የፌደራሊዝሙ ቁማርተኞች!

ፀሃፊ፦ ጌታቸው ወንዲራድ (Ethio Wiki Leaks)

አላዋቂነት በዋጠው ግብታዊ እርምጃው የማይቀረውን ሞት የሞተው አምባገነኑ የደርግ ሥርዓት ውድቀት ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ እጣ ምን ይሆናል የሚለው ጉዳይ ባለድሉን ህወሓት/ህአዴግ ጨምሮ በርካቶችን የሚያሳስብና የሚያስጨንቅ ነበር። ስጋቱ አሸናፊነቱን ያረጋገጠው ህወሓት ብቻ አልነበረም። በህዝቡም ዘንድ ለአስራ ሰባት አመት ሲነገረው ከኖረው የ‹ገንጣይ› ‹አስገንጣይ› ተረክ ጭምር የአገራዊ ደህንነት ስጋቱ ጥብቅ ነበር። በብሔራዊ ዘመቻ ግዴታዎችና ‹ሁሉም ወደጦር ግንባር ዘመቻ› በመርዶና ስጋት ተወጥሮ የኖረው ህዝብ ከደርግ ቢገላገልም ቀጣዩ አገራዊ ሁኔታም እፎይታ ሊሰጠው የመቻሉ ነገር አሳሳቢ ነበር። ህዝቡ ድል ያደረገውን ህወሓት ከመጠራጠር ጀምሮ የደህንነትና አገራዊ ህልውና ስጋት ሲይዘው ህወሓት ደግሞ አገራዊ ተቀባይነት – የፖለቲካና ሕግ ቅቡልነት ያስጨንቀው ነበር።

ስለሆነም ህወሓት/ኢህአዴግ ከያዛቸው አላማዎች አኳያ አገር ለመያዝ የሚያበቃ ስዕል እና ተቀባይነት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ የስትራቴጂካዊ ግንባር እና ታክቲካዊ አጋር ለመፍጠር አበክሮ ሰርቷል። መጀመሪያ ከኢህዴን ቀጥሎ በተማረኩ የደርግ መኮንኖች በተመሰረተ ድርጅት ቀጥሎም በምርኮ ኢህዴን ውስጥ እንዲታገሉ የተደረጉ ከኦሮሞ የሚወለዱ ወታደሮችን በማሰባሰብ ኦህዴድ የተባለ የኦሮሞ ድርጅት በስትራቴጂያዊ አጋርነት በመመስረት ነበር የመሀል አገር ፖለቲካውን ለመጋለብ ራሱን በካፒቴንነት ያስቀመጠው።

ከዚያ በኋላም ወደአራት ኪሎ ለመዝለቅ የተሟላ አገራዊ ስዕል አስፈላጊ ነበረና ከሌሎች ምርኮኞች የደቡብ ድርጅት ለመመስረት ሲደረግ የነበረው ጥረት በደርግ ድንገተኛ ውድቀት ሳይሳካ እንደቀረ ገብሩ አስራት በመፅሐፉ ይተርካል። ስለሆነም የደርግ መኮንኖችን ጨምሮ በሦስት ድርጅቶች ‹‹ግንባር ቀደም መሪ- Van guard) የተመሠረተው ኢህአዴግ አራት ኪሎ ገባ። ከዚህ በኋላም ከድል በፊት ያሰበውን የደቡብ ድርጅት መስርቷል። ህብረብሔራዊው ኢህዴንም ስምሪት ተሰጠው (ምንም እንኳ የታገለለት አጀንዳ አገር አቀፍ ቢሆንም ከህወሓት ፍላጎት አንጻር የተገራ የ‹‹አማራ ጸባይ ማረሚያ›› ሆኖ ወደሚያገለግል የፖለቲካ ድርጅት እንዲወርድ ተደረገ) ከደቡብ ድርጅት ምስረታ በኋላ የደርግ መኮንኖች ድርጅት ወደሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች እንዲበተን ተደረጓል። አምባሳደር እስሌማን ደደፎና ጓዶቹ በዚህ መልክ ነበር ኦህዴድን የተቀላቀሉት፡፡

