ህወሓት የወላይታ ህዝብ ጠላት የሆነበት 5 ምክንያቶች!

የደቡብ ክልል ዓቃቤ ህግ የወላይታ ምድብ ፅ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት የወላይታ ተወላጅ የህግ ባለሙያ አቶ ጸጋዬ ማቲዎስ <<ወላይታ የሴረኞች ምሽግ እንድትሆን አንፈቅድም>> በማለት የሚከተለውን ሰፊ ሀተታ ጽፈውልናል።

ህወሃት የተባለው የሽብርተኛ ቡድን ላለፉት 28 ዓመታት የመላ ሀገሪቱን ፖለቲካ ሥልጣን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ በነገሰበት ጊዜ ሁሉ ህዝብን በብሔር፣ በጎጥና በሃይማኖት ከፋፍሎ እርስ በርስ በማጋጨትና በማገዳደል ለዘመናት የተገነባውን የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነትና ትስስር ለመበጣጠስና ብሎም አገርን ለማፈራረስ የወጠነው ሴራ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ለሞት፣ ለእስራት፣ ለአካላዊና ሥነልቡናዊ ስቃይ፣ ለስደት ዳርጓቸዋል፡፡

ብሔር ብሔረሰብ ራስን በራስ ማስተዳደር በሚል ሽፋን ከእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ የሚመለምላቸውን ሆድ-አደር ካድሬዎች መረማመጃ አድርጎ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ በፈፀመው ሌብነት፣ ዘረፋ፣ አፈናና ሽብር በኢትዮጵያ ታሪክ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የህወሃት ቡድን ብሶት በወለደው በህዝባዊ ዐመፅ ከዙፋኑ ተንከርብቶ ወደ መቀሌ ከፈረጠጠ ሁለት ዓመታትን ደፍኗል፡፡ ህወሃትን ወደ ስልጣን ላመጣው የኢትዮጵያ ህዝብ ውለታ የህወሃት ምላሽ “ወርቅ ላበደረው ጠጠር” ሆነና “ደርግ ማረን” ለማለት አብቅቷል፡፡

ለመብቱና ለፍትህ የጮኸን ሁሉ “ሽብርተኛ” “ፀረ-ሠላም” “ፀረ-ህዝብ”… ወዘተ በሚል እየወነጀለ ወደ ማሰቃያ ካምፕ ሲያጉር እንደነበር ማንም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ብቻ ሳይሆን ራሱ ህወሃትና ተባባሪዎቹ በአደባባይ ያመኑት ሀቅ ነው፡፡ የህወሃቶች ግብ ናዚዎች የጀርመንን ህዝብ አሳስተው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ጀርመንን የመሰለ ትልቅ ሀገርና ህዝብ ለውድቀትና ለውርደት የዳረጉበትን አሳፋሪ ታሪክ በኢትዮጵያ ላይ ለመድገም እንደሆነ በ27 ዓመት አገዛዛቸው ወቅት የፈፀሟቸው ሴራዎች ህያው ማሳያዎች ናቸው፡፡

በደርግ መወገድ ማግስት ህወሃት ወደ መንበረ ሥልጣኑ ሲወጣ ስለኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት ሲያሰማ የነበረው ዜማ የሐሰት መሆኑንና ሲያፈስ የነበረውም የዐዞ እንባ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ የተረዳው ገና የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ሳያበቃ ቢሆንም ታጋሹ የኢትዮጵያ ህዝብ እየደማም እየቆሰለም፣ እየተጠማ እየተራበም ህወሃት እንዲታረም የሰጠውን ረጅም ጊዜ ሁሉ ጆሮ ዳባ ያለው ቡድኑ የህዝብን ትዕግስት እንደ ፈሪነት የራሱን እኩይ ድርጊት ደግሞ እንደ ጀግንነት ቆጥሮ ሁሉንም ጥያቄ በጉልበት መፍታትን ብቸኛ መንገድ አድርጎ ለዘለዓለም ለመኖር ተግቷል፡፡

ከስህተትና ከነውር አለመታረም መጨረሻው ውርደት መሆኑ አይቀርምና የዛሬ 28 ዓመት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ/ም “ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት…..” በሚል ፉከራና ቀረርቶ የምኒልክን ቤተመንግስት የተቆጣጠረው ህወሃት በተራው እሳትና ብሶት በወለደው በጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብ ተጋድሎ ወላፈን ተለብልቦ ጨርቄን ማቄን ሳይል በጓሮ በር ወደ መጣበት ለመፈርጠጥ ተገድዷል፡፡

