የተፈጠረው ምንድነው? ዶ/ር አብይ ደርግ ሆነ ወይስ ኦቦ ለማ ህወሓት ሆነ?

አንድ የረጅም ግዜ ወዳጄ “የኦቦ ለማ ንግግር ሌላ መንግስቱ ኃይለማሪያም የስልጣን ማማ ላይ ካወጣን በኋላ እሱን መልሶ ለማውረድ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከመክፈላችን በፊት ልጓም እናብጅለት ነው” የሚል እንደሆነ ፅፎ ተመለከትኩ። በእርግጥ የወዳጄ ሃሳብ በከፊል ልክ ነው። ይህን ወዳጄን ጨምሮ ለከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀር “የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ነገሮችን በሰከነ መልኩ ማየትና መያዝ ካልቻሉ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ‘ቀዩ መንግስቱ ኃይለማሪያም’ ሊሆን ይችላል” ብዬ ተናግሬያለሁ። ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው በጭፍን ድጋፍ እና ተቃውሞ አማካኝነት እንደሆነ እገልፃለሁ።

በአንድ በኩል ጭፍን ድጋፍ በስልጣን ላይ ያለ መንግስትን በተጨባጭ ያለውን እውነታ ከማየት፣ የህዝብን ጥያቄና ብሶት ከመስማት ያግደዋል። የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ሲያነሱ ጥያቄያቸውን በአግባቡ ተቀብሎ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የፀረ-ልማትና ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሴራ፣ እንዲሁም በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ለማስወገድ የተደረገ እንቅስቃሴ እንደሆነ በመግለፅ በጉልበት ለማፈንና ለማዳፈን ጥረት ያደርጋል። በሌላ በኩል በህዝባዊ አመጽና ተቃውሞ ወደ ስልጣን የመጣ ቡድን ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጭፍን የሆነ ተቃውሞ ሲገጥመው፣ ልዩነቶችን በውይይት እና ድርድር ከመፍታት ይልቅ በአመፅና በጉልበት ከስልጣን ለማውረድ ጥረት የሚደረግ ከሆነ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን የመንግስትን መዋቅር፣ ሃብትና የፀጥታ መዋቅር ተጠቅሞ የአፀፋ እርምጃ ሊወስድ ይችላል።

ጠ/ሚ አብይ አህመድ እና የመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ (ከግራ ወደ ቀኝ)

በዚህ መሰረት በህዝባዊ አመፅ ወይም አብዮት አማካኝነት ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ቡድን ልክ እንደ ደርግ ወደ አምባገነንነት የሚቀየረው፤ አንደኛ በጭፍን ድጋፍ ምክንያት በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ማየትና መረዳት ሲሳነው፣ ሁለተኛ፡- ኃይል በተቀላቀለበት ጭፍን ተቃውሞ ምክንያት በተመሳሳይ የአፀፋ እርምጃ ከመውሰድ ውጪ ምርጫና አማራጭ ሲያጣ ነው። “መንግስታት አምባገነን የሚሆኑት በህዝባቸው ጥያቄ ነው” የሚባለው ለዚህ ነው። የመንግስት ስልጣን በያዘ ማግስት፤ በአንድ በኩል የዜጎችን የመብትና ተጠቃሚነት ጥያቄ መመለስ፣ በሌላ በኩል የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ሲሳነው፣ የመንግስትን መዋቅር፣ ሃብትና የሰው ኃይል ተጠቅሞ ነገሮችን በጉልበት ለማፈንና ለማዳፈን ጥረት ያደርጋል።

ዶ/ር አብይ ከላይ በተገለፀው አጣብቂኝ ውስጥ ቢገባ በመግቢያዩ ላይ እንደገለፅኩት “ቀዩ” መንግስቱ ኃይለማሪያም እንደሚሆን አትጠራጠሩ። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ “የዶ/ር አብይ አመራር በጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ወይ?” የሚለው ነው። እንደሚታወቀው የዶ/ር አብይ አመራር ከውስጥም ሆነ ከውጪ በጥርጣሬና ተቃውሞ የተሞላ ነው። ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን የመጣ ሰሞን ዲያስፖራዎች “የህወሓት ቅጥረኛ/ተላላኪ” ሲሉት ነበር። ህወሓቶች ደግሞ “ደርግ ነው፣ የአሜሪካ ቅጥረኛ ነው፣ የግብፅ ወዳጅ፣ የኢሳያስ ተወካይ፣ የአረቦች አገልጋይ፣…” ይሉታል። የአማራ ተቃዋሚዎች ደግሞ “ዶ/ር አብይ ኦነግ ነው፣ ጃዋር አማካሪው ነው፣ ተተኪነት ነው” ሲሉ ደቡቦች ደግሞ “ጨፍላቂ ነው፣ አምባገነን ነው፣ ኦሮማራ ነው” ይላሉ። የተቀረው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ “ዶ/ር አብይ ልፍስፍስ ነው፣ አቅመ ቢስ ነው፣ ፓስተር ነው! አፈ-ቅቤ ነው” ይላል። አሁን ደግሞ ኦቦ ለማ መገርሳ የዶ/ር አብይ ተቃዋሚ ሆነው መጥተዋል።