ከዚህ የድርጅቶቹ ምስረታ የምንረዳው እውነታ ድርጅቶቹ ይዘውት የተነሱት ብሔራዊ ጥያቄና የአደረጃጀት ፍላጎት አለመኖሩን ነው። በነበራቸው ድርጅታዊ የትግልና አደረጃጀት ቁመና ሳይሆን ግንባሮችን ለመመስረት ፍላጎት ይዞ በተነሳው ህወሓት የአደረጃጀት ፍላጎትና ፈቃድ ብቻ ነበር የተደራጁት። እናም፣ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የብሔራዊ (ዘውጋዊ) ንቃት ልዩነት፣ ከዚህ የሚመነጨው የዓላማ እና ግብ ጥራት (ተልዕኮን የማወቅ) ልዩነት ለንጽጽር የሚቀርብ አልነበረም፡፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ተከታታዮች ‹ህወሓት ከአናሳ ቡድን ወጥቶ እንዴት ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በበላይነት ሀገር መምራት ቻለ?› ለሚለው ጥያቄ የተለያየ መላ ምት ሲያስቀጡ ቢታይም፤ እውታው የህወሓት አመራርም ሆነ ካድሪው ከሌሎች (ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደኢህዴን፣…) አኳያ ለንጽጽር የማይቀርብ ብሔራዊ ንቃት (ስለቡድናዊ ማንነት፣ቋንቋ፣ ታሪክና ባህል በማወቅ ከሌሎች በተሻለ ጥቅምን ለማስከበር የትኛውንም አማራጭ [ታንክ እና ባንክ] ለመጠቀም የሚያስችል ትጉነት) ነበራቸው፡፡

በብሔር ፖለቲካ ቀዳሚው መስፈር ይሄው ነው፡፡ ብሔራዊ ንቃት! በዚህ ንቃት ውስጥ የሌሎች መብት ተከበረ አልተከበረ ቦታ የለውም፣ ከራስ ጥቅም ቀጥሎ ሌሎች (በልሂቃን ደረጃ) ተዋረዳዊ ጥቅም (ፍርፋሪ) ሊወረወርላቸው ይችላል፡፡ በአጭር አገላለጽ ብሔራዊ ንቃት ከኬኩ ትንቁን ድርሻ ለብቻ መውሰድ ማለት ነው፡፡ በዚህ ስሌት ነበር ህወሓት ‹‹ኢትዮጵያ ትድማ፤ትግራይ ትልማ› የሚለውን የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ምዝበራ መዋቅራዊ ቅርጽ የሰጠው፡፡ ይሄ መዋቅራዊ ምዝበራ ‹የጨነገፈው› የሻቢያ ‹‹ኤርትራ የግላችን ኢትዮጵያ የሁላችን›› የሚለው የበዝባዥ ፖሊሲ ሌላ ገጽታ ነው፡፡ ቅድመ-1990 ኢሳያስ አፍወርቂና አስተዳደሩ ኢትዮጵያን መዚህ መልኩ ግጠው በልተዋታል፡፡ ህወሓት ይሄን መሰል የበዝባዥ ፖሊሲ ያለከልካይ ገቢር አድርጓል፡፡ ዛሬ ትግራይ ጠፍራ እንደጠፍር አልጋ በመንገዶች ልማት ስትቆራኝ ‹‹ጨቋኝ›› የተባለው የሸዋ አማራ በመንገድ እጦት ቋጥኝ ሲቧጥጥ ይውላል፡፡ የፊስካል ፌዴራሊዝሙን አይን ያወጣ ነውር በሌላ ግዜ እንመለስበታለን፡፡