“ያደቆነ ሰይጣን……” እንዲሉ ህወሃት በአደባባይ ለዓመታት ሠርቶ ያልተሳካለትንና የወደቀበትን የሴራ ፖለቲካ ዛሬም በመቀሌው ምሽግ ሆኖ በስውር እጁ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ህወሃት በአመራር ሰጭነትና በቀጥታ ተሳትፎ ሞክሮ ያልተሳካለትን ህዝብን የመከፋፈልና የማተራመስ አጀንዳ ከቤተመንግሰቱ ከተባረረበት ማግስት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በእጅ አዙር የቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊና ሥነልቡናዊ ቀውስ ታሪክ የሚረሳው አይደለም፡፡

ህወሃቶች በአንድ በኩል “የለውጡ አካል ብቻ ሳይሆን የለውጡ ቀያሽም መሪም ነን” እያሉ በሌላ በኩል ለውጡን ለመቀልበስ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ለውጡንና የለውጥ ኃይሎችን በይፋ ከመኮነንና ከማጥላላት ባሻገር የለውጥ መሪዎችን ለመግደል በአደባባይ ባደረጉት ሙከራ አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ የሴራና የሽብር ስራ የሚውሉ የጦር መሳሪያዎች ግዢ እና ተልኮአቸውን ለሚፈፅሙላቸው ቅጥረኞቻቸው የሚከፈለው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ምንጩ ህወሃቶች በሥልጣን ዘመናቸው ሁሉ ንፁህ ውሃ ካላገኘው ደሃው የኢትዮጵያ ህዝብ የተዘረፈ መሆኑን መጠራጠር አያስፈልግም፡፡

ህወሃቶች ከህዝቡ የዘረፉትን ሀብት መልሰው ህዝቡን ለመግደልና ለማሰቃየት የሚያውሉ ጨካኞች ናቸው፡፡ የመጠን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ይህ የህወሃት ሴራ በሀገሪቱ ውስጥ ያልዳሰሰው አካባቢና ያላቆሰለው ህዝብ የለም፡፡ ትላንት እነርሱ (ህወሃቶች) በስልጣን በነበሩበት ጊዜ በአሸባሪነት፣ በትምክህተኝነት፣ በጠባብነት፣ በተላላኪነት…ወዘተ ሲከሷቸውና ሲያሳድዷቸው የነበሩትን ግለሰቦችና የብሔር ነጋዴ ፖለቲከኞችን ከሀገር ዙሪያና ከውጭ ሀገር እየጠሩ መቀሌ ላይ እየሰበሰቡ መመሪያና መሳሪያ እያስታጠቁ በየክልሎቹ በማሰማራት መላ ሀገሪቱን በማተራመስ ስራ ተጠምደው ይገኛሉ።

ለሴራ ተልዕኮው ህወሃት በደቡብ ክልል ከመረጣቸው አካባቢዎች አንዱ ወላይታ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ ፍንጮች አሉ፡፡ ህወሃት በሥልጣን በነበረበት ዘመን ከፍተኛ ጥቃት ከፈፀመባቸው ህዝቦች አንዱ ወላይታ እንደሆነ የወላይታ ህዝብ ያውቃል፡፡ የወላይታን ማንነት ለማጥፋት አስቦ የወሰዳቸው የጭካኔ እርምጃዎች ህዝባችንን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉ ከማናችንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ወላይታ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ ጥያቄን በማንሳቱ ብቻ ህዝቡን በጥይት ያጨደው ህወሃት የክልል ጥያቄ ማቅረብ “ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን መቃወምና ማፍረስ ወንጀል” በሚል ባልተፃፈ ህግ እየወነጀለና እየከሰሰ ለሩብ ምዕተ ዓመት የህዝቡን ጥያቄ ባፈነበት አንደበቱ ዛሬ ራሱ ከስልጣን ስለተባረረ የወላይታና የሌሎችም ህዝቦች የክልል ጥያቄ ህገመንግስታዊ ስለሆነ ሊከለከል አይገባም በማለት በአደባባይ መግለጫ ሲያወጣ ይሰማል፡፡

የህወሃትን መውደቅ ተከትሎ ህዝቦቹ ላነሷቸው የክልል ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መንግስት ጥናት ላይ እንደሆነ በገለፀበት ባሁኑ ሰዓትም የህወሃት ሰዎች የወላይታ ህዝብ መብቱን እንደተከለከለ አስመስለው ህዝቡን ለሁከት ሲያነሳሱ ይስተዋላል፡፡ የዚህ ቅስቀሳ ዓላማው ለወላይታ ህዝብ መብት በማሰብ ነው ብሎ የሚያምን ካለ ህወሃትን የማያውቅ ሰው ነው፡፡ ቆሻሻ ባለበት ዝንብ እንደማይጠፋ ሁሉ ነውጥና ሁከት ባለበት ህወሃት አይጠፋም ብቻ ሳይሆን ሁከት በሌለበትም ሁከት ካልፈጠረ እንቅልፍ የማይወስደው ድርጅት ነው፡፡ በመሆኑም የወላይታ የክልል ጥያቄ ምላሽ አላገኘም የሚለውን የህዝብ ቅሬታ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ህዝቡን በለውጥ ኃይሉ ላይ ለመቀስቀስና ወላይታን ማዕከል አድርጎ በክልሉ ውስጥ ትርምስ ለመፍጠር ማሰፍሰፍ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ህወሃት ዛሬ የአክሱምን ሀውልት ምስል ለወላይታ በስጦታ ሲያበረክት ትላንት “የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው?” ሲል የተናገረውን ረስቶ ሳይሆን ቅጥፈትና መሰሪነት የህወሃት ተፈጥሮአዊ መገለጫ በመሆኑ በእኩይና ነውረኛ ተግባር የሚያፍርበት ስብዕና የሌለው ቡድን መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ባህርይው ደግሞ ህወሃት ምን ጊዜም በችግር ፈጣሪነትና የችግሩ አካል በመሆን እንጂ መፍትሔ ሲያመጣ ስላላየን የወላይታ ህዝብ የሚያነሳው የክልል ጥያቄም ሆነ ሌላ ማናቸውም ህጋዊ መብቱን ለመጠየቅና ምላሽ ለማግኘት የህወሃት ድጋፊ አያስፈልገውም፡፡ እንኳን ክልል ሊሰጠን “የራሴን ቋንቋ ልናገር” በማለቱ ብቻ ህዝብ ላይ ጦር ያዘዘው ህወሃት ዛሬ ክልል ለመስጠትም ሆነ ለማስሰጠት የሞራል ብቃት የለውምና፡፡

ምናልባት ህወሃት ልማትን አመጣለሁ በሚል ህዝቡን ከማታለል እንደማይቆጠብ ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡ ህወሃት ልማትን ለማምጣት ሐሳብም ሆነ ፍላጎት የሌለው መሆኑን በአገዛዝ ዘመኑ በተጨባጭ ያየነው ጉዳይ ነው፡፡ የህወሃት ልማት “ዶሮ ታምማ በግ ታረደላት” እንደሚባለው አንድ መቶ ልማት ለማምጣት አንድ ሚሊዮን የሚያለማ ሀብት የሚዘርፍ ሌባ ድርጅት እንደሆነ በአደባባይ የተዘከዘከው የ27 ዓመት የወንጀል ታሪኩ ይመሰክራል፡፡ ምንም የረባ ልማት ሳያመጣ በሐሰት ፕሮፓገንዳና በባዶ ተስፋ ህዝቡን ሲያጃጅል እንደኖረ ህወሃት ከራሱ አንደበት በተደጋጋሚ መስክሯል፡፡ ህወሃት ራሱ ልማት አለማምጣት ብቻ ሳይሆን ጥቅሙ በተነካ በማንኛውም ጊዜ አስቀድሞ ህዝቡ በላቡና በወዙ ያመጣውን ልማት ጭምር በአንድ ጀምበር አመድ ከማድረግ የማይመለስ ሽፍታ ቡድን ነው፡፡ በመሆኑም ከህወሃት ልማትን መመኘት ውጤቱ “አተርፍ ባይ አጉዳይ” ይሆናል፡፡

በመሆኑም ማንም ግለሰብ ራሱን ብቻ ወክሎ ከህወሃቶች ጋር በግል የመገናኘትና የመፋቀር መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ውጭ ግን በወላይታ ህዝብ ስም ከህወሃት ጋር ምንም ዓይነት አጀንዳ የሚጋራ ግለሰብም ሆነ አመራር ካለ ነገ በአካባቢውና በህዝቡ ላይ ሊመጣ ስለሚችለው ማንኛውም አደጋ ከወዲሁ ሃላፊነት ሊወስድ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በጉብዝና ወራቱ ህዝባችንን፣ ቋንቋችንን፣ ማንነታችንን የረገጠው ህወሃት ከመንግስትነት ተባርሮ በሽብርተኝነት በተሰማራበት ሰዓት ከህወሃት ጋር ዝምድና መፍጠር በራስ አንገት ገመድ ማስገባት ነው፡፡ የወላይታ ህዝብ አሁን በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ ተጠቅሞ ልማቱን በማፋጠንና ለውጡን በመደገፍ በፍጥነት ከግብ ለማድረስ ከለውጥ ሃይሉ ጎን ተሰልፎ ፀረ-ለውጥ ኃይሎችን በማጋለጥና በመታገል የሚጠበቅበትን አገራዊ ሃላፊነት በፅናት መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

