የፖለቲካችን ስብራት እና መለያየት!

እስኪ ፖለቲካው ይቆየንና ስለ እውነት እንናገር። ለአንድ አፍታ፤ ሳናዳምጥ አናውራ፣ ሳናውቅ አንቃወም፣ ሳይገባን አንደግፍ። እስኪ ለአፍታ እንኳን ከግብታዊ ስሜት እንውጣ፣ በምክንያት እናስብ። የአንድ ሃሳብ ትክክለኝነት የሚመዘነው በተናጋሪው ስልጣንና ማንነት ሳይሆን በምክንያታዊ ዕውቀት ነው። ምክንያታዊ ዕውቀት የትላንቱን ጠንቅቆ ማወቅ፣ የዛሬን በዝርዝር መገንዘብ፣ የነገን በትክክል መገመት ያስችላል። የትላንቱን ታሪክ እና የወደፊቱን ሁኔታ መሰረት ያደረገ በሰዎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥና መሻሻል ሊያመጣ የሚችል ሃሳብ ትክክልና አግባብ ነው። እንዲህ ያለ ሃሳብን ላለመቀበል መቃወም ራስን ማታለል፣ ሌሎችን መበደል ነው።

አዎ… ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ስንል ቆም ብለን እናስብ፣ በምክንያት እንጠይቅ፣ የምንሄድበትን መንገድ፣ የምንደርስበትን ቦታ እንወቅ። ለዚህ ደግሞ ትላንት ላይ አንጠልጠል፣ ዛሬ ላይ እናስተውል፣ ነገ ላይ ተስፋ አንቁረጥ! የትላንት ታሪካችን በጅምላ መፈራረጅና መገዳደል የተሞላ ነው። በተለይ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን አብዮትና ፀረ አብዮት፣ ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር፤ ኢትዮጵያ ወይም ሞት፣ አንድነትና ተገንጣይ፣ ሰላምና ፀረ-ሰላም፣ ልማትና ፀረ-ልማት፣ ሽብርና ፀረ-ሽብር፣… ወዘተ በሚል የጅምላ ፍረጃ የአንድ ዘመን ትውልድ እርስ በእርሱ ለሞት፣ እስራትና ስደት ተዳርጓል።

የአብዮቱ ድል የሚረጋገጠው ፀረ-አብዮቶችን በማስወገድ ነው። ፀረ-አብዮቱ እንዲኖር አብዮተኛው መወገድ አለበት። የአብዮቱ ስኬት ለፀረ አብዮቱ ሽንፈት ነው። ስለዚህ የአንዱ ድል ለሌላው ሽንፈት፣ የአንዱ ህይወት ለሌላው ሞት ነው። በእርግጥ ያ ትውልድ አብዮተኛ ነው። አብዮተኛ እና ፀረ-አብዮተኛ በሚል በጅምላ ከመከፋፈል በስተቀር መሰረታዊ የሆነ የአቋም ልዩነት አኪያም የርዕዮተ-ዓለም ተቃርኖ አልነበራቸውም።

ሁሉም አብዮተኞች “ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል! የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ ይገባል!” የሚል አቋም የሚያራምዱ ናቸው። ከሞላ ጎደል ሁሉም አብዮተኞች የማርክሲስት/ሌኔኒስት ጥራዝ ነጠቆች ነበሩ። ይሁን እንጂ ሁሉም ራሳቸውን “አብዮተኛ” ሌሎችን ደግሞ “ፀረ-አብዮተኛ” ብለው ይፈርጃሉ። በጅምላ ፍረጃ የተጀመረው ልዩነት በሂደት ወደ እርስ በእርስ መጠላለፍ፣ ቀጥሎ በጠላትነት መፈላለግ፣ በመጨረሻም በጥይት መገዳደል ይጀምራሉ። ይሄ የቢሆን-ዓለም ተረት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ላለፉት ሃምሳ አመታት የሀገራችን ፖለቲካ የመጣበት መንገድ ነው።

