የኢህአዴግ ውህደት ሌሎቹን ለምን ያስጨንቃቸዋል?

ብሩክ ሲሳይ

ብዙዎቻችን አባል ላልሆንበትና ከዚህ ቀደም ዓይንህን ለአፈር ስንለው ለነበረው ፓርቲ ውህደትና የውስጥ ሽኩቻና ፍትጊያ ትኩረት ሰጥተን እንድንከታተለው ያደረገንና ውህደቱ እንዳሰቡት ይሳካ ዘንድ የተመኘነው በውስጠ ፓርቲያቸው ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት አልያም በማያገባን ጉዳይ ለማውራት ሳይሆን የፓርቲው 27 ዓመት ጉዞና አሰራር ከአገራችን እጣ ፋንታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ስለሆነብን ነው። የኢህአዴግ የ28 ዓመት ጉዞ ፓርቲውና መንግስታዊ መዋቅሩ አንድ አካልና አምሳል ሆነው መለየት እስኪያቅተን ድረስ ከቀበሌ እስከ ፌድራሉ መንግስት ማዕከል ድረስ በእጅጉ የተቆራኙ እንዲሆኑ ተደርገዋል። የኢህአዴግ ፈጣሪወች እነ መለስ ዜናዊ በወረቀታቸውና በዲስኩራቸው ፓርቲና መንግስት ሁለት የተለያዩ አካላት እንደሆኑ ቢሰብኩም በግብር ግን አንድ አካልና አምሳል ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ራሱ ሰውየው ትዕዛዝ በመስጠት ሲያስፈጽም መኖሩ የአደባባይ ሀቅ ነው።
.
እንደሚታወቀው እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ያላደገ ኢኮኖሚ ያለውና የግል ኢኮኖሚ ዘርፉ ድርሻ እጅግ ጥቂት የሚባል በሆነበት አገር ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው በመንግስት ሲሆን፤ ከፍተኛውን ኤክስፔንዲቸርም የሚያወጣው መንግስት ነው። መንግስት በአገራችን የኢኮኖሚ ዘርፍ ትልቁ ተዋናይ በመሆኑ እና ይኸው መንግስት ደግሞ ከገዥውና ዘዋሪው ፓርቲ ጋር እጅግ የተቆራኘ በመሆኑ በአንድም በሌላ መልኩ የፓርቲው ኢህአዴግ ተጽእኖ እና ቁርኝት በስልጣን ላይ ሆኖ የአስተዳደር ሥራ ከመስራት ባሻገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ እንዲሁም የኅብረተሰቡ የቀን ተቀን ኑሮ ጋር የተቆራኘ እንዲሆን ስላደረገው የፓርቲው ጉዳይ የደጋፊና አባላቱ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ ጉዳይ ለመሆን አብቅቶታል። ጠሚ ዓቢይ ስልጣን በያዙ ማግስት ይኼን ነገር “ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲንና መንግስትን መለየት እስከማይቻልበት ደረጃ ድረስ አንድ ዓይነት ሆነዋል” በማለት ችግሩን መግለጻቸውን ማስታወስም ተገቢ ነው። እንደ ህወሓት ዓይነቱማ ፓርቲውን ከመንግስት ጋር አንድ ከማድረግ በላይ ከትግራይ ሕዝብ ጋርም መለየት አይቻልም፤ “ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው” በማለት ጽፈው ካጸደቁት ህገ መንግስት በተቃራኒ አስቂኝ ንግግር ሲያደርጉ መስማት የተለመደ ሆኖብናል።
.