የህወሓትን የመሀል አገር የተቀባይነት ችግር ለመፍታት ተብለው የተፈጠሩት ድርጅቶች ‹‹ትወክሉታላችሁ›› በተባሉት ሕዝብ የተቀባይነት ቅራኔ ገጥሟቸው፣ ቅራኔው እስከ 2010 ድረስ ሊዘልቅ ችሏል፡፡ በዋናነት ብዓዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን በሚመሩት ክልል ውስጥ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ የገጠማቸው የተቀባይነት ቅራኔ ምንጩ ከእውነተኛ የፖለቲካ ውክልና እጦት ይመነጫል፡፡ በሌሎች አይን ሲታይ በአንጻሩ ህወሓት በሚመራው ክልል ቅቡልነቱ ምራቅ የሚያስውጥ ነበር፡፡ ሌሎችን ከሚመሩት ሕዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ የከተተው ይሄው ኃይል፣ የድርጅታዊ ህልውና ስጋቱ ከመነሻው (ከትግራይ) ሳይሆን፤ ከሌላው ሊመነጭ እንደሚችል በማሰብ ሌሎችን በሚመሩት ሕዝብ የተጠሉ በማድረግ ቅርቃር ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ በህወሓት ‹‹ትወክሉታላችሁ›› ተባሉ እንጅ ሕዝቡ በድምጹ ‹‹ወክሉኝ›› አላላቸውም ነበር፡፡ እነዚህን ብሔራዊ ድርጅቶች ‹‹የተልዕኮ ፓርቲ›› ብንላቸው ስያሜው ከታሪካቸው ጋር ስምም ይመስላል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶቹ አፈጣጠር ህወሓት ስትራቴጂካዊ ግንባር ባላቸው ብቻ ሳይሆን ታክቲካዊ አጋር ተብለው በድህረ ደርግ የተመሠረቱትንም የሚመለከት ነው።

ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢትዮጵያን የመሩት ድርጅቶች በሙሉ በህወሓት ፈቃድ ተመስርተው ክልል ተሠርቶ ተሰጥቷቸው ‹ከፊት ለፊት ምሩት፤ እኛ ከኋላ እንደግፋችኋለን› የተባሉ ናቸው። የራሳቸውን ጥያቄ ይዘው ደርግን የተቃወሙና የተነሱ ድርጅቶች ሁሉ ከሽግግር መንግስቱ ዘመን አልተሻገሩም። ኦነግ፣ ሲአን፣ ኦብነግ፣ ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ የሽግግሩ ተሳታፊ ሲሆኑ እንጅ ከሽግግሩ በኋላ በነበረው የፌዴራል ሥርዓተ መንግሥት ተዋናይ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ እዚህ ላይ የድርጅቶቹ የውስጠ ፓርቲ ድክመትና ተቃርኖ ሳይዘነጋ፣ እንወክለዋለን ላሉት የማንነት ቡድን ‹‹አለን›› የሚሉትን ‹‹የብሔር ጥያቄ›› ይዘው የተነሱ በመሆናቸው፣ አጋር ፍለጋ በረሃ ላይ ሲንከራተት ከነበረው ህወሓት ጋር አብሮ ሊያሰነብት የሚያስችል አቋም አልነበራቸውም፡፡ ሕወሓት ከሽግግር መንግሥት ምስረታው ጀምሮ ‹‹አጋር ድርጅት›› ሳይሆን ገባር ድርጅት የመፍጠር ፍላጎት ስለነበረው ከኦነግ፣ ሲአን፣ ኦብነግ፣..ጋር ሊስማማ አልቻለም፡፡ እናም ታክቲክና ስትራቴጂ የወለዳቸው ድርጅቶች በህወሓት መሪነት አገር ያዙ ቢባልም በባለቤትነት ስሜት መዝለቅ አልቻሉም ነበር። ያም ሆኖ አዲሱ አሰላለፍ፣ ለህወሓት የመጀመሪያው የፖለቲካ መሠረት፣ ለበላይነቱ ማስረገጫ መደላድልን የፈጠረለት ሊሆን ችሏል።