ለወላይታ ህዝብ የሚጠቅመው የክልል ጥያቄም ሆነ ማናቸውንም ህጋዊ መብቶቹን በሠላማዊ መንገድ መጠየቅና ውጤቱን በትዕግስት መጠባበቅ እንጂ ወደ ፀብና አላስፈላጊ ግጭቶች ገብቶ የነውጠኛ ኃይሎች ስውር ሴራ ማስፈፀሚያ መሆን አይደለም፡፡ ህወሃት እንኳን ለወላይታ ህዝብ ውግንና ሊቆም ቀርቶ ወከልኩ በሚለው በትግራይ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልጆችን ምን ያህል እያሰቃየ እንዳለ በተጨባጭ የምናውቀው እውነታ ነው፡፡ የወላይታ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ፀቡ ከህወሃት ጋር እንጂ ወንድም ከሆነው ንፁሁ የትግራይ ህዝብ ጋር አንዳች ፀብ እንደሌለው ተገንዝበን ሽፍታውን የህወሃት ቡድን ከትግራይ ህዝብ ነጥሎ ማየትና የትግራይ ህዝብም ከህወሃት ጭቆናና አፈና ነፃ ለማውጣት በሚያደርገው ትግል አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ህወሃት የሸረሸረውን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ዳግም ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡

“ህወሃት ለወላይታ ህዝብ አስፈላጊ አይደለም” ለማለት ከሚያበቁን ምክንያቶች መካከል በህወሃት አገዛዝ ዘመን በወላይታ ህዝብ ላይ ከፈፀማቸው ወንጀሎችና በደሎች መካከል የሚከተሉትን ማስታወስ በቂ ይሆናል፡፡

1) የአረካ ጭፍጨፋ

በደርግ መውደቅ ማግስት ህወሃትን በደስታና በእልልታ የተቀበለው የወላይታ ህዝብ ሥርዓቱን የተዋወቀው 200 ንፁሐን ዜጎችን ደም ለህወሃት ቦምብ በመገበር ነው፡፡ የህወሃት ሠራዊት ወላይታን በተቆጣጠሩ በቀናት ዕድሜ ውስጥ በአረካ ከተማ የሚቆመው ትልቁ ገበያ ቀን አገር ሠላም ብሎ ገበያ እየተገበያየ በነበረው ህዝብ መሐል ቦምብ ወርውረው በአንድ ቀን የ200 ንፁሃን ዜጎች ደም (አረጋዊያንን፣ እናቶችንና ህፃናትን ጨምሮ) በከንቱ ያፈሰሰው የህወሃት ሠራዊት ህግ ፊት አልቀረበም፣ የሟቾችና የተጎጂዎች ቤተሰቦች ካሳ አልተከፈላቸውም፣ ሠራዊቱን ያሠማራው ህወሃት እንደ መንግስት ኃላፊነት ወስዶ ይቅርታ እንኳን አልጠየቀም፡፡