እንግዲህ ይኼን ነባራዊ ሁኔታ ከተረዳን በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ ገዥ የሆነው ፓርቲ የሚኖረው የፖለቲካ ርዕዮትና ቀጣይ አቅጣጫ የመጭውን ጊዜ የፖለቲካ አቅጣጫ፣ የአገሪቱን የሰላምና የአንድነት አልያም የልዩነት ጉዞ መወሰኑ አይቀርም። ዛሬ ሁሉም እየተነሳ ክልል ካልሆንኩ የሚለው፣ በየጊዜው በየመንደሩ የዘውግ ፓርቲወች እየተፈለፈሉ ነጻ አውጭ ነኝ የሚሉት፣ የወሰን ጥያቄ አለብኝ፣ የማንነት ጥያቄ አለብኝ፣ ይቺ ከተማ የኛ ናት፣ ያችኛዋን ደግሞ የኛ ማድረግ አለብን ወዘተ ዓይነት አሁን በዚህ ዘመን ጎልተው የምንሰማቸው የፖለቲካ ጥያቄወች እንደ አገር በጋራ ጉዳዮችን ከመመልከት ይልቅ በተናጠል እየተጠቋቆምን በባላንጣነት እንድንተያይ የሆንበት ዋናው ምክንያት ባለፉት 28 ዓመታት አገሩን ሲገዛ የነበረው ፓርቲ ሀሳብ፣ ፍልስፍና፣ ርዕዮትና አቅጣጫ ስለሆኑ ነበር። ይኼ ገዥ ፓርቲ በህጻናት መማሪያ መጽሀፍ ሳይቀር ይኼኑ ርዕዮቱን፣ አቅጣጫውንና አገዛዙን በማስረጽ መንግስታዊ ተቋማትም ከፓርቲው ጋር በፈጠሩት ኢህጋዊ አንድነት የፓርቲው ሁሉ ነገር የመንግስት ሁሉ ነገር እንዲሆን ስላደረጉት ይኼው ዛሬ ለደረስንበት ፖለቲካ ሁኔታ በቅተናል።
.
ዛሬ በየቦታው የምናየው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የብሄር ግጭትና ግጭቱን ተከትሎ የሚመጣው እጅግ አውሬያዊ የሆ የአረመኔ ድርጊቶች ባለፉት ዓመታት ፓርቲው መንግስታዊ ተቋማዊ ቅርጽ በመስጠት ወደ ሕዝቡ ያሰረጻቸውና የዘራቸው ሲሆኑ ውጤቱን ደግሞ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ድረስ እያጨድን እንገኛለን። እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር የአገራችን ገዥ ፓርቲ የሆነው ኢህአዴግ አሁን በዚህ ወቅት የሚኖረው የፖለቲካ አቅጣጫና ርዕዮት የመጭውን ዘመን የፖለቲካ መድረክና አጠቃላይ የመንግስት አስተዳደርና የፖለቲካ አደረጃጀት የሚያመላክት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ፓርቲው ጠባብ ዘውጌያዊ አደረጃጀትና እንደተለመደው የተናጠል የፖለቲካ መንገድን ከመረጠ፤ ፉክክሩም ሆነ የፉክክሩ ሜዳ በዚያው የተቃኘ መሆኑ አይቀርም። አልያም ደግሞ ኅብረ ብሄራዊነትን በማያንፀባርቅ መልኩ ጠባብ የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ አቅጣጫን ከተከተለም ሜዳው በዚያው ሊቃኝ ይችላል። ይሁንና ገዥው ፓርቲ ሁለት ጫፍ ላይ የቆሙትን የዘውጌ ፖለቲካ ሀሳብና የጠባብና ነጠላ ኢትዮጲያዊነት ፖለቲካን ከመከተል ይልቅ ከሁለቱም ወገን ያለውን መልካም ነገር በመውሰድ ኅብረ ብሄራዊ ወጥ የሆነ አንድ ፓርቲ ለመመስረት ችሏል። በዚህም ምክንያት የቀጣዩ ዘመን የፖለቲላ አቅጣጫና የፉክክር መድረክ በዚህ አውድ የተቃኘ ብቻ ሳይሆን ከዚህም የተሻለ አማራጭ ስለሌለ ሌሎችም እየተከተሉት ያለና የሚከተሉት የፖለቲካ አቅጣጫ እንደሚሆን አያጠራጥርም። የፓርቲው ውህደትም ከውጭ ሆኖ የሚመለከተውን አካል ትኩረት የሳበው ከዚህ አንጻር ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።
.