የስልጣን ክፍፍል እና የይስሙላ ፌደራሊዝም

ከራሳቸው ባልመጣ ጥያቄ፣ ባልታገሉበት አጀንዳ በፓርቲነት የተደራጁት ግለሰቦች የተጫነባቸውን አስተሳሰብ ይዘው በፓርቲነት መቀጠላቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅራኔ ተውጦ እንዲቀጥል አድርጎታል። በተመሳሳይ ፍላጎታቸው ይሁንም አይሁን በቋንቋና ማንነት ተሰምሮ የተሰጣቸውን ክልልና ዞን ወደማስተዳደር ሲገቡ፣ የህወሓት የሞግዚት አስተዳደር ፌዴራሊዝሙን የጅብ እርሻ እንዲሆን አድርጎታል።

በሌላ በኩል የፌደራል ክልሎች አከላሉ የመገንጠል አማራጭን ታሳቢ ባደረገው ህወሓታዊ እሳቤ ሲሰመር ቢያንስ እንደፌደራል ስርዓት አመቺ አስተዳደራዊ መዋቅር ÷ አመቺ የልማት እድል÷ እና የህዝቦችን ለዘመናት የዘለቀ የመንግስትነት ታሪክና ስነ-ልቦናዊ አንድነትና አብሮነት ከመፍጠር ይልቅ በቋንቋ ማንነት አሻጥሮች መሠራቱ የፈጠረው አገራዊ የመለያየት ጣጣው ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ያደረሰው ኪሳራ በቀላሉ አይታይም።

የቀደመው የብቻ ቁማር ጨዋታ፣ ዜጎች ለፌደራሊዝም የተዛባ አመለካከት እንዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡ የፌደራሊዝምን እውነተኛ መገለጫ በሃሳዊነት ገልብጦ አሳይቶናል፡፡ በመሠረቱ ከሆነ፣ ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚባለው አንዱ ከሌላው ተለይቶ የተሰጠው እውነተኛ የራስ ገዝ-መብት የተቀናጁ ቢያንስ ሁለት የአስተዳደር እርከኖችን እንዲይዝ ተደርጎ በሕገመንግሥት የተቋቋመ ሥርዓት ነው። በተለያዬ እርከን ላይ የሚገኙት መንግሥታት አገልጋይነታቸውም ሆነ ተጠያቂነታቸው ለመረጣቸው ሕዝብ ነው።

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ያየነው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነበር ። በፌዴራሊዝም ጭንብል የአንድን ቡድን ፖለቲካል-ኢኮኖሚ የሚያስጠብቅ በገዥ መደቡ ኀይል የሚመራ አሃዳዊነትን ያነበረ፣ ስታሊናዊ አገዛዝ ነበር። ‘ዘመናዊ የገባር ሥርዓት’ ልንለው እንችላለን። በሃሳዊ ትርክት የጎንዮሽ በጠላትነት እየተያዩ የበላይ ሆኖ ለኖረው ኀይል ገባር ለመሆን የተገደዱበት መዋቅራዊ እግር ብረት ነበር የህወሓቱ ፌዴራሊዝም፡፡

ሆኖም እኒያ ድርጅቶች የተሰጣቸውን ግዛት ይዘው ስልጣን ያዙ። በርግጥ ስልጣን ነውና ሳያላምጡ የዋጡትን ‹‹የብሔር ጭቆና›› ትርክት ይዘው የስርዓቱን አማላጅነት ከመዘመር አልቦዘኑም። ይህን የሚያላምዱ ህወሓታዊ ታጋዮችም በብዙዎቹ የክልሎች አስተዳዳሪዎች ስር ቁጭ ብለው እንዲዘውሩ ሲደረግ ‹‹ለአቅም ግንባታ ድጋፍ ነው›› ቢባልም፣ አሰራሩ የሞግዚት አስተዳደር ማሳያ ሆኖ ታይቷል፡፡ የህወሓት የፌዴራሊዝም ቁማርተኛ ባህሪ ገና ከጅምሩ ነበር የተጋለጠው፡፡ያልተማከለ አስተዳደርን እና የስልጣን ተዋረድ ክፍፍልን በሚጠይቀው ፌደራሊዝም ከፊል ሉዓላዊነት የሚጠይቅ ቢሆንም የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞው ከዚህ የተለየ ነበር።

የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም በህወሓት ጥቂት ግለሰቦች ‘ተገዶ የተደፈረ’ የአንድ ቡድን ፍላጎት ማሳኪያ እንደነበረ ከሰሞኑ አዲሱን ውህድ (ብልጽግና) ፓርቲ እያፀደቁ ያሉ የክልል አመራሮች እየመሰከሩ ነው። የቀድሞው የጋምቤላ ፕሬዝደንት “ህወሓት ሳያውቅ የምወስነው ውሳኔ አልነበረም” ብለዋል። የሶማሌው ምሁር ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ደግሞ “በአገራችን ‘አጋር’ ተብለን ባይታወር ሆነን ኖረናል” ሲሉ የፌደራሊዝሙን ይስሙላ፣ የራስ በራስ አስተዳደር ስብከት ሸፍጥ ገልጠዋል። “በጦርነት ተጎጅ” በሚል የሶማሌ በጀት በትግራይ ልማት ማህበር/ትልማ/ ስም ወደ ትግራይ ሲጋዝ አይተዋልና ባይተዋርነቱ ብሔራዊ ቁጭት እንደፈጠረባቸው በቴሌቭዥን መስኮት በግልፅ ይታይባቸው ነበር። የሌሎቹም አጋር ድርጅቶች መሪዎችና አባላት የሃያ ሰባት ዓመቱ ፖለቲካ ቁጭት የባይተዋርነት እና የተበዝባዥነት ስሜት ይታይባቸው ነበር።

በእነመለስና ስብሐት ጥቂት ቡድን ፈላጭ ቆራጭነት የየክልሎቹን ፕሬዝደንቶች ሲሾምና ሲሽር የኖረው ራሱ ህወሓት ነው። ለዚህ ድርጅት አመራር መልካም አቀባበል አላደረክም ተብሎ በግምገማ መገላመጥም ነበር። ወገናችን ያሉትን ለይቶ “አስተናግዱት” እየተባለ የክልሎቹን ውስን ሀብት ሲመዘብር መኖሩ በአፋሮች የጨው ቁፋሮ እና በጋምቤላ የእርሻ መሬት ወረራ ታይቷል። ይህ ኃይል ዛሬ የፌደራሊዝም ጠበቃ መስሎ ሲመጣ የትናንት ተግባሩን ባንረሳ እንኳ የድርጅቱ ተፈጥሮ የት ድረስ እንደሆነ ህዝብ እንዲታዘብ አስገድዷል።

ህወሓት በራሱ ፖለቲካዊ ስሌት ያደራጃቸውን ክልሎች ታዳጊና ድጋፍ የሚሹ በሚሉ የስነልቦና የበታችነት ስሜት የሚፈጥሩ ፍረጃዎች ሲያመልኩት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። የልማትና አስተዳደር አመቺነትን ማሰብና መተግበር አለመፍቀድ ክልሎቹን እንዲህ ባለ የዝቅተኛነት ስሜት እስከ ህገመንግስት ድረስ ፈረጇቸው ኑሯል።

