“የህወሓትን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ሲባል የትግራይን ህዝብ ለመነጠል የሚሰራውን ስራና ሴራ በጥብቅ እንታገላለን!” ብልፅግና ፓርቲ

ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

ከሁሉ አስቀድመን በመቐለ ከተማ በፀጥታ ሀይሎች በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ባለፈው ትግራዋይ ወጣት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን፤ ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹና ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ እንዲሁም ለሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ መፅናናትን እንመኛለን ::

ህዝባችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ያጋጠመውን ድርብ ፈተናና ችግር በማለፍ ወደሚፈልገውና ወደሚገባው የሰላም፣ የብልጽግና የመረጋጋት፣ የዲሞክራሲና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት ሆነ በፓርቲ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግስት አመራሮችና ሰራተኞች ህዝባዊነታቸው፣ የአመራር እሴቶቻቸውና ጥበባቸው የሚፈተንበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ እንደምንገኝም ማስተዋልና መበርታት ይገባል።

የትግራይ ህዝብ ከመላው የኢትዮጲያ ህዝብ ጋር በአንድነት በመሆን ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በከፈለው መስዋእትነት የሰላምና ዴሞክራሲ ብልጭታ የማየት ፍላጎቱ በቀረበው ቁጥር የሚሸሽበት ምናባዊ አለም ብቻ እየሆነበት መጥቷል።

በቅርቡ የአንድ ወጣት ህይወት እንዲያል ከመደረጉም በሻገር ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ የተከሰተው ለአንድ ወጣት ክቡር ህይወት ህልፈትና ለሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ በክልሉ ዉስጥ የሰላምና ዲሞክራሲ እጦት ማሳያ ነዉ፡፡ ሰላም ወዳዱና እንግዳ አክባሪ በሆነዉ የመቐለ ከተማ ነዋሪ መሪር የሀዘንና ውጥረት ድባብ ዉስጥ ይገኛል። ይህ ክቡር የሰው ህይወት የጠፋበትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመበት ክስተትም ሰላምንና ፀጥታን በህግ አግባብ ለማስጠበቅ ሃላፊነት በተሰጠው የፀጥታ አካል የተፈፀመ መሆኑ እጅጉን በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል። ይህም ድርጊት ብዙ መስዋእት ለከፈለ ህዝብ የማይገባዉ ነዉ፡፡ በመሆኑም የወጣቱ ግብረመልስም በክልሉ ሰላምና ዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ የኔ ጉዳይ ነዉ የሚል ከፍተኛ የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ፍላጐቶችና ቁርጠኝነት እንዲሁም ዝግጁነት መኖሩን በግልፅ አሳይቷል።

እንደሚታወቀዉ በአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደርና የማሰፈፀም አግባቦች ውስጥ የሰው ልጅን ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ማክበርና በህግ የማስከበር የመንግስት ግዴታ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ እንደ አለመታደል ሆኖ በትግራይ ክልል በወቅቱ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ክስተቶች አፈናና ግልፅ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳለ ማስተዋል ተችሏል።

በተለይም እራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ መተኪያ የሌለውን ክቡር ህይወታቸዉን እስከመቅጠፍ የደረሰ የሃይል እርምጃ በየትኛውም መለኪያ መወገዝ ያለበትና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር ነው። ድርጊቱም በፍጥነት ተጣርቶ የተወሰደው የእርምት እርምጃ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን ::

ይህንን ዓነቱን የክልሉ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እና መሰል የአፈና ተግባራት የክልሉ ወጣት ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መልኩ አጥብቆ እንዲታገለው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በአጠቃላይ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማድረግ በክልሉና በሀገር ደረጃ የተደቀኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ድጋፉ እንደማይለያችሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

“ወደ ህዝብ የተኮሰ ውድቀቱን አፋጠነ” እንደሚባለው፣ የገዢዎች የውድቀት ምልክት የሚጀምረዉ ወደ ህዝብ መተኮስ የጀመሩ እለት ነው። ስለሆንም በትግራይ ክልል በተለይ ደግሞ በመቐለ ከተማ ባጋጠመው ክስተት፣ በክልሉ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ የክልሉ ገዢ ፓርቲና መንግስት አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲመረምር አስገዳጅ ማንቂያ ደወል ነው። የትግራይ ብልፅግና ፓርቲም ጉዳዩን በአፅንኦት እንደሚከታተለውና ለሚመለከታችሁ ሁሉ በጥብቅ ያሳስባል።

በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም የትግራይ ወጣት እና ለውጥ ፈላጊ አካላት በሙሉ ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጋር በመሆን የለውጥ ሂደቱን እንዲያፋጥኑ ከፓርቲያችን ጋር እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን:: ፓርቲያችን የትግራይ ህዝብ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሚገባዉን ጥቅም እንዲረጋገጥ እና ሃገራዊ አንድነቱ እንዲጠናከር ይሰራል፡፡ በጥቂት ገዥ የህወሓት ቡድን በተለይ በዝምድና እና ጥቅም ትስስር እንዲሁም በሥልጣን ጥማት ምክንያት ትግራይን ከሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ለመነጠል የሚደረግ ስራም ሆነ ሴራ በጥብቅ የምንታገለዉና የምናወግዘዉ መሆኑን በጥብቅ እናሳዉቃለን::

በመጨረሻም ለሟች የዘለዓለም እረፍት፣ ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ከልብ እንመኛለን። ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም