አውቆ የተኛን የፖለቲካ ቡድን እንኳን በሰላማዊ ሰልፍ በመድፍ ተኩስ አይቀሰቅሱትም❗

ብሩክ ሲሳይ

የህውሃት ጭንቀት ለራሱ ወይስ ለትግራይ ክልል ህዝቦች? አልዋሃድም ማለቱ ለትግራይ ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ እንዳልሆነ ይታወቃል፤ ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ቢጨነቅ ኖሮ ለ27 ዓመታት በግለሰብ ደረጃ የዘረፉትን ገንዘብ ትግራይ ላይ ቢያፈሱት እንዳለሙት ትግራይ ሲንጋፖር በሆነች ነበር። ለትግራይ ሕዝብ ቢጨነቁ ኖሮ የትምአት (Effort) ድርጅቶች ንብረትነታቸው ወደ ትግራይ ሕዝብ ይዛወር ሲባል እነ ስብሃት ነጋ አሻፈረኝ አናስነካም የእኛ ነው ባላሉ ነበር። ለትግራይ ሕዝብ ቢጨነቁ ኖሮ በስሙ ከመነገድና የትግራይ ሕዝብ በመላ አገሪቱ ያሻውን ሰርቶ እንዳይኖር የሚያደርግ የፖለቲካ አካሄድ በመከተል የትግራይ ሕዝብ እንዲጠላ የሚያደርግ ሥራ ባልሰሩ ነበር።

