‹‹የህዳሴው ግድብ ሐውልት ሳይሆን የኃይል ማመንጪያ ነው!›› ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ

‹‹ ግድቡ ተሰርቶ እንደ ሐውልት የሚቆም ሳይሆን ውሃ ተሞልቶበት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ነው ›› ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በአአዩ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ

ግብጽ የምትፈልገው እስካሁን የውሃ ተጋሪ አገሮችን ሳታስፈቅድ ከዚህም ባለፈ ምንም መረጃ ሳትሰጥ የጋራ የሆነውን የናይል ውሃ ስትጠቀም በቆየችበት መንገድ መቀጠልን ነው። አልፎ ተርፎም ሁሉም ውሃ የእርሷ፣ ሌሎች አገሮች ምንም የውሃ መብት እንደሌላቸው በመቁጠር ማልማት ቢፈልጉ እንኳ ግብጽን ማስፈቀድ እንዳለባቸው ትጠብቃለች።

የማዕቀፍ ስምምነቱ ድርድር ይህን የተሳሳተ የውሃ አጠቃቀም እና አስተሳሰብ ለመቀየር ነበር። የናይል አገሮች የግብጽን ጥቅም ለማረጋገጥ እና የራሳቸውን ሉዓላዊ ጥቅም ለመጉዳት የሚያደርጉት ድርድር ሊኖር አይችልም።

በግብጽ ወገን በርካታ እንዲሁም በጣም ብዙ መግለጫዎች ይወጣሉ፤ ይሰራጫሉም። እንደ አለመታደል ሆኖ አብዛኛዎቹ መግለጫዎች፣ መረጃዎች፣ እንዲሁም ሪፖርቶች የተደራሲውን አስተሳሰብ ለማዛባት ሆነ ብለው የሚነገሩ ናቸው። በጥቅሉ የግብጽ መረጃዎችም ሆኑ ሪፖርቶች የተደራሲውን አስተሳሰብ ለማዛባት የታለሙ ናቸው። ይህ የሚደረገው በጋዜጣዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም በፖለቲካዊ መስመር ብቻ ሳይወሰን በአካዳሚክ እና በሳይንስ ነክ ሪፖርቶችም አንጻር ነው።

በዚህ ረገድ የግብጽን ድርጊት መወዳደር መጣር አስፈላጊ አይመስለኝም። የሆነው ሆኖ በኢትዮጵያ በኩል ትክክለኛ አቋሞችን እና ማስረጃዎችን በተሻለ ፍጥነት እና ስፋት ማካሄድ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የተሻለ ታታሪነት ከመንግስትም ሆነ ከሌሎችም ወገኖች ይጠበቃል።

የአሜሪካ መንግስት ለመግባባት ይረዳችሁ ዘንድ በድርድራችሁ ወቅት በታዛቢነት የ‹‹አሳትፉኝ›› ግብዣ ለሶስቱም አገሮች አቅርቧል። የአሜሪካ መንግስት የታዛቢነት ግብዣ ጥቅሙና ጉዳቱ በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በኩል ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በጥቅሉ የአሜሪካ መንግስት ለግብጽም ለኢትዮጵያም ወዳጅ መሆኑ ታሳቢ ሆኖ ነበር። ምናልባትም ጫፍ እየረገጠ የመጣው የግብጽ አቋም በታዛቢ ፊት አደብ ይገዛ ይሆናል በሚል እሳቤ የአሜሪካ ታዛቢነት ጥያቄ በአመዛኙ ተደግፏል።

የሆነው ሆኖ ታዛቢ ኖረም አልኖረም ኢትዮጵያ በመርህ መግለጫ ስምምነቱና (DOP) በቆየው ብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ መብቷ አንጻር አቋሟ ግልጽ ስለሆነ ስጋቱ የተጋነነ አልነበረም። ቀስ በቀስ አሜሪካ ከታዛቢነት ራሷን ወደአደራዳሪነት ከዚያም ለግብጽ የወገነ በሚያስመስል መልኩ ሰነድ እያረቀቀች ለፊርማ ለማቅረብ መሞከሯ በኢትዮጵያ በኩል የአሜሪካ ሚና ፈር መሳቱ ተገልጾላቸዋል። ሂደቱ እንዲቋረጥም ተደርጓል። በድርድር ወቅት የሶስተኛ ወገን ሚና ያልተለመደ አይደለም። ጠቃሚ ካልሆነ ይጣላል።በኢትዮጵያም በኩል የተደረገው ይኸው ነው።

ለተጨማሪ ይሄን ሊንክ ይጫኑ