2) በወላይታ ማንነት ላይ የተፈፀመው ወንጀል

የወላይታ ብሔር የራሱ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህልና መልክዓ ምድር ያለው ህዝብ ነው፡፡ ይህ ማንነቱ ህወሃት የሰጠው ሳይሆን ከዛሬ 2ሺ ዓመታት በፊት ጀምሮ የራሱ ፖለቲካዊ አስተዳደር ሥርዓት የነበረውና የመንግስትነት ህልውናው እስካከተመበት እስከ 1887 ዓ/ም ድረስ ከ50 በላይ በራሱ ነገሥታት ሲተዳደር የኖረበት የሉዓላዊ ሥልጣንና ብሔራዊ ማንነት የነበረው ህዝብ ነው፡፡ ምኒልክ በፈፀመው የማዕከላዊ መንግስት ምስረታ ወረራ የወላይታ ብሔር የመንግስትነት ህልውናውን ቢነጠቅም እስከ ደርግ ሥርዓት ማብቂያ ድረስ ወላይታ በአውራጃ ደረጃ መንግስታዊ መዋቅር ሲተዳደር ቆይቷል፡፡
ነገር ግን የታገልኩት ብሔር ብሔረሰቦች ከማዕከላዊ መንግስት ጭቆና ነፃ እንዲወጡ፣ ማንነታቸው እንዲታወቅና እንዲከበር፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ…ለማስቻል ነው እያለ የዛሬ 28 ዓመት የመጣው ህወሃት የወላይታን ብሔር ማንነት ባለመቀበል ከነበረበት አውራጃዊ አስተዳደርም አውርዶ በወረዳዎች በመከፋፈል ወላይታን ጨምሮ ከ12 የማያንሱ ብሔረሰቦችን አንድ ላይ በመጨፍለቅ “የሰሜን ኦሞ ህዝቦች” የሚል ፈጠራ ማንነት ለጥፎ በአንድ ዞን (ሰሜን ኦሞ) ጠቅጥቆ “ወጋጎዳ” የሚባል እንግዳ ቋንቋ ፈጥሮ የእነዚህ ሁሉ ብሔረሰቦች የጋራ መግባቢያ እንዲሆን በማዘዝና በሓይል በመጫን የወላይታን ማንነት ለማክሰም የወሰደው ህገወጥ እርምጃ ብሔረሰቡን ለ10 ዓመታት ያህል ዋጋ አስከፍሎታል፡፡

3) የወላይታ ህጋዊ ጥያቄና የህወሃት ህገወጥ ምላሽ

ማንነቱን ተነጥቆ አዲስ ማንነት የተጫነበት የወላይታ ህዝብ ማንነቴ ይመለስልኝ፣ ቋንቋዬን ልናገር፤ ራሴን በራሴ የማስተዳድርበት የዞናዊ መዋቅር ይሰጠኝ… በማለት ያነሳውን ህገመንግስታዊ ጥያቄ ህወሃት/ኢህአዴግ ጆሮ-ዳባ በማለቱ ጥያቄውን በአደባባይ ለማሰማት ሠላማዊ ሠልፍ መውጣቱን “የመንግስት ግልበጣ ሙከራ” በሚል ውንጀላ በሺዎች የሚቆጠርና እስከ አፍንጫው የታጠቀ መከላካያ ሠራዊት ከወረቀትና ከባዶ እጅ ውጭ ምንም ባልያዘው ህዝብ ላይ በማሠማራት በዕለቱ በወሰደው እርምጃ በጥይት ከተገደሉ 5 ተማሪዎች በተጨማሪ ከዕለቱ ጀምሮ ለሳምንታት ጊዜ በተከታታይ በፈፀመው የድብደባ፣ የእስራትና የማሰቃየት እርምጃ በደረሰባቸው ጉዳት ውሎ አድሮ ህይወታቸውን ያጡ፣ አካለ ጎዶሎ የሆኑ እንዲሁም የጭካኔ እርምጃውን በመፍራት የተሰደዱ፣ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የብሔሩ ተወላጆች (ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሌሎች የመንግስት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች …ወዘተ) የህወሃት ህገወጥ እርምጃ ሰለባ ሆነዋል፡፡

4) ለህወሃት ሥልጣን ማራዘሚያ የወላይታን መሬት የመንጠቅ ሴራ

ወላይታና ሲዳማ አጎራባች ህዝቦች ሲሆኑ የሚያዋስናቸውም ክረምት ከበጋ የማይደርቀው ትልቁ የብላቴ ወንዝ የተፈጥሮ ወሰን ሆኖ ከጥንት ጀምሮ በሁለቱ ህዝቦች ታምኖ የቆየ እንደመሆኑ እስከ ህወሃት/ኢህአዴግ መምጣት ድረስ በመካከላቸው አንድም ጊዜ የመሬት ይገባኛል ጥያቄና የወሰን ክርክር አልተነሳም፡፡ የብላቴ ወንዝ ወሰንነት ዛሬ የሚታወቅ ሳይሆን የቀድሞ የወላይታ አውራጃና የሲደማ አውራጃ ከተፈጠሩበት ጊዜም ጀምሮ በአዋሳኝነት የታወቀ፤ ቀጥሎም ከደርግ ውድቀት ዋዜማ ጀምሮ የሰሜን ኦሞ ዞንና የሲዳማ ዞን አዋሳኝ ሆኖ የቀጠለና እስከ ዛሬ በአካባቢው ምንም ዓይነት የአከላል ለውጥ ሳይደረግበት ዛሬም በቦታው ያለ የተፈጥሮ ወሰን ነው፡፡

ነገር ግን ይህን እውነታ በመካድ ጥቂት የፖለቲካ ነጋዴዎች ለፖለቲካ ትርፍና እርካሽ የህዝብ ተወዳጅነት ለማግኘት አስበው “ሲዳማ ከብላቴ ባሻገር (ወላይታ ክልል ውስጥ) መሬት አለው” በማለት በሁለት ሠላማዊ ህዝቦች መካከል የጫሩት እሳት ከሁለቱም ወገን የበርካታ ንፁኃንን ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሰ ቢሆንም ከግጭት ማትረፍ የህወሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎችና የሥርዓቱ ዓይነተኛ መገለጫ እንደመሆኑ የብሔር ነጋዴዎች ራሳቸው ያነሱትን ጥያቄ የህዝቡ ጥያቄ አስመስለው ወደ ፖለቲካ አጀንዳነት አሸጋግረው ህዝቡን ሲቀሰቅሱና ክስ ሲያቀርቡ ቆይተው በ1997 ምርጫ የተከሰተውን የህወሃት ውድቀት ተጠቅመው “በሲዳማ ዞን ኢህአዴግ የተሸነፈው የሲዳማን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ምላሽ ባለመስጠቱ ነው” የሚል ሰበብ በማቅረብና ድጋሚ ለሚደረግ ምርጫም እንደቅድመ-ሁኔታ በማስቀመጥ የህወሃትን እጅ መጠምዘዝ ቻሉ።

መቼም ቢሆን በሥልጣኑ የማይደራደረውና እንኳን የወላይታን መሬት የወላይታን ህዝብ አሳልፎ ከመስጠት የማይመለሰው ህወሃት በመሪው በአቶ መለስ በኩል ለፌዴሬሽን ም/ቤት ባስተላለፈው ቀጭን ትዕዛዝ መሬቱ የሲዳማ ነው ተብሎ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ አካባቢው የፈንጂ ቀጠና ሆኖ ወቅት እየጠበቀ ሲፈነዳ ቆይቷል፡፡ በውሳኔው መሠረት ወሰን ለማካለል በተለያየ ጊዜ ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ውሳኔው የታሪክም የህግም መሠረት የሌለው በመሆኑ ጥያቄው የተነሳበትም ሆነ ውሳኔው ያረፈበት መሬት እስከየት ነው የሚለው ጥያቄ ሁለቱን ወገን አለማስማማት ብቻ ሳይሆን ጠያቂው ወገን ራሱ ስለጠየቀው መሬት እርስ በርስ ሊግባባ ባለመቻሉ ውሳኔው በአካባቢውና በሁለቱ ህዝቦች መካከል የፈጠረው ውጥረት ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡

5) በወላይታ ላይ የተፈፀመ የሞራል ጥቃት

እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ በራሱ መልክዓምድር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሉዓላዊ መብት ያለው ከመሆኑም በላይ በጋራ በሚመሠርቱት ክልል እና በፌዴራሉ መንግስት ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና ይዞ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ከሌሎች ጋር የመሳተፍ እኩል መብት አለው፡፡ ከዚህ መብት አንፃር በማንኛውም መስፈርት በበላይነትና በበታችነት የሚፈረጅ ህዝብ የለም፡፡ ህወሃት ግን ይህን ሀገመንግስታዊ መርህ በመጣስ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በተለያየ ደረጃ ፈርጆ የሚያከብራቸው፣ የሚንቃቸው፣ የሚጠላቸውና የሚወዳቸው፣ የሚያጠቃቸውና የሚጠብቃቸው…ወዘተ እንዳሉ በተግባር ሲያረጋግጥልን የኖረ ዘረኛ፣ ቡድንተኛና አድሎአዊ ድርጅት ነው፡፡