በደርግ የተጠለፈውን የተማሪዎች አብዮት ለማስመለስ የነጭ ሽብር ጥቃት ተፈፀመ። ነጭ ሽብርን ለመመከት ቀይ ሽብር ተፋፋመ። በዚህ መልኩ ሀገርና ህዝብ በፀረ-ፖለቲካ ታመሰ፣ የአንድ ዘመን ትውልድ እርስ በእርስ ተጨፋጨፈ። እናት ልጇ ለተገደለበት ጥይት ካሳ ከፈለች። አባት የልጁን ሬሳ ከመንገድ ላይ ማንሳት ተሳነው። ወዳጅ ዘመድ ከገዳዮች ፊት ማልቀስ ተከለከለ። ያ… ትውልድ በጅምላ እየፈረጀ በጅምላ ተፋጀ።

ከነጭ ሽብር ጥቃት የተረፉት ሶሻሊስት አብዮተኞች ደርግ እና መኢሶን በሚል ተከፋፍለው ተገዳደሉ። ደርግ’ም “ስርጎ-ገብ” በሚል እርስ በእርስ መገዳደል ጀመረ። ከቅይ ሽብር ዘመቻ የተረፉት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቀንቃኞች ኢህአፓ እና ህወሓት በሚል ተከፋፍሉ።ደርግን ለማስወገድ ጫካ የገቡት ሁለቱ የአማፂ ቡድኖች እርስ በእርስ በመገዳደል ትግል ጀመሩ። በመቀጠል ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የትግራይ ማርክሲስት ልኔኒስት ሊግ (ትማልሊ) በሚል ለሁለት ተከፈለ።

ከሞት፣ ስደትና እስራት የተረፉት ደርግ እና ህወሓት በሀገርና ብሔር ስም እርስ በእርስ መገዳደል ጀመሩ። አዎ… እንዲህ እያለ ያ… አብዮተኛ ትውልድ በጅምላ ተከፋፍሎ፣ በጅምላ ታሰረ፣ በጅምላ ተገድሎ በጅምላ ተቀበረ። ደርግና ህወሓት የ1960ዎቹ ትውልድ እንደመሆናቸው መጠን ሁለቱም “የፀረ” ፖለቲካ አራማጆች ናቸው። ልክ እንደ ደርግ ህወሓትም ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት ከእሱ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን ዜጎች፤ ሰላምና ፀረ-ሰላም፣ ልማትና ፀረ-ልማት፣ ህገ መንግስትና ፀረ-ህገ መንግስት እያለ ዜጎችን ለሞት፣ እስራትና ስደት ዳረጋቸው። በመጨረሻም ማንኛውም ዓይነት ሃሳብና እንቅስቃሴን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የሚያስችለውን “የፀረ-ሽብር አዋጅ” በማውጣት ሀገርና ህዝብን ማሸበር ጀመረ።

ላለፉት ሃምሳ አመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በበላይነት የተቆጣጠረው የ1960ዎቹ አብዮተኛ ትውልድ ነው። ይህ ትውልድ በዋናነት “የፀረ” ፖለቲካ አራማጅ ነው። በፀረ ፖለቲካ የመንግስት ስልጣን የያዘው ቡድን ራሱን አብዮታዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ልማታዊና ህጋዊ በማለት ከእሱ የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ያላቸውን ደግሞ ፀረ-አብዮት፣ ፀረ-ዴሞክራሲ፣ ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ልማት፣ ህገወጥና አሸባሪ በሚል ይፈርጃል።
በዚህ መሰረት ከደርግ መምጣት እስከ ህወሓት ውድቀት ድረስ ያለው ታሪካችን አንድና ተመሳሳይ ነው። አብዮተኞች ከሃሳብ የበላይነት ይልቅ በጉልበት የበላይነት፣ ከውይይት ይልቅ በጦርነት፣ ከመነጋገር ይልቅ በመገዳደል የሚያምኑ ስለመሆናቸው የቀይ ሽብር ዘመቻ እና ፀረ-ሽብር አዋጅን መጥቀስ ብቻ በቂ ነው። ላለፉት ሃምሳ አመታት የመጣንበት የፀረ-ፖለቲካ ኢትዮጵያ የቆመችበትን መሰረት ሸርሽሮ ሸርሽሮ ከቋፍ ላይ አድርሶታል።

