“የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚለው አማራጭ የተሻለ ነው” ኢዜማ

‹‹የምንሰጠው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታገደን፣ አገረ መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል›› በሚል ርዕሰ ኢዜማ ባወጣው መግለጫ አስረድቷል፡፡ ምንም እንኳን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ ፓርቲው በፅኑ ቢያምንም ነገር ግን፣ ‹‹አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም፤›› ብሏል፡፡

‹‹አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የሥራ ዘመንና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58 ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ድንገተኛና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘምና ምርጫው እስከሚደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውንና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልጽ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ የማያዳግምና ተቀባይነት ያለው መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ነው፤›› ሲል ኢዜማ አቋሙን ገልጿል፡፡ 

ይህ የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊ ከተደረገ፣ ‹‹በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ተከትሎ የሚፈጸም በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም፤›› ያለው ኢዜማ፣ ‹‹እንዲሁም በቅርቡ ልናደርገው ከምናስበው ምርጫና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃርም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፤›› የሚል እምነት እንዳለውም አስታውቋል፡፡
‹‹የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ፣ የክልል ምክር ቤቶችንና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር አለበት፤›› ብሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት ወቅታዊውን የፖለቲካና የሕገ መንግሥት ቀውስ ለመፍታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ እንዲሁም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉ አራት አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን መንግሥት ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚለውን አማራጭ ማፅደቁ የሚታወስ ነው፡፡

‹‹ኢዜማ ይህ አማራጭ የተሻለ ነው ብሎ ባያምንም አማራጩ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባራቱን ማከናወን አለበት፤›› በማለት አሳስቦ፣ ጉባዔው በሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያፀድቀው ትርጉም፣ ‹‹የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዝመው ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከአንድ ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ፣ በዚህ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ተግባራትን ከመፈጸም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆንም አለበት፤›› ሲል ኢዜማ አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ እንደ አገር የሚወሰዱ ማንኛቸውም አማራጮች፣ ‹‹አሁን ያለንበትን  አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የአገር መረጋጋት፣ ሰላምና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደቱን የሚያስቀጥሉ፣ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን አለባቸው፤›› ሲል አሳስቧል፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