በ56 ብሔረሰቦች የተመሠረተውን የደቡብ ክልል ከምስረታው ጀምሮ በርዕሰ-መስተዳድርነት የመራውና የሲዳማ ተወላጅ የሆነው አቶ አባተ ኬሾ ከ10 ዓመት በላይ ክልሉን ከመራ በኋላ በህወሃት ውሳኔ የወላይታ ተወላጅ በሆነው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መተካቱ ያላስደሰታቸው የብሔር ነጋዴ ካድሬዎች “ክልሉን የሲዳማ ተወላጅ ካልመራ የራሳችንን ክልል እንመሠርታለን” የሚል የጠባብነትና ኢ-ህገመንግስታዊ ጥያቄ አንስተው ባቀነቀኑበት ወቅት የህወሃቱ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ህገመንግስታዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የጥገኛውን ጥያቄ በማስተናገድ አቶ ኃይለማርያምን አንስቶ አቶ ሺፈራው ሽጉጤን የሾመበት ውሳኔ ህወሃት ለህግና ህገመንግስት ደንታ የሌለው፤ ማንኛውንም ውሳኔ ከራሱ ሥልጣንና ጥቅም አንፃር የሚወስን ጥገኛ ድርጅት መሆኑን ያመላከተና የወላይታ ብሔረሰብን በበታችነት የፈረጀበት በመሆኑ በብሔረሰቡ ላይ ታሪክ የማይሽረውን የሥነልቡና ጠባሳ ያኖረ ውሳኔ ነው፡፡

ተጠያቂው ማነው?

በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈፀመው መንግስታዊ ወንጀል በመጠንም በዓይነትም በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩና እጅግ የከፋ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ነው፡፡ እንደ ህዝብም ሆነ እንደ ዜጋ የወንጀሉ ሰለባዎች ቁጥር እንደዚሁ አቻ የማይገኝለት ጥቁር የታሪክ ምዕራፍ የተመዘገበበት ነው፡፡ መንግስታት በየትኛውም ዘመን በየትኛውም አገር ወንጀል ሊፈፅሙ ይችላሉ፡፡ መንግስታዊ ወንጀሎችን ከሚያመሳስሉ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የወንጀሉ ዓላማ የገዥዎችን የሥልጣን ዘመን ማራዘም መሆኑ ነው፡፡

ነገር ግን ከየትኛውም ወንጀለኛ መንግስት ህወሃት/ኢህአዴግን ልዩ የሚያደርገው የወንጀሉ ዋነኛ ዓላማ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን ለማሳካት የተጠቀመበት ሀገር የመበተንና በህዝቦች መካከል ዘላቂ ጥላቻና የርስ በርስ ጦርነት የመፍጠር ሴራ በየትኛውም አገር መንግስት ያልታየና ያልታሰበ ነገር ግን ህወሃት/ኢህአዴግ አቅዶና አስቦ የፈፀመው ስትራቴጂ መሆኑ ነው፡፡

የዚህ ሰይጣናዊ ስትራቴጂ ቀያሽና መሪ ህወሃት ቢሆንም ተጠያቂው ግን ህወሃት ብቻ እንዳልሆነ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን ወንጀሎች በወላይታ ላይ ያስፈፀመው ህወሃት ቢሆንም የገዛ ህዝባቸውን በሆዳቸው ሸጠው በቀጥታ ከህወሃት ትዕዛዝ እየተቀበሉና ከህወሃት ጋር አብረው እየወሰኑ የህወሃት ፈረስ ሆነው በህዝባቸው ላይ ታሪክ ይቅር የማይለውን ወንጀል የፈፀሙት በወላይታ ህዝብ ስም በየመንግስት መዋቅሩ የተሰገሰጉ ከሀዲዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ወንጀሎች በወላይታ ህዝብ ላይ በሚፈፀሙበት ጊዜ በፌዴራልና በክልል የመንግስት መዋቅሮች ሆነው የህወሃትን ትዕዛዝ ከሚቀበሉና አብረው ከሚወስኑት ጀምሮ ወንጀሉን በማስፈፀም በቀጥታ የተሳተፉት የዞንና የወረዳ የፊት አመራሮች ጭምር በምኒልክ ወረራ ዘመን የንጉስ ጦናን ሠራዊት ለሽንፈት ከዳረጉ የወላይታ ተወላጅ ባንዳዎች ተለይተው የሚታዩ አይደሉም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የህወሃት ባንዳዎችና የወላይታ ህዝብ ጠላቶች በመሆናቸው በዘመናቸው በወላይታ ህዝብ ላይ በፈፀሙት ወንጀል በህግ ባይጠየቁ እንኳን አሳፋሪ ድርጊታቸው በወላይታ ህዝብ ታሪክ ተፅፎ ለልጅ ልጆቻቸው ማፈሪያ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑ አይቀርም፡፡