እንደ አጠቃላይ የፖለቲካ ግምገማና የኢህአዴግ የ27 ዘመናት ጉዞ ስናየው የፓርቲው ውህደት ከኢትዮጵያ የረዝም ዘመን የመንግስት ታሪክ አንጻር መሆን ካለበት ጊዜ የዘገየ ነው ለማለት ይቻላል። በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ብሄሮችን የሚወክሉ ፌደራል ክልሎችን የሚመሩ የፖለቲካ ፓርቲወች በብሄር የተደራጁ እንዲሆኑ ከመደረጉ በላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የተወሰኑ ብሄሮችን ብቻ ያካተተ የፖርቲወች ግምባር ማዕከላዊ መንግስትን የተቆጣጠረበት የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር ከኢትዮጵያ ውጭ በየትም አገር የማይገኝ ነበር። እሰከዛሬ የነበረው የኢህአዴግና አጋሮቹ አደረጃጀት ከኢትዮጵያ አንድነት ይልቅ ለብሄርና ብሄረሰቦች መብት የቆመ ነው ቢባልም በተግባር ግን በሁሉም የአገራችን ክፍል የሚገኙ ዜጎች አገር ለመምራት ጠቅላይ ሚኒስተር የማይሆኑበት፤ በአራት ብሄራዊ ክልሎች ከሚገኙ ዜጎች ውጭ ያሉ ብሄረሰቦችና ብሄሮች እንዲሁም ዜጎች በአገራቸው ዕጣ ፈንታ ለመምከርና ለመወሰን ዕድላቸውን የሚገድብ የፓርቲ አደረጃጀት ሆኖ ቆይቷል።
.
እንደሚታወቀው ኢህአዴግ ሥልጣን ከመያዙ በፊት የነበሩ የፖለቲካ አደረጃጀቶችና የመንግስት አቅጣጫዋች ወጥ የሆነ አሃዳዊነት የሚስተዋልበት ትኩረቱ አገራዊ አንድነት ላይ ብቻ ያደረገ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ኅብራዊነት የማያንጸባርቁ ነበሩ። ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ቀደም ሲል ከነበረው የፖለቲካ ፓርቲ ቅርጽና መንግስታዊ አወቃቀር በተቃራኒ አንድነትና አገራዊ ትስስርና መስተጋብርን በዘነጋ መልኩ የብሄርና ብሄረሰቦች ጉዳይን በማጉላት የዘመናት የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችን ትስስርና አንድነትን ገሸሽ ያደረገ የፖለቲካ ስልት በመከተል በርካታ ክፍተቶችን ፈጥሯል። ይሁንና ከኢህአዴግ በፊትም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን የነበሩ ገዥ ፓርቲወች አደረጃጀት የበጎ ጎናቸውን ያክል የየራሳቸው ድክመት ነበራቸው።
.
#የብልጽግና_ፓርቲ_ከእነዚህ_ጫፍና_ጫፍ_ከቆሙ በአገራችን ገቢር የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀቶች ጠንካራ ጎናቸውን በመውሰድና ድክመታቸውን በማስወገድ የረዝም ዘመናት መንግስታዊ ታሪካችን በሚገልፅ መልኩ የአገር አንድነትን የሚያጸና፤ የበርካታ ነገዶች አገር የመሆናችንን ያክል ይኼንን ኅብራዊ ቀለማችንን የሚያንፀባርቅ ሆኖ በጠንካራ አንድነት ላይ የተመሰረተ ኅብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑ እጅግ ጠቃሚ ነው ማለት ይቻላል። ባለፉት 28 ዓመታት ኢህአዴግ በመንግስት መሪነት ካጋጠሙት ፈተናወችና ስኬቶች ትምህርት ቀስሞና እነዚህ ከተሞክሮ ያገኛቸው መልካም ልምዶችን በመጠቀም የተሳሳቱን በማስወገድ ከራሱ ከድርጅቱ ውስጣዊ ፍላጎት መሻሻልና ለውጥ አስፈላጊ ነው ተብሎ ታምኖበት ለዚህ ደረጃ መብቃቱ ለመሻሻልና ወደ ውስጥ ተመልክቶ የችግርን ምንጭ በማድረቅ በተሻለ መልኩ ሕዝባዊ አደራነት የበለጠ ለመወጣት ያለውን ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ተግባር ተደርጎ የሚወሰድ ነው ለማለት ይቻላል።
.
