የኢትዮጵያ የፌደራሊሰት ኃይሎች ጥምረት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን አገራችን አደጋ ላይ ስለሆነች፤ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ አገርን ማዳን በመሆኑና ለሕገ-መንግስትና ለህብረ ብሄራዊ ፌደራል ስርዓት ዘብ የሚቆሙ ሓይሎች ሁሉ አገርን ከትርምስ፣ ከህልውናና ዕድገት ጉዞ ቅልበሳና ብተና ለማዳን ሕብረት ሊፈጥሩ እንደሚገባ በማመን ከ2011ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የተለያዩ እንቅስቃሳዎች እያካሄደ ቆይቶ ጥር 2012 ዓ.ም ባፀደቀው ማኒፌስቶ አገራችን ከገባችበት ቅርቃር፣ የመበታተን ኣደጋና የደረሰችበት መስቀለኛ መንገድ ለማዳን የተለያየ ትግል እየተካሄደ ቆይቷል። ይህንኑ ስኬታማ ለማድረግ በሕገ-መንግስትና ሕብረ-ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓት ጠንካራ ኣቋም ያላቸው ሓይሎች በጋራ ለመታገል የተለያዩ መድረኮች አካሂዷል። በእነዚህ መድረክ ሂደቶች በፎረም ተጀምሮ እስከ ጥምረት እንዲደርስ አስተዋፆ አድርጓል። ጥምረቱ 25 የፓርቲ ኣባላት በመያዝ የተቋቋመ ሲሆን የሚመራበት ማኒፌስቶ፣ የኣሰራርና አደረጃጀት መመሪያ ተዘጋጅቶለት ከከፍተኛ ውይይት በኃላ ፀድቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን በጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ አንቀፅ 5 (ሀ) መሰረት ለሕገ-መንግስቱና ለህብረ ብሄራዊ ዴሞክራቲክ ፌዴራሊዝም ታማኝ የሆኑ ፖለቲካዊ ኃይሎች ስብስብ ነው፡፡ ነገር ግን በአክራሪ አሃዳውያንና ፀረ-ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም ኃይሎች ጥምረቱ በፈጠረባቸው ስጋት በምርጫ ቦርድ እውቅና እንዳያገኝና እንዲበታተን የተለያዩ ሴራዎች ሲሸርቡና ህገ-ወጥ ተግባሮች በጥምረቱ ላይ ሲያከናውኑ ቆይቷል። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ደግማ የጥምረቱ ኣባላት ስም በማጥፋት፣ ስብሰባ እንዳይካሄድ በማደናቀፍ፣ በማሰር፣ በማሳደድና በመደብደብ ከጥምረቱ ለማስወጣት ፖለቲካዊ የህዝቦች አላማ በወረደና የጥቅም ማማለል ርካሽ የመደለል ተግባራት ጭምር ሲያከናወኑ አልተሳካላቸውም እንጂ ጥምረቱ ለማፈረስ አላማ አድረገው ነበር።

የዚህ ውጤት አንድ ማሳያ የሆነውና በሁለት የአመራር አባላት አስተባባሪነትና በአክራሪ አሃዳውያንና ፀረ-ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም ኃይሎች ድጋፍ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ/ም በኣዲስ ኣበባ በድብቅ ስብሰባ እንዲካሄድ የተደረገው የአማተሮች ድራማ አንዱ ነው፡፡ በአክራሪ አሃዳውያንና ፀረ-ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም ኃይሎች ካሰማርዋቸው ኣካላት በቂ ጥበቃና ሚድያ ተዘጋጅቶላቸው ከአምስት ፓርቲ ሰዎች ያልበለጡ አባላት በመሰብሰብ በመቐለ ከተማ እንዲካሄድ የተወሰነውና ሊቀመንበሩ የጠራው በተለያዩ ነጥቦች ውይይት ለማድረግ በዝግጅት ላይ በነበርንበት ጊዜ የጥምረቱ የመቐለው ስብሰባ ለማደናቀፍ፣ ጥምረቱ ለመጥለፍ ከተሳካም ለማፍረስ በኣዲስ ኣበባ በድብቅ ስብሰባ እንዲካሄድ ሆኗል፡፡

