የተበልጠናል ፖለቲካ እና የግጭት አዙሪት!

ፀሃፊ፦ መሀመድ ይማም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ mohammedyimam2003@gmail.com

(ይህ ፅሁፍ መጀመሪያ የታተመው ፍትህ መፅሔት ላይ ነው)

የልማት ኢኮኖሚስቶች (Development Economists) በባህል እና በቋንቋ በተለዩ ቡዲኖች መካከል በፖለቲካ ውሳኔ ሰጭነት፣በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ በጦር ሰራዊቱ ወስጥ ባለቸው ተሰትፎ፣ በማህበራዊ ፍትህ እና ባህልን በማንጸባረቅ ረገድ ልዩነት ሲኖር ግጭት ይከሰታል፤ በወቅቱ መፍትሄ ካልተበጀለትም ደም አፋሳሽ ሊሆን ይችላል የሚል ትወራ አላቸው፡፡ ይህንን እይታቸውን የጎንዮሽ መባላለጥ እና ግጭት ትስስር ትወራ (Horizontal Inequality and Violent conflict nexus) ብለው ይጠሩታል፡፡ ይህን ትወራ በተግባር ለመፈተን በብራድ ፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ፍራንሲስ ስቲዋርት የሚመራው ቡዲን ብዙ ርቀት ተጉዞ በበርካታ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካ እና የኤዥያ ሀገሮች ፈትነውታል ወይም ሞክረውታል፡፡

በውጤቱም በባህል እና በቋንቋ በተለዩ ቡድኖች መካከል የሚፈጠር መበላለጥ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳስከተለ አረጋግጧል፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ ጊዜ ቡድኖች በሌሎች መበለጣቸውን በተፈጥሮ የተሰጣቸው እና እነሱ የበታች መሆናቸው የአርባ ቀን እድላቸው መሆኑን አምነው ከተቀበሉ ወይም መጨቆናቸውን ካላወቁ ግን ግጭት ላይነሳ ይችላል የሚል ግኝት አለ፡፡ በተጨማሪም ይህ የአንድ ሀገር ልጆች ሆነን በሌሎች ተበልጠናል የሚለው በተግባር የሌለ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል በፕሮፓጋንዳ ሰዎች እምሮ ውስጥ የሚፈጠር ቅዠት (Perception) ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ለመቅረፍ ባለሙያዎቹ በቡድኖች መካከል የጎንዮሽ መበላለጥ መኖሩን የሚለኩበት ተጨባጭ የሆኑ መስፈርቶች እና ቀመሮችን አዘጋጅተዋል፡፡

የጎንዮሽ መበላለጥ አራት ክንፎች ያሉት ሲሆን እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ አንድ ቡድን በፖሊቲካ ውስኔ ሰጭነት ላይ ብልጫ ካገኘ በኢኮኒሚውም ብልጫ ለመውሰድ እድል ይኖረዋል፤ በኢኮኖሚው የተሻለ ከሆነ የተሻለ ህክምና እና ትምህርት የማግኘት (ማህበራዊ ተጠቃሚነት) እድሉን ያሰፋለታል፡፡ በተጫማሪም ባህሉን በራሱ ከማንጸባረቅ አልፎ በመንግስት ዘንድ እንደ ብሄራዊ አርማ ተደርጎ ሊወሰድለት እና በሌሎች ላይ ተጽእኖ እንዲያሳርፍ ሊደረግ ይችላል፡፡