ክልሎቹ ራሳቸውን በራሳቸው እንደማይመሩ እየታወቀ ለሚነሳው ቅሬታ ምክርቤትና ካቢኔው ውስጥ የእኛ ሰው የለም÷ ራሳቸው ናቸው ወሳኞች በሚል የሞኝ ክርክር ሲሳለቅ ኖሯል። እንኳንስ የየክልሎቹ ምክር ቤቶች የኢህአዴግ ምክርቤትና ስራ አስፈፃሚም ሳያውቀው ጥቂት ህወሓታውያን እራት እየበሉ በሚያሳልፉት ውሳኔ በስልክ ይመሯቸው የነበሩ ክልሎች በነበሩበት ፌደራሊዝሙ ተገዶ መደፈሩ ሊታወስ የተገባ ነው።

ለነገሩ ህወሓት የፈጠርኳችሁ ናቸው የሚላቸውን ክልሎች ይቅርና ያኔ 2010ዓ.ም አጋማሽ ላይ ለኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሽፈራው ሽጉጤን በጓዳ ሲያዘጋጅ እንደነበር በብርሃነ ፅጋብ መፅሐፍ [2011] ላይ አንበናል። መቀሌ ድረስ እየጠራ ታዛዡን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያዘጋጅ መኖሩን ረስቶ የድርጅት ደንብና አሠራር ተጣሰ በሚል ዛሬ ሲወቅስ የሚያውቁት የቀድሞ እህት ድርጅቶቹን ትዝብት አልፈራም።

ከመጋቢት/2010 ለውጥ ወዲህ እንኳ የፌደራል እና የክልል መንግስት የስልጣን ድርሻን በመጣስ እንደአንድ ሉዓላዊ አገር እየሰራ ባለበት ደረጃ “የፌደራሊስት ጠበቃ ነኝ” ለማለት የሚያሳየው ድፍረት የለመደው ፌደራሊዝሙን አስገድዶ የመድፈር ባህሪውና ቁማርተኝነቱ እንዳልተላቀቀው አመላካች ነው። ከፌደራሉ መንግስት ድጎማ እየወሰደ ከትግራይ የሚቀርብን ሰሊጥና ወርቅ አግዶ በኮንትሮባንድ እየነገደ፤ ከፌደራሉ መንግስት በላይ ጦር አደራጅቶና ታጥቆ፣ የፌደራል መንግስቱን ዘልሎ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እየሠራ “የፌደራሊዝም ጠበቃ ነኝ “ማለትን የመሰለ ስላቅ ከየት ይገኛል?

እንደ እውነቱ ቢሆን የፌደራል መንግስት እና የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ እርምጃ አለመግባታቸው “ለትክክለኛ ፌደራሊዝም የሚከፈል ዋጋ “ተደርጎ እየታየ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው። በርግጥ ህወሓት “ስላልቻሉን አርፈው ተቀመጡ፣ ትግራይን መድፈር ከታሪክ አለመማር ነው” በሚል በነጌታቸው ረዳ ሲፎከር ሲሰማ፤ “እንኳንስ ለዐቢይ አህመድ መንግስት ለየትኛውም ኃይል የሚመጥን የጦር ዝግጅት አድርገናል” ብሎ ደብረጽዮን በአደባባይ ሲያውጅ ፌደራሊዝም ዛሬም እንደትናንቱ ተገዶ መደፈሩን የቁማርተኞቹ መጫዎቻ መሆኑን ያሳያል። መልሶ ደግሞ ፌደራሊዝሙን እናድነው ይላል።

የፌደራል መንግስትን ስልጣን ተጋፍቶ የጋራ ህልውና ስጋት ላይ ተሰማርቶ ህግ ይከበር: “ፌደራሊስት ነን” እያለ ሲያላገጥ ህዝብ ማገናዘብ አይችልም ከሚል ንቀት እና ‘ዐይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ’ ነው። የአምሳለ መንግሥት (Defacto state) ከበሮ እየደለቁ ፌደራሊዝሙ ተደፈረ ከማለት በላይ ስላቅ የት አለ?

