ይህ መግለጫ ሰምቶ በቸልታ ማለፍ ሽብርተኝነትን በተግባር መደገፍ ነው!

EthioWikiLeaks

ከአስር አመት በፊት “የኢህአዴግ መንግስት ጨቋኝና አምባገነን ነው!” ብሎ መናገር ልክ እንደ ሃጢያት ይታይ ነበር። “ጭቆና እና አምባገነንነት መጨረሻው ውድቀትና ውርደት እንጂ ልማትና እድገት ሊሆን አይችልም” የሚል ምክር አዘል ተግሳፅ የተናገሩ ልሂቃንን በጠላትነት ያድኑ ጀመር። ከአምስት አመት በኋላ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሠረታዊ ችግር የኢህአዴግ ጨቋኝነትና አምባገነንነት” እንደሆነ በይፋ የሚናገር አዲስ ትውልድ መጣ። ይህን ግዜ የኢህአዴግን ጨቋኝነት እና አምባገነንነት አምነው ተቀብለው የህወሓትን የበላይነት መቃወም ጀመሩ። ከሁለት አመት በፊት ደግሞ የችግሩ መሠረት “የብሔር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ልዩነትን መሰረት በማድረግ በዜጎች መካከል ጥላቻና ቂም የሚሰብከው፣ ያለመግባባት እና ጥርጣሬ ምንጭ የሆነው የአፓርታይድ ስርዓት ነው” ሲባል እንደ ወራሪ ጠላት ጨርቄን-ማቄን ሳይል ፈርጥጦ ወደ መቀሌ በመሄድ ሆቴል ውስጥ መሸገ።

ህወሓትን ከስልጣን ለማስወገድ የተደረገው ትግል ብዙ አመት የወሰደው፣ አላስፈላጊ መስዕዋት ያስከፈለው በሌላ ምክንያት ሳይሆን በራሱ በኢትዮጵያ ህዝብ መዘናጋትና ቸልተኝነት ነው። በእርግጥ ይሄ በሁሉም የህይወት ዘርፍ የሚስተዋል መሠረታዊ ችግር ነው። የህወሓት ጉዳይ ደግሞ ከሁሉም የባሰ ነው። ከመጥሪያ ስሙ ጀምሮ እስከ የዕለት መግባሩ የሚያሳየው ሌላ ሆኖ ሳለ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ከምሁራን ምክር ይልቅ የህወሓቶችን ምክር ያዳምጣል። “የትግራይ ነፃ-አውጪ ግንባር (ትህነግ) ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ይሰራል?” ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ “መንግስታዊ ስርዓቱ ፌደራላዊ ወይስ አሃዳዊ ነው?” እያለ ይጨነቃል። የህወሓት ባለስልጣናት መቀሌ ከገቡበት እለት አንስቶ ሆቴል ውስጥ የሚያድሩት ውሏቸው እንጂ መቀሌ ህልማቸው ተመልሶ መምጣት እንደሆነ መረዳት የተሳነው ማህብረሰብ ስለ ቀጣዩ ምርጫ ማሰላሰል ይቃጣዋል።

እንሆ አሁን ደግሞ “ህወሓት ሽብርተኛ ድርጅት መሆኑን በይፋ አስታውቋል”። ነገር ግን ህዝቤ ምንም እንዳልተፈጠረ በቸልታ አልፎታል። ነገ፥ ከነገወዲያ መላው ሀገሪቱ በብሔርና ሃይማኖት ግጭት ትርምስምሱ ሲወጣ ህዝቤ እንደ ወትሮ ሬሳና እየቆጠረ ያለቅሳል። ይህ ሁሉ የሆነውና ወደፊትም የሚሆነው፣ ይሄንን ማፊያ ቡድን በሆነው ልክ መረዳት አቅቶን፣ በትክክለኛ ስሙ መጥራት ተስኖን ነው። እውነታውን በይፋ ሲነገር መስማትና መረዳት ከተሳነን ደግሞ በየቦታው የሚቀሰቀሰውን የብሔርና የሃይማኖት ግጭት እንደ ተፈጥሮ አደጋ መቀበል አለብን።

ሽብርተኛን “አሸባሪ” ማለት ካቃተን መሸበር የለብንም። “ከኢትዮጵያ ብሔሮቾ፥ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመተባበር በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለማስወገድ ወስኛለሁ!” የሚል ይፋዊ መግለጫ ሲወጣ በቸልታ ካለፍን፣ ነገ እዚህና እዚያ የብሔር ግጭት ሲከሰት፣ በዚህም ምክንያት የሰዎች ህይወትና ንብረት ሲጠፋ ምንም የማለት ሞራል የለንም። ዛሬ “ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች የእኔ አገልጋይ ባሪያዎች እስካልሆኑ ድረስ ሀገሪቱ በሃይማኖት ግጭት ትታመሳለች!” ብሎ በይፋ መግለጫ ሲያወጣ ለማውገዝ ድፍረት ካሌለን ነገ መስጂድ እና ቤተክርስቲያን በእሳት ሲቃጠል፣ ሰው በጭካኔ ሲገዳደል መንግስትን ለመውቀስ ቀርቶ በሃዘን ለማልቀስ እንኳን የሚሆን ሰብዓዊ ርህራሄ የለንም። ምክንያቱም የትኛውም መንግስት ቢሆንም ሀገርና ህዝብ የሚያስተዳድረው በብዙሃኑ አመለካከት (Public Opinion) ነው። ዛሬ “ሀገሪቱን በብሔርና ሃይማኖት ግጭት ለማሸበር ወስኛለሁ!” የሚል መግለጫ ሲያወጣ በቸልታ ካለፍነው ነገ ላይ የሚነሳው ሁከትና ብጥብጥ የእኛ ዕውቅና እና ፍቃድ የተቸረው እንደሆነ ልናውቅ ይገባል።

ዛሬ በግልጽ እየተነገረን በቸልታ ያለፍነው ነገር ነገ በተግባር እውን ሲሆን ከራሳችን በስተቀር ሌላ ማንም ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ጉዳዩን ዳግም ለማስታወስ “ህወሓት የብሔርና የሃይማኖት ግጭት በመቀስቀስ ህዝብና መንግስትን ለማሸበር መወሰኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ በይፋ አስታውቋል!” የሚል ነው። ነገ በሁለት ግለሰቦች መካከል የተነሳ ፀብ ምክንያቱ እንኳን በውል ሳይታወቅ ወደ ብሔር ግጭት ተቀይሮ የብዙዎች ህይወት ሲቀጠፍ፣ ንብረታቸው ሲዘረፍ፤ የፀሎት ቦታ የነበሩ ቤተክርስቲያን እና መስጂድ በእሳት ጋይተው የፀብ መነሻ ሲሆኑ፣ ያኔ የሆነው ሁሉ የሆነው በእናንተ ፍቃድና ይሁኝታ መሆኑን ለማስታወስ ይህን ፅሁፍና ቪዲዮ መልሼ የምለጥፈው ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን ህወሓት ሽብርተኛ ድርጅት መሆኑ ይገለጥላችሁ ዘንድ በህወሓት መገለጫ ይዘትና አንድምታ ዙሪያ የቀረበውን ትንታኔ ታዳምጡ ዘንድ ተጋብዛችኋል። https://youtu.be/xWluTzGqux0