ችግር ሚፈጠረው ታዲያ ይህን ሁኔታ የሚያስተውሉ ከተገፉ ወገኖች ብቅ የሚሉ ንቁዎች የሰፈነውን መድሎ እንደ ማንቀሳቀሻ ሞተር ተጠቅመው በተቃውሞ ለመፋለም ሲወስኑ ነው፡፡ የጎንዮሽ መበላለጥ አገዛዙ በፖሊሲ የሚያራምደው ሲሆን የሚያሳድረው ተጽዕኖም አጅግ የከፋ እንደሆነ በዚህ ዘርፍ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ያሰምሩበታል፡፡ በሰላም ጥናት ዘርፍ ደግሞ የጎንዮሽ መበላለጥ ከመዋቅራዊ ጥቃት ወይም ጭቆና ጋር ተመሳሳይነት አለው፤አንድን ህዝብ/ብሄር በባህሉ፣በሀይማኖቱ ወይም በቋንቋው ምክንያት ተገልሎ ለእርዛት፣ ለበሽታ፣ ለድንቁርና እና ለፍትህ እጦት እንዲጋለጥ ማድረግ ማለት ነው፡፡
በጎንዮሽ መበላለጥ ትወራ መነጸር ሲታይ ይህን አይነት የተዛባ ሥርዓት ለመቀየር በሚሞከርበት ሰአት ወደ ጎንም ወደ ላይም ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ወደ ጎን (Horizontally) ተበድለናል የሚሉ በአንድ ወገን፤ ተጠቅመናል የሚሉ ደግሞ በሌላ ወገን ተሰልፈው ደም ሊቃቡ ይችላሉ የሚለው ሲሆን ወደ ላይ (vertically) ደግሞ የኢፍትዊነት መሳሪያ በሆነው ሥርዓት/መንግስት እና በለውጥ ፈላጊዎች መካከል ፍጥጫ እና ዓመጽ ሲከሰት ማለት ነው፡፡ አስከፊ የሚሆነው ግን ወደ ጎን በህዝቦች መካከል ቁርሾ እና ቂም በቅሎ የቀረ እንደሆነ ነው፡፡ የጎንሽ መበላለጥ ግጭት ትስስር ትወራ በዚህ ጽሁፍ ብዙ ባልሄድበትም ከሕወሐት መራሹ ኢህአዴግ ጋር የተደረገውን የሁለት አስርታት ተጋድሎም ሆነ፣ አሁን ደግሞ ከኦዴፓ-መራሹ ኢህአዴግ ጋር የተጀመረውን መተጋገል በሚገባ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡የተበልጠናል ፖለቲካ ከተነሳ የተወሰኑ ነጥቦችን ብንጨምር መልካም ነው፡፡

በዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ “አንድ ህዝብ፣ እንደ ህዝብ በሀገሪቱ መሪ ተገልሎ ለመከራ ተዳርጓል” የሚል ወቀሳ ያነሱት ነጋድራስ ገብረ ሕወት ባይከዳኝ ናቸው፡፡ በወቅቱ ተራማጅ እና የምጡቅ እምሮ ባለቤት የነበሩት ገብረሕወት የትግራይን ህዝብ “መገፋት” አጼ ምኒሊክ እና አትዮጵያ በሚለው መጽሀፋቸው እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፤

“ትግሬ በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ጠፍታለች፡፡ የትም ብትሄድ በዚያች አገር የለማ መንድር አታገኝም፡፡ ሰው ከሚኖርባቸው ጎጆዎች ይልቅ የድሮ ልማትዋን የሚመሰክሩ ፍራሾችዋ ይበዛሉ፡፡ የትግሬ ጎበዝ በዛሬ ዘመን ባባቱ አገር አይገኝም፤ አውራ እንደሌለው ንብ አድራሻው ሳይታወቅ ወደ አራቱም የዓለም መዓዘኖች ተዘርተዋል፡፡ …..ምኒሊክ በአንድት ነገር ሊታሙ ይገባል፡፡ የትግሬን ህዝብ እንደ ህዝባቸው አልቆጠሩትም፡፡ እውነትም በትግሬ ነገድ ልማትና ጉዳት ምን ቸገረኝ የሚል ንጉስ ለራሱ ይጎዳል፡፡ ትግሬን የሚያከል ታላቅ ነገድ ቢጠፋ ለኢትዮጵያ ታላቅ ጉዳት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሰረት ትግሬ ነው፡፡ ከቀሩትም የኢትዮጵያ ነገዶች ይልቅ የኢትዮጵያን መንግስት ዕድሜ ሊመኝ የሚገባው ትግሬ ነው (ገ ሒ 11)”

