋበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ስለሆነም በጥልቀት መገምገም እና የእርምት ርመጃ መወሰድ ይኖርበታል፡፡

አሁን ያለው ሁኔታ እንደሚጠቁመው ከለውጥ በኋላ አሮሞያ እና ሌሎች ህዝቦች ከሰሜኑ የፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ ስለወጡ፤ለወደፊቱም ቢሆን ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል አማራ ላይ ያነጣጠረ ስራ እየተሰራ ይመስላል፡፡ በተለይ የቅማንትን የማንነት ጥያቄን በሚዲያ ጣልቃ ገብነት አላግባብ በማጓን አማራው ላይ የጎን ውጋት የተፈጠረ ይመስላል፡፡ ዶ/ር (አቶ) ፀጋዬ ረጋሳ ቅማንቶች በአማራ ማንነታቸውን እንደተቀሙ፣ ጭቆና እና በደል እንደደረሰባቸው በኩሽ ሚዲያ ሀውስ ትንታኔ ሰጥቶበታል፡፡ ፀጋዬ ቅማንቶች በጅኦግራፊ በሰሜኑ ክፍል ቢገኙም እንደ ደቡቡ የተጨቆኑ ህዝቦች ናቸው (they are the South in the North) በማለት እይታውን እስቀምጧል፡፡ በሚዲያው ረገድ OMN፣ ONN፣ ድምጺ ወያኔ እና አልፎ አልፎም የትግራይ ቴሌቪዥን የቅማንት ጉዳይ ዋና አጀንዳቸው አድርገው ያራግቡታል፡፡ አጅግ ወገንተኛ በሆነ መንግድ ነገሮችን በማጋነን በቅማቶች ላይ የዘር ፍጅት እየተካሄደባቸው እንደሆነ ይዘግባሉ፡፡ በአማራው ላይ በታጠቁ የቅማንት ሐይሎች የሚደርስበትን መፈናቀል እና ግዲያ እንዳላየ እና እንዳልሰማ ያልፉታል፡፡ ለምን? ምን ጥቅም ለማግኘት? የክልሉ መንግስት የቅማንትን ጉዳይ ከስር መሰረቱ መፍታት ለምን ተሳነው?

የአማራ ክልል ብዝሀነትን በማስተናገድ የተሻለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ክልሉ ቀደም ባሉት ገዚያት ሶስት ልዩ ዞኖችን ከመመስረቱ በተጨማሪ የክልሉ ሕገ-መንግስት የክልሉ የስልጣን ባለቤቶች የአማራ ክልል ህዝቦች ናቸው ብሎ በማወጅ ተራማጅነቱን አሳይቷል፡፡ አርጎባዎች ጥያቄ ሲያነሱ ልዩ ወረዳ እንዲመሰርቱ ፈቅዷል፡፡ ቅማንቶችም የተለየ ማንነት ነው ያለን የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ልዩ ዞን እዲመሰረት ውሳኔ ማሳለፉን በተለያየ ጊዜ ሲገልጽ ሰምተናል፡፡ ክልሉ የተለያዩ ማንነቶች ከመጨፍለቅ ይልቅ መፍቀድ የተሻለ መሆኑ ላይ ጥልቅ እምነት ያለው መሆኑን ከየትኛውም ክልል በተሻለ በተግባር አሳይቷል፡፡ ታዲያ እንዴት አማራ ክልል ለውለታው መልስ ጠጠር (ጥይት) ሆነ? የሚገርመው ነገር ቅማንትን እንወክላለን የሚሉ ሰዎች ከባህር ዳር ይልቅ መቀሌ ቅርብ ሆኖላቸዋል፡፡ ይህች የቅማንት ጉዳይ የማንነት ጥያቄ ብቻ ሳትሆን የፖለቲካ ሚዛን እና ሌሎች ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የትግራይ፣የአማራ እና የአሮሞ ልሂቃን ፉክክር ውጤት ትመስላለች፡፡ ልሂቃኑ የማይፎካከሩበት ምንም ነገር የለም፤ሰልፍ ላይ በሚያዝ የባንዲራ ቀለም፣በህዝብ ቁጥር ብዛት፣በሐይማኖት በአላት ድምቀት፣በሴራ ፖለቲካ አዋቂነት እና ትንታኔ በመበሳሉት ውድድሩ ጦፏል፤ወደ መሀል መጥቶ የጋራ አጅንደ ቀርጾ ለመነጋር ዕድሉ የጠበበ መስሏል፡፡

ሕወሀትን ከስልጣን የበላይነቱ ገለል ለድደረግ አስደናቂ ትብብር አደርገው ነበሩት ኦሮሞ እና አማራ አሁን ላይ ግንኙነታቸው ሌላ መልክ ይዟል፡፡አማራው ከኦሮሞዎች ጋር ባለው የፖለቲካ ስነ ልቦና ልዩነት እና አማራዎች በተለያዩ ቦታዎች እየደረሰባቸው ባለው መገፋት ምክንያት መተባበር እንደማይቻል አሳይ ምልክቶች ተስተውለዋል፡፡አሮሞዎቹም አማራው የድሮውን ስርዓት እያቀነቀነ እና ንጉሶቹን እያሞጋገሰ ሰለሆነ ከነሱ ጋር መተባበር ለዳግም “ውርደት” ራስን መጋበዝ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ከዚህች ነጥብ ተነስተን በሁለቱ ልሂቃን መካከል ያለውን ሽኩቻ እና የፍላጎት መራራቅ ለመፍታት ከሁለቱም ህዝቦች የፖለቲካ ትውፊት ውስጥ መፍትሔ መፈለግ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ያለፈውን ታሪክ ማሻሻል እና መለወጥ ባይቻልም የወደፊቱን ግን ማስተካከል ይቻላል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያየዘም የሴራ ፖለቲካው ፣ ፉክክሩ እና መሻኮቱ በጣም የጎዳው አዴፓ ከሌሎች ጋር መተባበር እንዳለ ሆኖ ራሱን ለታዳኘነት እንዳያጋልጥ የክልሉን ሰላም እና ደህንነት ለማስከበር ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ለህዝብ በማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ከህዝቡ ጋር በመተባር መስራ፣ የክልሉ ፖሊስ ሰራዊት እና ልዩ ሀይል የህዝብ ድጋፍ እና ተአማኒነት እንዲያገኙ ማድረግ፣አዴፓ የተሸረሸረበትን ቅቡልነት ለማስመለስ ጠንካራ ፖለቲካዊ ስራዎችን መስራት ፤በክልሉ ውስጥ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመደራደር በዲሞክራሲያዊ መንገድ በመፍታት ከውጪ ተጋላጭነት ክልሉን መታደግ ይኖርበታል፡፡