ህወሓት ትናንትም ሆነ ዛሬ ፌደራሊዝሙን አስገድዶ ሲደፍር እና “አሃዳዊነት መጣባችሁ” እያለ ሲሳለቅ እንደኖረ አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነው፡፡ ትላንትም ሆነ ዛሬ ይዞት ያለው ሩጫ ብቻውን የሚጫወተው የፌዴራሊዝም ቁማር እንጅ እውነተኛው እና ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ሊያደርግ የሚችለውን የፌዴራል ሥርዓት ለመተግበር አይደለም፡፡

ህወሓት በኢትዮጵያ ያሉ ብሔሮችን ማለቂያ ወደሌለው የአስተዳደር ጥያቄዎች እና የልዩነት አዙሪት ማስገባቱ አንዱ ውርሱ ነው። ብሔር ዘለል ተቋማትን አመንምኖ የልዩነት አጥር የገነባው ኃይል ኢትዮጵያውያንን አብሮ እንዳልኖረ ህዝብ በእርስበርስ መጠራጠርና መጠቃቃት ውስጥ ዘፍቋቸዋል። ወትሮም ኢኮኖሚያዊ ስሌትን እና በትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ስነልቦና ጫና አራት ኪሎ ለነበረው የህወሓት ቡድን፣ ‹ነገር ቢበላሽ› የራሴን አገር እመሠርታለሁ በሚል ስሌት ያዋቀረው ፌደራሊዝም ዛሬ ህዝብ የሚተራረድበት እንዲሆን የሚያስችል ፖለቲካዊ ስምምነት ሊፈጠር ሲል “የራሴ አገር” እመሰርታለሁ በሚል ወደጥጉ ሄዶ ይመለከታል። አልፎም በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ታሪክ ከሌላቸው የቤተሰብ ፓርቲዎች ጋር ሆኖ ‹‹ፌዴራሊዝሙን እንታደግ›› ሲል ይመጻደቃል፡፡

የብቻ ቁማርተኛው ውስር የሆነው ፌዴራሊዝሙ፣ ለሀገራዊ ህልውናችን ፈተና ሆኗል፡፡ ከአያያዝ ጉድለት ሀገሪቱን ውልቅልቋን ሊያወጣት ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያን እንጂ አማራጭ አገርን ሳያሰሉ ለኖሩት ኢትዮጵያውያን ደግሞ መለያየትና ሞት የእለት ግብራቸው ሆኗል። የዚህ ሂደት ጠንሳሹም ከርቀት እየተመለከተ ‹እኔ ባለመኖሬ ነው› በማለት ላይ ይገኛል። ይባሱኑ የኖርንበት ልዩነት ህዝብ እያፋጀ ባለበት የሽብር ተግባሩ፣ ዛሬም አገሪቱ ሰማንያ ብሔረሰቦች ሰማንያ ክልልና አገር እንዲሆኑ በመመኘት ለሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ከኔ በላይ ጠበቃ የለም በሚል ከሰሞኑ መቀሌ ላይ በመመጻደቅ ላይ ነው፡፡ ዛሬም ደም እያፋሰሰ ያለውን የልዩነት መስመር በፋይናንስና በሚዲያ ፕሮፖጋንዳ እየደገፈ ይገኛል። ትግራይ ምንም አትሆንም ኢትዮጵያ በልዩነቶች ትፈረካከስ በሚል ስሌት መቀሌ የመሸገው ኃይል ዛሬም የፌዴልዝም የብቻ ቁማርተኝነቱ ላይ ተጠምዶ ይገኛል። ገንዘብ የሁሉ ነገር መለኪያቸው የሆኑ፣ በአንድ ፉጨት ሲጠሩ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ የሚደርሱ የቁማርተኞቹ የአንቀልባ ልጆች ሀገር በማፍረሱ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