ይህን ያረጀ-ያፈጀ ፖለቲካ የሚቀጥል ከሆነ በቀጣይ ጥቂት አመታት ውስጥ ሀገሪቱ ትፈርሳለች። ስለዚህ አዲሱ ትውልድ እንኳን የመንግስት ስልጣን በሰላም የሚኖርበት ሀገር አይኖረውም። ኢትዮጵያ የፈረሰች ዕለት “ሁሉም ብሔሮች የድርሻቸውን ይወስዳሉ፤ የራሳቸው ሀገር መስርተው በጉርብትና በሰላም ይኖራሉ” የሚለው እሳቤ የቢሆን-ዓለም ቅዠት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የፈረሰች ዕለት ምስራቅ አፍሪካን የሚያጥለቀልቅ የደም ጎርፍ ይፈስሳል፣ ተቆጥሮ የማያልቅ ሬሳ ይከመራል። ያለ ምንም ጥርጥር ኢትዮጵያ የፈረሰች እለት ምስራቅ አፍሪካ ወደ ምድራዊ ሲዖል ይቀየራል።

ስለዚህ አዲሱ ትውልድ የትላንቱን ያረጀ ፖለቲካ ለማስወገድ፣ ዛሬ ላይ የሚስተዋለውን የብሔር ግጭትና መፈናቀል ለመግታት፣ በዚህም ነገ ላይ የሚከሰተውን አስከፊ ጦርነትና እልቂት ለማስቀረት ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ የሚያስፈልገው ከዚህ ኋላቀር የፀረ-ፖለቲካ ራሱን መላቀቅ ነው። ነገር ግን “ለውጥ” እና ፀረ-ለውጥ” በሚል በጅምላ መፈራረጅ ከቀጠለ ግን ማንም ሰው ቤቱ ውስጥ በሰላም ተኝቶ አያድርም። ላለፉት ሃምሳ አመታት በመጣንበት መንገድ ከቀጠልን እንኳን ሀገርና መንግስት ቤትና ንብረት አይኖረንም።

ምክንያቱም በፀረ-ፖለቲካ የአንዱ ስልጣን ሌላውን በመጣል፣ የአንዱ ድል ሌላውን በመግደል የተገኘ ነው። በዚህ የጥሎ ማለፍ ፖለቲካ ህይወት የሚገኘው በተቀናቃኞች ሞትና ውድቀት ነው። የአቋምና አመለካከት ልዩነት የመኖር እና አለመኖር ጉዳይ ነው። በዚህ ኋላቀር የፖለቲካ አመለካከት መሰረት ልዩነት ሞት ነው። በሰለጠነ ማህብረሰብ ዘንድ ግን፤ ልዩነት ለውጥ ነው፣ ልዩነት እድገት ነው! ልዩነት መማር፣ ልዩነት ማወቅ፣ ልዩነት ብስለት፣ ልዩነት ዕውቀት፣ ልዩነት ነፃነት ነው። አዎ… ልዩነት በራስ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ነው። ስለዚህ ልዩነት ሞት ሳይሆን መብት ነው።

በፖለቲካ መሪዎች መካከል የአቋምና አመለካከት ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ወደ ፀብና ግጭት ከመግባት ይልቅ ምክንያቱን እንጠይቅ፥ እንመርመር፥ እንወቅ፤ በልዩነቱ ዙሪያ እንነጋገር፥ እንምከር፥ እናስታርቅ። የተለየ ሃሳብና አመለካከት የተሻለ ሃሳብ ለማመንጨት እንጂ እርስ በእርስ ለመጋጨት ምክንያት ሊሆን አይገባም። ከእኛ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በጠላትነት ከመፈረጅ ይልቅ በሃሳብ እንሞግት። የራሳችንን እምነትና አመለካከት በሌሎች ላይ ለመጫን ከመጣደፍ ይልቅ በንግግርና ውይይት ለማሳመን እንጣር።