ገብረሂወት በመጽሃፋቸው ንጉሱን ወቀሱ እንጅ ንጉሱ የወጡበትን አማራን አልወቀሱም፡፡ በኋላ ግን ይኸው በባህል እና በማንነት በተለያዩ ቡዲኖች መካከል ያልተመጣጠነ ግንኙነት (የጎንዮሽ መበላለጥ) ስላለ በብሄሮች ጥያቄ ማዕቀፍ ውስጥ በመተንተን ችግሩን ለመፍታት የዚያ ትውልድ አባላት ሞክረዋል፡፡ የተወሰኑትም ላነሱት ጥያቄ ከመሳሪያ አፈሙዝ መልስ ለማግኘት ጫካ ገብተዋል፡፡ ይህን የመበላለጥ ጉዳይ በብሄሮች ጥያቄ መርህ ስር እነ ዋለልኝ መኮንን ደም እና ስጋ አልብሰውት እስካሁንም ከእነ ግለቱ አለ፡፡ ሕወሀትም በዚህቹ መስመር በሶስት አንጓዎች ላይ አጅንዳ ቀርጾ በርሃ ከትሞበታል፡፡ አማራ ተጋሩን ከኢኖሚ እና ከፖለቲካ አግልሏል ፣የትግራይን ታሪክ ዘርፏል እና የዩሐንስን ዙፋን ተቀምተናል በሚሉ ስሜት ኮርኳሪ ሀሳቦች የትግራይ ልጆችን ለጦርነት አንቀሳቅሶ ጊዜው ደግፎት ቤተመንግስት ግብቶ ነበር፡፡ ፍትህን እና እኩልነትን ለማስፈን በብሄሮች መብት ጥያቄ መስመር ሰልጣን የያዘው ሀይል የተጠበቀውን ሳይተግብር ቀርቶ የከፋ የመበላለጥ ፍርሐትን አንግሶ እና የብሄሮች መብት ጥያቄም ከጥያቄ ወደ “ትንግርትነት” ቀይሮት ወደ መቀሌ ሸሽቷል፡፡

አዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ነጥብ ሕወሀት የሀገርቱን ሀብት ዘርፎ ያጓዘ ቢሆነም በኔ አተያይ የሰሜናን ኮከብ መቐለ እድገት ከመጥላት አይደለም፡፡ እድገቷ ግን የእድሜ አቻዎቿ በሆኑት በማርቆስ፣ በደሴ፣ በድሬዳዋ እና በጅማ ውድቀት ላይ መሆን የለበትም ነው፡፡ ሁላችንም ለሀገር ክብር ተዋግተናል፤ ሞተናል የእድገቱ ትሩፋት ለሁሉም ይድረስ ለማለት ነው፡፡

ኤርሚያስ ለገሰ ባለቤት አልባ ከተማ እና የመለስ ልቃቂት በሚሉት መጽሀፍቶቹ ሕወሀት/አህአዴግ ለራሱ ፖሊካዊ ግብ ሲል የመበላለጥ ፖሊቲካን ስር ለማስያዝ እና የማይነቃነቅ ለማድረግ የሄደበትን ርቀት በማስረጃ አስደግፎ አስነብቦናል፡፡ እንደ አርሚያስ አገላለጽ በክልሎች መካከል ሰፍኖ ለነበራው መበላለጥ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ሕወሀት የፖለቲካ ስልጣኑን፣ ወታደራዊ መዋቅሩን እና የደህንነት መስሪያ ቤቱን በመያዝ እና ኤፌርት ደግሞ ኢኮኖሚውን በሞኖፖል በመቆጣጠር አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከኤርሚያስ በፊት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በርካታ ምርሞሮችን ያካሄደችው ሎቪስ አላን እንዲህ ከትባው ነበር፤የሕወሀቱ አህአዴግ የፌደራል ስርዓት መስርቶ ህበረ-ባህላዊነት ላይ አመርቂ ውጤት ቢያመጣም በሌሎቹ ዘርፎች ባሰፈነው አስከፊ መዛነፍ እና አፈና ምክንያት በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ገለል ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ ይህ ጽሁፍ ሊያሳስብ የሚፈልገው ጉዳይ፤የህዝብ ተቃውሞ እና ትግል ፍሬ አፍርቶ በ2010 ወደ ለውጥ ጎዳና የተገባ ቢሆንም የተበልጠናል ፖለቲካ ግን ማቆሚያ አላገኝም፡፡ የአሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በተራው ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደጠቅላይነት እየተሸጋገረ ነው የሚለው ወቀሳ የብዞዎች ስጋት ሆኗል፡፡ የመባለለጥ እና ግጭት ግንኙነት ትወራ እንደሚለው ይህ እየጎለበተ የመጣው አድስ አይነት የመበለጥ ስሜት በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት ወደሌላ የግጭት አዙሪት ማንደርደሩን ያስረግጣል፡፡

the popular perception is that the Tigryians are the new ruling ethnic elite and that they are attempting to monopolize political power and direct state resources to their own region in the north of the country (Aalen 2006:250).