እንደ መውጫ፡- ህወሓትና ትግራይ

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ህወሓት፣ ትግራይን በመርህ ደረጃ ገንጥሎ ለብቻው ተቀምጧል፡፡ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋርም ሆነ እንደሀገር ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት በመርህ አልባ ግንኙነትነት (ህገ-ወጥነት) የሚታይ ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ አባልነት (ክልል) ስም ከማዕከላዊ መንግስት በጀት ይመደብለታል፤ ከመሀል አገር ጋር ያልተመጣጠነ ነጻ ገበያ ያገኛል፡፡ በከባድ የኮንትሮባንድ ስራ ተጠምዷል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ግጭት አምራች የሆነ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት አለው፡፡ ለማዕከላዊ መንግስት ምንም ትብብር ወይም ተጠሪነት የሌለው ክልል በተጨባጭ እየመራ ይገኛል፡፡

ትግራይ ውስጥ ህወሓትን ጨምሮ ‹‹የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ››፣ ‹‹አረና››፣ ‹‹ባይቶና››፣ ‹‹ሳልሳዊ ወያኔ›› እና ‹‹ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ›› የተሰኙ ስደስት የፖለቲካ ድርጅቶች ቢኖሩም፣ሁሉም የቅድሚያ ትኩረት ጉዳያቸው የትግራይን ግዛታዊ አንድነት መጠበቅ ላይ ነው፡፡

በጸጥታው እና ደህንነቱ ይዞታ ራሱን እንደነጻ-ሀገር መሪ ያደራጀው ህወሓት፣ ከሚሊሻ እስከ ልዩ ኃይልና መደበኛ ፖሊስ ድረስ ስድሳ ሺህ የታጠቀ ሰራዊት መገንባት ችሏል፡፡ እንደድርጅቱ ወታደራዊ ግምገማ ከሆነ አራት መቶ ሺህ የሚደርስ የውጊያ አቅም ያለው የሰው ኃይል መመልመል እንደሚችል እርግጠኛ ሆኗል፡፡ ይሄ ኃይል ዝግጁነቱ ከማዕከላዊው መንግሥት አልያም ከአማራ ይመጣብኛል ለሚለው ጥቃት መመከቻ የተዘጋጀ ብቻ ሳይሆን የኢሳያስ አፍወርቂንም ኃይል ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

ባለፉት ሃያ ወራት የውክልና ጦርነቶችን በአማራ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል፣… ክልሎች ሲያካሂድ፣ ያስተናገደው ኪሳራ ቢኖር በዘረፋ የሰበሰበው ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ አሁንም ህወሓት በጸረ-አማራ ብሎም በጸረ-ኢትዮጵያ አቋሙ ላይ ይገኛል፡፡ ከየትኞቹም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በአማራው ዘንድ ያለውን አንቅስቃሴ እንደቀዳሚ ስጋት ይመለከተዋል፡፡ ‹ጦርነቱ እኛ ዘንድ ሳይመጣ እዛው በራቸው ላይ እናቀጣጥለው› በሚል በቅማንት የሽብር ቡድን የተከፈተው የውክልና ጦርነት መግፍዔው ከዚህ ይመነጫል፡፡ ህወሓት የምኒልክን ቤተ መንግሥት ከለቀቀበት መጋቢት/2010 ጀምሮ ራሱን ጦርነት ላይ እንዳለ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡

በየትኛውም ፖለቲካዊ ዕድል ተመልሶ ሥልጣን ላይ እንደሚወጣ ለማመን የሚቸገር በመሆኑ፣ በተቻለው መጠን የራሱን አምሳለ ነጻ-ግዛት (de-facto state) በማቆየት ሀገሪቱ በወረቀት ወደ ተጻፈ ኮንፌዴሬሽን እንድትቀየር ማድረግ፣ ይህ ካልተሳካ ነጻ-ሀገር (Republic) የመመስረት ሙሉ ፍላጎት አለው፡፡ በሁኔታዎች የሚገለባበጠው ይሄ ኃይል፣ እስከ ዓላማው ስኬት ድረስ በፌዴራሊዝሙ ላይ የብቻ ቁማርተኛ ሆኖ ይቀጥላል፡፡