የዶ/ር አብይ አመራር የኃይል እርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፉ በጣም ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ተከስተዋል። ከእነዚህ ውስጥ፤ የሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት፣ የአብዲ ኢሌ የመጨረሻ ሳምንታት፣ በአዲስ አበባ በሚኖሩ የጋሞና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት፣ ቤተ መንግስት የገቡት ወታደሮች፣ የኦነግ-ሽኔ ትጥቅ አለመፍታትና በወለጋ የነበረው ወታደራዊ እንቅስቃሴ፣ በጉጂ ዞን የሚኖሩ የጌዶኦ ተወላጆች መፈናቀል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በኦሮሞና አማራ ተወላጆች ላይ የተፈፀመው ጥቃት፣ በሀረር ከተማ የሚታየው ውጥረትና ግጭት፣ በቴፒ ዞን በተደጋጋሚ የሚታየው ግጭትና አለመረጋጋት፣ በቦረና እና ጌሪ ጎሳዎች መካከል የነበረው ግጭትና ብጥብጥ፣ ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ፣ በምዕራብ ጎንደር ዞን በቅማንት ማህብረሰብ የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ፣ በከሚሴና አጣዬ አከባቢዎች የተፈጠረው ብጥብጥ፣ በአዊ ዞን ጃዊ አከባቢ የተፈጠረው ግጭት፣ በአማራ ክልል አመራሮች እና በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ የተፈፀመው ግድያ፣ በጃዋርና ህወሓት ጥምረት የተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የተፈጠረው ሁከትና ግድያ፣ በአፋርና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ በተደጋጋሚ የሚታየው ሁከትና ብጥብጥ፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታየው ግጭትና አለመረጋጋት እና የመሳሰሉትን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

ከላይ በተገለፀው መሰረት የዶ/ር አብይ አመራር በጭፍን ተቃውሚዎች፣ አክራሪ ብሔርተኞች እና ህወሓቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በፈጠሩት ጥምረት አማካኝነት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በሚያስነሷቸው ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ምክንያት የመንግስት መዋቅር፣ ሃብትና ተቋማዊ አቅምን ተጠቅሞ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ አጣብቂኝ ውስጥ ከትተውታል። በሌላ በኩል አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የዶ/ር አብይ መንግስት የኃይል እርምጃ በመውሰድ ነገሮችን ፀጥ-ለጥ እንዲያደርግ ግፊትና ጫና ከማድረግ አልፎ የፀጥታ መዋቅሩ አቅመ-ቢስ እንደሆነና የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስከበር እንደተሳነው እስከመግለፅ ተደርሷል።

“መንግስት አቅመ-ቢስ ነው” ብለው የሚንቁት ሆኑ “መንግስት ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅሟል” ብለው የሚወቅሱት ኃይሎች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ዶ/ር አብይ “ቀዩ” መንግስቱ ኃይለማሪያም እንዲሆን የሚማፀኑ መሆናቸው ነው። ነገሩ ከተራ የቃላት ጨዋታ አልፎ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት የዜጎች ህይወትን ከመቅጠፍ ወደ ቤተ መንግስት ወደታደር እስከማዝመት ደርሷል። በአንፃሩ የዶ/ር አብይ አመራር እነዚህ ኃይሎች በሚፈልጉት ደረጃ የኃይል እርምጃ ላለመውሰድ፣ በዚህም የመንግስቱ ኃይለማሪያምን ታሪክ ላለመድገም ሲታገል ቆይቷል። ዶ/ር አብይ እንደ ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያም የቀይ ሽብር ዘመቻን ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ የተፈጠረው ሰኔ 16/2010 ዓ.ም ላይ ነው። የሰኔ 16/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ለዚህ በቂ አልነበረም የሚል ካለ በአመቱ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በባህር ዳር እና አዲስ አበባ የተፈጠረው ችግር ከበቂ በላይ መሆኑን አይክድም። ይሁን እንጂ የዶ/ር አብይ አመራር የደርግን ስህተት ላለመድገም ተጠንቅቆ በመጓዝ ዛሬ ላይ ደርሷል። ወደፊትም ቢሆን በጭፍኖች ወጥመድ ውስጥ ይወድቃል ብዬ አላስብም።