በመጨረሻ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት ሃምሳ አመታት ውስጥ የመጣበትን መንገድ፣ የፖለቲከኞቻችንን አመለካከትና አካሄድ፣ እንዲሁም ዛሬ ያለውን ነባራዊ እውነታ በዝርዝር ለመዳሰስ እንደ መነሻ የወሰድነው በትላንትናው ዕለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ኦቦ ለማ መገርሳ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ የሰጡት አስተያየት ነው። ምክንያቱም ኦቦ ለማ የሀገራችንን ፖለቲካ ከ1960ዎቹ ትውልድ ወደ 1990ዎቹ ትውልድ ለማሸጋገር በተደረገው ትግል ትልቅ ሚና የነበራቸው መሪ ናቸው። አዲሱ ትውልድ እስካሁን የነበረውን የፀረ-ፖለቲካ አመለካከት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ በማስወገድ በእኩልነትና ፍትህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ማሳካት አሊያም ማስተጓጎል የሚያስችል ድጋፍና ተቀባይነት አላቸው።

በመሆኑም የኦቦ ለማ አቋምና ውሳኔ ላለፉት አመታት የተደረገውን ትግልና የተከፈለውን መስዕዋትነት በከንቱ ሜዳ ላይ ሊያስቀረው አሊያም ደግሞ በተጨባጭ ትርጉም ያለው ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችል ነው። በብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ኦቦ ለማ የሚታዩት እንደ ለውጥ ብስራት፣ እንደ የትግል ችቦ ነው። ስለዚህ የኦቦ ለማ አቋምና ውሳኔ የብዙዎችን ተስፋ ሊያጨልም አሊያም ሊያለመልም ይችላል። እሳቸው የሚናገሩት ነገር ሀገርን ሊያሳድጋት ወይም ሊያፈርሳት ይችላል። በመንግስት ሆነ በፓርቲ ደረጃ ኦቦ ለማ ከሌሎች የለውጡ መሪዎች ጋር በሃሳብ ቢጣሉ የሚወዱት ህዝብ በጭካኔ ይገዳደላል።

ፎቶ፦ ዶ/ር አብይ አህመድ እና ኦቦ ለማ መገርሳ

ኦቦ ለማ ከትግል ጓዶቻቸው ጋር ያላቸውን የአቋምና አመለካከት ልዩነት በውይይትና ድርድር ከመፍታት ይልቅ በቁጣና ብስጭት ስሜት አደባባይ ሲያወጡት አምኖ ሲከተላቸው የነበረው ህዝብ በቋንቋና ኃይማኖት ይከፋፈላል። በአመራር ደረጃ ያለው የሃሳብ ልዩነት በቀጥታ ወደ ህዝብ ሲያወርዱት መከፋፈልና መለያየት ያስከትላል። በኦቦ ለማ ላይ ተስፋ የጣለው ህዝብ እርስ በእርስ ይጣላል። ይህን ግዜ በኦቦ ለማ መሪነት ለተሸነፉት ህወሓቶች ትንሳዔ ይሆናል። ህዝብን በግጭት በማተራመስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የነበራቸው ህልም እውን ይሆናል። አሁን ባለው ሁኔታ በለውጡ መሪዎች መካከል የሚፈጠር ልዩነት፣ በህዝብ ላይ ዕልቂት፣ በሀገር ላይ ውድቀት ይዞ ይመጣል። ስለዚህ የእናንተ መለያየት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሞት ስንቅ ነው! አዎ… በፀረ- ፖለቲካ መለያየት ሞት ነው!!!