ህወሓት ዘመቻ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የሚከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና ለ5000 ዓመታት በላይ መንግስታዊ ታሪክ ላላት ጥንታዊ አገር የማይመጥን፣ የትግራይ ሕዝብ በአሮጌዋ ኢትዮጲያ ላይ ያሳረፈውን አሻራ የሚቃረን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብና ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችን እስከ ቀለማቸው አንድነታቸውን ከማስጠበቅ ይልቅ በጥላቻና በስጋት እንዲተያዩ ከሚገባው በላይ በፖለቲካ በመከፋፈል 27 ዓመት ሀገር በማፍረስ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምዶ የቆየ ነው። ሰውየው እናንተ ትፈርሳላችሁ እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም እንዳሉት እብሪተኛ አገር አፍራሾች ለመፍረስ እየተንደረደሩ ጫፍ ላይ ደርሰዋል፤ ኢትዮጵያ ግን አሁንም ትቀጥላለች።
.
የዘውጌ ፓርቲንና የጎሳ ፖለቲካን የልህቀት ጫፍ አድርገው የሚመለከቱ የህወሓት ሰዎችና በአምሳላቸው የፈጠሯቸው ወደረኞቻቸው ስለ አዲስ ህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ ምስረታ የሚያነሱት የነቀፋ ሃሳብ የብሄር ውክልና ያሳጣል የሚል ነው። እንግዲህ ዘውግም ሆነ ጎሳና ነገድ የግለሰቦች ስብሰብ ናቸው። የአንድ ግለሰብ መብትና ፍላጎት ካልተከበረና ካልተመለሰ የቡድኑ/የዘውጉ መብትና ፍላጎትም ሊመለስ አይችልም።
.
ግለሰብ ብቻውን መቆም የሚችል ሲሆን ቡድን ግን በግለሰቦች ፍላጎት የቆመ ነው። ለቡድን/ለዘውግ ህላዌ የግለሰቦች መኖር ወሳኝነት አለው። ለግለሰቦች ህላዌ ግን የዘውግ መኖር ግዴታ አይደለም። የትግራይ ሰው አሜሪካ ሲኖር ግዴታ አስፈላጊ የሆነው ግለሰብነቱ እንጂ ትግሬነቱ አይደለም፤ ወይም ደግሞ በግልህ መኖር ስለማትችል ቡድን/ዘውግ ሆነህ ተመልሰህ ና ሊባል አይችልም። ፓርላማ ላይ አዋጅ ሲወጣ እጁን እያወጣ ድምፅ የሚሰጠው ዘውጉ ወይም ብሄሩ ሳይሆን ግለሰቡ ነው። ብዙ ጊዜም ከአንድ ዘውግ የመጡ ሰወች የተለያየ ሀሳብና ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል።
.
ህወሓት ስለ ብሄረሰብና ዘውግ ተቆርቋሪና እንባ ጠባቂ መስሎ ሁልጊዜ ለመታየት የማያደርገው ጥረት ባይኖርም በግብር ግን እንኳን ተቆርቋሪ ሊሆን በጭራሽ ስለ ዘውግና/ቡድን መብት ለማውራት ሞራል ሊኖራቸውም አይገባም። ህወሓት በሚመራው ትግራይ ክልል እስከ አሁን ድረስ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ የተደረጉ የራያና የወልቃይት ሕዝቦች አሉ። እስካሁን ድረስ በትግራይ ክልል አርባጊዜ እንደሚጮሁት ሳይሆን የብሄረሰቦች መብት በተግባር አልተከበረም። ትግራይ ክልል እስካሁን ድረስ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት የለም። የአክሱም ሙስሊሞች መስገጃ እና የቀብር ቦታ እስከ አሁን ድረስ የላቸውም። ይኼን መብታቸውን ሲጠይቁም የቡድን መብት ተቆርቋሪ የሆኑት የህወሓት ባለስልጣናት ቄሶቹን ጠይቁና ይፍቀዱላችሁ በማለት አፊዘዋል። እንግዲህ ህወሓት በቡድን ደረጃ ወከልኩት ለሚለው ህዝብ በተግባር መፍትሄ እንኳ የማይሰጥ ከዚያም በላይ እንደ ሃይማኖት ዓይነት የቡድን የመብት ጥያቄወች ላይ የሚያፌዝ ነገር ግን ዓይኑን በጨው አጥቦ የቡድን/የዘውግ መብት ተቆርቋሪ ነኝ የሚል ነው።
.
ህወሓት ብናወራለት፣ ብንነቅፈው ዞሮ ዞሮ ፍላጎታቸው፣ ሀሳባቸው፣ ክርክራቸው፣ ፕሮፖጋንዳቸው ወደ አንድ አቅጣጫ ያመራል እሱም ስልጣን እንዴት አድርገን ለረዥም ዘመን ይዘን ኢትዮጵያን እንዝረፋት፣ አጋድመን እንጋጣት የሚል ነው። ህወሃት ገና ስልጣን ሳይወጣ በትግራይ ህዝብ ስም የተለገሰ የእርዳታ ሰንዴን አከፋፍላለሁ ብሎ ለጋሾችንና ሕዝቡን በማታለል ለሱዳን በመሸጥ ክላሽንኮቭ የሚገዛና የትግራይ ህዝብ እየተራበ ሲሞት ቆሞ የሚያይ ድርጅት ነው። የእንደርታንና ሌሎች ህዝቦችን አግልሎ በአሽአ ሥርወ መንግስት ስልጣን ላይ የሚያስቀምጠው ደግሞ የስብሀት ነጋ ቤተሰብ የዘር ግንዶቹንና አምቻ ጋብቻወችን ብቻ ነው። ኢትዮጵያን አጋድመው የጋጧትም የአቦይ ስብሃት ነጋ ቤተሰቦችና ሌሎች አፍቃሪ መለስ ዜናዊ ግለሰቦች ናቸው።
.
የትግራይ ሕዝብ ጥሩ መንግስት ቢኖረው አሁን ከሆነውና ከአደገው በላይ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በአንድነት ከዚህም በላይ በብዙ መልኩ እድገት ያሳይ ነበር። ህወሃት የትግራይን ህዝብ እስከ አሁን ድረስ ሳያለማ ለራሳቸው ግን የቢልዮን ዶላር ቢዝነሶችን እያንቀሳቀሱ ነው። ህወሓት የመጠጥ ውሃ እንኳን በአግባቡ ለማያቀርብለት ህዝብ ህውሃት ከጠፋ ትጠፋለህ እያለ ሽብር መንዛት የክፍለ ዘመኑ ምጸት ነው። እውነታው ግን የትግራይ ሕዝብ የሚጠፋው ህወሓት ሲጎለብት ነው፤ የትግራይ ሕዝብ እድገትና ልማት ደግሞ በህወሓት መቃብር ላይ ነው። ህወሓት አያደርገውም እንጂ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ጦርነት እንኳን ቢጋጠም ከራያ እና ከወልቃይት ህዝብ አያልፉም።
.
አንድ ምክንያት ሳይኖራቸው ገና ቂጣቸውን ሳይጠርጉ በአስራወቹ ዕድሜያቸው ጀምሮ ኢትዮጵያ ምን እንደበደለቻቸው እንኳን የሚያቀርቡት አሳማኝ ሀሳብ ሳይኖራቸው አገራቸውን አምርረው የሚጠሉ ስንኩሎች ስብስብ ነው ህወሓት። ይሁንና በተቃራኒው ደግሞ ለእነዚህ የኢትዮጵያ ጥላቻ ለሰፈረባቸው ስንኩሎች ኢትዮጵያውያን እጅ እንደማይሰጡ በተግባር ለዘመናት አስመስክረዋል። ኢትዮጵያ በልጆች ታፍራና ተከብራ ትኖራለች። ኢትዮጵያ ጠላቶችዋ ተስፋ ቆርጠው የማይተዋአት፤ እርሷም የማትሞት የማትፈርስ ዘላለማዊ አገር ሆና ትቀጥላለች። ህወሓት ራሷ በመሰረተችው ድርጅት ኢህአዴግ አማካኝነት ቀብሯ ተፈጽሞ፤ ጥላቻን የተላበሰው ዘረኝነት አክትሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች በእኩልነትና በነፃነት በመቻቻል እና በመከባበር ይኖራሉ።