በዚህ መሰረት ከ2010 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ባለው ግዜ ውስጥ ዶ/ር አብይ ልክ እንደ መንግስቱ ኃይለማሪያም ጨቋኝና አምባገነን እንዲሆን ከሚያስገድድ አጣብቂኝ ውስጥ ወጥቶ አያውቅም። ይሁን እንጂ እንደ መንግስቱ ኃይለማሪያም የመንግስትን ሙሉ አቅምና መዋቅር ተጠቅሞ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ተቆጥቧል። በዚህም የዓለም የሰላም ኖብሌ ሽልማት አሸናፊ ከመሆን ጀምሮ የኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶችን ውህደት ጫፍ ላይ ማድረስ ችሏል። አመራሩን ጠልፎ ለመጣል ከሚደረገው ያላሳለሰ ጥረት አንፃር እስካሁን ድረስ የለየለት ጨቋኝና አምባገነን አለመሆኑ በራሱ እንደ ትልቅ እምርታ ሊታይ ይገባል።

ለፅሁፍ መነሻ የሆነው “የኦቦ ለማ ንግግር ሌላ መንግስቱ ኃይለማሪያም የስልጣን ማማ ላይ ካወጣን በኋላ እሱን መልሶ ለማውረድ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከመክፈላችን በፊት ልጓም እናብጅለት ነው” የሚለው ሃሳብ ከዚህ አንፃር ሲታይ ሚዛን አይደፋም። ኦቦ ለማ መገርሳ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት መሰረት ከመጀመሪያው ጀምሮ የመደመር ፍልስፍናን የማይቀበሉና የኢህአዴግን ውህደት የሚቃወሙ ከነበረ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እያሉ ሂደቱን ማስተጓጎል ይችሉ ነበር። ከርዕሰ መስተዳደርነት ከወረዱ በኋላም ቢሆን እንደ ኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበርነታቸው የውህደቱን አካሄድ ማረምና ማስተካከል የሚችሉበት እድል ነበረ። ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እንደመሆናቸው መጠን ከእሳቸው ሃሳብና አመለካከት ፍፁም ተቃራኒ መልኩ የሚወክሉትን ሀገርና ህዝብ ጥቅም የሚፃረር ተግባር ሲፈፀም ማስቀየር አሊያም ማስቆም የሚችሉበት ስልጣንና ኃላፊነት ነበራቸው።

ይሁን እንጂ ኦቦ ለማ ከላይ ከተጠቀሱት አማራጮች አንዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍና ተቀባይነት ሳይኖራቸው፣ ወይም ደግሞ ሃሳባቸውን ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅምና አደረጃጀት መዘርጋት ተስኗቸው ቆይተው ቆይተው ከህወሃት በስተቀር ሁሉም የኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች ለመዋሃድ ሲስማሙ “አይ እኔ እኮ ከመጀመሪያው ጀምሮ አልተስማማውም ነበር” ማለት ተሸናፊነት ነው። “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ያሉት መሪ ለኢትዮጵያ አንድነት የህልውና አደጋ የሆነው የኢህአዴግ አደረጃጀትና ከፋፍለህ ግዛ ስርዓት ሊቀየር ሲል ተቃዋሚ መሆን “ባልበላው ጭሬ ላፍሰው!” የሚሉት ዓይነት አካሄድ ነው።

ድርጅቱ ስልጣን ከያዘበት ግዜ ጀምሮ የኢህአዴግን ውህደት ሲያቀነቅን የነበረው ህወሓት በ2010 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ከአቀንቃኝነት ወደ ተቃዋሚነት የተሻገረው ተሸናፊ ስለሆነ ነው። በተመሳሳይ ከ2010 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን ሲያቀነቅን የነበረው ኦቦ ለማ መገርሳ በ2012 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ከኢትዮጵያዊነት ወደ ብሔርተኝነት ያፈገፈገው ልክ እንደ ህወሓት ተሸናፊ ስለሆነ ነው። በአንፃሩ የዶ/ር አብይ አመራር ግን የኢህአዴግን ውህደት ሆነ የኢትዮጵያን አንድነት እውን ለማድረግ ከጫፍ ላይ ደርሷል። ይህን ደግሞ በስማ-በለው ወሬ ከሚጋልበው ግልብ ስሜታዊ ይልቅ ነገሮችን በጥሞና የሚያየው አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። የህዝብና ሀገርን ህልውና ማስያዢያ በማድረግ ተሸናፊነቱን በንፁሃን ህይወትና ንብረት ለማወራረድ የሚጥርን ግለሰብ ሆነ ቡድን የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም። በመሆኑም በቅድሚያ እንዲታረም ይመክረዋል፣ አልሆን ሲል ደግሞ አንቅሮ ይተፋዋል። እንዲህ እያለ ይቀጥላል….!!!

2 thoughts on “የተፈጠረው ምንድነው? ዶ/ር አብይ ደርግ ሆነ ወይስ ኦቦ ለማ ህወሓት ሆነ?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