አዲሱ ውህድ ፓርቲ የአገር አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ የብሄር ብሄረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የማይጋጭና እያንዳንዱ ብሄርና ብሄረሰብ ባህልና ቋንቋውን እንዲያበለጽግ የሚያስችሉ አሰራሮችና ደምቦችን በማካተት ለዘመኑ ትውልድ እና ንቃተ ኅሊና በሚመጥን መልኩ ሆኖ የተመሰረተ እንደሆነም ከሰማናቸው ማብራሪያወችና ከፕሮግራሙ ለመረዳት ችለናል። ከኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ እድገትና መስፋፋት ጋር ተያይዞ ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየሄደችና የዓለም ሕዝቦች የበለጠ ቅርብ እየሆኑ ባለበት ዘመን የኢትዮጵያ ብሄርና ብሄረሰቦች በአንድ መንግስት ጥላ ስር ሆነው ወጥ የሆነ ኅብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ድርጅት መስርተው መንቀሳቀስ ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር በመሆኑ ውህደቱ በዚህ በኩል የሚደነቅ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ብሄሮችና ብሄረሰቦች እንዲሁም ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች አንዳቸው ከሌላው ተለያይተው በተናጠል ለየብቻ ተፈናጥረው መኖር የማይችሉ ከመሆናቸው በላይ በሚኖራቸው መስተጋብር በእኩልነት መርህ በመከባበር ተዋዶና ተፋቅሮ ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም። እንዲህ ዓይነቱን ማኅበረሰብ የሚመራ መንግስትና ፓርቲ ደግሞ አወንታዊ ሚናወችን በመጫወት የማኅበረሰቡ መስተጋብር የተቀና እንዲሆን ኢህአዴግ በአዲስ መልኩ ውህደት ፈጥሮ የብልጽግና ፓርቲን መመስረቱ ታላቅና በሳል የፖለቲካ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ነው።
.
እንግዲህ የገዥው ፓርቲ የበላይ አመራሮች የሆኑት ጠሚ ዓቢይ አህመድ፣ ም/ጠሚ ደመቀ መኮነን እንዲሁም የእያንዳንዱ ግምባርና አጋር ፓርቲ የሆኑት ከፍተኛ አመራሮች ከትህነግ እና መሰሎቹ በኩል ያለባቸውን ጫናና እጅግ በክፋትና በተንኮል የተሞላ አፍራሽ አካሄድና ሴራ ለመቋቋም ይህን ውህደት ለመፈጸም በመቻላቸው እጅግ የሚደነቅ ተግባር እንደሆነ ለማስቀመጥ እወዳለሁ። ምክንያቱም ይህ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና በራስ መተማመን የሚጠይቅ ነገር ከመሆኑም በላይ በብሄር ፖለቲካ ጥርሱን የነቀለው ህወሓት የነበረውን ተቋማዊ የበላይነት ለማስቀጠል ከዚህ የተሻለ አማራጭ ስለሌለው ይህ የውህደት ፕሮጀክት እንዳይሳካ ከመሬት በታች ባለው አቅሙ ማድረግ የሚችለውን ነገር ሁሉ በማድረግ ሊያሰናክላቸው ባለመቻሉ ነው። ከዚህም በላይ ያለፉት 50 ዓመታት ጫፍና ጫፍ የቆሙ በባላንጣ የሚተያዩ የፖለቲካ እሳቤወችን ገልብጦ በመጣል፣ ውስንነታቸውን በማስወገድ የእሳቤወቹን መልካምና ጠቃሚ ጎኖች ወሰዶ ወደ ማዕከል መጥተው ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት የፖለቲካ ርዕዮትና አቅጣጫ የሚከተል የመጭውን ዘመን ፖለቲካ ለመወሰን አቅም ያለው አሳታፊ ኅብረ ብሄራዊ ወጥ እና አንድ ፓርቲ መመስረት እንደ ታላቅ ተግባር የሚቆጠርና ራሳቸውንም በፖለቲካ ታሪካችን ስማቸው ጎልቶ እንዲጻፍ የሚያደርግ ነው። በዚህ የውህደት ፕሮጀክት ድርሻ ያለውና ሚናውን በቅንነት የተወጣ አመራርና ባለሙያ ሁሉ መልካም ነገር እንደሰራ ሊቆጥረው የሚገባ ነው።