“የብሄር መብት የለም!” በመ/ር ሙክታር ኡስማን

ፀሃፊው መምህር ሙክታር ኡስማን ሲሆን በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የህግ አስተማሪ ነው!

“መብት” ምንድነው? ለማን ነው የሚሰጠው? “መብት” ለሚሰማ፣ ለሚናገር፣ ለሚርበው “አካል አዕምሮ” ላለው፣ ግዝፈት ላለው እና ለሚዳሰስ ነገር እንጂ በጥቅል የግለሰቦች ስብስብ ውጤት ለሆነ “አካል አዕምሮ” ለሌለው፣ በረደኝ አልብሱኝ፣ ጠማኝ አጠጡኝ፣ የህሊና እስረኛ ሆኛለሁ ነፃነት ስጡኝ ብሎ ለማይጠይቅ አካል የሚሰጥ አይደለም። “ብሄር” እና ሌላ የማንነት መሰባሰቢያ የማይጨበጥ አካል አዕምሮ የለሽ፣ ግዝፈት የለሽ እና የማይዳሰስ “ቡድን” ነው።

የ”ቡድን” መብት የሚባለው፣ የአካል እና የአዕምሮ ባለቤት ለሆነው “ግለሰብ” በሚሰጠው የመብት ማዕቀፍ ውስጥ እንደ ውጤት (effect) ምላሽ የሚያገኝ እንጂ በራሱ መብት ሊሰጠው የማይችል ነው። የግለሰቡን መብት ማክበር ማለት እሱ አባል ለሆነለት ቡድን መብትም ማክበር ነው። የግለሰቡ መብት ማለት “ጥቅል” የመብቶች ንብርብር ማለት ነው። ከነዚህ “ጥቅል” የመብቶች ንብርብር ውስጥ የ”ብሄር” መብት አንዱ ሰበዝ ነው። የሀይመኖት፣ የሞያ ማህበራት እና ሌሎች በተፈጥሮ የሚገኙም ሆነ በፍቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የመሰባሰቢያ የ”ቡድን” ማንነቶችን ይዞ የሚመጣ መብት፣ ከግለሰቡ “ጥቅል” መብቶች ጋር የሚታሰብ ፅንሰሀሳብ ነው ማለት ነው።

እንደ ስብስብ “የብሄር መብት” እውን የሚሆነው ለእያንዳነዱ ግለሰብ በፖለቲካዊ ተሳትፎ ውስጥ መንግስት “ጥቅምና አመመለካከትን” (በሌላ አነጋገር “በሀሳብ” ላይ የሚመረኮዝ) ለማስተዳደር ሲዋቀር በህግና በፖሊሲ የሚመልሰው መብት ነው። ሰው እንደዜጋ መብቱ ሲከበር እንኳ የስብስቡ የጋራ መብት፣ የእንስሳና የዕፅዋትን መብት ያስከብራል።

የእኛ የፖለቲካ ቅርቃር ግለሰቡን ትቶ “የብሄር መብት” ብሎ መነሳቱ ነው። የግለሰቡ መብት ዜሮ ሲሆን፣ ዜሮ መብት ያላቸው ግለሰቦች ተሰባስበው መገለጫዬ የሚሉት “ብሄር” መብቱ ዜሮ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ብሄር በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፈው በግለሰቦች መንገድ እንጂ እንደ ግብ የእራሱን መብት ለማስጠበቅ አይደለም። ለምሳሌ የአማራን የህልውና ጥያቄ እንደመብት ውጤታማ ምላሽና መዳረሻው ያማረ የተጨበጠ ምላሽ የሚያገኘው አማራ ነኝ ብለው የሚያምኑ ዜጎችና ይህ አሳሳቢ ጉዳይ አስጨንቋቸው ድጋፍ የሚሰጡ ግለሰቦች በፖለቲካዊ ተሳትፎ “መብታቸው” ተጠቅመው እውን ሲያደርጉት ነው።

እንጂማ “አማራ” የሚባል ግዝፈት ያለው፣ የሚያስብ እና የመብቱ መገፈፍ የሚያሳስበው፣ ለዚህም ከመንግስት ጋር “በመብቱ” ጉዳይ መደራደር የሚችል አካል የለም። ያሉት የአማራ ማንነት አለን የሚሉ ዜጎች ናቸው፣ ለህልውናቸው፣ ለማንነታቸው እና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ “መብታቸው” ይቆማሉ፣ ይጠይቃሉ፣ ይደራደራሉ፣ ሰልፍ ይወጣሉ፣ ይፅፋሉ፣ ይህን ፅሁፍ ያነባሉ፣ ኮሜንት ያደርጋሉ፣ ላይክ ያደርጋሉ። ይህ የብሄር መብት ሳይሆን የእያንዳንዱ አማራ መብት ነው። የብሄር መብት ከፈረሱ ጋሪውን የሚያስቀድም በመሆኑ የለም።

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.