የህወሃት/ኢህአዴግ ወንጀል በወላይታ ህዝብ ላይ ብቻ የተፈፀመ ሳይሆን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ዜጎቻቸውን እንደ ክፉ ወረርሽኝ ያዳረሰ ነው፡፡ በአንዳንዶቹ ላይ (አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ…ወዘተ) የተፈፀመባቸው ዘግናኝ ወንጀል ጋር ሲነፃፀር የወላይታ ጥቃት ኢምንት ነው ያስብላል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች የወንጀሉ ቀያሽና መሪ ህወሃት ቢሆንም በቀጥታ ፈፃሚዎችና አስፈፃሚዎች በየብሔሩ ስም በህወሃት ጉያ የተሰገሰጉ ባንዳዎች መሆናቸው የሚደበቅ አይደለም፡፡ ሁሉም ተጠያቂ ሆነው ህግ ፊት የሚቀርቡበት ጊዜ አይመጣም ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡ አንድ ቀን ህዝብ እንደሚፋረዳቸው ተስፋ መሰነቅና ቢያንስ ቀጣዮቹ ባለጊዜዎች ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈፅሙ ህዝቡ ሉዓላዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ የመንግስትን ልጓም በእጁ ይዞ አምባገነንና ወንጀለኛ መንግስትን ጊዜ ሳይሰጥ ህግ ፊት እያቀረበ በመቅጣት የህግ የበላይነት የተረጋገጠበትንና መብቱ በምልዓት የሚከበርበትን ሥርዓት እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዞ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ በመውሰድ ዘላቂ መፍትሔ ራሱ ህዝቡ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡

ባጠቃላይ ህወሃት የተባለው ጠባብ ቡድን እንኳን ለወላይታ ቀርቶ ወከልኩ ለሚለው ለትግራይ ህዝብ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ ይህን ሸፍጠኛ ቡድን አምኖ ጥሪውን ተቀብሎ በትጥቅ ትግል ወቅት ልጆቹንና ሀብት ንብረቱን ገብሮ ለሥልጣን ያበቃው የትግራይ ህዝብ ንፁህ ውሃ አጥቶ ሲቸገር ህወሃቶቹ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በውጭ ባንኮች እያከማቹና በአሜሪካና አውሮፓ ከተሞች የግዙፍ ህንፃዎች ባለቤት መሆን የቻሉበትን የሀገር ሀብት ሲዘርፉ የትግራይን ህዝብ ድርሻ አስቀርተው አይደለም፡፡ በውሸት የልማት ፕሮፓገንዳ የኢትዮጵያን ህዝብ ባዶ ተስፋ እያበሉ ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው በምቾት ጣሪያ ላይ ሲንደላቀቁ በአንፃሩ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው ለሥልጣን ያበቋቸውን መቶ ሺዎች የትግራይ ሰማዕታትን ታሪክ ለራሳቸው ፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ከማዋል በዘለለ ስለሰማዕታቱ ደንታ-ቢሶች ናቸው፡፡

ለዚህም በውጊያው የተለያየ አካል ጉዳት ደርሶባቸው በህይወት ቢተርፉም ሠርተው መብላት የማይችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኛና ጀግና የትግራይ ልጆች ዛሬ አስታዋሽ አጥተው እዚያው ትግራይ ውስጥ የሚገፉት የመከራ ህይወት በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በተጨማሪም ከ27 ዓመት የአፈና አገዛዝ በኋላ በኢትዮጵያ ህዝብ ተጋድሎ ተባርሮ መቀሌ ላይ የመሸገው ህወሃት የትግራይን ህዝብ ለክፉ ቀን መደበቂያነት ከመጠቀም በዘለለ አንዳች የተለየ ውግንና ኖሮት አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሌላው ቀርቶ የትግራይ ህዝብ አማራጭ መገናኛ ብዙኃን እንኳን እንዳያዳምጥ፣ ከህወሃት ውጭ የማንንም ሀሳብ እንዳይቀበል፣ ማንኛውም ተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት በትግራይ ውስጥ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስ…ወዘተ በክልሉ በዘረጋው የተለያየ የአፈና መዋቅር ህዝቡን መፈናፈኛ አሳጥቶ መያዙ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ስለዚህ ከእንደዚህ ዓይነት ወንበዴ ቡድን መልካም ነገር መጠበቅ ከእባብ እንቁላል እርግብ መጠበቅ ነውና ወላይታም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ከህወሃት ሴራ ሊጠነቀቅ ይገባል እላለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! ህዝቦቿን ፈጣሪ ይባርክ!

ኢትዮጵያዊነታችን አንድነታችን ነው!