ይህ ስብሰባ በጥምረቱ ምክር ቤት የፀደቀ የጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ አንቀፅ 5 (ለ) መሰረት የጥምረቱ አባላት ድርጅታዊ ነፃነታቸውና ህጋዊ ህልውናቸው ጠብቀው በእኩልነት የሚሳተፉበት መድረክ ባህሪ የጣሰ ነው፡፡ በተጨማሪም በአንቀፅ 6 መሰረት “በማንኛውም ጉዳይ ጥምረቱ የሚያስተላልፈው ውሳኔዎች በጉዳዩ ላይ ሰፊና ነፃ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደአስፈላጊነቱ በተባበረ ድምፅ (ኮንሰስስ) ወይም ጥምረት ድምፅ ድጋፍ ሲያገኝና ምልአተ ጉባኤ ተሟልቷል የሚባለው ደግሞ ከጠቅላላ አባላት (50%+1) በስብሰባው ሲገኙ ሆኖ ሳላ ነገር ግን ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ/ም በኣ/ኣበባ በድብቅ የተካሄደው ስብሰባ ከአምስት ያልበለጡ የጥምረቱ ከፍተኛ ኣመራሮች ተታልለው፣ ተጠልፈውና ተደናግረው ከኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን ውሳኔ ውጪ የራሳቸው ህገ ወጥ ውሳኔ ያስተላለፉ መሆኑ ታውቃል፡፡ በስብሰባው የተገኙ አምስቱም ፓርቲዎችም በጥምረቱ ምክር ቤት የፀደቀ የጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ አንቀፅ 10 (1)-(4) መሰረት የጥምረቱ ምክር ቤት ያፀደቀው ማኒፌስቶ፣ የአደረጃጀትና አሰራር መመሪያ፣ ውሳኔዎችና ዕቅዶች የማክበርና ተግባራዊ የማድረግ፣ ሕገ-መንግስቱና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓትን የሚቃወሙና በሃገር ሉኣላዊነትና ጥቅም የሚደራደሩ አመለካከቶችና ተግባራት በግልፅ የመታገል፣ የህብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረትን የሚፃረሩ ማንኛቸው የውስጥና የውጭ እንቅስቃሴዎች የመታገልና የጥምረቱ አንድነት እንዲጠናከር የማድረግ ግዴታ እያለባቸው በተቃራኒው ተንቀሳቅሷል፡፡

ይህ ተግባር በጥምረቱ ምክር ቤት የፀደቀ የጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ አንቀፅ 11 መሰረት ከጥምረቱ አባልነት ሙሉ በሙሉ የሚያሠርዝ ነው፡፡ የጥምረቱ ሊቀ መንበር በጥምረቱ ምክር ቤት የፀደቀ የጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ አንቀፅ 13 (4) መሰረት ከተቀመጠ ተግባርና ኃላፊነት ውጪ ተንቀሳቅሷል፡፡
በመሆኑም ጥምረቱ በነዚህ ጉዳዮች ላይ በጥልቅ ተወያይቶና በጥምረቱ ምክር ቤት የፀደቀ የጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ መሰረት የሚከተለው ውሳኔ ወስኗል፡፡

1. የአክራሪ አሃዳውያንና ፀረ-ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም ኃይሎች ጥምረቱ ላይ እያካሄዱ ያለው ሴራ እንዲያቆሙና የሰለጠነ ፖለቲካዊ ትግል እንዲያደርጉ፤ የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን በጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ አንቀፅ 5 (ሀ) መሰረት ለሕገ-መንግስቱና ለህብረ ብሄራዊ ዴሞክራቲክ ፌዴራሊዝም ታማኝ ሆኖ እንዲመክታቸው፤

2. በመቐለ ከተማ እንዲካሄድ የተወሰነው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በመንገድ ላይ የነበሩ (አቶ ገብሩ በርሄ፣ ልጅ መስፍን ሸፈራው፣ አቶ ተሻገር አራጌ፣ ወ/ሮ መዲና አሚንና አቶ ጉዕሽ ገብረስላሴ) የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን ኣባላት በብልፅግና ፓርቲ እንዲታሰሩ ሆኗል፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ እንዲደረግ፤ ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን ኣባላት በማሰር፣ በማሳደድና በመደብደብ ከጥምረቱ ለማስወጣት የወረደና የጥቅም ማማለል ርካሽ ተግባራት ከማድረግ እንዲቆጠብና የህዝብና የመንግስት ኃብት ለህዝባዊ አላማ እንዲያውል፤

3. ከጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ ውጪ ምንጩ ባልታወቀ ገንዘብ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ/ም በኣ/ኣበባ በድብቅ ስብሰባ እንዲካሄድ የተደረገው የአማተሮች ድራማ ላይ የተሳተፉ አባላት በጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ አንቀፅ 5 (ለ)፣ አንቀፅ 6፣ አንቀፅ 10 (1)-(4) መሰረት ከጥምረቱ አላማ ውጪ የተደረገ እንቅስቃሴ በመሆኑ በጠብቅ እናወግዛለን፤

4. የጥምረቱ ሊቀ-መንበር በጥምረቱ ምክር ቤት የፀደቀ የጥምረቱ አሰራርና አደረጃጀት መመሪያ አንቀፅ 13 (4) መሰረት ከተቀመጠ ተግባርና ኃላፊነት ውጪ በመንቀሳቀሳቸው ግዝያዊ የአመራር ማሰተካከያ እንዲደረግ በተባበረ ድምፅ ተወስኗል፡፡

5. ይህ ውሳኔ ለምርጫ ቦርድ እንዲላክ14 የጥምረቱ አባላት በፊርማችን አረጋግጠናል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን!

ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም
መቐለ

Source: TPLF Facebook Page